Friday, January 31, 2014

ወደ እኔ የገባው ሰው ይድናል ይገባል ይወጣል መሠማሪያም ያገኛል

‹‹የሉተራውያን ስህተት በሊቃውንት አስተምህሮ ሲገለጥና ሲጋለጥ››ክፍል 1

እንደ አብና መንፈስ ቅዱስ የአምልኮት ስግደት የሚቀርብለት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ክብር ምስጋና ይግባውና ምንም እንኳን መናፍቃኑ ከ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ኃይሉን ክደው አማላጅ ቢሉትም ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ያሳደገቻቸው ልጆቹ ግን የጌቶች ጌታ የነገስታት ንጉሥ የገዥዎች ገዥ መሆኑን አምልተውና አስፍተው አርቀውና አራቀው ትውልዱን ሲያስተምሩ ቆይተዋል፡፡
በቅዱሳት መጻሕፍት በጎላና በተረዳ ሁኔታ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት መገለጹ ይታወቃል፡፡ ለቤዛነትና ዓለምን ለማዳን መድኀኔዓለም ክርስቶስ ከቤተልሔም እስከ ቀራኒዮ የተጓዘበትን የድኅነት ሥራ ባለመረዳት ተቋዋሚዎችና ተረፈ ሉተራውያን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አማላጃችን ሲሉት ይሰማሉ፡፡









ለዚህም የተሳሳተ ትምህርታቸው ዋቢ በማድረግ የሚያቀርቧቸው ኅይለ ቃሎችን ትክክለኛ ትርጉም ፍቺ ምን እንደሆኑ ከዚህ በታች ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ በመመራት የሰጡትን ምላሽ ለመመልከተ እንሞክራለን፡፡
1.   ሉተራውያን ኢየሱስ ክርስቶስ አማላጅ ነው ሲሉ ከሮሜ 8፡35 በተጨማሪ በ(ዮሐ 10፡9) እና
(ዮሐ 14፡63) ይጠቅሳሉ፡፡
ለመሆኑ ጥቅሶቹ ስለ ምልጃ ይናገራሉን? ወይስ ስላሌላ? ቅድስት ቤተክርስቲያን በዮሐ 10፡9 ያለውን ንባብ እንዲህ ታብራራዋለች፣ ወደ ቤት ለመግባት በበር መግባት እንደሚያስፈልግ ወደ መንግስተ ሰማያት ለመግባት በኢየሱስ ክርስቶስ የባሕሪ ልጅነት የባሕርይ አምላክነት አምኖ መጠመቅ ያስፈልጋል ሳያምኑበት መዳን አይቻልምና (ዮሐ 6፡47 ፣ ሐዋ 8፡36) የበጎች ደጅ ክርስቶስ ነው፣ በጎቹ ምዕመናን ናቸው፡፡
ወደ እኔ የገባው ሰው ይድናል ማለቱ በእኔ አምላክነት ያመነ ሰው ከክህደት ይድናል ማለቱ ነው ይገባል ይወጣል መሠማሪያም ያገኛል ሲል ወደ ሃይማኖት ይገባል በጎ ሥራ ለመሥራት ይወጣል፡፡ ስለሃይማኖቱም እሳቱን ስለቱን መስቀሉን ሰማዕትነትን ያገኛል ስለ ስሜ ይመሰክራል ማለት ነው በተጨማሪም እኔን አብነት ያደረገ ከፍዳ ከኩነኔ ከገሀነም ይድናል ወደ ወንጌል ይገባል በወንጌል ያምናል ለማስተማር ይወጣል፣ ጉባኤ ምዕመናንን ያገኛል ማለት ነው (1ዮሐ 2፡2-6) እኔን በኩር ያደረገ ከፍዳ ከኩነኔ ይድናል ከፍቃደ ሥጋ ይወጣል ወደ ፈቃደ ነፍስ ይገባል ክብረ ሥጋ ክብረ ነፍስን ያገኛል፤ መንግስተ ሰማይን ይወርሳል ማለት ነው፡፡ (ገላ 5፡16-26) ፣
2.     በዮሐ 14፡6 ላይ የተጠቀሰውም ስለ ሃይማኖት ይናገራል እንጂ ስለ ምልጃ ወይም ኢየሱስ ክርስቶስ አማላጅ ነው አይልም ቢጽ ሐሳውያን ያልተጻፈ ያነባሉ ይተረጉማሉ በዚህ ምዕራፍ የመጀመሪያው የቁጥሩ ኃይለ ቃል በእግዚአብሔር አመኑ በማለት ስለሃይማኖት እንደሚናገር ይታወቃል፡፡
በቁጥር ሦስት (3) ላይ መንግስተ ሰማያትን ጎዳና (መንገዱን) ታውቃላችሁ ሲላቸው መንገዱን እንዴት እናውቃለን ብለው ነበርና መንገዱ በክርስቶስ በማመን መሆኑን ማለትም ሃይማኖት ወንጌል መሆኑን ስላልተረዱ በቁጥር ስድስት (6) ላይ ወደ አብ የምወስድ እኔ ነኝ ይላቸዋል ንባቡ አማላጅ ነኝ አይልም ቁጥር ሰባት (7) ላይ እኔንስ ብታውቀኝ አባቴን ደግሞ ባወቃችሁ ነበር ከአሁን ጅምራችሁ ታውቁታላችሁ አይታችሁትማል በማለት መንገድ ያለውን እውቀት መሆኑን ተርጉሞ ወልድን በሃይማኖት ፣ አብንም በሃይማኖት ማወቅ ወይም ማየትን ያስረዳቸዋል፡፡
3.   ቢጽ ሐሳውያን 1ዮሐ 2፡1 ያለውን ይዘው ክርስቶስ ጠበቃችን ነው ይላሉ በመሠረቱ ንባቡ ትክክል አለመሆኑን እየገለጽን እንደሚከተለው መሆኑን ለማስታወስ እንወዳለን ‹‹ደቂቅየ ዘንተ እጽሕፍ ለክሙ ከመ ኢትአብሱ ይህድግ ለነ ኃጣውኢነ›› ነጠላ ትርጉም ‹‹ልጄቼ እንዳትበድሉ ይህንን እጽፍላችኋለሁ የበደለም ቢኖር ጰራቅሊጦስ አለን ከአባት ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ቸር ነው ኃጢዓታችን ያስተሰርይልን ዘንድ የምልከው››  ይላል ጳራቅሊጦስ ማለት መስተሰርይ (ኃጢዓትን የሚያስተሰርይ): መስተፈስሒ (ደስ የሚያሰኝ)፣ መጽንኢ (የሚያጽናና ፣ አጽናኝ) መንጽሂ (የሚያነጻ)፣ ከሳቲ (ገላጭ) ማለት ነው፡፡
ከዚህ በላይ የገለጽነው የንባብ ትርጉም ደግሞ እንደሚከተለው ይነበባል በድሎ ንስሐ የገባ ሰው ቢኖር ኃጢዓታችንን የሚያስተሰርይልን ኢየሱስ ክርስቶስ ከአብ ዘንድ የሚሰድልን ጰራቅሊጦስ አለን ኃጢዓታችን ያስተሰርይልን ዘንድ ቸር የባሕርይ አምላክ ነው የሚል ነው፡፡
4.   ከዚህ በላይ ከተገለጸው በተጨማሪ (1ኛ ጢሞ 2፡5-7)ን በመጥቀስ ሉተራውያን ክርስቶስ አማላጅ ነው በማለት የተዋህዶ ልጆችን ለማደናገር ይሞክራሉ እስኪ በቅድሚያ የጥቅሱን ኃይለ ቃል እንመልከት
‹‹አንድ እግዚአብሔር አለና፣ በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ እርሱም ሰው የሆነው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፡፡ ራሱንም ለሁሉ ቤዛ ሰጠ፤›› ይላል እንግዲህ ይህን ንባብ ያለትርጉም እንኳን ብናየው ክርስቶስ አማላጅ ነው የሚል ቃል አናገኝም በቅድስት ቤተክርስቲያናችን (1ኛጢሞ 2፡5-6)እንደሚከተለው ተነቦ ይተረጎማል፡፡ ‹‹አሐዱ እግዚአብሔር እንግዚአብሔር አንድ ነው አለ በተለየ አካሉ አንድም ከወልድ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በባሕርይ በሕልውና አንድ እንደሆነ ሊያውቁ ይወዳልና›› ‹‹ወአሐዱ ኅሩይ ማዕከለ እግዚአብሔር ወሰብዕ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘከነ ሰብዐ›› (ኢሳ 45፡21-22 ፣ ዮሐ 17፡3 ፣ ዕብ 12፡24)
ሰው ሆኖ ሰውና እግዚአብሔርን ያስታረቀ ኢየሱስ ክርስቶስን አንድ ነው አለ፤ በተለየ አካሉ አንድም ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በባሕርይ በሕልውና አንድ ነው፡፡












‹‹ዘመጠወ ርእስ ቤዛ ኩሉ›› ለሁሉ ቤዛ አድርጎ ራሱን አሳልፎ ለሕማም ለሞት የሰጠ ይላል::
በተጨማሪ (በ1ኛ ጢሞ 2፡5-7) ላይ ያለውን ኅይለ ቃል በምስጢር ስንገልጠው መድኃኔዓለም ክርስቶስ ስለፈጸመው የማዳን ሥራ እናስታውስ ዘንድ ግድ ይለናል በአገዛዝ በፈቃድ በሥልጣን ዓለምን በመፍጠር በዕለተ ምጽዓት በማሳለፍ አንድነት ካላቸው ሦስት አካላት መካከል አንዱ ወልድ ወይም የአብና የመንፈስ ቅዱስ ቃላቸው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ለማዳን ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከእመቤታችን ከቅደስት ድንግል ማርያም ተወልዷል የመጣው በትህትና ነውና በበረት ተወልዶ እንደማንኛውም ሰው በየጥቂቱ ከማዳኑም በላይ በአምላክነቱ ማንም የማያዘው ቢሆንም ለቅድስት እናቱ ይታዘዛት ነበር ከፍጹም ትህትናው የተነሣ ከተርታ ሰዎች ጋር ተሰልፎ ውኃውን ሊባርክልን በባሪያው እጅ ተጠምቋል ጾሟል የጸሎት ስርዓትንም አሳይቷል ሥጋን ተዋህዷልና፡፡ በባሕርይው እንቅልፍ የሌለበት ትጉህ ጌታ አንቀላፍቷል፣ በልቷል፣ ጠጥቷል ፣ ደክሟል፣ አልቅሷል ከዚህ በላይ የገለጽነውን ሁኔታ ፍጡራን በፍጹም ሊመረምሩት አይቻላቸውም ፍጡራን ሁሉ ሊያስተውሉት የሚገባቸው ታላቅ ጉዳይ አለ:-
ይኽም አምላክ ሰው ሆኖ ከፅንስ እስከ መስቀል ከዚያ አልፎ ሞቶ የመነሣቱን ዕርገቱን ሊመረምሩት ቀርቶ ሊያስቡት እንኳን የማይቻል ድርጊት መሆኑን ነው: ዋናው ነገር አምላክ የወደደውን ለማድረግ ይችላል በማለት ማመን ነው እንግዲህ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ፣ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው›› ያለው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አማላጅ በማለት ሳይሆን ድህነታችን በእርሱ በኩል መፈጸሙን ለማመልከት ነው በመሠረቱ የጌታችን ጥምቀት፣ ጾም፣ ጸሎት ፣ ሥግደት ፣ ድካም፣ ለቅሶ፣ ተአምራት ሁሉ ለቤዛ ዓለም የተፈጸመ ነው በጽንስ የተጀመረው ዓለምን የማዳን ሥራም በቀራኒዮ ኮረብታ መፈጸሙ ይታወቃል፡፡ ሰውና እግዚአብሔርን ለማስታረቅ አበይትና ደቂቀ ነቢያት የብሉይ ኪዳኑ ካህናት በሱባኤ በጾምና በጸሎት ስግደት መስዋዕትና ምጽዋት ፈጣሪያቸውን በመረረ ለቅሶ ለምነዋል ነገር ግን ሰውና አምላክ አልታረቁም ስለዚህ አምላክ ሰውን ሊታረቀው የሚገባው በፍጹም ቸርነቱ ነውና፡፡
መድኃኒታችን ራሱን የተወደደ መስዋዕት አድርጎ ለባሕርይ አባቱ ለአብና ለባሕርይ ሕይወቱ ለመንፈስ ቅዱስ ለራሱም ጭምር አቀረበ የእርሱ መስዋዕትነት ወደር የሚገኝለት አልነበረም ራሱ መስዋዕት ሰዊ፣ ራሱ መስዋዕት፣ ራሱ መስዋዕት ተቀባይ ሆኖ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ከራሱም ጋር አስታረቀን (2ቆሮ 5፡15-21) ታረቀንም::
ይህ የቤዛነት ሥራ የማስታረቅ አገልግሎትም የተፈጸመው ለአንድ ጊዜ በዕለተ አርብ ሲሆን የመድኃኒታችን ቤዛነትም እስከዘላለም ሕያውነት ያለው ነው ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስም ዘወትር በእርሱ በኩል ወደ እግዚአብሔር (አብ) የሚቀርቡትን ሊያድናቸው ይቻለዋል ለዘላለም ሕያው ነውና ያስታርቃቸዋል ይላል (ዕብ 7፡25)
አንዳንድ ወገኖች ግን በተለይም ሉተራውያን መድኃኒዓለም ክርስቶስ በሥጋ ተገልጾ የፈጸመው የማዳን ሥራ በዕለተ ዓርብ ጌታ ‹‹ተፈጸመ›› (ዮሐ 19፡3) ባለ ጊዜ ለአንዴና ለዘላለም የተደረገ አገልግሎት መሆኑን ባለመረዳት ክርስቶስ አማላጃችን ነው ዛሬም ያማልደናል ይላሉ ይህ አባባል ግድፈት ወይም ስህተት ብቻ ሳይሆን ክህደትም ነው፣ አለበለዚያም ምስጢርን አለመረዳት ይሆናል፡፡ ጌታችን የፈጸመው ዓለምን የማዳን ሥራ አንድ ጊዜ የፈጸመውና ዘላለማዊነት ያለው መሆኑን እናስተውል: ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹በልጁ ሞት ታረቀን›› (ሮሜ 5፡10) ብሏል፡፡
በትንቢት መጽሐፍም "የእስራኤልን ፈራጅ ጉንጩን በበትር ይመታሉ" (ሚክ 5፡1) ተብሎ ተጽፏል ለመሆኑ ጉንጩን በጥፊ የተመታው ማነው? መድኃኔዓለም ክርስቶስ አይደለምን? እንግዲህ ፈራጁን አማላጅ የሚሉት ታላቅ ማስተዋል ጎድሏቸው ሲስቱ እናያለን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከአብ ቀኝ የተቀመጠ የቅዱሳንን ነፍስም የሚቀበል እንደሆነ ከዚህ በታች ከተገለጸው የመጽሐፍ ክፍል እንመልከት ‹‹ጌታ ኢየሱስ ሆይ ነፍሴን ተቀበል›› ብሎ ሲጣራ ይወግሩት ነበር ተንበርክኮም ‹‹ጌታ ሆይ ይህን ኃጢዓት አትቁጠርባቸው›› ብሎ በታላቅ ድምጽ ጮኸ (ሐዋ 7፡59) እንግዲህ ቅዱስ እስጢፋኖስ ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጸሎት አቅርቦ ነፍሱን አደራ ሲሰጥ ስለ ኃጥአንም ሲማልድ እናነባለን ስለዚህም መድኃኒታችን ፈራጅ እንጅ አማላጅ አለመሆኑን በዚህ ታሪክ በማያሻማ መልኩ መገለጡን እናስተውላለን፡፡
5.   ‹‹አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ›› (ማቴ 27፡46)
መድኃኒታችን ከዚህ በላይ የተገለጠውን ኃይለ ቃል የተናገረበት ምክንያት ለአቅርቦተ ሰይጣን ነው ዲያብሎስም ፍጡር መስሎት ስጋውን በመቃብር ነፍሱን በሲኦል ሊቆራኝ ቀረበ ጥንት ዲያብሎስ የአዳምን ልጆች እንደ መሶብ ፍርፋሪ ሲለቃቅም ሲያስጨንቅ ኖሯል፡፡ በድህነት ዕለት በዕለተ ዓርብ ግን ዲያብሎስ ጉድ ፈላበት ጌታችንም ክብሩን ገለጠለት ቅዱሳን መላዕክትም በመስቀሉ ዙሪያ ወድቀው ሲያመሰግኑት ነበር ዲያብሎስ ተጨነቀ እንዳያመልጥ በእሳት ሰንሰለት፣ በነፋስ አውታር ወጥሮ ያዘው ‹‹ሰው ሆኖ ስጋን ተዋህዶ ድል የነሣኝ ማን ነው? ብሎ ወዶ ፈቅዶ ጌታውን ፈጣሪውን አወቀ፣ ከእንግዲህ በእሱ ካመኑ ሰዎች በማንም ላይ ክፉ ማድረግ አይቻለኝም ማንንም ለመጉዳት ስልጣን የለኝም››
መድኃኒታችን በአንድ በኩል ዲያብሎስን ሲያስር ለነፍሳት ደግሞ ነፃነትን ሰጣቸው ሞታቸው በሕይወት ኃዘናቸው በደስታ ተለወጠ
6.   ‹‹ወደ አባቴ ወደ አባታችን ወደ አምላክችሁ አርጋለሁ›› (ዮሐ 20፡17) ይላል::
ጌታችን ከአብ የሚያንስ ሆኖ አይደለም ከዚህ በላይ ያለውን ኃይለ ቃል የተናገረው: ይህንን የጌታችንን ንግግር የዘመነ ሊቃውንት መብራት የነበረው ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንደሚከተለው ይተነትነዋል፡፡
‹‹ነገር ግን እርሱ በዚህ ክርስቶስ በእውነት ሰው እንደሆነ አስረዳ ፤ ፈጽሞ ወደ አልተለየው ወደ አብ ከማረጉ አስቀድሞ ለደቀመዛሙርቱ አምላኩ አምላካችሁ አለ ይህን በሰሙ ጊዜ ይህን የተናገረ ስጋ ብቻ እንዳይመስላችሁ ሰው የሆነ እርሱ እግዚአብሔር ቃል አስቀድሞ አባቴ ብሎ ከዚህ በኋላ አምላኬ አለ እንጂ ፤ እኔ ሰው የሆንኩ አምላክ ነኝና እኔም አንድ ነኝና ይህንንም ያንንም እኔ እላለሁ፤ ይላል የሰውን ባሕርይ ገንዘብ አድርጌያለሁና ኃጢዓት የሌለበት እርሱ እኔ ነፍስና ሥጋን በእውነት ተዋህጃለሁና ከእኔ ጋር አንድ አካል አንድ ባሕርይ ላደረግሁት ለሥጋ ሥርዓት እንደሚገባ እንዲህ አባቴን አምላኬ ብየ ጠራሁት›› ሃይ አበ ገጽ 248

 

No comments:

Post a Comment