‹‹የዓለም ብርሃን ተወለደልን››
‹‹ሕዝብ ዘይነብር ውስተ ጽልመት
ርእየ ብርሃነ››
ልዑለ ቃል ነቢዩ ኢሳይያስ እግዚአብሔር የራቀውን
ስላቀረበለት የረቀቀውን ስላጎላለት የመሲሁን መምጣት የክርስቶስን መወለድ የእግዚአብሔርን ልጅ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት መወሰን
በትንቢት መነጽር ተመልክቶ ሲናገር ‹‹ሕዝብ ዘይነብር ውስተ ጽልመት ርእየ ብርሃን ዐቢየ ወለእለሂ ይነብሩ ውስተ ጽልመት ወጽላሎት
ሞት ብርሃን ሠረቀ ሎሙ›› (ኢሳ 9፡2) በጨለማ የሄደ ሕዝብ ብርሃንን አየ በሞት ጥላ በጨለማ ሀገር ለኖሩ ሰዎችም ብርሃን ወጣላቸው
አለ፡፡
በድንቁርና በኃጢዓት በዕውቀት ማነስ በቀቢፀ ተስፋ
ለነበሩት ሰዎች ፍጹም እውቀት ተሰጣቸው፣ ሞት ባመጣው ምስል ሞትን በመምሰል ለነበሩ ሰዎች ክርስቶስ ተወለደላቸው፣ በሞተ ሥጋ በሞተ
ነፍስ ለነበሩ ልጅነት ተሰጣቸው፣ በኃጢዓት ለነበሩ ስርየት፣ በክህደት ለነበሩ ሃይማኖት ተሰጣቸው በብርሃንህ ብርሃንን እናያለንና
ተብሎ እንደተጻፈ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም የመጣው በጨለማ ውስጥ የሚኖሩትን ወደ ብርሃን ለማውጣት በሞት ጥላ ሥር የነበሩትን
ወደ ዘለዓለም ሕይወት ለማሸጋገር ነው፡፡ (መዝ 35(36)፡9)
በሌላው በኃጢዓት ሰላም አጥቶ ለነበረው ዓለም
ብርሃን ክርስቶስ ሰላም ሆኖ ተወልዶልናል ይህንንም ሲያስረዳ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ‹‹ይእዜኒ ለሰላም ንትልዋ መድሀኒነ ተወልደ ነዋ››
እነሆ መድሀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተወልዶልናልና ከዛሬ ጀምሮ ሰላምን እንከተላት በማለት የጌታ ልደት ለዓለም ሰላም መሆኑን ይናገራል፡፡
እንዲሁም ሐዋርያው ‹‹ነአምር ከመ ኩሉ ዓም ሕሙም ወትኩዝ እስከይእዜ›› ‹‹ዓለሙ ገና እስከዛሬ ያዘነ የተከዘ እንደሆነ እናውቃለን››
(ሮሜ 8፡22) ብሎ እንደጻፈው ዓለም በጠና ታሞ ፈዋሽ መድሀኒትም አጥቶ በማጣጣር ላይ እንዳለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወዶና
ፈቅዶ ባደረገው ‹‹አትሕቶ ርዕስ›› ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ መገለጡ ለዓለም ፍቱን መድኃኒት ሆኖታል፡፡
ከህመምና ከትካዜም አድኖታል ‹‹እስመውዕቱ ያድኀኖሙ
ለሕዝቡ እምኃጢዓቶሙ›› እርሱ ሕዝቡን ሁሉ ከኃጢዓታቸው ያድናቸዋል ተብሎ እስቀድሞ በመልአክ ተነግሮ ነበረና፡፡(ማቴ 1፡21)
ከአዳም ጀምሮ እስከ ክርስቶስ መምጣት ድረስ ብዙ
ታላላቅ አበው ተወልደዋል ልደቱ አዳም እምምድር ልደተ ሔዋን እምገቦ፣ ልደተ በግዕ እምዕፅ፣ ልደተ አቤል እምከርሥ፣ ልደተ ሙታን
እምመቃብር ብለው እንዲያመሰጥሩ ሊቃውንት በዘመኑ ኦሪትም እነ ኖህ እነ አብርሃም እነ ይስሐቅ እነ ያዕቆብ በዘመነ መሳፍንት እነ
ዳዊት እነ ሰሎሞንና እነ ሳሙኤል በዘመነ ነቢያትም አብይት ነቢያትና ደቂቀ ነቢያት የመሳሰሉ መንፈሰ እግዚአብሔር ሥራ የሰራባቸው
ሰዎች የተወለዱ ሲሆን ነገር ግን አበውም ሆኑ ነገሥት መሳፍንትም ሆኑ ነቢያት እንኳን ለሌላው ሊተርፍ ራሳቸውንም ሊያድኑ እንዳልቻሉ
ሰሎሞን በጥበቡ ‹‹ነፍሰሙሰ ለጻድቃን ውስተ እደ እግዚአብሔር ሆነ ርወኢለከፎሙ ሥቃይ›› የደጋግ ሰዎች ነፍስ ግን በእግዚአብሔር
እጅ ናት መከራ አላገኛቸውም በማለቱ በሥልጣነ እግዚአብሔር እየተጠበቁ በሰዖል መቆየታቸውን ይገልጣል፡፡
ነቢያትም ቢሆኑ ‹‹አንሥእ ኃይለከ ፈኑ እዴከ፣
ፈኑ ብርሃነከ ወነዓ አድኃነነ›› (መዝ42፡6፣ መዝ 143፡5) እያሉ ይረልዩ ነበር እንጂ ይህን ዓለም ከዲያብሎስ ቁራኝነት ማላቀቅ
አልተቻላቸውም ነበር ከዚህም የተነሣ መላው የዓለም ሕዝብ ከዲያብሎስ ቀንበር በታች ወድቆ ለ5500 ዓመታት በግፍ አገዛዝ ሲገዛ
ኖሯል፡፡
እንግዲህ ይህን ሁሉ ወደ ኋላ መለስ ብለን ስናይ
ነው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ልዩ የሚሆንብን፣ በመጽሐፍ ቅዱስ በግልጥ እንደተቀመጠው ጌታ ሲወለድ ጨለማው በብርሃን ተተካ
ለዓለምም የተሰበከው ሰላም ደስታና ድኅነት ነበር ‹‹ወይቤሎሙ መልአከ ኢትፍርሁ እስመ ናሁ እዜንወክሙ ዐቢየ ዜና ፍስሐ ዘይከውን
ለክሙ ወለኩለ ዓለም እስመ ናሁ ተወልደ ለክሙ ዮም መድኀን ዘውእቱ ክርስቶስ እግዚእ ቡሩክ ወሀገረ ዳዊት›› መልዓኩ አይዟችሁ አትፍሩ
መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስን የሚያርቅ በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስን የሚያድል የዓለም መድኃኒት የሚሆን የባሕርይ አምላክ ክርስቶስ
ከዳዊት ከተማ ከዳዊት ባሕርይ ተወልዷልና እናንተም ሰውንም ሁሉ ደስ የሚያሰኝ ነገር (ዜና) እነግራችኋለሁ (ሉቃ 2፡10)
በመሆኑም አስቀድሞ በነቢያቱ ‹‹ስሜን ለምትፈሩ
ለእናንተ የጽድቅ ፀሐይ ትወጣላችኋለች ፈውስም በክንፎ ይሆናል›› (ሚል 4፡3) ተብሎ እንደተፃፈ ፀሐየ ጽድቅ ክርስቶስ ከድንግል ማርያም ተወልዶ ሰላምን
ፈውስን ደስታን ሰጥቶናል፡፡
ይህ የተፈጸመው በምድረ ፍልስጤም ቢሆንም ሀገራችን
ኢትዮጵያም ለዚህ የሰላምና የድኅነት ፀጋ የታደመችው ወዲያውኑ ሳይውል ሳያድር እንደሆነ ሊቃውንት ይናገራሉ፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ
የጌታችንን ልደት ከማንም በላይ በራሷ የሃይማኖት ቀኖና የትውፊት አገላለጥ ስታከብር እስከአሁን ቆይታለች ወደፊትም በበለጠ ታከብራለች
ለዚህም አብነት የሚሆነው ታላቁ ኢትዮጵያዊ የቤተክርስቲያናችን ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ‹‹ናሁ እምየእዜሰ አልቦ ኃዘን እስመ በልደቱ ገብረ
ለነ ሰላመ›› እነሆ ከዛሬ ጀምሮ ኃዘን የለም ጌታ በመወለዱ ሰላምን አድርጎልናልና እያለ ዘምሯል፡፡
በመሆኑም የጌታ ልደት ብዙ በረከትን ያገኘንበት
ፍርሃታችን ተወግዶ ሰላምን የተጎናፀፍንበት ድካማችን ጠፍቶ ፍጹም ዕረፍትን ያረፍንበት ከምንም በላይ ከጨለማ ካለማወቅ ከኀጢዓት
ወጥተን በብርሃን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃንን ያየንበት ዕለት በመሆኑ በተዋህዶ ቤተ ክርስቲያናችን ከዋዜማው ጀምሮ በማህሌቱ በቅዳሴው
በቃለ እግዚአብሔር በዝማሬና በሽብሽባ እግዚአብሔርን እናመሰግናለን፣ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን በመቀበል ከክርስቶስ ጋራ በብርጋን
እንመላለሳለን ፣ ከዚያም በበዓሉ ዕለት የጌታን ውለታ በማሰብ በፍጹም ደስታና ሰላም የተቸገሩትን በመርዳት የተራቡትን በማብላት
የተጠሙትን በማጠጣት የታረዙትን በማልበስ የደስታችን ተካፋዮች እናደርጋቸው ዘንድ ግድ ይለናል፡፡
አሁን አሁን ግን የጌታን ልደት ለማክበር የምናያቸውና
የምንሰማቸው ነገሮች ብርሃን ወደ ዓለም ከመጣበት ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ ከተወለደበት ዓላማ ጋር ፍጹም የሚቃረን ሆኖ እናስተውላን፡፡
ለዳንኪራ ለጭፈራ ለአስረሽ ምቺው ልፈፋና ማስታወቂያ
ውትወታ ከሚወተውቱት ጀምሮ ከልክ በላይ ለመብላትና ለመጠጣት ለዝሙትና ለመዳራት የሚሆኑ የምሽት ጭፈራ ቤቶችን በማዘጋጀት ገንዘብን
እስከሚሰበስቡት አላዋቂዎች ድረስ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ሕዝቡን ወደ ሞት የሚመሩ የበዓሉን መንፈሳዊ ትርጉም ያልተረዱ ብዙ ናቸው፡፡
እኛም በዚህ ሕይወት ውስጥ ለምንኖር ክርስቲያዊ
በዓላት በመጡ ቁጥር ዳንኪራ ለመርገጥ፣ ለመጨፈር ለመዝፈን ለአሸሼ ገዳሜ ገንዘባችንን ጊዜያችንን ማንነታችን አሳልፈን የምንሰጥ
ሁሉ ቆም ብለን ራሳችንን እንመርምር ምክንያቱም ይህንን እያደረግን የጌታን ልደት እያከበርን ነው ካልን፣ አከባበራችን መንፈሳዊ
ሳይን ሥጋዊ ነው፣ የአባቶቻችን ልጆች ከሆን የበዓል አከባበራችንም የእነሱን መምሰል አለበት እግሮቻችን በዳንስ ሳይን በሽብሸባ
አዕምሮአችን በወይን ጠጅ ሳይሆን በቃለ እግዚአብሔር መሞላት አለበት፣ አፋችንም ለዘፈን ሳይሆን ለመዝሙርና ለውዳሴ መከፈት አለበት፣
ሆዳችንም በምድራዊው በሚጠፋው ሥጋ ሳይሆን በጌታ ሥጋና ደም መጥገብ አለበት፣ ያገኘነውንም እንደ ድመት ለብቻ ይዞ ማኩረፍ ሳይሆን
ምንም ከሌላቸው ከችግረኞች ጋር አብረን በመመገብ ፍጹም ክርስቶስን መስለን የክርስቶስን ልደት ማክበር አለብን፡፡
ይህንን ስናደርግ ግን ሰላምን የምንሻ ፍቅርን
የምንፈልግ ብርሃንን ለማየት የምንመኝ ካለን ‹‹ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ›› እንዲሉ አበው ጻድቅን በኃጢዓት ሥፍራ ሰላምን በሁከት
፣ ዕረፍትን በድካም ብርሃንን ከጨለማ ለማግኘት ከንቱ ልፋት እየለፋን ነውና እናስተውል፡፡
ሐዋርያው ጳውሎስ ለሮሜ ሰዎች በጻፈው መልዕክቱ
‹‹ሌሊቱ አልፎአል ቀኑም ቀርቦአል እንግዲህ የጨለማውን ሥራ አውጥተን የብርሃንን ጋሻ ጦር እንልበስ፣ በቀን እንደሚሆን በአግባብ
እንመላለስ በዘፈንና በስካር አይሁን በዝሙትና በመዳራት አይሁን፣ በክርክርና በቅናት አይሁን፣ ነገር ግን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ
ክርስቶስን ልበሱት›› (ሮሜ 13፡12)
ሌሊት የተባለ ጨለማ የኃጢዓት ሥራ ሲሆን ብርሃን
መድኃኔዓለም ከድንግል ማርያም ተወልዶ በተገለጠ ጊዜ ጨለማ ለብርሃን ቦታ ለቀቀ ኃጢዓት ተወገደ፣ ‹‹የዓለምን ኃጢዓት የሚያጠፋው
ብርሃን ፈንጥቋልና›› ‹‹ነዋ በጉ ለእግዚአብሔር ዘያአትን ኃጢዓት ዓለም›› (ዮሐ 1፡29) ተብሎ የተነገረለት የማይጠልቀው ፀሐይ
ክርስቶስ መትገምን ሽሮ ተወልዷልና በብርሃን እንሁን ስጦታ ለተሰጠን ለእኛ ብርሃኑ ለበራልን ደግሞም የማይጠልቀው ፀሐይ ለወጣልን
ሁሉ ‹‹እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ›› ተብለናል (ማቴ 5፡14) የብርሃኑ ፍሬ በበጎነትና በጽድቅ በእውነትም ሁሉ ነውና ለጌታ
ደስ የሚያስኘውን እየመረመርን እንደ ብርሃን ልጆች እንመላለስ፣ ቀድሞ በጨለማ ከነበረን አሁን ግን በጌታ ብርሃን ሆነናልና ፍሬ
ከሌለው ከጨለማ ሥራ ጋር አትተባበሩ ይልቁንም ግለጡት እንጂ እነርሱ ባለማወቅ በስውር ስለሚዘፍኑ ስለሚጨፍሩ ዳንኪራ ስለሚረግጡ
ስለሚያደርጉት መናገር እንኳ ነውር ነውና፣ ሁሉ ግን በብርሃን ሲገለጥ ይታያል የሚታየው ሁሉ ብርሃን ነውና (ኤፌ 5፡7፡10)
እንግዲህ እኛ ግን ከጨለማ ወደ ሚደነቅ ብርሃኑ
የጠራን የእርሱን በጎነት እንድንነግር የተመረጥን ቅዱስ ሕዝብ ለርስቱ የተለየን ወገን መሆናችን አውቀን በብርሃን እንኑር ጨለማውም
ያልፋልና እውነተኛውም ብርሃን ይበራል በቀን እንደሚሆን በጽድቅና በቅንነት ሆነን (1ጴጥ 2፡9 ፣ 1ዮሐ 2፡8) የጌታችንን የመድኃኒታችንን
የኢየሱስን ልደት እናክብር፡፡
No comments:
Post a Comment