Monday, January 6, 2014

‹‹በተወደደችው ዓመት››






በተወደደችው ዓመት እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ወደ ዓለም ላከ የተነገሩ ትንቢቶች ተፈጸሙ የተቆጠሩ ሱባኤዎች ተጠናቀቁ በቤተልሄም ይሁዳ በእኩለ ሌሊት ፀሐይ ፍንትው ብላ ወጣች የተናቁት ሰዎች ከቁጥር የማይገቡት እረኞች የፀሐይን ብርሃን ፈጥነው አዩ ‹‹የሚያከብረውና የከበረው አከበራቸው ብርሃንን ቀድሞ አሳያቸው ስብሐት ለእግዚአብሔር በአርያም ወሠላም በምድር ስምረቱ ለሰብዕ›› በማለት ሰዎችና መላዕክት በአንድ ላይ ዘመሩ፣ የብርሃን አምድ ከሰማይ እስከምድር ተተክሎ ታየ፣ ለወትሮው በሥነፍጥረት ፀሐይ የታዘዘችው በቀን እንድትሰለጥን ነበር ነገር ግን በተወደደችው ሰዓት ጨረቃና ከዋክብትን ተባበረች በእኩለ ሌሊት ለምስጋና መጣች ለመኖሯ ዋስትና ፈጣሪዋ የማይጠልቀው ፀሐይ ባልተለመደ ሁናቴ ተወስኖ አይታለችና፣ ደግሞስ ዳዊት ‹‹ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ›› ብሎ የለ ሰማያት ያለው ሰማያዊ ፍጥረታትን ሰማያትን ጨምሮ እንዲህ ፀሐይ ጨረቃ ከዋክብትን ነውና የከበረውን ለማክበር መጣች አዎ! የተወደደች ዓመት ስቃይ ያበቃባት መርገም የተደመሰሰባት ፍዳ የተፋቀባት የአመጽ መዝገብ የተገለጠባት መቃብር የተዘጋባት፣ ሞት የተሻረባት ሲዖል ተዘግቶ ገነት የተከፈተባት ምርኮ የተመለሰባት እውነትም የተወደደች ሰዓት የአልቃሾች እንባ የታበሰባት የደስታ ዘመን፣








የተወደደች ዓመት የማይሰለች የማያረጅ የማይታደስ አዲስና ልዩ ዜና የተነገረባት ዓመት፣ የዓለምን ሕዝብ አንድ አድርጎ ያግባባ ልዩ የሆነ የፍቅር መስሕብ ያለው የሰዎችን ታሪክ የቀየረ ነገራቸውን የገለበጠ እንግዳ ሰው የተወለደባት ዓመት፣ በዚች ዓመት ነበረ የጠብ ግድግዳ የፈረሰው የተራራቁት የተቀራረቡት የተጣሉት የታረቁት ሰውና እግዚአብሔር ችግራቸውን በአዳም በኩል የፈቱት ዳግም ላይጣሉ ወልደ አብ ወልደ ማርያም ብለው በተወለደው ሕጻን ያመኑት የተወደደ ዓመት:
     እኛስ መቼ ይሆን የምንታረቅ፣ መቼ ይሆን በሰላም ለሰላም የምንቆም በፍቅር ለፍቅር የምንሰራ በግል ሕይወታችን በኑሯችን በትዳራችን በቤተክርስቲያን በሀገራችን ከራሳችን ተጣልተን የምንሰራውን የማናውቅ የምንጽፈውንና የምንናገረውን የማናስተውል ሰላም አጥተን ሰላም የምንነሳ ብዙ ነንና የተወደደውን ሰዓት እንጠቀምበት
ለቤተክርስቲያን ለሀገር ራዕይ የሌለን መለያየትን እየሰበክን ዘረኝነትን የምናስፋፋ ውለታን ረስተን ታሪክን እያዛባን ያልተጻፈ እያነበብን ያልተሰራ ያልተደረገውን እየተረክን የትውልድን ንጽሕ አእምሮ በጥላቻ በቂም በቀል የምንመርዝ ‹‹ጊዜ የሰጠው ቅል ድንጋይን ይሰብራል›› እንዲሉ አበው ጊዜ ስላገኘን ፍርድ የምናጓድል ደኃ የምንበድል የተሰወረ የማይገለጥበት ጊዜ አይቀርምና ነገር ሲገለበጥ ፈተኞች ኋለኞች ኋለኞች ፍተኞች ሳይሆኑ ዛሬ በተወደደችው ዓመት በጎ ሰርተን ጥሩ ታሪክን እናስመዝግብ፡፡
ግለኝነት ተጠናውቶን ስልጣን ጠምቶን እንደ ቅርጫ ሥጋ 33 ቦታ ተከፋፍለን አኩሪ ታሪክና ማራኪ ባሕል ያለውን ሕዝብ እንደ ጉም ተኖ እንደ ጢስ በኖ በሚጠፋ ባዶ ተስፋ እያጃጃልን ከፍቅር ማዕድ ርቀን ፍቅርን የምናስርብ በአንድነት በሕብረት ቆመን የተሻለ ለውጥ ላለማምጣት ላለመስማማት የተስማማን፣ የዓለምን ታሪክ የቀየረው ኢየሱስ ክርስቶስ በተወደደችው ዓመት ሁለቱን ሕዝብና አሕዛብን፣ ነጭና ጥቁርን፣ ወንድና ሴትን ፣ ይስሐቅአውያንና እስማኤላውያንን በፍቅር አንድ አድርጓልና እኛም እናስተውል ዘንድ ዓይነ ልቡናችን የብራ
በቤተክርስቲያናችን ለመንጋው ምሳሌ በመሆን  በእረኝነት ተሹመን በጎችን ማሰማራት የደከመውን ማጽናናት የታመመውን ማከም የተሰበረውን መጠገን የባዘነውን መሰብሰብ የጠፋውን መፈለግ ሲገባን፣ ነገር ግን ራሳችንን የምናስማራ ጮማውን የምንበላ ጠጉሩን የምንለብስ የወፍራሙን የምናርድ በጎችን ግን የማናሰማራ፣ የሰላምን መስቀል ይዘን ለሰላም መቆም የተሳነን፣ ለዓለምና ለኃጢዓት ሙት ሆነን ለጽድቅ ግን ሕያው እንሆን ዘንድ ቃል ገብተን ቃላችን ግን ያፈረሰን እዚህና እዚያ ለሁለት ተከፍለን በእኛ ጸብና ክርክር በጎችን የበታተንን፣ ለምድርም አራዊት ሁሉ መብል ያደረግን፣ በጎችን በተራሮች ሁሉ ላይ በኮረብቶች ላይ እንዲሁም በዓለም ሁሉ እንዲበታተኑ ያደረግን በተወደደችው ዓመት እውነተኛው እረኛ ተገልልና በንሰሐ ተመልሰን የተወደደ ሥራ እንስራ፡፡

No comments:

Post a Comment