‹‹ስሜን ለምትፈሩ ለእናንተ የጽድቅ
ፀሐይ ትወጣላችኋለች›› (ሚል 4፡2) እንዲል ነቢዩ ፀሐይ የተባለ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ይህንን ፀሐይ ወልዳ የሰጠችን የነቢያት
ትንቢታቸው የአበው ተስፋቸው የድህነት ምክንያታችን ከዋክብት አክሊል የሆኑላት ጨረቃ ከእግሮቿ በታች ያሏት ፀሐይን የተጎናፀፈች
ጨረቃ የተባለችው ድንግል ማርያም ናት (ራዕ 12፡2)
ድንግል ማርያም በሥጋ ከእናትና ከአባቷ ቤት ከመወለዷ
በፊት ዓለም ሳይፈጠር በአምላክ ሕሊና ታስባ ትኖር ነበር እግዚአብሔር መላዕክት ከፈጠራቸው በኋላ የሰውን ልጅ በአርአያውና በአምሳሉ
እንደሚፈጥር ነገር ግን ሰው ክብሩን ባለማወቅ እንደሚበድል ነገራቸው መላዕክትም ሰው የሚበድል ከሆነ ለምን ይፈጠራል ቢሉት ከፍጥረት
ሁሉ የከበረች ከሰው ወገን የሆነች ምክንያተ ድኅነት እንደምትኖር ክብሯም ገናና እንደሆነ ሥዕለ አድኀኖዋን በቅዱስ ሚካኤል ክንፍ
ላይ አሳያቸው እነሱም ዕፁብ ብለው የእግዚአብሔርን ግሩም ሥራ አደነቁ እመቤታችንንም በአርያም አመሰገኑ::
ልዑለ ቃል ኢሳይያስ ይህንን ሲያፀና በትንቢት
መነጽር የሩቁን አቅርቦ እየተመለከተ በአምላክ ኅሊና በንጽህና በቅድስና ታስባ ስለነበረችው ስለድንግል ማርያም ‹‹የሠራዊት ጌታ
እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ እንደ ሰዶም በሆን እንደ ገሞራም በመሰልን ነበር›› (ኢሳ 1፡9) በማለት ጽፏል፡፡
ዓለም ከተፈጠረም በኋላ በአዳም ሕግ ማፍረስ እምነት
ማጉደል በደል ምክንያት ዘመኑ ሁሉ ዓመተ ፍዳ ዓመተ ኩነኔ ዓመተ መርገም እየተባለ ሲጠራ እርሷ ግን ያ በዓለም የነገሠው መርገም
ፍዳ በደል (ጥንተ አብሶ) በዘር የውርስ ኅጢዓት ሳያገኛት ተጠብቃ የቀረችልን ንጽሕት ዘር ናት (ሮሜ 9፡29)
ወላዲተ አምላክ ትንቢት ከተነገረላቸው ሱባኤ ከተቆጠረላቸው
ከደጋግ ዘሮች ከዳዊት ዘር ወጥታ 5485 ዓ.ዓ ሲፈጸም ከኢያቄምና ከሐና አብራክ በሊባኖስ ተራራ ላይ ግንቦት አንድ ቀን ተወለደች
በመወለዷ መላዕክት ተደሰቱ የአዳም አባታችን ተስፋው ለመለመች ደጋጎች አበው ሴም ሄኖክ አብርሃም
ይስሐቅ ያዕቆብ ሐሴት አደረጉ ከዘር ሐረጋቸው ተወልዳለችና ጨረቃ በማለዳ ፀሐይ ወጥታለችና ፣ ነቢያት ኃዘናቸው ወደ ደስታ ተቀየረ
ትንቢታቸው ናትና፣ ሐሴትም አደረጉ ምስራቀ ምሥራቃዊት ሆና የጽድቅ ፀሐይን ታወጣለችና፣ ሁለተኛ ሰማይ ሆና ለነገስታት ንጉሥ ዙፋን
ትሆናለችና ፡፡
ነገር ግን ከዚያ በፊት እናትና አባቷ መካን የነበሩ ልጅም በማጣት ቆይተው እድሜያቸው ገፍቶ ስለነበር በእስራኤል ዘንድ
ልጅ ያጡት በኃጢዓታቸው ብዛት ነው በማለት አምተው አሳሟቸው በዚህም ምክንያት በማዘን ልጅ እንዲያገኙ እግዚአብሔርን ዘወትር በጾም
በጸሎት እየጠየቁ ኖረው ልጅ ቢሰጣቸውም እኛን በዚህ ዓለም ታገልግለን ወይም ያገልግለን አላሉም ለቤተ እግዚአብሔር ሰጥተን እግዚአብሔርን
ያገልግል እንጂ በማለት ስዕለት ተሳሉ እግዚአብሔርም የነገሩትን የማይረሳ የለመኑትን የማይነሣ ነውና ስዕለታቸውን ሰምቶ ፀሐይን
የምትጎናጸፈውን ፣ ለክዋክብትም ድምቀታቸውን ውበታቸው የሆነችውን ጨረቃን ወለዱ ለሦስት ዓመታትም በፍቅር አሳደጓት ከዚህ በኋላ
ግን ምንም እንኳን የልጅነት ጣዕሟን ባይጠግቡም ፍቅሯን አጣጥመው ባይጨርሱም ‹‹መጽሐፍ የተሳልከውን ፈጽም ይላልና›› የተሳሉትን
ስዕለት አስበው በ3ዓመቷ ብላቴናዋን ማርያምን ይዘው ወደ ቤተ እግዚአብሔር ወሰዷት፡
በወቅቱ በቤተመቅደስ የነበሩት ካህናት ካህኑ ዘካርያስን ጨምሮ ብላቴናዋን ማርያምን ለመቀበል ፈቃደኛ ቢሆኑም የምግቧና
የመጠጧ ነገር ግን አስጨንቋቸው በመነጋገር ላይ ሳሉ የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ፋኑኤል ከሰማይ እየበረረ መጣ ከመሬት ከፍ
ከሰማይም ዝቅ ብሎ በክንፉ ጋርዶ እመቤታችንን መና ሰማይ መግቧት ተመለሰ፡፡
ድንግል ማርያም በሦስት ዓመቷ ከእናት ከአባቷ እቅፍ ወጥታ አማናዊ ቤተ መቅደስ ሆና ሰው ወደሰራው ቤተ መቅደስ ተሰደደች
ነቢዩ ዳዊት በመዝሙሩ ‹‹ልጄ ሆይ ስሚ ጆሮሽንም አዘንብይ ንጉሥ ውበትሽን ወዷል የአባትሽን ቤት እርሺ›› (መዝ 45፡10) በማለት
ከእናትና ከአባቷ ቤት ወጥታ ወደ መቅደስ የመግባቷ ትንቢት አስቀድሞ ተናግሮላታልና የአባትሽን ቤት እርሺ ሲል የወላጅ አባትሽ የኢያቄም
ቤት ትዝ አይበልሽ እርሺ፣ ከእንግዲህ ወዲህ ቤትሽ ቤተ መቅደስ ሆኗል፡፡
ለእግዚአብሔር እናትነት ተመርጠሻል ፣ ንጉሥ እግዚአብሔር ውበትሽን ንጽሕናሽን ቅድስናሽን ወዷል በአባትሽ በአዳም ቤት
ያለውን ዘር ኃጢዓት የሴቶች ፀባይ በእኔ ላይ አለ አትበይ፣ እርሺ አንቺ ይህ ሁሉ የለብሽም ፣ ንጽሕት ቅድስት ነሽ ተብሎ ተነግሮላታል፡፡
ስለዚህም ድንግል ማርያም በታህሳስ 3 ቀን በ5488 ዓ፣ም ወደ ቤተ መቅደስ ወደ ምኩራብ ገባች፣ ቅዱሳን መላዕክት እያጫወቷት
እና እየተላላኳት ‹‹እህትነ›› እያሉ እህታቸው ሆና ሐርና ወርቁን አስማምታ እየፈተለች ከሰማየ ሰማያት የወረደ ህብስትንና ወይንን
እየተመገበች አንገታቸውን እንደሚያገዝፉ እንደዕብራውያን ሴቶች ሳይሆን በክሳደ ስቢር በትህትናና በንጽሕና አስራ ሁለት ዓመት በቤተ
መቅደስ ኖረች፡፡
አስራ አምስት ዓመት (3+ 12 ) ሲሞላት ግን በቀናተኞች በአይሁድ ላይ ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስ (ሰይጣን) አደረና
‹‹ይህች ወጣት ለአቅመ ሔዋን ስለደረሰች መቅደሳችንን እንዳታጎድፍ ትውጣ ብለው ተማከሩ፣ ነገር ግን ከዚያ አውጥተው ብቻዋን እንዳይተዋት
ፈርተው ካህናቱ ተሰብስበው እጣ እንጣጣልና እጣው የደረሰው ወስዶ ተረክቦ ይጠብቃት ብለው ተስማሙ በትራቸውንም ሰብስበው ዕጣ ተጣጣሉበት
በወቅቱ ለእጣ የተሰበሰው በትር 1985 ሲሆን ከዚያ መካከል የአረጋዊው የቅዱስ ዮሴፍ በትር አብባ አፍርታ ተገኘች፡፡ እጣውም ለዮሴፍ
ነው የደረሰው ብለው እንዲጠብቃት ለዮሴፍ አደራ ሰጡት አረጋዊው ዮሴፍም በጉባኤው ፊት በአደራ የተረከባትን እመቤታችን የአስራ አምስት
ዓመቷን ብላቴና ሊጠብቃት፣ ሊያገለግላት ወደ ቤቱ ይ³ት ሄደ፡፡
ነገር ግን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እድገቷ በንጽሕና በቅድስና ቅዱሳን መላዕክት እያጫወቷት ፍጹም መላዕክትን
መስላ ነው እንጂ እንደ ዕብራውያን ልጃገረዶች ሥርዓት በነበረ ጠባያዊ ሂደት አልነበረም፡፡ ምንም እንኳን ከቅዱስ ኢያቄምና ከቅድስት
ሐና አብራክ ተወልዶ የባሕርያችን መመኪያ ሆና የሰውን ዘር ብትሆንም የአዳም የመርገም ኅጢዓት (ዘፍ 3፡19) ያላገኛት በሴቶች
የሚሆነው ልምድና ጠባይ የሌላት ንጽህት ቅድስት ናት፡፡
ይህንንም ጠቢቡ ሰሎሞን በመኃልይ መኃልይ፣ ከመዝሙር ሁሉ በሚበልጥ መዝሙሩ ‹‹እህቴ ሙሽራዬ ሆይ ሁለንተናሽ ውብ ነው
ነውርም የለብሽም›› (መኃ 4፡12) ሲል ንጽሕናዋን ገልጧል፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም ዘሀገረ ሦሪያም በረቡዕ ውዳሴ ማርያም ድርሰቱ ‹‹የዐቢ ክብራ ለማርያም እምኩሎሙ ቅዱሳን፣ የማርያም
ክብር ንጽሕና ከቅዱሳኑ ሁሉ ክብር የበለጠ ነው›› በማለት አስተምሮናል፡፡
አረጋዊው ቅዱስ ዮሴፍ እመቤታችንን በአደራ ተቀብሎ ሊጠብቃት ይ³Eት ወደ ቤቱ ሄደ ዮሴፍ በንግድ ሥራ እየተዳደረ ልጆቹን እንደ እናትም እንደ አባትም ሆኖ የሚያሳድግ አዛውንት ነበረ ድንግል
ማርያም ወደ ዮሴፍ ቤት ከገባች በኋላ ያለ እናት ያሳደጋቸውን ልጆቹን እንደ እናትም እንደ እህትም ሆና ታሳድግለት ነበር ከዕለታት
አንድ ቀን ዮሴፍ ለንግድ ወደ ሩቅ ሀገር ሄዶ ቆይቶ ወደ ቤቱ ተመልሶ ሲመጣ የድንግል ማርያምን መፀነስ ከደጅ ሰማ እጅግም ደነገጠ፣
ምክንያቱም በእስራኤል ባህል አንዲት ሴት ከባሏ ውጪ ወይም ከሕግ ውጪ ፀንሳ ከተገኘች በድንጋይ ተወግራ ወይም ማየዘለፋ የተባለ መሪር ቅጠል አካልን በጣጥሶ የሚያፈርስ ዕፅ ጠጥታ ቁርጡ እንዲለይላት
ይደረግ ነበርና ዕብራውያኑ እንደሚሉት ማየ ዘለፋው ከሕግ ውጪ ካልሆነ ሴቲቱን አይጎዳትም ብለው ያምኑ ነበርና፡፡
አረጋዊው ዮሴፍ ይህንን እያሰላሰለ ተጨንቆ ሳለ አስቀድሞ መጽነሷን ያበሰራት ብርሃናዊ መልአክ መጋቢ ሐዲስ ቅዱስ ገብርኤል
ተገለጠለትና ዮሴፍ ሆይ እጮኛህ ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ ከሷ የሚወለደው በግብረ መንፈስ ቅዱስ ነውና አትደንግጥ ብሎ አረጋጋው
(ማቴ 1፡20) ዮሴፍም በመልአኩ ቃል ጸና ቅናት ያደረባቸው አይሁድ ግን ይህ ነገር እንዴት ይሆናል ጠብቅ ብለን ብንሰጠው ጸንሳ
ተገኘች ብለው አጉረመረሙ እንደ ሥርዓታቸውም ድንግል ማርያም በአደባባይ ማየ ዘለፋ እንድትጠጣ አደረጓት ያቺ የአዳም ተስፋው የመላዕክት
እህት የአበው መመኪያ የሆነች እናታችን ድንግል ማርያም ያንን ማየ ዘለፋ አባቷ ዳዊት ‹‹ብዙ ውሾች ከበቡኝ የክፋተኞችም ጉባኤ
ያዙኝ›› እንዲል በክፋትና በቅናት በተሰበሰቡት አይሁድ ፊት ግጥም አድርጋ ብትጠጣው ከፀሐይ ሰባት እጅ አበራች፣ ያ ማየ ዘለፋ
በእሷ ላይ ምንም ኃይል አልነበረውምና አይሁድ ተገረሙ ግራም ተጋቡ ሰይጣንም አፈረ በአይሁድ ልቡና ያደረውም ቅናት ጠፋ፡፡
የፀነሰችውም በግብረ አምላካዊ በመንፈስ ቅዱስ ፀሐይን ነውና ፊቷ ያበራ ነበረ ገéE ዕለት ዕለት ይቀያየር ነበር ዮሴፍ የሚሆነውን ነገር እያየ የፈጣሪን ሥራ ያደንቅ ነበር፣ ሊጠብቃትና
ያገለግላት ዘንድ ቢወስዳትም የበኩር ልጇን እስከምትወልድ ድረስ ግን አላወቃትም ፣ የአምላክ እናት መሆኗን ከእርሷ የሚወለደው ታሪካችንን
የሚቀይር የአዳምን እንባ የሚያብስ የአመጻ መዝገባችን የሚገለብጥ ፀሐየ ጽድቅ ክርስቶስ እንደነበር አልተረዳም ነበረ፣ ትሁት ነበረና
በትህትናና በትጋት አገለገላት ድንግል ማርያምም የሚሆነውን ሁሉ ዕለት ዕለት እያየች ነገርን ሁሉ በልቧ ትጠብቀው ነበር እንጂ ፈጽሞ
ምንም ዓይነት ነገርን በአንደበቷ አትናገርም ነበር ግርሞትና ድንቅ እመቤት ሱላማጢስ ፀሐይን ተጎናጽፋ ፀሐይን የወለደች ጨረቃ ንጽሕት
እናት፡፡
No comments:
Post a Comment