Thursday, December 19, 2013

‹‹ፆምን ቀድሱ›› (ኢዩ1፡14)









‹‹ፆምን ቀድሱ›› (ኢ 1፡14)
አምላካችን እግዚአብሔር በነቢዩ በኢዩኤል ላይ አድሮ የእግዚአብሔር በረከት ከእስራኤል ጠፍቶ በምትኩ መቅሠፍትና መዓት ረሃብና ቸነፈር በመጣባቸው ጊዜ (ኢዩ 1፡1-13) ፆምን ቀድሱ ጉባኤውንም አውጁ ሽማግሌዎችንና በምድር የሚኖሩትን ሁሉ ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር ቤት ሰብስቡ ወደ እግዚአብሔር ጩኹ (ኢዩ 1፡14) አላቸው፡፡ ለመሆኑ ፆምን መቀደስ ማለት ምን ማለት ነው? እንዴትስ ይፈጸማል?






‹‹ቀደሰ›› የሚለው ቃል ቅዱስ አደረገ ፤ ለየ፤ አከበረ፤ አመሰገነ፤ ስዕለት ሰጠ የሚለውን ፍቺ ይዞ እናገኘዋለን፡፡ በዚህ መሠረት እግዚአብሔር አምላክ ለሙሴ እንዲህ ብሎ ተናግሮታል ‹‹በእስራኤል ልጆች ዘንድ ከሰውም እንሰሳም ማህፀንን የሚከፍት በኩር ሁሉ ለእኔ ቅድስልኝ የእኔ ነው›› (ዘጸ 13፡2) ይህም ማለት የበኩር ልጅ የሆነው ሁሉ ለእርሱ ይቀደሳል ፣ ለእርሱ ይለያል፣ ለእርሱ ይውላል፣ ለእርሱ እንደ ስዕለት ይሰጣል እንጂ ለሌላ ለተለየ ዓላማ አይውልም ማለት ነው አሮንና ልጆቹ ለክህነት ሥራ ከመመረጣቸው አስቀድሞ ሰዎች የበኩር ወይም የመጀመሪያ ልጆቻቸውን ለእግዚአብሔር አገልግሎት ይውሉ ዘንድ በእርሱ ፊት ይሰጡ ነበር ከከብት ወገኖችም የበኩር የሆኑት ሁሉ ለእግዚአብሔር መስዋዕት ሆነው ይቀርቡ ነበር፡፡
የተቀደሱ ልብሶች እግዚአብሔርን ለሚቀሰድሱ ካህናት አገልግሎት ይውሉ ዘንድ ተለይተዋል ከዚህ ጋር በተያያዘ እግዚአብሔር ለሙሴ እንዲህ ብሎት ነበር ‹‹እነዚህም ካህናት ይሆኑልኝ ዘንድ በወንድምህ ለአሮን ለልጆቹም የተቀደሰ ልብስ ያድርጉ›› (ዘጸ 26፡4)
የመሰዊያ ነዋየ ቅዱሳት ለእግዚአብሔር አገልግሎት ይውሉ ዘንድ አንድ ጊዜ ስለተለዩ ለሌላ አገልግሎት ወይም ዓላማ አይውሉም ማለት ነው ቤተ መቅደስም ለእግዚአብሔር የተለየ ልዩ ሥፍራ ነው፡፡ ቤትን ለእግዚአብሔር መቀደስ ማለት ለእግዚአብሔር አገልግሎት ማዋል ማለት ነው ይህ ቤት እግዚአብሔርን ለማምለክ ብቻ እንጂ ለሌላ አገልግሎት አይውልም ማለት ነው ጌታ ይህን አስመልክቶ ሲናገር ‹‹ቤቴ የጸሎት ቤት ተባለች›› (ማቴ 21፡13) ብሏል
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ለደቀመዛሙርቱ ‹‹… እኔ ራሴን ስለ እነርሱ እቀድሳለሁ›› (ዮሐ 17፡1) በማለት እርሱ ወደዚህ ዓለም የመጣው ራሱን ለእነርሱና ለቤተክርስቲያን ሊሰጥ መሆኑን ገልéEል ከዚህ በተመሳሳይ ቀናት ለእግዚአብሔር ተለይተዋል ተቀድሰዋልም ይህ በመሆኑም ‹‹የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ›› (ዘጸ 20፡8) ተብሎ እንደተፃፈ የሰንበት ቀን ተለይቶ ለእግዚአብሔር ስለተሰጠ በዚያን ቀን ምንም ሥራ አይሰራም እንዲሁም ወቅቶችን የእግዚአብሔር በዓላት የሚውሉባቸውን ቀናትና ስብሰባዎች የሚደረጉባቸውን ቀናት ለእርሱ ስለተቀደሱ በእነዚህ ቀናት ውስጥ የዓለምን ሥራ መሥራት አይፈቀድም (ዘሌ 23፡3-36)
ልክ እንደዚህ ሁሉ ጾምን መቀደስ ማለት ጾምን ለእግዚአብሔር መለየት ማለት ነው የጾም ቀናት የተቀደሱ ቀናት ናቸው ይህም ማለት ለእግዚአብሔር ተለይተዋል ማለት ነው እነዚህ ቀናት ለዓለም ለሚገቡ አይደሉም በእነዚህ ጊዜያት ራስን ከዓለምና ከዓለማዊ ሥራ በማራቅ ለእግዚአብሔር ራሳችንን የምንሰጥበት መንፈሳችንን በእግዚአብሔር ፊት የምናዋርድበት ተቋዋሚያችንን ዲያብሎስንና ሠራዊቱን በረቂቅ መሣሪያ የምንዋጋበት ጊዜ ነው፡፡ (ኤፌ 6፡10)
የጾማችን ዓላማ ምንድን ነው?
የምንጾመው ጾም ሥርዓት ስለሆነ ነው ወይስ መጀመርን የቀን መቁጠሪያ ስላሳወቀን ነው ወይስ ቤተክርስቲያን ስላወጀችልን የጾም ዓላማችን ይህ ከሆነ ውስጣዊውና ልባዊው ምክንያታችን ገና የተሟላ አይደለም በእርግጥ የቤተክርስቲያን ቀኖናና ትዕዛዛትን መቀበላችን ግድ ቢሆንም እንኳን ትዕዛዛትን ስንቀበል እንደ መንፈሳዊነቱ እንጂ እንዲሁ እንደ ጥራዝ ነጠቅ መሆን የለበትም ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያን ጾምን ስታቅድ የምትመለከተው የጾምን መንፈሳዊ ጥልቀት ነውና፡፡
በጾም ወቅት በክርስቲያኖች ዘንድ የሚስተዋሉ የተሳሳቱ የጾም ዓላማዎች ያሉ ሲሆን ከነዚህም መካከል አንዳንዶች የሚጾሙት የራስ ማረጋገጫ ለመስጠት ፣ ጻድቅ ወይም ሃይማኖተኝነት እንዲሰማቸው የራሳቸውን መንፈሳዊ ዜና ለማሰራጨት ፣ ትዕዛዛትን ያልዘነጉ መስለው ለመታየት ወይም ስለጾማቸውና ስለደረሱበት ደረጃ ከሰዎች ውዳሴ ከንቱ ለመቀበል ነው እንዲህ ባለው መንገድ የሚገዛ ሰው እርሱ  ወደ ተሳሳተ የክብር መስክ ይኸውም ወደ ኃጢዓት ውስጥ ይገባል፡፡
የክርስቲያች ጾም ዋነኛ ዓላማ ሊሆን የሚገባው ለእግዚአብሔር ካለን ፍቅር የተነሣ በተሰበረ ልብ ከእርሱ ጋር እንድንጣበቅ ሊሆን ይገባል በዚህ ወቅት ሥጋዊ ብልቶቻችን በነፍሳችን መንገድ ላይ እንቅፋት እንዳይሆኑ ይልቁንም በጾም አማካኝነት ከነፍሳችን ጋር ተባብረው እንዲሰሩ ማስማማት ይገባል በዚህ ዓይነት መልኩ በምንጾምበት ጊዜ በነፍሳችን ውስጥ እንድንኖር ከቁሳዊና ከሥጋዊ ደረጃ በላይ ከፍ እንላለን ይህንንም የምናደርገው መንፈሳችንንና ነፍሳችንን በአሰራሩ ውስጥ ካለው ከእግዚአብሔር መንፈስ ጋር አንድ ለማድረግና በእግዚአብሔር ፍቅርና ወዳጅነት ለመደሰት ነው፡፡ በእግዚአብሔር ፍቅርና ወዳጅነት መደሰት በእርግጥም የሕይወት ሁሉ መንገድ ነው ማለት ይቻላል ይሁን እንጂ ይህንን በጾም ጊዜ በስፋት በተጨማሪ ጥልቀት በተጨማሪ ጥበቃ እንደምንቀበለው መዘንጋት የለብንም ከዚህም በላይ ከእግዚአብሔር ጋር የሚሆን ይህ ደስታ በመላው ሕይወታችን ውስጥ እንዲዘልቅ ልምምድና ዝግጅት ልናደርግ ያስፈልገናል፡፡
ሌላው የጾም ዓላማችን ሊሆን የሚገባው እግዚአብሔርን ወደ እኛ ለማቅረብ ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስን ከእኛ ለማራቅ ሊሆን ይገባል ‹‹እንግዲህ ለእግዚአብሔር ተገዙ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙ ከእናንተም ይሸሻል ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል›› (ያዕ 4፡8) ተብሎ እንደተፃፈልን፡፡ 






ለጸሎት መንፈሳዊ ንባብን ለማንበብና ለተመስጦ ዕድሉን ስለሚሰጥ በጾም መካከል ተለይቶ የመቀመጥ ሁኔታ ይኖራል በመሆኑም ጾም ሰውን እንዲነቃና እንዲሰግድ እገዛ ያደርግለታል ንቁ መሆንና ስግደት ደግሞ የጾሎትን መስክ ያደራጃሉ ጾም ፈቃድን ይቆጣጠራል ፍላጎታችንም ድል ይነሣል ይህ ደግሞ የእግዚአብሔር መንገድ ወደ ሆነው ወደ ንስሐና ከእርሱ ጋር ወደ መታረቅ ይመራል፡፡ ስለዚህም ክርስቲያን የሚጾመው ስለ እግዚአብሔር ፍቅርና ከእርሱ ጋር ለሚሆን ወዳጅነት ነው ከምንም በላይ የምንጾመው ጾም ዓለማዊና ቁሳዊ ነገሮችን ከእኛ ለማራቅ ነው ይህ ደግሞ ዘላለማዊነትንና ከእግዚአብሔር ጋር ለመጣበቅ ያግዘናል፡፡
በእግዚአብሔር ያልተቀደሱ አፅዋማት
እግዚአብሔር የማይካፈልባቸው አጽዋማት ሁሉ ለእግዚአብሔር ያልተቀደሱ አጽዋማት ናቸው፡፡ ክርስቲያን እግዚአብሔር በሕይወቱ ውስጥ ተካፋይ ሳይሆን ጾም የሚጾም ከሆነ ቢጾምም ማንነቱ ስለማይለወጥ በከንቱ ይለፋል የሚኖረው ከስህተቶቹ ሁሉ ጋር ስለሚሆን ምንም ዓይነት መሻሻል በእርሱ ዘንድ አይታይም፡፡ አንዳንድ አገልጋዮችም ጾምን እንደተለመደ ድርጊት አድርገው ሲቆጥሩ ወይም ስለ ዝና ሲሉ ብቻ በእፍረት ሲጾሙ ይስተዋላሉ ነገር ግን የእንደነዚህ ዓይነት ሰዎች ጾም ነፍስ ምንም ዓይነት ተካፋይነት ሳይኖራት ሥጋ ጋር ብቻ የተዛመዱ ሥጋዊ ጾም ነው፡፡
በሌላው ጾማቸው የተራ ጥበብ መግለጫና ከምግብ የመከልከል ችሎታ የሚገለጥበት ወይም ሥጋዊ ምኞታቸውን ሳይገቱ ከክፉ ሥራና ሀሳብ ሳይቆጠቡ እንዲሁ ከምግብ ብቻ የሚጣሉ ምስኪኖችም ይስተዋላሉ፡፡
አንዳንዶችም ጾም እግዚአብሔርን ሦስተኛ ወገን አድርጎ ሳይጨምር እንዲሁ በሰውና በምግብ መካከል ብቻ የሚደረግ ዝምድና እንደሆነ አድርገው ያቀርብታል እነዚህ ሰዎች በጾማቸው ወቅት ጥንቃቄ የሚያደርጉት፡-
·         ከምግብ የምንከለከልበት ጊዜ ምን ያህል ረዥም ነው?
·         የሚመገቡት መቼ እንደሆነ?
·         ከምግብ የመከልከላቸውን ጊዜ ሊያራዝሙት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ?
·         የሚመገቡትስ ምግብ ምንድን ነው?
·         ከተወሰኑ የምግብ ዓይነቶች ራሳቸውን የሚጠብቁት እንዴት ነው?
·         ለቀናት የሚጾሙትስ እንዴት ነው? በሚሉት ጥያቄዎቻቸው ዙሪያ ነው እነርሱ የሚያስቡት በጾም ውስጥ ያሉት ወገኖች ሁለት እንደሆኑ ነው፤ እነርሱና ምግብ ወይም እነርሱና ሥጋቸው ብቻ ሲሆኑ እግዚአብሔርን በምንም ዓይነት መንገድ በጾማቸው ውስጥ ተካፋይ አያደርጉትም፡፡
ጾም ከሥጋ ጋር የሚደረግ ተራ ድርድር አይደለም ይልቁንም ከእግዚአብሔር ጋር የሚደረግ ድርድር ነው እግዚአብሔርን በመካከሉ የማያስገባ ማንኛውም ዓይነት ጾም ሙሉ ለሙሉ ጾም ሳይሆን የተሃብ አድማ ነው፡፡ የምንጾመውም የምንበላውም ለእግዚአብሔር ክብር ሊሆን ይገባል ‹‹ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት›› እንዲል መጽሐፍ የምንበላው ለእግዚአብሔር ነው፡፡
ይህ የሚሆነውም ሰውነታችን እግዚአብሔርን ያገለግል ዘንድ ብርታቱን እንዲያገኝና ሥራውን በታማኝነት ለሰዎች ማከናወን እንዲያስችለው ነው የምንራበው ስለ እግዚአብሔር ብለን ስለሚሆን በጾም ሥጋችን በእግዚአብሔር ላይ ኃጢዓት እንዳይፈጽም እንረታዋለን ይህም ማለት እኛ ከቁጥጥራችን በታች እናውለዋለን እንጂ እርሱ በቁጥጥር ሥር አያውለንም ማለት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሥጋዊ ፍላጎቶችና ምኞቶች ሊቆጣጠሩን እንዳይችሉ እናደርጋቸዋለን ጠባያችንን እንደ መንፈስ ፈቃድ እንጂ እንደ ሥጋ ፈቃድ የማናስለምደው ስለ እግዚአብሔር ፍቅር ብለንና ከመንፈሱ ጋር ያለንን ተካፋይነት ለመግለጽ ነው ‹‹በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ›› (1ቆሮ 6፡20) ተብሎ እንደተፃፈ፡፡
የተሳሳቱ ተቀባይነት የሌላቸው አጽዋማት
1.   ከሰዎች ውዳሴ ለማግኘት ሲባል የሚደረግ ጾም አንዱ ነው
እንዲህ ዓይነቱ ጾም ሰዎች ተመልክተው ያወድሱት ዘንድ ሆነ ተብሎ የተገለጠና የተጋለጠ ጾም ነው መድኅኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለዚህ ጾም በተራራው ስብከቱ ውስጥ እንዲህ በማለት አስተምሮናል፡፡
‹‹ስትጠሙም እንደግብዞች አትጠውልጉ ለሰዎች እንደ ጦመኛ ሊታዩ ፊታቸውን ያጠፋሉና፤ እውነት እላችኋለሁ ዋጋቸውን ተቀብለዋል አንተ ግን ስትጦም በስውር ላለው አባትህ እንጂ እንደ ጦመኛ ለሰዎች እንድትታይ ራስህን ተቀባ ፊትህንም ታጠብ፤ በስውር የሚያይ አባትህ በግልጥ ያስረክብሃልና›› (ማቴ 6፡16-18)
ስለዚህም ለሰዎች ውዳሴ ተብሎ የሚቀርብ ጾም ለእግዚአብሔር ምንም ሊያደርግለት የማይችል ጾም ነውና እንዲህ ያለው ጾም የተሳሳተ ጾም ነው፡፡
2.   የትዕቢተኞው ፈሪሳዊ ጾም ተቀባይነት ከሌላቸው አጽዋማት መካከል አንዱ ነው
ይህ ፈሪሳዊ በእግዚአብሔር ፊት ለይስሙላ ቆሞ ‹‹…. በየሣምንቱ ሁለት ጊዜ እጾማለሁ ፤ ከማገኘውም ሁሉ አስራት አወጣለሁ›› ነበር ያለው ይህም ሳይበቃው ቀራጩን በንቀት እየተመለከተ ‹‹እንደ ሌላ ሰው ቀማኞችና አመፀኞች አመንዝሮችም ወይም እንደዚህ ቀራጭ ስላልሆንሁ አመሰግንሀለሁ›› (ሉቃ 18፡9-14) በማለት ተናግሯል ይህን በማለቱና በማድረጉ ልቡ እንደተሰበረው ቀራጭ ጸድቆ ወደ ቤቱ ሊመለስ አልቻለም፡፡
ይህ ምሳሌ የሚያሳየን በትህትናና በተሰበረ ልብ የማይታጀብ ጾም በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት እንደሌለው ነው ምክንያቱም ይህን የሚያከናውነው ሰው ራሱን ጻድቅ አድርጉ ስለሚቆጥር ሌሎችን ይንቃል፤ ይጠላልም (ሉቃ 18፡9)  
3.   የተሳሳተ ዓላማ ያለው ጾም ተቀባይነት የለውም ለዚህ ምሳሌ የሚሆነን ጾም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስን ለመግደል አይሁድ የተማማሉበት ጾም ነው ስለ እነርሱ ሴራ የተጻፈው ቃል እንዲህ የሚል ነው፡- ‹‹…..አይሁድ ጳውሎስን እስኪገድሉት ድረስ እንዳይበሉና እንዳይጠጡ በመሀላ ተስማሙ ይህንንም ሴራ ያደረጉት ሰዎች ከአርባ ይበዙ ነበር፣›› (ሐዋ 23፡12-13)
የእነዚህ ሰዎች ጾም ኃጢዓት ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም በመንፈሳዊ ዐይን ከተመለከትነውም ጾም ብለን ልንጠራው አንችልም፡፡
4.   በነቢዩ ኤርሚያስ ዘመን የነበሩት ሰዎች የኃጢዓት ጾም ሌላው ተቀባይነት የሌለው ጾም ነው
እግዚአብሔር አምላክ ይህን ጾም ስላልተቀበለው ስለ ሕዝቡ ለኤርሚያስ እንዲህ በማለት ነግሮት ነበረ ‹‹… በዚህ ሕዝብ ስለመልካም አትጸልይላቸው በጾሙ ጊዜ ጸሎታቸውን አልሰማም፤ የሚቃጠለውን መስዋዕትና የእህሉን ቁርባን ባቀረቡ ጊዜ አልተቀበላቸውም በሰይፍና በራብ እና በቸነፈር አተፋቸዋለሁ›› (ኤር 14፡11-12)
እግዚአብሔር አምላክ የእነዚህን ሰዎች ጾም ጸሎትና ቁርባን አልተቀበላቸውም ምክንያቱም እነርሱ ይመሩት የነበረው የክፋት ሕይወት ስለሆነና ልባቸው በእርሱ ፊት ንጹሕ ስላልነበረ ነው ስለሆነም ያለንስሐ የሚደረግ ጾም ተቀባይት የለውም፡፡
እግዚአብሔር ከተራበ ሰውነት ይልቅ ንጹሕ ልብ ይፈልጋል የሰው ልብ ከኃጢዓት አንደበቱም ሀሰት ከመናገር ካልታቀበ በስተቀር ጾሙ ተቀባይነት የለውም ይህን ሳያደርግ ሥጋውን ለመቃጠል አሳልፎ ቢሰጥም እንኳ አንዳች የሚያተርፈው ነገር አይኖረውም (1ቆሮ 13፡3)
5.   ከምህረትና ከምጽዋት የራቀ ጾም ተቀባይነት የለውም እግዚአብሔር ይህንን ነጥብ ለነቢዩ ለኢሳይያስ እንዲህ በማለት በስፋት አብራርቶለታል ‹‹ስለ ምን ጾምን አንተም አልተመለከትከንም ሰውነታችንንስ ስለምን አዋረድን አንተም አላወቅህም ይላሉ?...እነሆ ለጥልና ለክርክር ትጾማላችሁ በግፍ ጡጫም ትማታላችሁ እኔ የመረጥሁት ጾም ይህ ነው? በውኑ ይህንን ጾም በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ ቀን ትለዋለህ? እኔስ የመረጥሁት ጾም ይህ አይደለምን? የበደልን እስራት ትፈቱ ዘንድ፤ የቀንበርንስ ጠፍር ትለቁ ዘንድ የተገፉትንስ አርነት ትሰዱ ዘንድ ፤ ቀንበሩንስ ሁሉ ትሰብሩ ዘንድ አይደለምን? እንጀራህንስ ለተራበ ትቆርስ ዘንድ ስደተኞቹን ድሆች ወደ ቤትህ ታገባ ዘንድ የተራቆተውንስ ብታይ ታለብሰው ዘንድ አይደለምን?››
ከምህረት ሥራና ከንጹሕ ልብ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዞ የማይሄድ ጾም ተቀባይነት የለውም፤ ጾም በትሕትና፤ ማቅ በመልበስ፤ አመድ በመነስነስና አንገትን ዝቅ በማድረግ ቢከናወንም እንኳ፡፡
6.   ለእግዚአብሔር ያልሆነ ጾም ተቀባይነት የለውም አንዳንድ ሰዎች ሐኪም ስላዘዛቸው ወይም የሚበሉት ምግብ ለጤናቸው ተስማሚ ስላልሆነ፤ ሌሎችም ደግሞ ማራኪ ተክለ ቁመና (ሰውነት)ና ገጽታ እንዲኖራቸው ለመክሳት ብለው ከምግብ ይከለከላሉ ይጾማሉ ነገር ግን እንዚህ ሰዎች የሚጾሙት ለእግዚአብሔር ብለው ስላልሆነ አንዳችም ዓይነት መንፈሳዊ ውጤት ሊያገኙ አይችሉም፡፡
በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ያለው ጾም
መንፈሳዊ ጾም ከእግዚአብሔር ጋር ፍጹም የሆነ ዝምድና የሚመሠረትበት ጾም ነው ጾም እግዚአብሔር በሕይወታችን ውስጥ እንዳለ የምናውቅበት ምልክት ነው ጾም ማለት እግዚአብሔር ያለበት የቅድስና ጊዜ እና እግዚአብሔር እስከመጨረሻ ድረስ ከእኛ ጋር ለመሆኑ በጠባያችን ውስጥ የሚታይበት መንገድ ነው በእያንዳንዱ የጾማችን ቀን ውስጥ ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ዝምድና መንፈሳዊነታችን ይጨምራል በመንፈሳዊነት ማደጋች ደግሞ የጾማችን ፍሬ ምን እንደሆነ ለማወቅ ስለምንሻ ዘወትር በጉጉት ውስጥ እንድንቆይ ከማድረጉም ባሻገር በጾማችንና በእግዚአብሔር መካከል ያለው ግንኙነት ምንድን ነው የሚለውን ጠቃሚ ጥያቄ እንድንመረምር ያደርገናል፡፡
እግዚአብሔር ከእኛ ጾም ያገኘው ምንድን ነው? እኛስ ከእግዚአብሔር ያገኘነው የጾማችን የሱባኤያችን ውጤት ምንድን ነው?
·         ጾማችን በሕይወታችን ውስጥ የተለየና ቀናቶቹ የተቀደሱ ሆነው መንፈሳዊ መነቃቃትን ለእኛ በማደል የእግዚአብሔርን ቸርነት መሐሪነት ጠብቆትና ፍቅር ልናስተውል ይገባል
·         እንደ መንፈሳዊ እንጂ እንደ ሥጋ ፈቃድ ላለመኖር ራስን ማለማመድ
·         በጾማችን ወቅት ልባችን ሐሳባችን ፈቃዳችን ለእግዚአብሔር መቀደስ ያስፈልጋል ጾም መንፈስን ስለሚቀድስ የእግዚአብሔርን ቁጣ በሚቀሰቅሱ ማናቸውም አመጻዎች ላይ መታቀብን ያውጃል
በመሆኑም ከእንሰሳት የሚገኙ ምግቦችን ወይም አጠቃላይ ምግቦችን ማቆማችን በተመሳሳይ ጊዜ የተለያዩ ኃጢዓቶቻችን ማቆም አለመቻላችን ለእኛ በቂ ነገር አይደለም ልናደርገው የሚገባን ነገር ቢኖር በምንሠራው ስራ ውስጥ ‹‹የአንተ ፈቃድ እንጂ የእኛ ፈቃድ አይሁን›› በማለት ፈቃዳችንን ሁሉ ለእግዚአብሔር ማስገዛት ብቻ ነው
·         በጾማችን ውስጥ የሕይወት ለውጥ ማምጣታችን እናስተውል፤ ደካማ ጎናችን ማስተካከላችን፤ ጉድለታችን መሙላታችን
እኛ በሕይወታችን ምንም ዓይነት ለውጥ ሳናመጣ አስቀድመን በነበርንበት ሁኔታ ውስጥ እያለን እስከ አሁን ድረስ ስንት አጽዋማት እንዳሳለፍን እናስተውል
·          ጾም እንዲሁ የሥርዓቶች ስብስብ ወይም የመከራ ጊዜ አይደለም ይልቁንም ቤተክርስቲያን ለእኛው መንፈሳዊ ጥቅም ለነፍሶቻችን መነቃቃት ልንከተለው የሚገባንን መመሪያ ለማስታወስና ከእግዚአብሔር ጋር እርቅ ለመመሥረት የምንችልበት ሌላ አዲስ ዕድልና ምዕራፍ ነው፡፡
ማጠቃለያ
ጾምን መቀደስ ማለት ጾምን ማክበር ማወጅ ሲሆን በእነዚህ  በተለዩ ቀናት ውስጥ ራሳችንን በፍጹም ሕይወት ውስጥ ለማኖርና ለፍጹምነት ሕይወት ልምምድ የምናደርግበት ጊዜ ነው በመሆኑም እነዚህ የተለዩ ቀናት እንደሌሎቹ ቀናት እንዲህ ማለፍ የለባቸውም ከእግዚአብሔር ጋር በሚኖረን ዝምድና ውስጥ አዲስ ምዕራፍ ይከፍታሉና ይህ ምዕራፍ ደግሞ በአዲስ ስሜትና በአዲስ መንፈስ ውስጥ የምናልፍበት በመሆኑ በእነዚህ ቀኖች ውስጥ ጠባያችን ካስተካከልን ለሙሉ ሕይወት ዘመናችን የሚበቃ ቅድስናን እናገኛለን ከምንም በላይ ይህ ጊዜ በምንችለው ሁሉ ራሳችንን ሙሉ በሙሉ ለእግዚአብሔር የምናስገዛበትና ከእርሱ ጋር የሚኖረንን ዝምድና የምናጠብቅበት ጊዜ ነው፡፡


No comments:

Post a Comment