Friday, December 27, 2013

‹‹ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ›› (ማር 13፡15)









     ቀድሞ ከእግዚአብሔር ለቅዱሳን አንድ ጊዜ የተሰጣቸውና በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ጸንታ የተመሠረተችው በሰማዕታትም ደም ያሸበረቀችው ቅዱስት ቤተክርስቲያን ከተመሠረተችበት ዕለት አንስቶ በውጊያ ላይ ብትሆንም እንኳ ሁል ጊዜ ድል ታደርጋለች እንጂ ተሸንፋ አታውቅም ታላቁ የቤተ ክርስቲያን አባት ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ስለቤተክርስቲያን በገለጸበት ድርሳኑ ‹‹ሰውን በትታገልና በትዋጋ ታሸንፈዋለህ ወይም ያሸንፍሃል ቤተክርስቲያንን ግን ለማሸነፍ አይቻልም፤ ቤተክርስቲያን ሁል ጊዜ ትዋጋለች ተሸንፋ ግን አታውቅም ዲያብሎስ ዝናሩን አራገፈ፣ ቀስቱን ጨረሰ ቤተክርስቲያንን ግን አልጎዳትም›› ብሏል፡፡
ርቱዐነ አንደበት የሆኑ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን መናፍቃንን በቃልም ሆነ በጽሑፍ ሲዋጉ ኖረዋል የአበውን አሰረ ፍኖት የተከተለ ይህ ትውልድም የአባቶችን አደራ ተቀብሎ በግብር ሊመስላቸው ይገባል፡፡








ውጊያው መልኩን ቀሯል እንጂ አልቆመም አጽራረ ቤተክርስቲያንም መልካቸውን እየቀያየሩ በክርስቶስ አፀደ ወይን በቤተክርስቲያን ላይ የኑፋቄ እንክርዳዳቸውን እየዘሩ ነው፡፡
የግብር አባታቸው ዲያብሎስም የትዕቢት ዝናሩን አስታጥቆ መምህረ ትህትና ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን አብነት ባደረጉ ትሁታን ላይ አዝምቱአቸዋል የዲያብሎስ ደቀመዛሙርት ራሳቸውን የእውነት ደቀመዛሙርት አስመስለው ምዕመኑን ወደ ጥፋት ገደል እየወረወሩት ነው፡፡
‹‹የክርስቶስ ኢየሱስ የሆኑ ስጋን ከክፉ መሻቱ ጋር ሰቀሉ›› በማለት የቤተክርስቲያን የአጥቢያ ኮከብ ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረው እውነተኛ ክርስቲያኖች የሥጋን ፈቃድ የማይከተሉ ስጋቸውን በተለያዩ መንፈሳዊ ተጋድሎች እየጎሰሙ ለነፍሳቸው የሚያስገዙ ናቸው፡፡
በወንጌል ስም የሚነግዱ አስመሳይ መምህራን ግን ‹‹በጸጋው ድነሃልና ሕግ መጠበቅ ተጋድሎ ማድረግ አያስፈልግም›› እያሉ ትዕዛዘ እግዚአብሔር እንዲጣስ መንፈሳዊ ተጋድሎ እንዲናቅ ‹‹ገድል ወይስ ገደል›› በማለት በትዕቢትና ባለማስተዋል ሽንጣቸውን ገትረው ያስተምራሉ፡፡
የዘመኑ ፍጻሜ የደረሰበት ይህ ትውልድ ሕይወት የሚገኝበት መጽሐፍ ቅዱስን በራሱ አንድምታ እንደገዛ ፈቃዱ፤ እንደ ሥጋ አምሮቱ እየተረጎመ በጥፋት ጎዳና እየነጎደ ነው አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ መዘው ጉንጭ አልፋ ክርክር የሚይዙ ሳያውቁ አውቀናል፤ ሳይበቁ በቅተናል የሚሉ መሳሐትያን መከሰት ከጀመሩ ዘመናት አልፈዋል፡፡
ቅዱስ ጴጥሮስ ስለ እነዚህ ቢጽ ሐሳውያን መናፍቃን ሲያስተምር ‹‹በእነዚያ ዘንድ ለማስተዋል የሚያስቸግር ነገር አለ ያልተማሩትና የማይጸኑትም ሰዎች ሌሎችን መጻሕፍት እንደሚያጣምሙ እነዚህን ደግሞ ለገዛ ጥፋታቸው ያጣምማሉ እንግዲህ እናንተ ወዳጆቼ ሆይ ይህን አስቀድማችሁ ስለምታውቁ በዓመፀኞቹ ስህተት ተስባችሁ ከራሳችሁ ጽናት እንዳትወድቁ ተጠንቀቁ ብሏል›› (ጴጥ 3፡16-18)
እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ቃልን በራስ ስሜት ተመርቶ መተርጎም እንደማይቻል ሲያስገነዝብም ‹‹ይህንን በመጀመሪያ እወቁ በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደም ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ›› (2ጴጥ 1፡20) ነው ያለው
በመጽሐፍ ቅዱስ ያለውን ቃል እግዚአብሔር ለጻሐፍቱ ምስጢሩን ገልጦ ያጻፋቸው በመሆኑ የቃሉን ትርጉም ለመረዳት የመንፈስ ቅዱስ እገዛ ያሻል አለበለዚያ በራስ ስሜት ተመርቶ ቃሉን እተረጉማለሁ ማለት ወደ ጥፋት ገደል ራስን መወርወር ነው፡፡
ንዋየ ኅሩይ ቅዱስ ጳውሎስም መጽሐፍ ቅዱስን በጥሬ ንባብ ብቻ መረዳት እንደማይቻል ሲያስረዳ ‹‹ፊደል ይገድላል መንፈስ ግን ሕይወትን ይሰጣል›› ብሏል (2ቆሮ 3፡6)
በዚህ ትምህርቱም በመንፈስ ቅዱስ ተርጓሚነት የተገለጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምስጢር ማወቅ የዘላለም ሕይወትን እንደሚያስገኝ አስረድቷል፡፡
ዳሩ ግን ከብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ መካከል አንዱን ለይቶ በማውጣት ብቸኛው የመዳን መንገድ በዚህ ጥቅስ ላይ የተጻፈውን መፈጸም ብቻ ነው ብሎ ጥቅሱንም በተሳሳተ መንገድ አዛብቶ ተርጎሞ የሚያስተምር ሰው እርሱም ጠፍቶ ሌሎችንም ያጠፋል እንዲህ ዓይነቱ ሰው እውነቱን ወደ ማወቅም አይደርስም እንደ ጋሪ ፈረስ በአንድ አቅጣጫ ብቻ የሚያይ ነውና፡፡
የእግዚአብሔር ቃል አንዱ ከአንዱ የሚጋጭ ሳይሆን ሁሉም አንድ ሃሣብን አንድ መንገድን የሚጠቁሙ ናቸው መጻሕፍት እርስ በእርሳቸው የሚጋጩ መስለው የሚታዩት ትርጉማቸውን ካለማወቅ የተነሣ ነው መጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ትርጉምና ምስጢር ያለው ስለሆነ ንባቡን ካነበቡ በኋላ ትርጉሙን ምስጢሩን መረዳት ያሻል ንባቡ እርስ በእርሱ የሚጣላ ቢመስልም ትርጉምና ምስጢር ግን ያስታርቀዋል፡፡
የመናፍቃን ትልቁ ችግራቸውም መጸሐፍ ቅዱስን በንባብ ብቻ በመረዳት መሞከራቸው ነው አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ በጥሬ ንባቡ ወስዶ መመሪያ ማድረግ ምን ያህል እንደሚጎዳ ከሚከተሉት ምሳሌዎች እንማራለን፡፡
ሕገ እግዚአብሔርን አምዘግዝገው በመጣል በእምነት ብቻ እንድናለን የሚሉ ክፍሎች ለዚህ ለተሳሳተ አመለካከታቸው መሠረት የሚያደርጉት ‹‹በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እመን አንተና ቤተሰቦችህም ትድናላችሁ›› የሚለውን ጥቅስ ነው ሐዋ 16፡31
ተጠራጣሪዎች ይህንን ቃል በተሳሳተ መልኩ ስለተረዱት በሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የተገለፀውን ለመረዳት እንዳይችሉ አእምሯቸውን ወስነውታል እንደ ሥጋ ፈቃዳቸው የሚመላለሱ በመሆናቸው ለምግባር ቦታ አይሰጡም ‹‹ምግባር ለጽድቅ አይጠቅምም›› ባዮች ናቸውና
ዳሩ ግን ‹‹ሰው በእምነት ብቻ ሳይሆን በሥራ እንዲጸድቅ ታያላችሁ እንደዚሁም ጋለሞታይቱ ረዓብ ደግሞ መልዕክተኞችን ተቀብላ በሌላ መንገድ በሰደደቻቸው ጊዜ በሥራ አልፀደቀችምን? ከነፍስ የተለየ ስጋ የሞተ እንደሆነ እንዲሁ ደግሞ ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው›› በሚለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት የዝሆን ጆሮ ይስጠን ብለዋል፡፡ (ያዕ 2፡24)
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚች ምድር በሥጋ ተገልጦ ይመላለስ በነበረበት ጊዜ አንድ ሰው ወደ እርሱ ቀርቦ ‹‹መምህር ሆይ የዘላለም ሕይወት እንዳገኝ ምን መልካም ነገር ላድርግ አለው እርሱም ስለ መልካም ነገር ለምን ትጠይቀኛለህ? መልካም የሆነ አንድ ነው ወደ ሕይወት መግባት ብትወድ ግን ትዕዛዛትን ጠብቅ አለው እርሱም የትኞቹን አለው ኢየሱስም አትግደል፣ አታመንዝር፣ አትስረቅ፣ በሐሰት አትመስክር አባትና እናትህን አክብር ባልንጀራህንም እንደራስህ ውደድ አለው›› (ማቴ 19፡16-20)
እንግዲህ ምን እንላለን? ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ የዘላለም ሕይወትን ለማግኘት ሕግጋትን ትዕዛዛትን ጠብቁ እያለ እነርሱ አይደለም የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት እምነት ብቻ ነው የሚያስፈልገው ሊሉ ይችላሉ? ቤየትኛው ሥልጣናቸው በየትኛው መብታቸው?
እኛስ ልዑለ ባሕርይ አምላክ የተናገረውን አክብረን በመያዝ ሰው በእምነት ብቻ ሳይሆን በመልካም ሥራውም ይጸድቃል እንላለን እንዲህ ስንል ግን ሰው ሕግን በመጠበቁ ብቻ ይድናል ማለታችን እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል ‹‹የሕግን ሥራ በመሥራት ሥጋ የለበሰ ሁሉ በእርሱ ፊት ስለማይጸድቅ ነው›› የሚለውን የሐዋርያውን መልዕክት እናስተውላለን (ሮሜ 3፡20)
 እንደ ቸርነቱ ብዛት በእምነት ሆነው ሕጉን የሚጠብቁ ትዕዛዙንም የሚያከብሩ ለመንግስቱ ይበቃሉ ጌታችን ፣ ሐዋርያትና ነቢያትም ያስተማሩን ይህንን ነው፡፡








ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ሁሉም በአንድነት ተስተካክለው የበደሉበትን ያን የኦሪት ዘመን ወደ ኋላ መለስ ብሎ በመቃኘት ሁሎችም ከአባታቸው ከአዳም የተነሣ የኃጢዓት ባሪያዎች ሆነው ሲኖሩ ሳለ የሰው ፍቅር አስገድዶት የተበደለውን በደል ሳይመለከት የሰው ልጅ በስህተት ምክንያት አጥቶት የነበረውን ክብር መልሶ ሊያጎናጽፈው ወልደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛ ሆኖ በመልዕልተ መስቀል ዋለ፣ ብሎ ይህን የቤዛነት ሥራ በአድናቆት ሲገልጽ እንዲህ አለ ‹‹ሁሉ ኃጢዓትን ሰርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሏቸዋል በኢየሱስ ክርስቶስም በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ››  (ሮሜ 3፡23)
ከላይ በተጠቀሰው የመጽሐፍ ክፍል እንደተገለጠው ሐዋርያው ‹‹በዘመነ ኦሪት አይሁዳዊ፣ አሕዛብ ሳይባል ሁሉም በአንድነት ተስተካክለው በድለው ስለነበረ ከእግዚአብሔር ጸጋ በታች ነበሩ ጌታም በቸርነቱ ብዛት እገሌ ወእገሌ ሳይል ከአዳም ጀምሮ እስከ እርሱ መሰቀል ድረስ በሲኦል ይማቅቁ የነበሩትን የሰው ልጆች ያለ ዋጋ በነጻ (በጸጋው) ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍሶ ቤዛ ሆኖ አድኗቸዋል›› ለማለት ነው የፈለገው ፡፡ ነገር ግን ‹‹…የተናገረውን መልካም ሥራ አያስፈልግም፣ በሕግ አይጸደቅም፣ ሕግን ሻሩ፣ በተጋድሎ አይደለም፣ የእግዚአብሔር መንግስት የምትወረሰው እንደው በነጻ ያለምንም ሥራ ያለምንም ተጋድሎ ነው…›› በማለት ከላይ የተጠቀሰውን ጥቅስ እየጠቀሱ ስተው የሚያስቱ ሰዎች ምንኛ የርኩስ መንፈስ መጫወቻ እንደሆኑ ሊረዱት ይገባቸዋል፡፡
ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የተማሩ ለሁሉ ነገር ቀዳሚ የሆኑት ቅዱሳን ሐዋርያት ‹‹ወደ እግዚአብሔር መንግስት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል›› በማለት የእግዚአብሔር መንግስት በዋዛ በፈዛዛ እንደማትገኝ አስገንዝበዋል (ሐዋ 14፡22) የዘመናችን ሐሳውያን ደግሞ እንዳው ያለምንም ተጋድሎ እጅህንና እግርህን አጣምረህ ተዛልለህ ‹‹ኢየሱስ ጌታ ነው›› እያልክ በየመንደሩና በየመንገድ በመጮህ ትድናለህ እያሉ ሰውን በቀሙ አጃጅለውት በየመጠጥ ቤቱ ሳይቀር ፎካሪ አቅራሪ አድርገውታል፡፡
በእርግጥም በማቅራራት ብዛት የሚዳን ቢሆን ኖሮ እኛም በመሰልናቸው ነበር ዳሩ ግን የእግዚአብሔር መንግስት ሐዋርያት እንዳስተማሩት መች በዋዛ የምትገኝ ሆነችና ‹‹ጻድቅም በጭንቅ የሚድን ከሆነ ዓመጸኛውና ኃጢዓተኛው ወዴት ይታይ ዘንድ አለው?›› ተባለ እንጂ መቼ ሰነፍ ይገባባትል ተባለ? (1ጴጥ 4፡18)
አበው ‹‹ከመጠምጠም መማር ይቅደም›› እንዲሉ መናፍቃን አስቀድመው ቢማሩ ኖሮ የጥቅስ ጭራ ይዘው በመሮጥ የዋሁን ምዕመን እናሳውቅህ በማለት ወደ ባሰ የጥፋት ማጥ ባልጨመሩት ነበር፡፡








እንግዲህ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ‹‹ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ ብዙዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉ ብዙ ሐሰተኛ ነቢያትም ይነሣሉ ብዙዎችንም ያስታሉ እስከመጨረሻው የሚጸና ግን እርሱ ይድናል›› ሲል እንደተናገረ ዛሬ በሀገራችን በኢትዮጵያ ብቻ ከ242 በላይ የተለያዩ ሃይማኖቶች ተመስርተዋል በስሜ ይመጣሉ ሲል በእኔ ስም ይነሣሉ ማለቱ ነው (ማቴ 2፡6 ፣ ማቴ 24፡11) እነርሱ ምንም እንኳን በተለያየ ስያሜ የእምነት ድርጅት መስርተው ቢመጡም እውነታው ግን ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ሕይወት የሚገኝበትን ትምህርት የማይታገሱበት ዘመን ይመጣልና ነገር ግን ጆሮዎቻቸውን ይመልሳሉ ወደ ተረት ፈቀቅ ይላሉ›› (1ኛ ጢሞ 4፡3)
‹‹አንዳንዶች ስተው የሚሉትን ወይም ስለ እነርሱ አስረግጠው የሚናገሩትን ሲያስተውሉ የሕግ አስተማሪዎች ሊሆኑ እየወደዱ ወደ ከንቱ ንግግር ፈቀቅ ብለዋል›› ሲል የተናገረው ነው (1ኛ ጢሞ 1፡7) በመካከላችሁ ደግሞ ሐሰተኞች አስተማሪዎች ይሆናሉ እነርሱም የዋጃቸውን ጌታ እንኳ ክደው የሚፈጥንን ጥፋት በራሳቸው ላይ እየሳቡ የሚያጠፉ ኑፋቄን አሾልከው ያገባሉ›› (2ጴጥ 2፡1)
እንደ ገዛ ምኞታቸው ለራሳቸው አስተማሪዎችን ያከማቹ፣ እውነተኛው የቤተክርስቲያን ትምህርት ጆሮአቸውን ያሳከካቸው ብቻ አይደሉም ‹‹እንዲህ ያሉት ለገዛ ሆዳቸው እንጂ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ አይገዙምና በመልካምና በሚያቆላምጥ ንግግርም ተንኮል የሌለባቸውን ሰዎች ልብ ያታልላሉ›› (ሮሜ 16፡17)
‹‹ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ ደቀመዛሙርትንም ወደ ኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎች በመካከላችሁ እንዲነሱ እኔ አውቃለሁ›› (ሐዋ20፡29) ተብሎ ትንቢት የተነገረባቸው ለክርስቶስ መስቀል ጠላቶች ሆነው የሚመላለሱ ሆዳቸው አምላካቸው የሆነ አባታቸው ዲያብሎስ ራሱን የብርሃን መልአክ እስኪመስል ድረስ ሲለውጥ እነርሱ አገልጋዮቹ ደግሞ የጻድቃን አገልጋዮች የሚመስሉ ነገር ግን የክርስቶስን ወንጌል የሚያጣምሙ ሐዋርያው ‹‹እኛ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰበክላችሁ የተረገመ ይሁን›› ብሎ ያወገዛቸው ናቸው (ፊልጵ 3፡18 ፣ ዮሐ 8፡41 ፣ 2ኛ ቆሮ 11፡14 ፣ ገላ 1፡6) ልዑለ እግዚአብሔር አስቀድሞ በነቢዩ ላይ አድሮ ‹‹ውሸታችሁን ለሚሰሙት ሕዝቤ እየዋሻችሁ ሞት የማይገባቸውን ነፍሳት ትገድሉ ዘንድ በሕይወትም መኖር የማይገባቸውን ነፍሳት በሕይወት ታኖሩ ዘንድ ስለ ጭብጥ ገብስና ስለ ቁራሽ እንጀራ በሕዝቤ ዘንድ አርክሳችሁኛል›› (ሕዝ 13፡19) እንዳለ ኃይማኖትህን (ሽን) ካልቀየርሽ እርዳታ አንሰጥህም(ሽም) እስከመባል ተደርሶ እንደነበር ተጨባጭ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡
አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማቴ 24፡24 ‹‹እነሆ ክርስቶስ ከዚህ አለ ወይም ከዚያ አለ ቢሏችሁ አትመኑ ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና ድንቅ ያሳያሉ እነሆ አስቀድሜ ነገርኳችሁ›› ብሎናል አዎን ዛሬ በዘመናችን ይህንን አረጋግጠናል፣ የቤተክርስቲያናችን መሪጌታዎች በመናፍቃን አዳራሽ ውስጥ ዳንኪራ ሲረግጡ፣ ቅድስት ቤተክርስቲያንንና አስተምሮዋን ሲተቹና ሲያጣጥሉ ከማየታችን ባሻገር በመንፈሳዊው የዕውቀት ተቋማችን በፈዳማት ውስጥ ከእውነተኞች አባቶች ጋር በመመሳሰል ቆብና አስኬማውን በማጥለቅ ጉዞ ከጀመሩ በኋላ ወደ አሕዛብነት ወደ መናፍቅነት መስመር የገቡ አባ ጨጓሬዎች ተበራክተዋል፡፡
ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተራራው ስብከቱ በማቴ 7፡15 ላይ ‹‹የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውስጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኩላዎች ከሆኑ ከሐሰተኛ ነቢያት ተጠንቀቁ ከፍሬአቸው ታውቋቸዋላችሁ ከእሾህ ወይም ከኩረንችትስ በለስ ይለቀማልን?›› እንዲሁም በዮሐ 16፡1 ላይ ‹‹እንዳትሰናከሉ ይህን ነግሬአችኋለሁ ከዚህ በላይ ደግሞ የሚገድላችሁ ሁሉ እግዚአብሔርን እንደሚያገለግል የሚመስልበት ጊዜ ይመጣል፣ ይህንንም የሚያደርጉት አብንና እኔን ስላላወቁ ነው፣ ነገር ግን ጊዜው ሲደርስ እኔ እንደነገርኳችሁ ታስቡ ዘንድ ይህን ተናግሬአችኋለሁ›› እያለ ነው የመከረን ‹‹የበግ ለምድ ለብሰው›› ሲል ወንጌልን ይዘው ሃይማኖትን ሽፋን አድርገው ፍጹም ሥጋውያን ሆነው ሳለ መንፈሳውያን መስለው ይመጣሉ ማለት ነው፡፡
‹‹ነጣቂ ተኩላዎች›› የተባሉትም ነፍሳትን ወደ ገሀነመ እሳት ስለሚያወርዱ ነው ‹‹የሚገድላችሁ ሁሉ እግዚአብሔርን እንደሚያገለግል የሚመስልበት ጊዜ ይመጣል›› ሲል አንድም ክርስቲያኖችን በአምላካቸው ስም በሰይፍ ሲገደሉ ‹‹ገነትን›› እንደሚወርሱ የማያምኑትን አሕዛብ ማለቱ ሲሆን በሌላው ቃል እግዚአብሔርን አጣመው በክህደትና በኑፋቄ ሰዎችን የሚጎዱ ፣ ስተው የሚያስቱ ሁሉ የእግዚአብሔር አገልጋዮች መስለው የሚናገሩበት ጊዜ ይመጣል ማለቱ ነው፡፡
እንግዲህ አሁን በዚህ ዘመን ላለን ክርስቲያኖች ይህ ሁሉ በጌታችንና በሐዋርያት ተነግሮናል ሐዋርያቱን ያሳሰባቸውና ያስጨነቃካቸው ብሎም ግድ ሆኖባቸው የነበረው ነገር ሰዎች እላካቸውን አውቀው ወልድ ዋህድ በሁለት ልደት የከበረ ብለው አምነው ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፍጹም ስለተሰጣቸው ሃይማኖት እየተጋደሉ ይኖራሉ ወይ? የሚለው ነበር፡፡ በቃ መጽሀፍ ቅዱሱም ያስፈለገው ለዚሁ ነው እናም ሐዋርያት ‹‹ወንድሞች ሆይ ምናልባት ሕያው እግዚአብሔርን የሚያስክዳችሁ ክፉና የማያምን ልብ ከእናንተ በአንዳችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ (ዕብ 3፡12) እንደተማራችሁት በሃይማኖት ጽኑ፣ ልዩ ልዩ ዓይነት በሆኑ እንግዳ ትምህርት አትወሰዱ፣ በዐመጸኖች ስህተት ተስባችሁ ከራሳችሁ ጽናት እንዳትወድቁ ተጠንቀቁ፣ ልጆች ሆይ መጨረሻው ሰዓት ነው የክርስቶስም ተቃዋሚ ይመጣ ዘንድ እንደሰማችሁ አሁን እንኳ ብዙዎች የክርስቶስ ተቋዋሚዎች ተነሥተዋል፣ ስለዚህም የመጨረሻው ሰዓት እንደሆነ እናውቃለን›› (ቆላ 2፡7 ፣ ዕብ 13፡7 ፣ 2ኛ ጴጥ 3፡6 ፣ 1ዮሐ 2፡18) እያሉ የመከሩንኮ ወደው አይደለም ይህንን የአሁኑን ዘመንና የወደፊቱንም ጭምር በዓለም ላይ በሃይማኖት ሰበብ የሚሆነውን ቀድመው ስላወቁ እንጂ፡፡
ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ በታናሻ እስያ ትገኝ በነበረችው የአውራጃ ከተማ ይኖሩ የነበሩ የገላትያን ሰዎችን አንድ የጠየቀው ጥያቄ ነበር ‹‹የማታስተውሉ የገላትያ ሰዎች ሆይ በዓይናችሁ ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተሰቀለ ሆኖ ተስሎ ነበር ለእውነት እንዳትታዘዙ እዚም ያደረገባችሁ ማን ነው?›› ብሎ ነው የጠየቃቸው (ገላ 3፡1) መቼም መጽሐፍ ቅዱስን እንደሆነ እንደመናፍቃን ተሸክሞት የሚሔድና ይዞትም የሚያድር ያለ አይመስለኝም ታዲያ ምነው ይህን ሁሉ እውነት መረዳት አቃታቸው? የቅዱስ ጳውሎስ ጥያቄ መልስ ያሻዋል ‹‹ለእውነት እንዳትታዘዙ አዚም ያደረገባችሁ ማነው?›› ነቢዩም ዘካርያስ ‹‹እግዚአብሔር በቀደሙት ነቢያት እጅ በመንፈስ የላከውን ሕጉንና ቃሉን እንዳይሰሙ ልባቸውን እንደ አልማዝ አጠነከሩ›› (ዘካ 7፡11) እንዳለው ሆኖ ነው እንጂ መጽሐፍ ቅዱስንማ እንደ እነሱ የሚያነበው አልነበረም አልጠቀምበት አሉ እንጂ ለነገሩ አባቶች በምሳሌ ‹‹አንድ የመጽሐፍ መደርደሪያ ዕድሜ ልኩንም ቢሆን መጽሐፎችን ተሸክሞ ቢኖርም እውቀት ግን አይገበይባቸውም›› እንዲሉ የመናፍቃንም ነገር እንዲሁ ነው መራመድ ብቻውን መጓዝን አያመለክትምና ‹‹መጻሕፍትን ያስተውሉ ዘንድ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው›› (ሉቃ 24፡45) ተብሎም እንደተጻፈ እግዚአብሔር አምላክ ዓይነ ልቡናቸውን ያብራላቸው አዚም ያደረገባቸውን ነገር እርሱ ያንሳላቸው እኛንም የትንቢቶች መፈጸሚያ ከመሆን ይጠብቀን፣ በሃይማኖት ኖረን ራሳችንን እንመረምር ዘንድ ይርዳን፡፡ አሜን!
እግዚአብሔር አምላክ ‹‹ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቷል›› (ሆሴ 4፡4) እንዳለ ለብዙዎች መጥፋት ዋነኛ ምክንያት ቀድመው ስለተዋህዶ እምነታቸው ጠንቅቀው አለማወቃቸው ነው ይህ በራሱ እምነትን ጠንቅቆ አለማወቅ አንድ ትልቅ ስህተት ቢሆንም የበለጠ ትልቅ ስህተት የሰሩት ከእነርሱ ያልተሻሉ ዓይነ ልቡናው የታወረ ስለ እምነትም የተጣለ ማንም መጥቶ በእምነት ጎዳና ልምራችሁ ሲላቸው መከተላቸው ነው ክርስቶስ በወንጌል ‹‹እውርን እውር ቢመራው ተያይዘው ገደል ነው›› (ማቴ 15፡1) እንዳለ፡፡
አበው በምሳሌ ሲናገሩ ‹‹የማያውቁት ስድብ ከምስጋና ይቆጠራል›› እንዲሉ እኛ ያልሰማነውንና ያላነበብነውን ጥቅስ በመምዘዝ እነርሱ በፈለጉት መልኩ ተርጉመው አሊያም እንዲሁ ትርጉሙና ምስጢሩ ያልገባቸውን በደረቁ ‹‹ሞኝ አስደንግጥ›› ጥቅሳቸውን ይዘው ስንቱን ነው በሞት መንገድ የመሩት ‹‹ጆሮ ያለው ቢኖር ይስማ ፣ ይማረክ ዘንድ ያለው ማንም ቢኖር ወደ ምርኮነት ይሄዳል›› (ራዕ 13፡9) እንዲል ባለራዕዩ ብዙዎች ተማረኩ
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹በውሸት እውቀት ከተባለ ለዓለም ከሚመች ከከንቱ መለፍለፍና መከራከር እየራቅህ በተሰጠህ አደራ ጠብቅ፣ ይህ እውቀት አለን ብለው አንዳንዶች ስለ እምነት ስተዋልና›› (1ኛ ጢሞ 6፡20) እንዳለ በፍጡራን ፍልስፍና በውሸት እውቀት የተፈለሰፈ ዘመን አመጣሽ በሆነ ሃይማኖት ተማርከው ብዙዎች ‹‹ለሰው ቅን የምትመስል መንገድ አለች ፍጻሜዋ ግን የሞት መንገድ ነው›› (ምሣ 14፡12) የተባለችውን የሞት መንገድ እየተጓዙበት ነው እግዚአብሔር አምላክ በነቢያት ላይ አድሮ ‹‹የምታስደንቅና የምታስደነግጥ ነገር በምድር ላይ ሆናለች ነቢያት በሐሰት ትንቢጥ ይናገራሉ፣ ካህናትም በእነዚህ እጅ ይገዛሉ፣ ሕዝቤ እንዲህ ያለውን ነገር ይወዳሉ፣ በፍጻሜውስ ምን ታደርጋላችሁ? ሲል ይጠይቃል›› (ኤር 5፡30) በወንጌሉም ‹‹የሰው ልጅ ለፍርድ በሚመጣበት ጊዜ ከሰው ልጆች እምነት ያገኝ ይሆን?›› (ሉቃ18፡81) ብሎ ነው የጠየቀን ‹‹ካህናትም በእነዚህም እጅ ይገዛሉ›› ሲል ሐሰጠኛ ካህናትን ማለቱ ነው፣ አንድም በየጊዜው የሚነሡትን ተሃድሶአውያን (Reformationist) የውስጥ ጠላቶች የእኛን መስቀል ይዘው፣ የእኛን ቆብና መጠምጠሚያ ጭነው የእኛን ቀሚስ (ሰናፈል) ለብሰው እኛን መስለው ውስጥ ለውስጥ በመንቀሳቀስ የቤተክርስቲያንን ዶግማና ቀኖና አስተምሮዋን ለመበረዝ ከተቻላቸውም ለማጥፋት የሚነሱትን ቢጽ ሐሳውያን ማለቱ ነው፡፡ በእርግጥም ወደፊት ገና ሞትን ያልቀመሱት እነ ኤልያስና ሔኖክ ሌሎችም ወደ ምድር መጥተው በሐሳዊው መሲሕ ላይ መስክረው በሰማዕትነት ያርፋሉ፡፡







እምነት ይጠፋና ክህደት የሚሰለጥንበት ጊዜ ገና ይመጣል እነ ዮሐንስ መጥምቅ የጌታን መንገድ ያዘጋጁና ይጠርጉ እንደ ነበር ሁሉ እነዚህ በየጊዜው በእውነተኛዋ የተዋህዶ ሃይማኖት ላይ የሚነሡት አጽራረ ቤተክርስቲያን የሐሳዊው መንገድ ጠራጊዎች ናቸው፡፡ ይህ ያለንበት ዘመንም የሐሳዌ መሢሁ መምጫ የመዘጋጃ ጊዜ መሆኑ በገሀድ እየታየ ያለ እውነት ነው ይህንን ክፉና አስጨናቂ ዘመን በአንክሮ በማስተዋል ለተመለከትን የዐፄ ናዖድ ዓይነት ጸሎት ሳያስፈልገን ይቀራል ትላላችሁ፡፡ ‹‹ዐፄ ናዖድ በስምንተኛው ሺህ ክህደትና ኃጢዓት በዓለም እንደሚበዛ ስለተገለጠላቸው ‹‹ከጊዜው አታድርሰኝ ከእህል ከውሃው አታቅምሰኝ›› እያሉ ይጸልዩ ነበርና፣ የለመኑትን የማይነሣ አምላክ ልመናቸውን ሰምቶ 8ኛው ሺህ ሲገባ 28 ቀን ሲቀረው በነሐሴ 7 ቀን አርፈዋል፡፡
ስለዚህም በነቢያትና በሐዋርያት መሠረትነት ላይ የታነጻችሁ በጥንታዊትና ሐዋርያዊት በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ያላችሁ የያዛችሁት መንገድ እውነት ነውና የትንቢት መፈጸሚያ እንዳትሆኑ የጸኑትን አስቡ ጸልዩ ከፊት ይልቅ ትጉ፣ ንቁ ጎልምሱ በሃይማኖት ቁሙ አምላካችን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም እንዳለ ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ፡፡
እግዚአብሔር ያጽናን አሜን!!
ዋቢ
መጽሐፍ ቅዱስ(81)
ኆኀተ ሃይማኖት
ከዘመኑ አርዮሳውያን ተጠበቁ
በሃይማኖት ብትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ

No comments:

Post a Comment