Wednesday, January 15, 2014

‹‹የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው››(ሉቃ 23:34)






ይህንን ቃል የተናገረው ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን የእግዚአብሔር ልጅ በተለየ አካሉ ከድንግል ማርያም ተወልዶ እንባቸውን ሊያብስ ነገራቸውን ሊገለብጥ ታሪካቸውን ሊቀይር ከምንም በላይ ሰዎች በኃጢዓት ሞት ተፈርዶባቸው መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ ተጭኗቸው ጸጋቸው ተገፎ ከክብራቸው ተዋርደው ነበርና፣ ክብራቸው ይመለስ ዘንድ ጸጋ ያለብሳቸው ዘንድ ሊቁ አትናቴዎስ በትምህርቱ ‹‹የእግዚአብሔር ልጅ የሰው ልጆችን የእግዚአብሔር ያደርግ ዘንድ የሰው ልጅ ሆነ›› እንዳለ ሰው ሆኖ ቢወለድ ሰዎች ግን ግብራቸው ክፉ ነበርና በመገለጡ ደስ አላላቸውም ይልቁንም ‹‹የዮሴፍ ልጅ ፣ የጸራቢ ልጅ›› ብለው አምተው አሳሙት ክፉ ስድብንም ሰደቡት ይባስ ብለው ይገድሉት ዘንድ ፈለጉ ጥዋትና ማታም መግቢያ መውጫ አሳጡት ዕለተ አርብ ቀን እስኪደርስም ፈታ አጥተው አሳደዱት፣ በመገለጡ ሐሴት አድርገው በድኅነቱ ታምነው፣ በተስፋው ተስፋ አድርገው ከዋለበት እየዋሉ ካደረባት እያደሩ የቃሉን ትምህርት የሚሰሙትን የእጁን ተአምራት የሚያዩትንም አብረው አሳደዷቸው በስሙም እንዳይማሩና እንዳያስተምሩ ማዕቀብ ጣሉባቸው ነገር ግን እውነት ለጊዜው ትዳፈን ይሆናል እንጂ አትጠፋም፡፡



ኢየሱስ ክርስቶስም የማዳን ሥራውን የሚሰራበት በቀራኒዮ አደባባይ ላይ መስዋዕት ሆኖ ንጹሕ ክቡር ሥጋውን ስለ አዳምና ልጆቹ የሚያቀርብበት ሰዓት ደረሰ አይሁድ ቀድሞውኑ ጠልተው አስጠልተውት አምተው አሳምተውት ነበርና ሴራን አሴሩ ተንኮልን ዶለቱ የክፋት መልዕክተኛ የጥፋት ልጅ ታምኖ የከዳውን ይሁዳን በ30 ብር ሸነገሉት፣ እሱም ጌታውን አሳልፎ ሰጣቸው፣ ከዚያ በኋላማ የተናገሩት ያደረጉት ምኑ ይወራል፣ እያዳፉ እያቃኑ ከሐና ቀያፋ ወደ ሄሮድስ፣ ከሄሮድስ ወደ ጲላጦስ፣ ከጲላጦስ ወደ ቀራኒዮ ይዘው አጣደፉት፡፡
በዚህ ሁሉ ግን ከሰዎች ክፋት ይልቅ የአምላክ ትህትና የፈጣሪ ትዕግሥት፣ የእግዚአብሔር ትከሻ ሰፊነት በሁሉ ተገልጦ አዎ ታያላችሁ ግን አያስተውሉም ተብሎ የለ በወንጌል አንድስኳ የሚያስተውል ጠፋ ካሣ ተከፍዩ ካሣ ከፈለ ይቅርታን አዳዩ ይቅርታ ጠየቀ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው ብሎ የባሕርይ አባቱን ጠየቀ፣ የባሕርይ ሕይቀቱን አማለደ ከራሱም ጋር አስታረቃቸው (2ቆሮ 517) ከዚህ በኋላ ግን ተፈጸመ አለ፣ እግዚአብሔር ሰው ሆነ ባጭር ቁመት በጠባብ ደረት የተገለጠበት ዓላማ ዕዳ በደልን ደምስሶ መርገምን ሽሮ ፍጹም ካሣን ከፍሎ የተጣሉትን ሰላም ሆኖ ለማስታረቅ ነበርና፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ የድህነት ሥራውን ሰርቶ ካረገ ከ1600 ዓመት በኋላ የዲያብሎስ የግብር ልጆች ተረፈ አይሁድ በመሮያቸው በማርቲን ሉተር አማካኝነት እንደገና የማይናገር ሥራቸውን ጀመሩ ቀድሞ አባቶቻቸው አይሁድ ተሰናክለው ያሰናክሉ ነበር፣ ዛሬም ሉተራውያን እነሱ ግራ ተጋብተው ብዙውን ግራ አጋቡት የእግዚአብሔር ልጅ ሰውን ለማዳን በተለየ አካሉ ሰው ሆኖ ቢገለጥ ፈጣሪነቱን ዘንግተው ‹‹ፍጡር›› ነው አሉ፣ ክብር ምስጋና ይግባውና እሱስ የፍጥረታት ፈጣሪ ነው ‹‹ሐዋርያት እንዳስተማሩን እኛ ፍጥረቱ ነንና እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን›› ኤፌ 210
በተሳሳተው ትምህርታቸውም ከባሕርይ አባቱ ከአብና ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ አሳንሰው የፍጡራንን ሥራ ይሠራል ተማላጁን ያማልዳል፣ ተለማኙን ይለምናል በማለት የስድብን ስድብ ይሰድቡታል፣ ከክብርም አዋርደው በሰይጣን መንፈስ በመሆን ያዋርዱታል፡፡
እነሆ በዚህ የክህደት ትምህርታቸውም በመቀጠል ላለፉት 400 ዓመታት አብዛኛውን የዋህ ሕዝብ ወደ ባዶ አዳራሻቸው አጋዙት፣ ‹‹ሕዝቤ ዕውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፋ›› ሆሴ 46 እንዲል አምላካችን በነቢያቱ አድሮ ብዙ ወገኖቻችን እውነታውን ካለመረዳት በቂ የሆነ መረጃን ካለማግኘት አንዳንዶችም ካለማስተዋል የተነሣ ከበረት ወጥተው ከመንጋው ተለይተው የበግ ለምድ ለለበሱ አውሬዎች ተዳርገዋል፡፡
እንዚህ ተረፈ አይሁድ ሉተራውያንና ተታዮቻቸው የማሳቻና የማታለያ ጥበባቸውን በመቀያየር በልሳን እንናገራለን በማለት ትርጉም በሌለው ተራ የቃላት ጋጋታ በወፍ ቋንቋ የእግዚአብሔርን ሕዝብ አጃጃሉት ‹‹ሐዋርያው ጳውሎስ በዓለም ቁጥር የሌለው በርካታ የቋንቋ ዓይነት ይኖራል ቋንቋም የሌለው ሕዝብ የለም እንግዲህ የቋንቋውን ፍቺ ባላወቅ ለሚናገረው እንግዳ እሆናለሁ›› እንዲሁም ትርጉም የሌለው ነገር መናገርም ዋጋ እንደሌለው ሲገልጽ ‹‹ነፋስ የመላበት ነገር እንኳ ዋሽንትም ክራርም ቢሆን ድምጽ ሲሰጥ የድምፁን ልዩነት ባይገልጥ በዋሽንት የሚነፋው ወይስ በክራር የሚመታው መዝሙር እንዴት ይታወቃል›› (1ቆሮ 14710) በማለት ነው ያስተማረው እነሱ ግን ማስተዋልን በማጣት ስተው ያስታሉ፡፡
በሌላው ከዚህ በፊትና ተአምር እናደርጋለን ፈውስ እንፈውሳለን በመንፈስ እንሞላለን እያሉ በርኩስ መንፈስ ኃይል እያንዘፈዘፉ አረፋ እያስደፈቁ በመዘረርና በማንከባለል መንፈስ ቅዱስን ሳይሆን ርኩስ መንፈስን እየሞሉ ኢየሱስ ክርስቶስ ከእስራት ፈትቶ ያዳነውን ሕዝብ እንደገና በዲያብሎስ እስር ሥር እያደረጉ በነፍስ ይገድላሉ በዚህ የማታለያ ጥበባቸው በቁጥር ይህ ነው የማይባሉ ነፍሳትን አጥምደውበታል፣ ወደ አምልኮ ሰይጣንም መርተው ወስደውበታል፡፡


ሰሞኑን ከወደ አፍሪካ የሰማነው ዜና ደግሞ አዲስ የማታለያና የማደናገሪያ ዜና ይመስላል አንድ በደቡብ አፍሪካ የሚገኝ ፓስተር ነኝ ባይ ለሚያስተምራቸው ተከታዮቹ እንደ እንሰሶች ጎንበስ ብላችሁ አልያም እየተንከባለላችሁ ሣር ግጣችሁ ከበላችሁ ወደ እግዚአብሄር ትቀርባላችሁ፣ መንግስቱንም ትወርሳላችሁ ብሎ በማስተማሩ፣ ከግባኤው በኋላ ታዳሚዎቹ ሁሉ እንደ ግጦሽ ከብት እየተንከባለሉ ሣር ሲግጡ እየነጩም ሲበሉ በፎቶ ግራፍ ላይ በማስደገፍ በመረጃ መረቦች ላይ በማየታችን ከመገረም አልፎ በጣም ሳናዝን አልቀረንም በመሠረቱ ፓስተሩ እንዳለው ‹‹ሁሉ ተፈቅዶልናል ብሉ ወደ እግዚአብሔር ትቀርባላችሁ ቢባልም›› ነገር ግን ምንም እንኳን ሁሉ ቢፈቀድልን ሁሉ ግን አይጠቅመንም ከኅሊና አንጻር ሳይቀር የማንበላው ነበር አለ፡፡


በሌላው የትም ቦታ ላይ በመጽሐፍ ቅዱስ በመብል ወደ እግዚአብሔር እንቀርባለን የሚል አልተጻፈም ይልቁንስ ወደ እግዚአብሔር መቅረብ የሚቻለው መንግስቱንም ለመውረስ በበጎ ምግባር በጾምና በጸሎት በመጽናት በፍጹም እምነት መሆንን ይጠይቃል፡፡
እነሱ ግን በሰይጣን አሸከላ ተይዘው ባለማወቃቸው ዋሁን ሕዝብ ማሰናከሉን ተያይዘውታል፣ ታዲያ እኛም አይተን ዝም ከምንል ለጥንቃቄ ይሆን ዘንድ ልንጽፍላችሁ ወደድን በጉዳዩና በሥራቸው እየተገረምን ለየዋሁ ሕዝብ ግን እያዘን የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው ማስተዋሉንም ስጣቸው ዓይነ ልቡናቸውንም አብራላቸው ብለን እንጸልያለን፡፡


1 comment: