Thursday, January 23, 2014

ባርነትና መንስኤው



‹‹ሰው ለተሸነፈበት ለእርሱ ተገዝቶ ባሪያ ነው›› 2ጴጥ 2፡20
በዕድሜ በጸጋና በአገልግሎት በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ የሸመገለው ሐዋርያው ጴጥሮስ በቀዳሜ ሰማዕት በቅዱስ እስጢፋኖስ ሞት ምክንያት በጳንጦስ፣ በገላትያ፣ በቀጵዶቅያና ታናሽቱ እስያ ተበትነው ለነበሩት ክርስቲያኖች ክፉ ባልንጀርነት ደባል ሱስን በተመለከተ ምክሩን ሲለግስ ‹‹ሰው ለተሸነፈበት ነገር ተገዝቶ የሚኖር ከሆነ ለዚያ ባሪያ ይሆናል›› ብሏል በጎም ሆነ ክፉ ሰው ለሚወደውና ለተለመደው ይማረካልና (2ጴጥ 220) ማንም ሰው ከእናቱ ማህፀን ውስጥ ክፉም ሆነ በጎ ልምድን ይዞ አይወለድም፣ ይልቁንስ በጊዜና በዕድገት በትምህርትም ከህብረተሰቡ ይወርሳል እንጂ የተወለድንበት ያደግንበትና የተማርንበት ህብረተሰብ በሕይወታችን ለምናካብታቸው ልምዶች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ አስተዋጽኦ አለው፡፡



ከተግባር ይዞታቸውና ውጤታቸው አንፃር ተቀራራቢ የስሜት ትርጉም ያላቸው ልምድ፣ ልማድ፣ ሱስ የሚል ስያሜ የተሰጣቸው በሕይወታችን ውስጥ በበጎም ሆነ በመጥፎ መልኩ ተጽዕኖ ያላቸው ነገሮች አሉ፡፡
የልምድ ትርጉም ከልማድ ብዙም የሚርቅ አይደለም ልምድ ማለት መልመድ ማወቅ መውደድ ማዘውተር ቤተሰብ መሆን ማለት ነው ያልሰሙትን ያላዩትን ያላወቁትንና ያልቀመሱትን ነገር ማየት መስማት ማወቅ ማሽተት መቅመስና በስሜት ሕዋሳት አማካኝነት ከሰውነት ከሕይወት ጋር ማስተዋወቅ ልምድ ይባላል፡፡ በቁሙ ልምድ የተለመደ ግብር ዐመል ጠባይ ተዘውትሮ ወይም አልፎ አልፎ የሚደረግ ልምድ ነው ልምድ በጎም ሊሆን ይችላል መጥፎ ወይም ጎጂም ሊሆን ይችላል፡፡




 



አንዳንድ ሰዎች ወደ ቤተ እግዚአብሔር አዘውትረው ወይም በየሳምነቱ በተወሰኑ ቀኖች የመሄድ ጸሎት የማቅረብና በቤተክርስቲያን አካባቢ ለሚገኙ ችግረኞች ምጽዋት የመስጠት ልምድ (ልማድ) አላቸው: አንዳንዶችም በዓመት በተወሰኑ ዕለታት በታላላቅ ገዳማትና አድባራት በሚከበሩ በዐላት የመገኘት በቤታቸው ወይም በሌላ ቦታ በእግዚአብሔርና በቅዱሳኑ ስም የመታሰቢያ ዝግጅት (ዝክር) እያዘከሩ በጎ ሥራ የመሥራት፣ ማልደው በመነሳት ታጥቀው ሥራ የመስራት ሰውን ከሰው የማስታረቅና ሌላም ይህን የመሰለ አገልግሎት የመስጠት ልምድ ይኖራቸዋል፡፡
ከነዚህም ሁሉ ጋር ማለዳ ተነስተው የሰውነት ማጠንከሪያና ጤንነት መጠበቂያ እንቅስቃሴ ካላደረጉ በቀዝቃዛ (ለብ ባለ) ውሃ ተጣጥበው ካልወጡ ቀኑ የማይመሽላቸው ፣ የሸሚዛቸው አንገት ሳያድፍ የጫማቸው ሽታ በመጥፎ ሳይሰማ በንጽሕና የመኖር ልምድ ያላቸው ብዙ ጠንቃቃ ሰዎች የመኖራቸውን ያህል በተቃራኒው ደግሞ ክፉና ጎዚ ልምድን አዘውትረው በመሥራት ራሳቸውን ቤተሰባቸውን ህብረተሰባቸውንና ሀገርን የሚጎዱ በቁጥር ጥቂት አይደሉም፡፡ ባገኙት አጋጣሚ ወደ መጠጥ ቤት በመግባት አንድ ለመነቃቃት አንድ ለመንገድ ብለው ጀምረው ራሳቸውን ስተው ጨርቅ በመሆን በመንገድና በቆሻሻ ቱቦዎች ሥር ተኝተው የሚያድሩ የመጥፎ ልምድ ሰለባዎች ናቸው ጠቢቡ ሰሎሞን እነዚህን ሲገስጽ ‹‹ዋይታ ለማን ነው? ኀዘን ለማን ነው? ጠብ ለማን ነው? ጩኸት ለማን ነው? ያለምንያት መቁሰል ለማን ነው?  የዓይን ቅላት ለማን ነው? የወይን ጠጅ በመጠጣት ለሚዘገዩ አይደለምን? የተደባለቀ የወይንን ጠጅ ይፈትኑ ዘንድ ለሚከተሉ አይደለምን? ወደ ወይን ጠጅ አትመልት በቀላ ጊዜ መልኩም በብርሌ ባንጸባረቀ ጊዜ እየጣፈጠም በገባ ጊዜ በኋላ እንደ እባብ ይነድፋል እንደ እፉኝትም መርዙን ያፈሳል›› (ምሳ 2329-35) ይላል፡፡




 



አንዳንዶች ደግሞ መዝናኛን ምክንያት በማድረግ የምሽት ቤቶችን (Night Clubs) ተገን በማድረግ ዳንኪራ የሚወዱ የሚጨፍሩ በአስረሽ ምቺውና በሰነፎች ዜማ እያቀነቀኑ ጮቤ የሚረግጡ ዘፈን ካልሰሙ ካላንጎራጎሩ የማይሆንላቸው የሁካታ ሱሰኞች ናቸው፡፡ የተቀሩትም ወጣትነታቸውን በወሬ አደባባይና በውስልትና ሥፍራ ከማሳለፋቸውም በሻጋር በጫቱ በሲጋራና በአደንዛዥ ዕጾች ክፉ ልማድ ተይዘው ዓይናቸው የማይከፈት አዕምሯቸው የደነዘዘባቸው ሆነዋል የወሲብ ስሜት ልምድ ተገዥ ሆነው ያዩት የማያልፋቸው ያም ካልሆነ ገንዘባቸውን ከፍለው ነፃ ፍቃዳቸውን የሚፈጽሙ የወሲብ ፊልሞችን ካላዩ ግብረአውናን ካልፈጸሙ ነግቶ የማይመሽላቸው ራሳቸውን መግዛት የተሳናቸውንም ሳንጠቅስ አናልፍም፡፡




 



ብቻ ምን አለፋን በመልካምም ይሁን በመጥፎ ገጽታው ሁሉም ልምድ ልማድና ሱስ ነው የመልካም ሥራ ልማድ ያላቸው ሰዎች ልማዳቸውን ቢያቋርጡ ሕይወታቸው ነፍሳቸው አንድ ነገር እንደሚጎድላት የሚሰማቸው ቅሬታና ጸጸት የሚያድርባቸው ሲሆን በመጥፎ ልምድና ጠባይ የተመረዘ ደግሞ ልምዳቸው ቢተጓጎል ሱሳቸው ያበሳጫቸዋል ያደነዝዛቸዋል የኅሊና ቀውስ ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ያድርባቸዋል ሕይወታቸውን የመጥላት ራሳቸውን ከኅብረተሰቡ የመለየትና የብቸኝነት ስሜት ያሰጥማቸዋል፡፡
በመሆኑም ሁሉም በየገጹ የሱስነት ባሕርይ አለው ለዚህም ነው ሐዋርያው ማንም ለሚወደው ነገር ተገዝቶ ባሪያ  ይሆናል ያለው ሱስ የልምድ (የልማድ) ጥንቅር ውጤት ነውና ልምድን (ልማድን) ከማወቅ ከመውደድና ከመለየት በጎ ገጽታው አኳያ ሲመረምሩት አብሮ የመኖርን ምስጢር የሚተረጉም ቋንቋ ነው ሰውን በመልኩ በቁመናው ባካሔዱ በስሙና በድምጹ ለይቶ ማወቅ የሚቻለው ለረጅም ጊዜ አብሮ በመኖር መልኩን በማየትና ድምጹን በመስማት የአኗኗር ጠባዮቹንና ስነልቡናውን በማጥናት በመልመድ ነው እንሰሳት እንኳን የጌቶቻቸውን ድምጽና ጠረን ፍቅርና ጥላቻ ለይተው ያወቃሉ በረታቸውንና መመስጊያቸውን ለይተው ስለሚያውቁ ከግጦሽ መስካቸው ውለው ይገባሉ፡፡ በልምድ ዕውቀትና ጥበብ አራዊት ከሰው ይኖራሉ፣ ይሰለጥናሉ በለመዱት ባወቁትና በሰለጠኑበት ተግባር አገልግሎት ይሰጣሉ  (ኢሳ13 ማቴ 2532 ዮሐ 103-5)




 



ይህ ሁሉ የሚገልጸው የልምድንና የልማድን ትርጉም ነው ሱስ በመጥፎ ስያሜውና አጥፊ ገጽታው የሚተረጎም የልምድ ወይም የልማድ ውጤት ነው ሱስ በአፍራሽ ገጽታው የሚያደርሰውን ጥፋትና ጉዳት ጥልቀቱን ምጥቀቱንና ክብደቱን በቀላሉ መግለጽ እጅግ አስቸጋሪ ነው የሱስ ዓይነቶችና ስሞች ምን ምን እንደሆኑ ዘርዝሮ ማቅረብም ብዙ የሚያደክም የሃሣብ አቀበት ነው፣ የሚጠቅሙ መስለው የሚጎዱ በመንፈሳዊ ዓይን ሲታዩ በእግዚአብሔር ቃል ሲመዘኑ ለክርስቲያች የማይበጁ በርካታ የሱስ ዓይነቶች ይኖራሉ፡፡
ረቡዕና አርብን ጨምሮ በአዋጅ አጽዋማት ጊዜ ሳይቀር ሰማይና ምድር ሳይላቀቅ በጥዋት ተነስተው ሻይና ቡና ካልጠጡ ምግብ ካልበሉ የሚሞቱ የሚመስላቸው እንዳሉ ሁሉ ብዙዎችም ለሚበሉበትና ለሚጠጡበት ጊዜና ልክ የሌላቸው በገቡ በወጡ ቁጥር እንደ አመንዣጊ እንሰሳት አፋቸው ሥራ የማይፈታም አሉ ነፍስ ያለ ሥጋ መቆም ስለማትችል መብላት መጠጣት ተገቢ ቢሆንም ከመጠን በላፈ መብላትና መጠጣት ግን ለጤና ጠንቅ ከመሆኑም ባሻገር ራስን ላለ መግዛት ዋነኛ ምክንያት ነው፡፡
በሕይወት ጎዞ ለዐይን በሚያስጎመዡ ለምላስ በሚጣፍጡና ጠቀሜታ የሚኖራቸው መስለው በሚታዩ ነገሮች ሽፋን ሕይወትን ለአደጋ የሚያጋልጥ የመጥፎ ልምድ ስርዐት ሱስ ነው ለዚህም የጫትን፣ የትንባሆን (ሲጋራን) የአልኮል መጠጥንና የአስካሪ አደንዛዥ ዕፅዋትን ሁካን የሱስ መጥመድነት በቂ ምሳሌ አድርጎ  ማቅረብ ይቻላል፡፡ ሁሉም ግን የሚሰጡት ጥቅም ወይም የሚያስከትሉት ጉዳት በየጊዜው በተለያዩ ባለሙያዎች የሚገለጽ ቢሆንም ከሃይማኖት ትምህርትና የስነምግባር አስተሳሰብ አንጻር የሚተላለፈው መልዕክት ብርቱ ምርምር ጥናትና ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ነው ሱስ በመሻት ኃይል ቁጥጥር ሥር መዋል ለተሸነፈበት ነገር ተገዝቶ ባሪያ መሆን፣ ፈቃድን ለመግዛት አለመቻልና የፈቃድ ተገዥ መሆን ነው፡፡
የሱስ ጦርነት ፍልሚያ ቀላል ፈቃድ ኃይል ሊቋቋመው የማይቻል በመሆኑ ወደ ግንባሩ የዘመቱ ሁሉ በሕይወትና በጤንነት መመለሳቸው እጅግ አጠራጣሪ ነው፡፡ ሳይታወቃቸው ዘምተው ወይም በቅብጠት የገቡበት ሁሉ እጅ እየሰጡ ይቀራሉ የሱስ ምርኮኞችን ሁሉ የሚጠብቃቸው ውድቀት ነው፡፡
ሱሰኝነት በሚያስከትለው መዘዝ የተጎዳ ሕይወት በተፈጥሮ የነበረው ጠንካራ የጤና መሠረት ስለሚናጋ መውደቅ ብቻ ሳይሆን አወዳደቁም የከፋና ታላቅ ይሆናል የፈተናን ጎርፍ መቋቋም የሚችልበት ጎን አይኖረውም፡፡
ሱስ በዓይን ከሚታዩ በጆሮ ከሚሰሙ ክፉ ነገሮች እንዲሁም በሚበሉና በሚጠጡ ነገሮች እየተለመደ ውስጣዊ የሰውነት ዋና ዋና ክፍሎችን በመበዝበዝ ደምን በመመረዝ የስሜት ሕዋሳትን በማጥቃትና ነርቮችን በማዳከም ሕይወትን ለአደገኛ ጥፋት ያጋልጣል፣ ማህበራዊ ሕይወትን ትዳርን ቤተሰባዊ ፍቅርን ያቃውሳል፡፡ ከሱሰኞች ብዙዎቹ ርግጠኛው የተፈጥሮ ሞት ከመድረሱ በፊት በሰመመን ኑሮ ሞተው የሚቆዩ የአካልም የመንፈስም ድሆች ናቸው፡፡ በጎጂነታቸውና በአጥፊነታቸው የሚታወቁት ብቻ ሳይሆኑ በተፈጥሮ ስርዓት ለሰውነት አስፈላጊ ሆነው የምንጠቀምባቸው የምግብ ቅመሞችና የመጠጥ ንጥረ ነገሮች ወይም ለፈውስ የሚቀርቡ መድኀኒቶች ሁሉ አግባብነታቸው እየተመረመረ በልክና በመጠን ጉዳት እንደማያስከትሉ ሆነው ካልተጠቀምንባቸው በጤና ላይ ችግር ያመጣሉ፡፡




 



ለማንኛውም ነገር መንስኤና ምክንያት ያለው ሲሆን በቅንጦት አብዝቶ ከመዝናናትና የመዝናኛ ቦታዎችንና ነገሮችን ከክርስትና ሕይወት አንጻር ለይቶ ካለማወቅም ባሻገር አደገኛ ወደ ሆነው የሱስ ምርኮኝነት ብሎም ወዳልታሰቡ የጠባይ ለውጥ የሚወስዱ መንስኤዎች በርካታ ናቸው፤ ለአብነት ያህልም:
የሚወዱትን የቤተሰብ አካል ወይም ወዳጅና ዘመድ (በሞት) ከማጣት የሚደርስ ኃዘን፣ ሥራ አጥነት ወይም ከዚህ ያልተሻለ የሕይወት ሸክምን ከአቅም በላይ የሆነ የኑሮ ውድድር አቅምን ያለማወቅ ችግር የአያያዝና የአጠቃቀም ጥበብ የሚያንሰው ብልጽግና መጠራጠር አለማመንና አለመታመን፣ የቤተሰብ የጓደኛና የአካባቢ ብልሽት በቀላሉ የመደሰት ወይም የመከፋትና የማዘን ጠባይ፣ የአእምሮ ድክመትና ፈቃድን የመግዛት ኃይል ማጣት የማህበራዊ ግንኙነት መበላሸትና የብቸኝነት ሥሜት በቤተሰብና ኅብረተሰብ ያጋራ ኑሮ ውስጥ የሚፈጠሩ የአስተሳሰብ የአቀራረብና የአኗኗር ግጭቶች (ፖለቲካ) የኅሊና ነፃነት ማጣት የሰብዓዊ መብቶች መጓደል የመንፈስ ከሃይማኖት ጸጋ መራቆትና በማን አለብኝ ስሜት መራመድ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ የሱስ ሌላውና ዋንኛው መጥፎ ገጽታው ማንነትንና ሕልውናን ከመጉዳቱ ባሻገር ባሪያ አድርጎ በኃይል መግዛቱ ምርኮኛ ማድረጉ ነው፡፡
ምንም ይሁን ምን የሱስ መንስኤው መፍትሔ ፈልጎ በጊዜና በወቅቱ ሥር ሳይሰድ ማስወገድ ያስፈልጋል ምናልባት በሕይወት ዘመን አብሮን የኖረ ክፉ ልምድ ረዥም ዕድሜን ያስቆጠረን ሱስ በሰው ሰውኛ በራስ ኃይል በደካማ ሥጋ ማስወገድ ይከብድ ይሆናል ነገር ግን በመንፈሳዊ ዓይን በእግዚአብሔር ቃል ግን ስንመለከት በእግዚአብሔር የማይሆን ምንም ነገር የለም በመሆኑም፡-
1.   ከሁሉ አስቀድመን ረድኤተ እግዚአብሔርን አጋዥ አድርገን ለለውጥ መነሳት




 



‹‹ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ›› እንዲል ሐዋርያው ጳውሎስ (ፊልጵ 413)
2.   በፍጹም እምነት እለወጣለሁ ብለን መነሳት
‹‹ለሚያምን ሁሉ ይቻላል›› (ማር 923)
‹‹ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም›› (ዕብ 16)
3.   እግዚአብሔር ነገርን እንደሚገለብጥ ታሪክን እንደለሚለውጥ ላመኑበት እንደማያሳፍር እርግጠኛ መሆን
‹‹እግዚአብሔርን አምኖ ያፈረ የለም›› (ሲራ 210)
4.   ለሱስ መንስኤ ከሆኑ ነገሮችና አካባቢዎች ጓደኞች መለየት
‹‹የተለያችሁ ሁኑ ከመካከላቸውም ውጡ ርኩስንም አትንኩ›› (2ቆሮ 617-18 ኢሳ 5211)
5.   መንፈሳዊ ስራዎችን ጥቂት በጥቂት መለማመድ
መንፈሳዊ ነገርን ጥቂት በጥቂት መለማመድ ለዚህ ለጊዜያዊው ዓለምም ለሚመጣውም እንደሚጠቅም ሲያስተምር ሐዋርያው ‹‹እግዚአብሔርን ለመምሰል ግን ራስህን አስለምድ ሰውነትን ለሥጋዊ ነገር ማስለመድ ለጥቂት ይጠቅማልና እግዚአብሔርን መመስል ግን የአሁንና የሚመጣው ሕይወት ተስፋ ስላለው ነገር ሁሉ ይጠቅማል›› (1ጢሞ 47-8) ይላልና፡፡
6.   የእግዚአብሔርን ቃል በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ መስማትና ማንበብ
‹‹ቃሌን የሚሰማ ከመከራ ስጋት ያርፋል›› (ምሳ 131)
የውሃ ጠብታ ቋጥኝ አለትን እንደሚሰብር ሁሉ የእግዚአብሔር ቃል የብዙ ዘመን የኃጢዓት ክምችትን ያጠፋል ‹‹የእግዚአብሔር ቃል (ድምጽ) ዝግባን ይሰብራል፣ የሊባኖስን ዝግባ ይቀጠቅጣል፣ የእግዚአብሔር ቃል የእሳቱን ነበልባል ይቆርጣል፣ የእግዚአብሔር ቃል ምድረ በዳውን (ባዶ የሆነውን ሕይወት) ያናውጣል፣ የእግዚአብሔር ቃል ዋላዎችን (ያልበረቱ ያልጠነከሩትን) ያጠነክራቸዋል›› (መዝ 285-9)
የእግዚአብሔር ቃል የደነደነ ልቡናን ይለውጣል ውስጥ ይፈትሻል
‹‹የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና የሚሰራም ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል የልብንም ስሜትና ሃሳብ ይመረምራል፣ እኛን በሚቆጣጠር በእርሱ በዓይኖቹ ፊት ሁሉ ነገር የተራቆተና የተገለጠ ነው እንጂ በእርሱ ፊት የተሰወረ ፍጥረት የለም›› (ዕብ 412-13)
7.   በሙሉ ፈቃደኝነት ወደ እግዚአብሔር መቅረብ
እግዚአብሔር አስፈቅዶ የሚፈውስና የሚምር በነጻነት የሚገዛ አምላክ በመሆኑ ‹‹ልትድን ትወዳለህ›› (ዮሐ 56) ፈውስን ትሻለህ መለወጥ ትፈልጋለህ በማለት በፍቅር ይጋብዘናልና እጃችንና ልባችንን በመስጠት እንማረክ ሙሉ ፈቃደኛም እንሁን፡፡






   


No comments:

Post a Comment