Friday, January 17, 2014

ክፍል ሁለት ዘመነ ዲዮቅሊጢያኖስ ዳግም በሮም ምድር



ዲዮቅልጥያስ ከደሀ ቤተሰብ የተወለደ በመሆኑ መንግስታዊ ዘር ባይቆጠርለትም አረግ ባይመዘዝለትም ተራ መታደር ሳለ ሀገሩ ከፋርስ መንግስት ጋር በተዋጋች ጊዜ ያሳየው ጀብዱና የጀግንነት ሙያው በመላው የንጉሠ ነገሥት መንግስት ውስጥ ለመታወቅ አብቅቆታል መልካም ዝናንም አትርፎለታል፡፡ እንዳጋጣሚም ሆኖ በዘመኑ የሮም መንግስት አስተዳደር ከስፋት የተነሣ ተዘበራርቆ ስለነበርና ወደ መውደቅም አዘንብሎ ስለነበር ዲዮቅልጥያኖስ የመንግስቱን ሥልጣን ይዞ (285 ዓ.ም) አውግስጦስ የሮም ንጉሥ ነገሥት ተባለ፡፡




ከአንድ ዓመት በኋላ 286 ዓ.ም የሮም ግዛት በጣም ሰፊ ከመሆኑ የተነሣ የሀገሪቱን ጸጥታ ለመጠበቅ እንዲመችና የአስተዳደር ጉድለት እንዳይፈጠር እርሱ የምሥራቁን ክፍል ይዞ የምዕራቡን ክፍል ለጓደኛው ለመክስምያኖስ ሰጠው መክስምያኖስም በሮም ምዕራብ ክፍል አውግስጦስ (ክቡር) ንጉሠ ነገሥት ተባለ፡፡ ከዚህ በኋላ ሁለቱም ዕሩያት መንበር ነገሥታት ቄሳር በሚያሰኝ የማዕረግ ስም ሁለት እንደራሴዎችን መርጠው ሾሙ በምስራቅ የዲዮቅልጢያኖስ አማች ጋሊሪዮስ ቄሳር ተብሎ የዲዮቅልጥያስ እንደራሴ ሆነ (293-311) በምዕራብ የታላቁ ቁስጠንጢኖስ አባት ከንስታንዲዮስ ክሎራን (293-306) ቄሳር ተብሎ የመክስምያኖስ እንደራሴ ሆነ የመንግስቱ ሥልጣን ከተረጋጋለት በኋላ ዲዮቅልጥያኖስ ታላቅ የሹም ሽር አድርጎ በፊት የነበሩትን እያስወጣ በምትካቸው የራሱን ታማኞች ሾመ ይህም ዘዴው ተቃዋሚ እንዳይነሣበት ረድቶታል፡፡
ዲዮቅልጥያኖስ ከሮማ ነገሥታት ተለይቶ የሚታወቅባቸው አንዳንድ አዳዲስ ነገሮች አሉ አይቶ አያውቅ እንደመሆኑ መጠን በጣም ተኩነስናሽ ጌጥ ወዳጅና ክብር የማይጠግብ ነበር በካባው አንገትና በቀሚሱ እጅጌ በመጫሚያው ዙሪያ የነበረው የወርቅና የእንቁ ዝምዝም ከሱ በፊት የነበሩ የሮማ ነገሥታት አድርገውት አያውቁም ነበር የቤተክርስቲያንን ታሪክ በሰፊው ያጠኑ ሊቃውንት ሮማን መሪዎች ጠባይና የፖለቲካ ይዞታም ሲናገሩ ይህ ዲዮቅሊጥያኖስ የፖለቲካ መሪነቱ ቢያግደውም የሰውን ልጆች ሃይማኖቶች ለማዋሐድ የሚጥር በሮማ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው አረማዊ ንጉሥ ነበር ክርስቲያኖችን ለመደምሰስና ለማጥፋትም እንደ ያለ ኃይለኛ የክርስቲያን ጠላት በሮም ነግሦ አያውቅም ነበር ይላሉ፡፡
ዲዮቅልጥያኖስ ክርስቲያኖችን አምሮ የጠላበት ምክንያቶች ነበሩት ከነዚህም ምክንያቶች አንዱ 296 ዓ.ም የፋርስ መንግስት የሮምን የግዛት ድንበር በመጣሱ ጋሌሪዮስ የሮም ጦር ሠራዊት አበጋዝ ሁኖ ወደ ፋርስ ዘመተ ነገር ግን በውጊያው ላይ የፋርስ ጦር አይሎ የሮምን የጦር ኃይል ድል አድርገው ጋሌሪዮስም ተማርኮ ወደ ፋርስ ከተወሰደ በኋላ አምልጦ አንጾኪያ ገባ፡፡
በዚህ ጊዜ ዲዮቅልጥያኖስ ወደ ፋርስ ዘምቶ ስለነበረው ሠራዊቱና ስለአማቹ ስለጋሌሪዮስም በደህና መመለስ ካህናተ ጣዖቱን ለማስጠንቆል ወደ ቤተ ጣዖቱ ሄዱ፡፡ ከዚያም ለጣዖት ለአጵሎስ (የፀሐይ አምላክ ለተባለው) የተለመደውን ገፈራ ካቀረበ በኋላ ከካህናቱ መልስ እገኛለሁ ብሎ ቢጠባበቅ ሳይነግሩት ቀሩ ምክንያቱን ቢጠይቅ ከተከታዮችህ መካከል በትእምርተ መስቀል የሚያማትቡ ስላሉ ነው አሉት፡፡ በዚህ ተናዶ በክርስቲያኖች ሁሉ ላይ የሞት ቅጣት እንዲፈጸምባቸው አዘዘ ከጥቂት ቀን በኋላ ጋለሪዮስም ወደ ግዛቱ ተመለሰ በተመለሰ ጊዜ ካህናተ ጣዖቱ ተሰብስበው ሄደው ‹‹ድል የሆንከው በሠራዊትህ ውስጥ ክርስቲያኖች ስለነበሩ ነው›› ብለው ነገሩት ዲዮቅልጥያኖስም ቀደም ብሎ የሰማውን መልስ ሳይነግረው አልቀረም፡፡
በዚህ ጊዜ እሱም ‹‹ድሉን ቢፈሩ መደላደሉን›› እንዲሉ ክርስቲያን የሆነ ሁሉ በጦር ሠራዊቱ ውስጥ እንዳይገኝ አዘዘ በሱ የሚመራ ክርስቲያኖችን እያደነ የሚያጠፋ የጸረ ክርስቲያን ድርጅት አቋቋመ ብዙ ክርስቲያኖችና የክርስቲያን ቅርሶቻቸው እንዳልነበሩ ሆኑ
ዲዮቅልጥያኖስ ክርስቲያኖችን የጠላበት ሌላው ምክንያት ደግሞ ከሱ በፊት እንደነበሩት የሮም ነገስታት ምስሉን አሠርቶ በምስራቅም ሆነ በምዕራብ ክፍል የሚገኙ የሮም ዜጎች ሁሉ ለምስሉ እንዲሰግዱለትና አምላካዊ ክብር እንዲያቀርቡለት አዘዘ ቤተክርስቲያን ይህን ትዕዛዝ አልተቀበለችውም፣ በቤተክርስቲያን ፈጣሪ እንጂ ፍጡር አይመለክባትምና ቤተክርስቲያን ይህን አሻፈረኝ በማለቷ ሁሉ የሚርድለትና የሚንቀጠቀጥለት ዲዮቅልጥያኖስ ተደፈርኩ ተናቅሁ ብሎ ያዙኝ ልቀቁኝ አለ፡፡
እንደተለመደውም ከጣዖቱ ከአጵሎስ ካህናት ጋር ስለ ጉዳዩ ተወያየ እነሱም ‹‹እነዚህን ደፋሮችና ሰው ናቂዎች ከግዛትህ ማጥፋት ነው፣ የነገሥታትን ክብር ይዳፈራሉ፣ የአምላኮቻችንንም ህልውና ይቃወማሉ፣ እነሱ ካልጠፉ ለመንግስታችንም ሆነ ለአምላቻችን ጤና አይሰጡም›› አሉት፡፡ ከነሱ ባገኘው ምክርና መመሪያ መሰረት ከመጋቢት ወር 303 ዓ.ም ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ በጠቅላለው በሮም ግዛት ውስጥ የሚገኙ ክርስቲያኖች ሁሉ በያሉበት እንዲረሸኑ አዘዘ ከተመሠረተች ጀምሮ በመከራ ታሪኳ ውስጥ ተመሳሳይ የሌለው እልቂት በቤተክርስቲያን ላይ ተፈጸመ፡፡ የዲዮቅልጢያኖስ ባለ ወጎች ክርስቲያኖችን መግደላቸው ሳይሆን የሚያሰቅቀው አገዳደላቸው ነበር፡፡
ክርስቲያኖች ሥቃይ ሲጸናባቸው ወደ ቤተ ጣዖት እንዲመለሱ በማለት ሳይገደሉ ሕዋሳቶቻቸው እየሰነጣጠቁ ያሰቃዩአቸው ነበር የሚቆራርጡትንም አካቸውን እየወሰዱ ለጣዖቶቻቸው ያጤሱት ነበር ግዳይ እንደመጣል ምርኮ እንደማቅረብ ይቆጥሩትም ነበር ክርስቲያኖች ግን ይህ ሁሉ ግፍ ሲፈጸምባቸው መከራውን ተሰቅቀው ከእምነታቸው ወደ ኋላ አላሉም እንደተለመደው ‹‹ጌታ ክርስቶስ ነው ሌላ ጌታ አናውቅም›› እያሉ እምነታቸውን በደማቸው አተሙት ግማሾቹም በዱር በገደል እየተወሰዱ በድብቅ ሃይማኖታቸውን ማስተማር ቀጠሉ፡፡ አዋጁ ከታወጀበት ቀን ጀምሮ ዲዮቅልጥያኖስ በኒቆሜዲያ ከተማ በሚገኘው ቤተመንግስት ሰገነት ላይ ሁኖ የከተማይቱ ክርስቲያኖች ሲታረዱና አቢያተ ክርስቲያናቱም ሲቃጠሉ ይመለከት ነበር፡፡
ይህ ሁሉ የጭካኔ እልቂት ቢፈጸምባቸውም ክርስቲያኖች ሲቆርጡት ከስሩ እንደሚያቆጠቁጥ ዛፍ ቁጥራቸው እየጨመረ ሄደ ከአንድ ዓመት በኋላ ክርስቲያኖችን ሞት እንዳተቃጠላቸው አይቶ አዲስ የማጥቂያ ዘዴ ለመፈለግ ሲል አዋጁን በአዋጅ ለወጠው የአሁኑ አዋጅ እንደፊተኛው ሳይሆን ጥቂት ዛሬ የተቀላቀለበት ስለነበር ትዕዛዙን እንደሚከተለው ይዘረዝረዋል
1.   አብያተ ክርስቲያናት ይትዐፀዋ አቢያተ ጣዖታት ይትረ ኃዋ
2.   ክርስቲያኖች እንዳይገናኙ
3.   ስለ ክርስትና ኃይማኖት የሚናገሩ መጻሕፍት ሁሉ እንዲቃጠሉ
4.   የቤተክርስሪያን ንብረት የሆነ ሁሉ እንዲወረስ
5.   ማንኛውም የሮም ዜጋ ክርስቲያን ከሆነ ከመንግስት ሥራ እንዲወገድ
6.   ባሮችም ክርስትናን ከተቀበሉ ነጻ የመውጣት መብት የላቸውም
7.   ክርስቲያኖች ምንም ህጋዊ ምክንያት ቢኖራቸው በማንም ላይ ክስ ለመመስረትና ስለመብታቸውም ለመከራከር አይችሉም የሚል ነበር
ይህም ሁሉ ሆኖ ዲዮቅልጢያኖስ ቤተክርስቲያንን ለመደምሰስ የነበረው ሕልም ቅዥት ሁኖ ቀረ ቤተክርስቲያን በሰው የምትፈርስ ሰው ሰራሽ አይደለችና፡፡
ይህንን ካልን ዘንዳ ወደ ርዕሳችን ስንመለስ ይቺን ትንሽ ጦማር ለመጻፍ ያነሳሳን የሰሞኑ የአውሮፓውያኑ ፍርድ ቤት ውሳኔ ነው ምንም እንኳን ዲዮቅልጥያኖስና መክሰምያኖስ፣ ትራጃንና ዳክዮስ ባይኖሩም ዛሬም የነሱ የግብር ልጆች አሊያም የዲያብሎስ የግብሩ ልጆች ቤተክርስቲያንን በመፈተናቸው ውጊያው አልቆመም ይልቁንም መልኩንና ይዘቱን በመቀየር ሁሌም ሲያውክ ይኖራል እንጂ፡፡
የአውሮፓውያን ታይምስን ዘግቦ የተጻፈው ጽሑፍ እንዳስነበበን የአውሮፓ ፍርድ ቤቶች በሕዝብ እይታ ስፍራ (Public Places) ማለትም በትምህርት ቤቶች፣ በመሥሪያቤቶች በፍርድ ቤትና በታላላቅ ቦታዎች የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት የሚያሳዩ ሥዕሎችና ሐውልቶች እንዲፈርሱና እንዲነሱ የሚያዝዝ ሕግ ነው፡፡
ይህ ትዕዛዝ ወይም አዲስ የሕግ ውሳኔ በርካታ ክርስቲያኖችን ያሰደነገጠ ከመሆኑም ባሻገር ብዙዎችንም አስቆጥቷል የቤተክርስቲያን ጻሐፊዎችና ተመራማሪዎች ይህንን አዋጅ ከላይ ከዘረዘርነው ከዘመነ ዲዮቅልጥያኖስ አዋጅ ጋር ተመሳሳይነት እንዳለው ይናገራሉ፡፡ መጽሔቱ በማከልም ምንም እንኳን ይህንን ውሳኔ ያሳለፉት አካላት ውሳኔውን ለመወሰን የተገደዱበትን ምክንያት ሲገልጹ የሌሎች የዕምነት ድርጅቶችን መብት ላለመጋፋት እንደሆነ ቢገልጽም የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮችና አዋቂዎች ግን ሆን ተብሎ ክርስትናን ለማጥፋትና እስልምናን ለማስፋፋት የተደረገ ሴራ ነው ይላሉ ያም ሆነ ይህ ግን አሳዛኝና አስደንጋጭ ውሳኔ ከመሆኑም ባሻገር የክርስትና ፈተና መልኩን ቀይሮ በመምጣት አካልን ወይም ሥጋን ከመጉዳት ወደ ሥነ ልቦና ቁስለት መዘዋወሩን ልብ ይላል፡፡
ምንም እንኳን ብዙዎች የምዕራባውያኑ አቢያተ ክርስቲያናት ከአማኞች ትኩረት ማጣትና አምልኮታቸው ወደ ዘመናዊነት ከመቀየሩ የተነሣ አንዳንዶቹም ሲሸጡ ሌሎችም ወደ ሙዝየምነት እየተቀየሩ ቢሆንም እንዲህ ዓይነት ስር ነቀል የጥፋት ዘመቻ ግን መታወጁ ሁሉንም ሳያሰደነግጥና ሳያስቆጣ አልቀረም፡፡
አባቶቻችን በምሳሌ ሲያስተምሩ ጓደኛህ ሲታማ ለኔ ብለህ ስማ ይላሉና፤ ምንም እንኳን በዶግማና በቀኖና ብንለያይም የክርስቲያኖች ሕመም ግን ሕመማችን ነውና፣ ዛሬ በሃይማኖቶች መብት ሰበብ አልያም በዘመናዊነት ሰበብ በዚህ ፈተና ሰለባ የሆኑት ቅዱሳን ሥዕላትና አቢያተ ክርስቲያናት ፈተና ወደ ሌላውም ክፍል እንዳይዛመት መጸለይ ይገባል፡፡
   


No comments:

Post a Comment