Friday, November 8, 2013

‹‹የእግዚአብሔር ቃል›



‹‹የእግዚአብር ቃል›
በዚህ ርእስ ውስጥ የእግዚአብሔር ቃል ስንል ከሶስቱ ቅዱስ አንዱን ቅዱስ ለዘመኑ ጥንት ወይም ፍፃሜ የሌለውና የእግዚአብሔር ልጅ እግዚአብሔር ስለሆነው ስለ ጌታችን ስለ መድሃኒታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡
ለባሕርይ አባቱ ለአብና ለባሕርይ ህይወቱ ለመንፈስ ቅዱስ ቃል ለሆነውንና በቅድምና በልዕልና ስለነበረው የዘመኑ ፍፃሜ በሆነ ጊዜ የተቆጠረው ሱባኤ ሲያበቃ የተነገረው ትንቢት ሲደርስ ፀጋና እውነትን ተመልቶ በእኛ ስላደረው አካላዊ ቃል (ሎጎስ) ወልድ ማንነት ለመፃፍ ፈልገን ነው፡፡
ወንጌላዊውና ሐዋርያው ቅዱስ ዮሀንስ በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ ‹‹በመጀመሪያ ቃል ነበረ፣ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፣ ቃልም እግዚአብሄር ነበረ፣ ይህም በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፣ ሁሉ በእርሱ ሆነ ከሆነውም አንዳች እንኳ ያለ እርሱ አልሆነም፡፡››(ዮሐ 1፣1-2) ‹‹ቃልም ስጋ ሆነ ፀጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ አንድ ልጅም በአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነውን ክብሩን አየን››(ዮሐ 1፣14)በማለት አስተምሮናል፡፡













በመሆኑም የእግዚአብሔር ቃል፡-
1)  አካላዊ ቃል (ሎጎስ) ነው
ነገረ መለኮት በተጥባበ ስጋ የማይደረስበት ከሰው አእምሮ በላይ የሆነ ስጋዊ አእምሮ ተመራምሮ የማይደርስበት ጥልቅ ረቂቅ ሰማያዊ ሚስጥር ነው፡፡ በእርግጠኝነት መናገር የምንችለው ይህን ረቂቅ ሚስጥር በቅዱስ ዮሐንስ ስጋና ደም እንዳልገለጠለት መንፈሰ እግዚአብሔር እንደገለጠለት ነው ምክንያቱም ቅዱስ ዮሐንስ (ወንጌላዊው ) የአሳ አጥማጅ ልጅ ነበረ እርሱም በአባቱ እግር ተተክቶ በገሊላ ባህር አሳ በማጥመድ ይኖር የነበረ ከመፃህፍት አለም የራቀ እንዳውም ፊደል ካልቆተሩ ተርታ የሚመደብ ሰው ነበር እንዲህ ተብሎ እንደተፃፈ ‹‹ጴጥሮስና ዮሀንስም በግልጥ እንደተናገሩ ባዩ ጊዜ መፅሀፍን የማያውቁና ያላተማሩ ሰዎች እንደሆኑ አስተውሎ አደነቁ›› (ሐዋ ስራ 4፣13)
ዳሩ ግን በመንፈሰ እግዚአብሔር ተቃኝቶ አካል ከህልውና ተገልጦለት ከሰው አእምሮ በላይ የሆነውን ነገረ መለኮት ለአለም ገለጠ፡፡ የክርስትናው አለም የተመሰረተበትን ይህን መሰረተ እምነት ቅዱስ ዮሀንስ ከአእምሮው አፍልቆ እንዳልተናገረው ከላይ ከተገለፀው የእርሱ ማንነት የምንረዳው ነው፡፡ ሚስጥረ መለኮት በምርምር በተጥባባተ ስጋ የሚደረስበት አለመሆኑን ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል ‹‹መንፈስም የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገርስንኳ ሳይቀር ይመረምራልና ለእኛ በመንፈሱ በኩል ገለጠው››(1ቆሮ 2፣10)
ቅዱስ ዮሐንስ ነገረ መለኮትን ከሌሎች ወንጌላውያን ይልቅ አምልቶና አስፍቶ በመናገሩ ቴዎሎጎስ (ነባቤ መለኮት) የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል ከተቀሩት ሶስቱ ወንጌላውያን ለየት ባለ መልኩ ነው ወንጌልን የጀመረው ፡፡ ወንጌላዊው ማቴዎስ የጌታን የዘር ሀረግ በመዘርዘር ነገረ ልደቱን በማስቀደም ሲጀምር ወንጌላዊው ሉቃስ ደግሞ ጌታ ከእመቤታችን እንዴት እንደተፀነሰ በመግለጽ ጀምሯል፡፡በአንበሳ የተመሰለው ማርቆስ ወንጌላዊው ደግሞ በጌታ ጥምቀት ይጀምራል፡፡ ሶስቱ ወንጌላውያን በስጋ ተገልጦ የመጣበት ላይ ሲያተኩሩ ወንጌላዊው ዮሀንስ ግን ከስጋዌ በፊት ስላለው በመግለጥ ነው ወንጌሉን የጀመረው፡፡
አራቱም ወንጌላውያን በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው የፃፉ እንደመሆናቸው ጌታ መንፈስ ቅዱስ ወንጌላውያንን ሲያፅፍ በመዋቅር አስጀምሮ በመሰረት አስጨርሷል፡፡ ነገር ግን ቤት ከመዋቅሩ እስከ መሰረቱ የተያያዘ ነው እንጂ የተለየ አይደለም፡፡ ተጠመቀ ለማለት ተወለደ ማለት ጥንቱ (መጀመሪያው) ነው፡፡  ተወለደ ማለት ደግሞ ተጸነሰ ማለት ጥንቱ ነው፡፡ ተጸነሰ ለማለት በቅድምዎ ነበረ ማለት ጥንቱ ነው፡፡ ቅዱስ ማቴዎስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በስጋ ከአብርሀም ወገን መወለዱን በማሳየት ምድራዊ ልደቱን በመግለጥ ወንጌሉን መጀመሩን ስናስተውል  ወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ ደግሞ ጌታ በዕደ ዮሀንስ በፈለገ ዮርዳኖስ መጠመቁን የወንጌሉ መግቢያ አደረገ፣ቅዱስ ሉቃስ የጌታን ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በብስራት መልአክ መጸነሱ መነሻ አድርጎ ወንጌሉን ሲጀምር ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ደግሞ ከንጽሕት ቅድስት ድንግል ማርያም የተፀነሰው በቅድምና የነበረ ከአብ ጋር የተካከለው የፍጥረታት ባለቤት አምላክ ወልደ አምላክ መሆኑን በማወጅ ወንጌሉን ጀምሯል፡፡
አብ መሠረት ሆኖ ሳለ ለምንድን ነው ‹‹በመጀመሪያ ቃል ነበር›› በማለት የጀመረው? ለሚለው መሠረታዊ ጥያቄ በመንፈስ ቅዱስ የተቃኙ አበው መልስ ሰጥተዋል፣ ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ዋና ዓላማ ያደረገው ሰው ሆኖ የተገለጠው የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስን የባሕሪ አምላክነት (እግዚአብሔርነት) ለዓለም መግለጥ በመሆኑ የወልድን በቅድምና መኖር በመግለጥ ጀምሯል፡፡ በዚህም በሥላሴ ዘንድ የስም ቅደም ተከተል የሥልጣን ተዋረድና መዓረግ ርቀት እንደሌለ አስገንዝቧል፡፡
በኋላ ጊዜ የተነሱ መዓረገ መንግሥት የሚሰጡ እነ አቡሊናርዮስ መዓረገ ርቀት የሚሰጡ እነ አርጌንስ በዚህ ተረተውበታል ‹‹በመጀመሪያ ቃል ነበር›› የሚለው አገላለጥ ‹‹በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይና ምድርን ፈጠረ›› (ዘፍ 1፡1) ከሚለው ከሊቀነቢያት ሙሴ አገላለጥ ጋር ንባቡ ተመሳሳይነት ስላለው መጀመሪያ የሚለው ቃል ጥንት እንዳለው የሚገልጽ ነውና ከአብ ጋር የተካከለ እንዴት ሊሆን ይችላል በማለት የሚከራከሩ አሉ በእርግጥ ቃላቱ ተመሳሳይ ቢሆንም በምስጢርና በትርጉም ግን የተለያዩ ናቸው ሙሴ ‹‹በመጀመሪያ›› የሚለውን ቃል መጠቀሙን ልብ ይላል፡፡ ቃላት እንደ አገባባቸው ትርጉማቸው ይለያያል ‹‹ፊተኛውና ኋለኛው መጀመሪያና መጨረሻ እኔ ነኝ›› ከሚለው  የእግዚአብሔር ቃል የምንረዳው ፈጣሪነቱን የሁሉ አስገኚ መሆኑን ነው እኔ ፊተኛው ነኝ እኔም ኋለኛው ነኝ እጄም ምድርን መሥርታለች ቀኜም ሰማያትን ዘርግታለች በጠራኋቸው ጊዜ በአንድነት ይቆማሉ እንዲል (ትን ኢሳ 48፡13)
አካላዊ ቃል ወልድ ያልነበረበት ዘመን የማይኖርበት ዘመን የለም ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በዘመን የተካከለ ነው ‹‹አባት ሆይ ዓለም ሳይፈጠር በአንተ ዘንድ በነበረኝ ክብር አንተ በራስህ ዘንድ አክብረኝ›› በማለት እንደገለፀው (ዮሐ 17፡5) ልቡናቸው የታወረ አንዳንዶች የስነፍጥረትን ሕግ በመከተል አባት ከልጅ በዕድሜ ይበልጣል ልጅም ከአባት በኋላ ነው፡፡ ታዲያ አብ አባት ከሆነና ወልድን ከወለደ እንዴት በዘመን አይቀድመውም ይባላል ? በማለት የወልድን በቅድምና መኖር ክደው ለማስካድ ይደክማሉ፡፡ በመሠረቱ ፍጡርና ፈጣሪ ማነፃፀር አግባብ እንዳልሆነ ብናውቅ እንዲህ ዓይነቱን ጥያቄ ለሚጠይቁ ሰዎች ጆሮአችንን መስጠት ሌላ አግባባዊ ያልሆነ ጥያቄ እንዲያመጡ መጋበዝ ቢሆንም ደካሞችን በክህደት ጠልፈው እንዳይወስዱ በማሰብ የዚህን ጥያቄ መልስ ሰጥተን ማለፍን መርጠናል፡፡
ለእነዚህም ወገኖች ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህን ጥያቄ ይጠይቃል ‹‹እስቲ ንገሩን የፀሐይ ጨረር ከራስዎ ከፀሐይ ወይስ ከሌላ አካል ነው የሚወጣው? የፀሐይ ጨረር ከፀሐይ አካል እንደሚወጣ በእናንተም በሁሉም ዘንድ የታወቀ ነው ዳሩ ግን በፀሐይ ጨረር እና በፀሐይ አካል መካከል የጊዜ መለያየት እንደሌለ አስተውሉ›› የፀሐይ ጨረር ከፀሐይ አካል የተለየበት ጊዜ እንደሌለ ሁሉ፣ ምክንያቱም ፀሐይ ሁል ጊዜ የምትወጣው ከጨረርዋ ጋር ነውና ወልድም አብን እህሎ አብን መስሎ ከአብ የተወለደ ቢሆንም ከአብ የተለየበት ጊዜ የለም በዘመን አይቀዳደሙም አብ ከወልድ ተለይቶ የነበረበት ዘመን የለም ወልድም ያልነበረበት ጊዜ የለም በቅድምና አንድ ናቸው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የአብ ነፀብራቅ ማለቱን ልብ ይላል (ዕብ 1፡1-3)
ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ጳውሎስ የዳዊትን መዝሙር አጣቅሶ ሲመሰክር ‹‹ጌታ ሆይ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ ሰማዮችም የእጆችህ ሥራ ናቸው እነርሱም ይጠፋሉ አንተ ግን ጸንተህ ትኖራለህ ሁሉም እንደ ልብስ ያረጃሉ እንደ መጎናጸፊያም ትጠቀልላቸዋለህ ይለወጡማል አንተ ግን አንተ ነህ ዓመቶችህ ከቶ አያልቁም›› (ዕብ 10፡10-12)
ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስም ‹‹ያለውና የነበረው የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ አልፋና ኦሜጋ እኔ ነኝ ይላል›› በማለት በራዕይ መጽሐፍ ላይ ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ቀዳማዊ ድኅራዊ መሆኑን ዐምልቶ አስፍቶ መስክራል (ራዕ 1፡8)
እርሱ ራሱ ጌታ በዘመኑ ሁሉ ያለ የነበረ መሆኑን በኢሳይያስ ‹‹ከሆነበት ዘመን ጀምሮ እኔ በዚያ ነበርሁ›› ብሎ ተናግሯል ፡፡ (ኢሳ 42፡16)  እንግዲህ ከባለቤቱ በላይ ሌላ ምስክር አይመጣም በነቢያት ተናገረ በሐዋርያት አስመሰከረ፡፡ ‹‹የምወደው ልጄ ይህ ነው›› በሚለው የአብ ምስክርነት እርሱ አብን መስሎ አብን አህሎ መወለዱን እኔና አብ አንድ ነን ባለው የጌታ ቃል መሠረት ደግሞ ከባሕሪይ አባት ከአብ ጋር የተካከለ በቅድምና ከአብ ጋር የነበረ መሆኑን እንገነዘባለን ስለዚህ ‹‹በመጀመሪያ ቃል ነበረ›› በሚለው አገላለጽ ወንጌላዊው ሊያስገነዝብ የፈለገው ሰው ሆኖ የተገለጠው አካላዊ ቃል መጀመሪያና መጨረሻ የሌለው ዘላለማዊ አምላክ መሆኑን ነው ለምን ቃል የሚለውን ስም መጠቀምን መረጠ? እንደ ነቢይ ልዑል ኢሳይያስ የእግዚአዘብሔር ክንድ ጥበቡ ወይም ወልድ በሚለው ስም አልጠራውም? ለሚለው ጥያቄ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን የሚከተለውን መልስ ይሰጣሉ፡- ‹‹ስለ ሦስት ነገር ‹‹ቃል›› ብሎታል ህብውናቸውን፣ ቅድምናቸውን ለመናገር ፈጠረበትም ለማለት››   (ወንጌል አንድምታ)
ሀ/ ህልውናቸውን ለመናገር
ከልብ ከእስትንፋስ ተለይቶ በአፍአ (በውጭ) የሚገኝ ቃል የለም ቃል ከልብና ከእስትንፋስ ተለይቶ አይኖርም በምስጢረ ስላሴ ትምህርታችን ላይ እንደተገለጸው አብ ልብ ወልድ ቃል መንፈስ ቅዱስ እስትንፋስ ነው፡፡ ወንጌላዊው ‹‹ቃል›› ብሎ የጠራው ወልድ ከባሕሪ አባቱ ከአብ ከባሕሪይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ በሕልውና አንድ ሆኖ ሳለ ሰው ሆኖ መገለጡን ለመናገር ነው፡፡
ለ/ ቅድምናቸውን ለመናገር
ቅድምናቸው ለመናገር ልብና እስትንፋስ ቀድመውት ኋላ ላይ የሚገኝ ቃል የለም ልብ ቃል እስትንፋስ በቅድምና አንድ ናቸው አንዱ ከአንዱ አይቀድምም፣ እነዚሁም የሥላሴ ቅድምናቸው አንዲት ናት በቅድምና አንድ ናቸው በልብ የተመሰለ አብ በቃል የተመሰለ ወልድ ቀድሞ የኖረበት ዘመን የለም ስለዚህ በቅድምና ከነበሩት ከሦስቱ አካላት አንዱ አካላዊ ቃል (ሎጎስ) ሰው ሆነ ለማለት ይመቸው ዘንድ ቃል በሚለው ስም ጠርቶታል፡፡
ሐ/ ፈጣሪነታቸውን ለመናገር
አብ በወልድ ዓለምን ፈጠረ ቢባል እንደ አርዮስ አረዳድ ሳይሆን አትናቴዎስ ሐዋርያዊ እንደተናገረው የእግዚአብሔር ቃል እኛን ለመፍጠር የተፈጠረ አይደለም እኛ በእርሱ ተፈጠርን እንጂ ‹‹በእርሱ ሁሉ ተፈጠረ›› እንጂ ለእኛ መፈጠሪያ እንዲሆን ልዑሉና ኃያሉ እንደ አገልግሎት መሣሪያ ተፈጠረ ብሎ ማውራት ከደካማ አስተሳሰብ የተገኘ ነው ዓለም በእርሱ እንደተፈጠረ ባይካድም ቃል ምን ጊዜም ነበረ ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን ሲመሰከር ‹‹እኛ ፍጥረቱ ነንና እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን›› በማለት ፈጣሪነቱን አስተምሮናል (ኤፌ 2፡10) ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስም ‹‹ሁሉ በእርሱ ሆነ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ ፈቃድ አልሆነም›› (ዮሐ 1፡3 ና 4) በማለት ‹‹የአካላዊ ቃልን›› ፈጣሪነት ይነግረናል፡፡
አብ በወልድ ዓለምን ፈጠረ ሲባል በእጅ ጥልፍ እንደ መጥለፍ ሥዕል እንደ መሣል ነው ስለዚህ ወንጌላዊው ዮሐንስ ሰው ሆኖ የተገለጸው የፍጥረታት ባለቤት ፍጥረታት የተፈጠሩበት መሆኑን ለመግለጽ ‹‹ቃል›› በሚለው ስም ጠርቶታል፡፡
አምላክ ወይም ወልድ ብሎ ለምን አልጠራውም? ቢሉ ቃል በሚለው ምትክ አምላክ ብሎት ቢሆን ኖሮ መናፍቃን የጸጋ አምላክነቱን እንጂ የባሕሪ አምላክነቱን አያሳይም ባሉ ነበር ምክንያቱም ሙሴን እግዚአብሔር ‹‹ለፈርኦን አምላክ አድርጌሃለሁ›› እንዳለው እግዚአብሔር ቃል የመጣላቸውን ነቢያትንም ‹‹አማልክት ናችሁ አልሁ›› እንደተባለው ሁሉ የእርሱንም የፀጋ አምላክነቱን ሲገልጽ እንጂ የባሕሪ አምላክነቱን መግለጹ አይደለም በማለት መናፍቃን ምክንያት እንዳይሆናቸው ብሎ መሆኑን ሊቃውንት ያመሰጥራሉ፡፡ (ዘዳ 7፡1፣ መዝ 31(32)፡6)
ወልድ ለምን አላለውም ለሚለውም ምክንያታዊ ምላሽን ሊቃውንቱ ሰጥተዋል ወልድ ቢለው እስራኤል የእግዚአብሔር ልጆች እንደተባሉ ዛሬም ምዕመናን የጸጋ ልጅነትን በጥምቀት እንደሚያገኙት ሁሉ እርሱንም መናፍቃን የጸጋ እንጂ የባሕሪይ ልጅ አይደለም እንዳይሉ በሌላም በኩል ወልድ የሚለው የአብንና የወልድን አንድነት ብቻ እንጂ የሦስቱን አንድነት ስለማያሳይ ቃል የሚለው የስጋ ዌን ስም ግን የሦስቱን ማለትም የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስን አንድነት የሚያሳይ በመሆኑ ነው ‹‹ቃለ አብ ወቃለ መንፈስ ቅዱስ ወልድኒ ቃሎሙ ለአብ ለመንፈስ ቅዱስ ›› እንዲል
ይቀጥላል

No comments:

Post a Comment