Tuesday, November 5, 2013

የብዙኀን እናት (እመ ብዙኀን)



 

የብዙኀን እናት (እመ ብዙኀን)
ቀዳሚት ሔዋን ‹‹እመ ሕያዋን›› የሕያዋን ሁሉ እናት (ዘፍ 3፡20) ተብላ ትጠራበት የነበረውና በኋላ ግን ባለማመኗ እና ባለመታዘዟ ምክንያት ያጣችው የክብር ስሟና የእናትነት ማዕረግ በዳግማዊት (አዲሲቷ) ሔዋን በድንግል ማርያም አማካይነት በመመለሱ ድንግል ማርያም በነገረ ድኅነት ውስጥ ያላትን ወሳኝ ድርሻ ከማሳየቱም ባሻገር የብዙኀን (የሕያዋን) እናት መሆኗን አረጋግጧል፡፡
ልዑለ ባሕርይ እግዚአብሔር በአንተና በሴቲቱ በዘርህና በዘርዋ መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል አንተም ሰኮናውን ትቀጠቅጣለህ (ዘፍ 3፡15) በማለት የተናገረው ይህ የትንቢት ተስፋ ሰውን ወዳጅ የሆነው አምላክ ለሰው ልጆች ያለውን አምላካዊ አድኅኖት ዕቅድና በጎ ፈቃድ የሚገልጥ መሪ የተስፋ ቃል ነው፡፡









በመሆኑም ይህ አምላካዊ ተስፋ ትንቢት በምክረ ከይሲ ተታለው በኃጢአት ተሰናክለው በመንጸፈ ደይን ወድቀው በእግረ አጋንንት ይጠቀጠቁ ለነበሩት ለአባታችን ለአዳምና ለእናታችን ለሔዋን እንዲሁም ለልጆቻቸው ሁሉ የተሰጠ የመጀመሪያ አምላካዊ የድኅነት ተስፋ ነው፡፡
ስለሆነም ኢትዮጵያዊው ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በመጽሐፈ ሰዓታት ድርሰቱ ‹‹ተፈጸመ ተስፋ አበው በማርያም ድንግል ወበቀራንዮ ተተከለ መድኃኒት መስቀል›› ‹‹የቅዱሳን አበው ተስፋ ድኅነት በቅድስት ድንግል ማርያም ተፈጸመ የድኅነት ዓለም የተፈጸመበት መድኃኒት መስቀልም በቀራኒዮ ተተከለ›› በማለት ወላዲተ አምላክ የዚህ ቃል ትንቢት ፍፃሜ መሠረት መሆኗን ያመለክታል፡፡
ይህ የምስጢር ድኅነት ቃለ ትንቢት ለጊዜው በቀዳሚት ሔዋንና በጥንተ ጠላታችን በዲያብሎስ መካከል ያለውን ፀብና ክርክር የሚያሳይ ሲሆን ፍፃሜ ምስጢሩ ግን በዳግሚት ሔዋን (አዲስቷ ሔዋን) በድንግል ማርያምና ምክንያተ ስህተት በሆነው በሰይጣን መካከል የሚኖረውን ጠላትነት የሚገልጥ ነው፡፡ (ራዕ 12፡1-17) ከዚህም ሌላ የሴቲቱ (የድንግል ማርያም) ዘር በሆነው በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስና በሠራዊተ አጋንንት መካከል የሚኖረውን ጠላትነትም ያስረዳል፡፡ ይህም ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ‹‹አንተም የዘንዶውን ራሶች ቀጠቀጥህ›› (መዝ 73፡14) ባለው መሠረት የድንግል ማርያም ልጅ መድኅን ዓለም ክርስቶስ ጥንተ ጠላታችን የሆነውን የዲያብሎስን ራስ በመስቀል ላይ ቀጥቅጧል፡፡
በአንፃሩም ደግሞ እጆቼንና እግሮቼን ቸነከሩኝ (መዝ 21፡16) ተብሎ እንደ ተፃፈ ጠላት ዲያብሎስ በአይሁድ ልቡና አድሮ የመድኃኒታችንን ቅዱሳት እግሮች በቀኖት አስቸንክሯል፡፡ (ዮሐ 19፡23) ታላቁ ሐዋርያ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን ድንቅ ምስጢረ ድኅነት አስመልክቶ ሲናገር ‹‹ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ላከ ከሴትም ተወለደ እንደ ልጆች እንሆን ዘንድ ከሕግ በታች ያሉትን ይዋጅ ዘንድ›› (ገላ 4፡4) በማለት መስክሯል፡፡
በዚህ ሐዋርያዊ ቃል መሠረት ከላይ የተገለፀው የድኅነተ ዓለም ተስፋ በቅድስት ድንግል ማርያም እንደተፈጸመ ልብ ይላል፡፡ ዳግመኛም በቅዱስ ወንጌል እንደተፃፈው አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያምን የመጀመሪያውን ተአምር ባደረገበት በገሊላ ቃና ሠርግ ቤት (ዮሐ 2፡4) እንዲሁም የድኅነት ዓለም ሥራን በፈፀመበት በቀራንዮ መስቀል ላይ (ዮሐ 19፡26) አንቺ ሴት ሲል መጥራቱ አስቀድሞ ለሰው ልጆች የሰጠውን የድኅነት ተስፋ በእርሷ በኩል መፈጸሙን በምስጢር ያጠይቃል፡፡
በቀዳሚት ሔዋንና በዳግማዊት ሔዋን በእመቤታችን መካከል ያለውን ምስጢራዊ ንጽጽር በየዘመኑ የተነሡ የተለያዩ አበው ሊቃውንትና መተርጉማን አሟልተውና አስፍተው ገልጸዋል፡፡ ይኸውም ቀዳሚት ሔዋን ለፈቃደ እግዚአብሔር ባለመታመኗ ባለመታዘዟ ምክንያት በመላው የሰው ዘር ላይ መርገምና ሞትን አምጥታለች በአንጻሩ ደግሞ ዳግማዊ ሔዋን የተባለችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለፈጣሪዋ ፈቃድ በመታመኗ እና በመታዘዟ ምክንያት በመርገምና በሞት ጥላ ሥር ወድቆ ለነበረው ዓለም በረከትና ሕይወትን አሰገኝታለች፡፡ ይህንን አስመልክቶ ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴው ላይ ሲናገር ‹‹በእንተ ሔዋን ተዐፅወ ኆኃተ ገነት ወበእንተ ማርያም ድንግል ተርኃወ ለነ ዳግመ›› በቀዳሚት ሔዋን ምክንያት የገነት ደጃፍ ተዘጋብን ዳግመኛም ሰለዳጋሚት ሔዋን ስለ ድንግል ማርያም ተከፈተልን በማለት አስገንዝቧል፡፡
ታላቁ የዜና አበው ሊቃውንት የነገረ ማርያም አባት እያሉ የሚጠሩት እውቁ የቤተክርስቲያን ሊቅ ቅዱስ ሔሬኔዎስ ከላይ የገለጥነውን ኃይለ ቃል መሠረት በማድረግ ሰፊና ጥልቅ በሆነው የነገረ ማርያም አስተምህሮው እመቤታችን የሄዋን ጠበቃ አለኝታ ብሎአታል፡፡

 


እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለነገረ ድኅነት መሠረት መሆኗንና የሕያዋን ሁሉ እናት መሆኗን በመግለጥ የተአምሯ መድሐፍ ‹‹እግዝእትነ ማርያም ነበረት እምቅድመ ዓለም በኅሊና አምላክ›› ይላል፡፡ ከዚህም ኃይለ ቃል ድኅነት ዓለም የተፈጸመበትና የተከናወነበት የምሥጢረ ሥጋዌ ጉዞ መፍቀሬ ሰብእ የሆነው እግዚአብሔር አምላክ አስቀድሞ የፈቀደውና ያሰበው የቸርነቱና የመግቦቱ ስራ መሆኑን እንረዳለን እንገነዘባለን፡፡ ከዚህም ጋር ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ‹‹ወበእንተ ዝንቱ አስተርአየ ወልደ እግዚአብሔር ከመ ይስዐር ግብሮ ለጋኔን›› ስለዚህ የዲያብሎስን ሥራ እንዲያፈርስ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ (1ኛ ዮሐ 3፡8) ሲል እንደመሰከረ ጥንተ ጠላታችን የሆነው ዲያብሎስ በሥራ ከይሲ ተሰውሮ አዳምንና ሔዋንን እንዳሳሳተ ሁሉ (ዘፍ 3፡1-14) አካላዊ ቃል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በሥጋ ብእሲ ተሰውሮ ወደ ቀድሞ ፀጋና ክብር መልሷቸዋል፡፡
ይህንንም ምሥጢር ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን አሞንዮስ አውሳቢዮስ በቅድመ ወንጌል ሲገልጡ ‹‹ወበከመ ተኃብአ ሰይጣን በጉሕሉቱ ውስተ ሥጋ ከይሲ ከማሁ ኮነ ድኅነትነ በተሰውሮተ ቃል እግዚአብሔር በዘመድኀ›› ሰይጣን በስጋ ከይሲ ተሰውሮ አዳምን እንዳሳተው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስም በሥጋ ብእሲ ተሰውሮ መጥቶ አለምን እንዳዳነ፡፡ (ትርጓሜ ወንጌል ገፅ 28) በማለት ተናግረዋል፡፡ በዚህም የትርጓሜ ምስጢር መሠረት የሰው ልጅ በምክረ ከይሲ ተታሎ ሕገ እግዚአብሔርን አፈረሰ በኃጥያቱም ምክንያት ከፈጣሪው አንድነት ተለየ ሲባል በአካለ ከይሲ ተደልሎ በልሳነ ከይሲ ተታሎ መሳቱን መናገር ነው፡፡
ስለሆነም ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስ አካለ ከይሲ መሠወሪያ ልሳነ ከይሲ መናገሪያ አድርጎ በማሳቱ በማህደሩ ህዳሬውን መናገር ነው እንጂ ለሰው ልጅ ስህተት ምንጩና መሠረቱ እራሱ ዲያብሎስ መሆኑን መረዳት ያሻል፡፡ ቤዛዊተ ዓለም ድንግል ማርያም በዘመነ ብሉይ በተለያየ ኅብረ አምሳል መገለጧን በብዙ ዓይነት ኅብረ ትንቢት መነገሯም በነገረ-ድኅነት ውስጥ ያላትን ሰፊ ድርሻ በጥልቀት ያስረዳል፡፡ በዚህም መሠረት የነገረ ማርያም ትምህርት ከነገረ ድኅነት ትምህርት ጋር የተያያዘ ጥልቅ ምስጢር እንደሆነ መረዳት ይገባል፡፡
የመጋቤ ሐዲስ ቅዱስ ገብርኤል ዜና ብሥራትና የእመቤታችን እምነትና ታዛዥነት የመሲህ ክርስቶስን ወደዚህ ዓለም መምጣትና የአዲስ ኪዳንን መጀመር ያበሥራል፡፡ ልዑለ ቃል ቅዱስ ኢሳይያስ ‹‹የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ እንደ ሰዶም በሆን ገሞራም በመሠልን›› (ኢሳ 1፡9) ብሎ ንጽህት ዘር የተባለችው ድንግል ማርያም በነገረ ድኅነት ውስጥ ያላትን ሚና ሲገልጽ ወንጌላዊው ቅዱስ ሊቃስ የእመቤታችንን ሁለንተናዊ ሕይወት በመግለጥ በልዑለ እግዚአብሔር ፊት ያላትን ክብርና የባለሟልነት ሞገስ ከመጻፍ ባሻገር ‹‹ይኩኒነ›› በማለት የብዙኀን እናት (መንፈሳዊት እናት) በመሆን የመልአኩ የቅዱስ ገብርኤልን ቃል በሙሉ ፈቃደኝነት መቀበሏን ተርኮልናል፡፡
በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የነገረ ማርያም አስተምህሮ አምላካዊ የድኅነት ዓለም ጉዞ በማኅፀነ ድንግል እንዲጀመር ምክንያትና መሠረት የሆነው የቅዱስ ገብርኤል ዜና ብስራት አስቀድሞ የሰው ልጆች በኃጢአት የወደቁበትን መርገምና ሞት ወደ ዓለም የገባበትን የመልአክ ጽልመት የዲያብሎስን ተንኮል የሻረና ክፉ ምክሩንም ያፈረሰ የበረከትና የሕይወት መንገድ ነው፡፡ በመሆኑም በእመቤታችን በድንግል ማርያም አማካኝነት የተፈጸመው የሥጋዌ ምስጢር ሰውን ወዳጅ የሆነው ቸሩ መድኃኔዓለም ለሰው ልጆች ያለውን ጥልቅ ፍቅር የገለጠበት ታላቅ የድኅነት ምሥጢር ነው፡፡
በቅዱስ መጽሐፍም እንደምናነበው የመጀመሪያይቱ ሔዋን በምክረ ከይሲ ተታላ የጠላት ዲያብሎስን ክፉ ምክር ሰምታ በመቀበሏ ምክንያት ለሰው ልጆች ሁሉ ድቀት (ውድቀት)ና የሞት ፍርድ ምክንያት ሆነች፡፡ (ዘፍ 3፡4-6)
ዳግሚት ሔዋን የተባለችው ቅድስት ድንግል ማርያም እመቤታችን ግን በልዑለ እግዚአብሔር ፊት በባለሟልነት የሚቆመውን የመልአከ ሰላም የቅዱስ ገብርኤልን ቃል ብሥራት ሰምታ ‹‹ይኩነኒ በከመ ትቤለኒ›› እንደ ቃልህ ይሁንልኝ ይደረግልኝ ብላ በእምነት በመቀበሏ ምክንያት ድኂነ ወመሠረተ ሕይወት ሆነችልን፡፡ የቤተክርስቲያን ሊቃውንት ‹‹ወድቀው ይነሷል በእጅ ዘግይተው ይከብሯል በልጅ›› እንዲሉ በሴት (በቀዳሚት ሔዋን) ምክንያት የመጣው ድቀት ኃጢአትና መርገም በሴት (በዳግሚት ሔዋን በድንግል ማርያም) አማካይነት ተሽሯል ተደምስሷል፡፡ ይህም ማለት (ቀዳሚት ሔዋን)  ለአዳም የሰጠችውና ያበላችው የዕፀ በለስ ፍሬ በመላው የሰው ዘር ላይ መርገምንና ሞትን አስከትሏል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ (ዳግሚት ሔዋን) እመቤታችን የሰጠችን ፍሬ ኢየሱስ ክርስቶስ ፍሬ ሕይወት ፍሬ መድኃኒት አንድም ዕፀ መድኃኒት ዕፀ ሕይወት ሆነልን፡፡ ዳግመኛም ወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያም ፍሬ ሕይወት የሆነ ጌታን ያፈራች ዕፀ ማየ ሕይወት ጌታን ያስገኘች አዘቅት ኅትምት ‹‹የተዘጋችና የታተመች የውሃ ጉርጓድ›› ስለሆነች ክብሯና ምስጋናዋ ልዩ ነው፡፡
በዚህም ነበር የብሕንሳው ሊቅ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ድርሰቱ ‹‹ኦ ማርያም በእንተዝ ናፈቅረኪ ወናዒብየኪ እስመ ወለድኪ ለነ መብልዓ ጽድቅ ዘበአማን ወስቴ ሕይወት ዘበአማን›› በማለት ክብሯን የገለጸው፡፡ ይህን የድንግል ማርያምን ሙሉ ፈቃደኝነት እምነትና ትህትና ምክንያት አድርጎም አካላዊ ቃል እግዚአብሔር ወልድ ከስጋዋ ሥጋን ከነፍሷ ነፍስን ነስቶ በማኅፀኗ አደረ፡፡ በመሆኑም ቀዳሚት ሔዋን ምክንያተ ስህተት ምክንያተ ሞት በመሆኗ ሲወቅሳትና ሲከሳት የነበረው የሰው ዘር በሙሉ ምክንያተ ድኅነት ምክንያተ በረከት ወሕይወት የሆነች ዳግሚት ሔዋን እመቤታችንን ‹‹ብፅዕት አንቲ እንተ ተአሞኒ ከመ ይከውን ቃል ዘነገሩኪ እምኀበ እግዚአብሔር›› ‹‹ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልከው ከእግዚአብሔር አግኝተው የነገሩሽን ቃል እንዲፈጸም የምታምኚ አንቺ በእውነት ብፅዕት ነሽ ንዕድ ክብርት ነሽ›› (ሉቃ 1፡28-38) በማለት አመስግኗታል፡፡ (አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መድሐፍ ምስጢር)፡፡
ወላዲተ አምላክ የቅዱስ ገብርኤልን ዜና ብሥራት ሰምታ በማመኗ ምክንያት መድኅን ዓለም ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም ስለመጣ ብሥራተ መልአክ የብሉይ ኪዳን አምሣልና ትንቢት ፍጻሜ ወይም መደምደሚያ ሆነ፡፡ ይህን ታላቅና ድንቅ ምስጢር አስመልክቶ የቤተክርስቲያናችን የነገረ ማርያም መጽሐፍ ሲናገር ‹‹ቅዱስ ገብርኤልም በምስራቹ ቃል የቅዱሳን ነቢያትን ትንቢት አተመ አጸና ፈጸመ ዘጋ አረጋገጠ›› ለዓለም ሁሉ የደስታ መጠጥንና ምንጭን ያፈለቀ ያስገኘ ያመኘጨ ጉዳይ ከሆነ የእባብ (የአውሬ) መርዝም የሚከፋ መራራ የኀዘን ውኃን (መጠጥን ምንጭን) ከሰው ሁሉ ልቡና ያስወገደ ያራቀ ይህ ቅዱስ ገብርኤል ነው፡፡

 


ኢትዮጵያዊው የዜማ ሊቅ ቅዱስ ያሬድም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የሕይወት መሠረት ወምክንያተ ድኅነት እመ ብዙኀን መሆኗን ሲናገር ‹‹በእንተ ተሠግዎቱ ለወልደ አምላክ እምኔኪ ቅሩባነ ኮነ እምድር ውስተ አርያም ብኪ ወበከመ ወልድኪ›› ቃል እግዚአብሔር ወልድ ከሥጋሽ ሥጋ ከነፍስሽ ነፍስን ነስቶ ካንቺ ሰው በመሆኑ ከምድር ወደ ሰማይ ከሞት ወደ ሕይወት ከመርገም ወደ በረከት ከኃሳር ወደ ክብር ከሲኦል ወደ ገነት ተሸጋገርንብሽ በማለት ጽፏል፡፡
በቀዳሚት ሔዋንና በዳግሚት ሔዋን መካከል ያለውን ምስጢራዊ ንጽጽር አስመልክቶ ‹‹ኢትዮጵያዊው ቄርሎስ›› በመባል የሚታወቀው ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ሲገልጽ ዳግሚት ሔዋን የተባለች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ፍሬ የሕይወት መድኃኒት የሆነው ጌታ የተገኘባት አማናዊት ዕፀ ሕይወት በመሆኗ የዕፀ በለስን ፍሬ በልታ ሞትን ላመጣችብን ለቀዳሚት ሔዋን ካሣ ናት፡፡ ምክንያቱም ከዳግሚት ሔዋን ከድንግል ማርያም የተወለደው የማህፀኗ ፍሬ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መርገመ ስጋ መርገመ ነፍስን የሚያርቅ በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስን የሚያድል ሕይወተ ሥጋ ሕይወተ ነፍስን የሚሰጥ ቀዳሴ ሥጋ ወነፍስ (ወመንፈስ) የሆነ ብሩክ አምላክ ነውና፡፡ (አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽሐፈ አርጋኖን ገጽ 328-329)፡፡ የዳግሚት ሔዋን የወላዲተ አምላክን የእናትነት ክብሯንና የምስጋናዋን ታላቅነት የድኅነተ ዓለም ሥራ በቀራኒዮ ተራራ በተፈጸመበት ዕለት ከእግረ መስቀል አጠገብ በነበረው ታማኝ ሐዋርያ ፍቁረ እግዚ ቅዱስ ዮሐንስ አማካኝነት ለዓለም ሁሉ እናት የብዙኀን እናት (እመብዙኀን) ሆና በጸጋ በመሰጠቷ ፍጻሜውን አግኝቷል፡፡ (ዮሐ 19፡26-27)
በዚህም ምክንያት ስህተት ወሞት የሆነችውን የመጀመሪያ የሥጋ እናቱን ቀዳሚት ሔዋንን በዕፀ በለስ ምክንያት በማጣቱ አዝኖና ተክዞ ይኖር የነበረው መላው የሰው ዘር በምትኩ ምክንያተ ሕይወት ወበረከት የሆነችውን ዳግሚት ሔዋን ድንግል ማርያምን በዕፀ ሕይወት መስቀል አማካይነት በማግኘቱ ፍጥረት ሁሉ ተደሰተ ለዚህም ነው ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም ‹‹ሙኀዘ ፍስሐ›› የደስታ መፍሰሻ ሲል ያመሰገናት፡፡
በመሆኑም እመ ብዙኀን የሆነችው ቤዛዊተ ዓለም ቅድስት ድንግል ማርያም ለዚህ የመንፈሳዊ እናትነት ጸጋዋ በልጇ በኢየሱስ ክርስቶስ ወርቀ ደም ለተመሠረተችውና ለከበረችው ቤተ ክርስቲያን (ማኅበረ ምዕመናን) የቃል ኪዳን እናት ለመሆን በቅታለች፡፡ ፍልተን ሸን የተባለው ሊቅ ይህን ታላቅና ድንቅ አምላካዊ ምስጢር (በሐዲስ ተፍጥሮ) የተከናወነበት ዕለት (ዕለተ ዓርብ) የቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ መንፈሳዊ የልደት ቀን በማለት ሰይሞታል፡፡
ዳግመኛም በዚህ ሊቅ አገላለጽ መሠረት ዕለተ ዓርብ የምዕመናን ሐዲስ መንፈሳዊ የልደት ቀን መሆኑንም በምስጢር እንረዳለን እንገነዘባለን፡፡
በመሆኑም እንደ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ የልጇ የኢየሱስ ክርስቶስን አደራ ፍጹም አምነውና አክብረው የተቀበሉ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች የቃል ኪዳን እናታቸው የሆነችውን ወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያምን በዘወትር የምስጋና ጸሎታቸው ‹‹ተፈስሒ ኦ ቅዱስት አሞሙ ለኩሎሙ ሕያዋን ናንቀዐዱ ኃቤኪ ትሰዕሊ በእንቲአነ›› በመንፈስ ልደት የከበሩ ቅዱሳን ሕያዋን የሆኑበት ማየ ገቦ የተገኘብሽ የሕያዋን ፃድቃን እናታቸው ንዕድ ክብርት እመቤታችን ሆይ ደስ ይበልሽ፡፡ አንድም በቅዱስ ዮሐንስ አንጻር ልጆችሽ የምንሆን እናታችን ድንግል ማርያም ሆይ ደስ ይበልሽ፡፡ ወደ ልጅሽ ወደ ወዳጅሽ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ትለምኚልን ዘንድ ዓይነ ኅሊናችንን ወደ አንቺ እናነሣለን እያሉ ዘወትር ያከብሯታል ያመሠግኗታል ይማጸኑባታልም፡፡ (ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ ገጽ 58፡59)፡፡
ስለዚህ ቀዳሚት ሔዋን ለእግዚአብሔር ፈቃድ ባለመታመኗ ባለመታዘዟ ምክንያት እግዚአብሔርን ፀጋ ስለተገፈፈችና የልጅ ጸጋዋንም ስላጣች በምትኩ የቅጠል ልብስን ለሯሳ አደረገች በአንጻሩ ደግሞ አዲሲቷ ሔዋን እመቤታችን ሁሉን በጸጋ ለሚያለብሰው ለወልደ እግዚአብሔር ንጽሕና ቅዱስ የሆነው ስጋዋን የከበረ ልብስ ይሆነው ዘንድ ሰጥታለች፡፡ ይህንን ታላቅና ድንቅ ምስጢር የብሕንሳው ሊቅ ቅዱስ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ድርሰቱ ‹‹ምዕናም አንቲ ዘእምኔኪ ለብሰ አማኑኤል ልብሰተ ሥጋ ዘአይተረጎም›› የማይመረመር አማኑኤል የስጋን ልብስነት ካንቺ የለበሳት የድኅነት መሣሪያው አንቺ ነሽ›› ሲል መስክሮላታል ቤዛዊተ ዓለም ድንግል ማርያም በዚህ የወላዲተ አምላክነት ጸጋዋ በድቀት ኃጢዓት የነበረው መላው የሰው ዘር ወደ ቀደመው ክብሩ የተመለሰባትና ወደ ጥንተ ርስቱ የገባባት ምክንያተ ድኅነት መሠረተ ሕይወት ናት፡፡ ጥንታዊትና ሐዋርያዊት የሆነችው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያናችንም የእመቤታችንን እናትነት አምነው ለተቀበሉ ሁሉ ‹‹የእናት ልመና ፊት አያስመለስ አንገት አያስቀልስ›› ነውና የጌታችንና የመድሀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ስጦታ እንደ ቅዱስ ዮሐንስ እስከ ቀራንዮ ተጉዘው በመስቀሉ ስር ለተገኙ የቁርጥ ቀን ክርስቲያኖች ሁሉ እነኋት እናታችሁ እያለች ላለፉት 2000 ዓመታት ስታስተምር ቆይታለች ወደፊትም ታስተምራለች፡፡

No comments:

Post a Comment