Wednesday, January 15, 2014

‹‹ከገሊላ ወደ ማዕዶተ ዮርዳኖስ››





የአበው ቃል ኪዳን ተስፋ የነቢያት ትንቢት ና ሱባኤ ተፈጸመ እግዚአብሔር መተኪያ የሌለውን አንድ ልጁን ላከ እርሱም ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ እርሱ ዳግም በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሻር ይኸውም ዲያብሎስ ነው፣ በሕይወታቸው ሁሉ ስለ ሞት በፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ፣ ከሕግ በታች ሆኖ በሞገስና በጸጋ ቀስ በቀስ አደገ በግዕዘ ሕጻናት በትን ከተማ በናዝሬት ገሊላ ተመላለሰ በተወደደችው ዓመት፣ የተወደደችውን የእግዚአብሔር ዓመት አምላካችንም የሚበቀልባትን ቀን የምስራች ሰበከ፣ የእግዚአብሔር መንፈስ በእሱ ላይ ነውና ለድሆች የምስራችን ይሰብክ ዘንድ እግዚአብሔር ቀባው ልባቸው የተሰበረውን ጠገነ ለተማረኩት ነጻነትን ለታሰሩትም መፈታትን የምስራች ተናገረ፡፡


ሕግና ነቢያትን ይፈጽም ዘንድ መጥቷልና ቅዱስ ዮሐንስ በማዕዶተ ዮርዳኖስ በቢታንያና በቤተ ራባ በሚያስተምርበት ጊዜ ከገሊላ (ናዝሬት) ወደ ማዕዶተ ዮርዳኖስ ወደ ዮሐንስ ዘንድ መጣ፡፡ ምድር ልትሸከመው አልቻለችም ፣ ዮርዳኖስ በፊቱ ጸንታ መቆም ስላልቻለች ወደ ኋላ ሸሸች ተራሮች እንደ እንቦሳ ኮረብቶችም እንደሚደቋ ዘለሉ በትዕዛዝ ፈጥሯቸዋልና ዮሐንስ ሰማይ ዙፋኑ ምድር የእግሩ መረገጫ የሆነ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ሁለተኛው አዳም ወደ እርሱ ሲመጣ  አይቶ ‹‹ነዋ በጉ ለእግዚአብሔር ዘየአትት ኃጢዓተ ዓለም፣ የዓለምን ኃጢዓት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ አንድ ሰው ከእኔ በፊት ነበር ከእኔም በኋላ ይመጣል እኔም ይልቅ የከበረ ነው ብዬ የነገርኳችሁ ይህ ነው እኔም አላውቀውም ነበረ ግን ለእስራኤል ይገለጥ ዘንድ በውሃ እያጠመቅሁ መጣሁ አለ›› (ዮሐ 129-30)
ጌታችንም ኢየሱስ መምህረ ትህትና ነውና፣ መጥቶ ሕዝቡ ሁሉ ከተጠመቀ በኋላ ‹‹አጥምቀኝ›› አለው ቅዱስ ዮሐንስ ግን ‹‹ፃድቅ ያለነውር ይሄዳል ልጆቹም ከእርሱ በኋላ ምስጉኖች ናቸው›› (ምሳ 20፡7) ተብሎ እንደተጻፈ ትህትናን ጻድቅና ትሁት ከሆኑት ከአባቱ ከካህኑ ከዘካርያስና ከእናቱ ከቅድስት ኤልሳቤጥ ተምሯልና ‹‹እኔ ከአንተ መጠመቅ ይገባኛል እንጂ አንተ ከእኔ ልትጠመቅ እንዴት ይቻላል›› ብሎ እምቢ አለው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ግን ‹‹ጽድቅን ሁሉ ልንፈጽም ይገባለና እሺ በልና አጥምቀኝ›› አለው ክርስቶስ የመጣው እውትን ለሰው ልጆች ለማደል አዲስ ኪዳን ሊሰራ እውነተኛውን ትምህርተ ወንጌልን ለመስበክ ስለነበር ጽድቅን እንፈጽም ዘንድ ይገባል አለው ያን ጊዜ ዮሐንስ ማጥመቁን እሺ ግን ‹‹ምን ብዬ ላጥምቅህ አለው›› ፣ ጌታችንም ‹‹ወልደ ብሩክ ከሳቴ ብርሃን ተሣሃለነ አንተ ካህኑ ለዓለም በከመ ሲመቱ ለመልከጼዴቅ››  ‹‹እንደ መልከጼዴቅ ሲመት (ሥርዓት) አንተ ለዘላለም ካህን ነህ ብርሃንን የምትገልጥ (ብርሃን ሆነህ የተገለጥክ) ብሩክ አብ የባሕርይ ልጅ ሆይ ይቅር በለን›› እያልክ አጥምቀኝ አለው፣ አንድም መንፈስ ቅዱስ ምን ብሎ ማጥመቅ እንዳለበት ገለጸለትና አጠመቀው ጌታችን ኢየሱስም ‹‹ከተጠመቀ በኋላ ወዲያው ከውሃው ወጣ እነሆም ሰማያት ተከፈቱ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድ በእርሱ ላይም ሲመጣ አየ እነሆም ድምጽ ከሰማያት መጥቶ በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው አለ›› (ማቴ 313-17)








ይህ ምስጢር ለቤተክርስቲያናችን ዶግማ ለምስጢረ ስላሴ ትምህርት መሠረት ነው የሥላሴ አንድነትና ሦስትነት በኦሪት ብዙ ጊዜ ቢነገርም እንደ እዚህ ግልጥ ሆኖ አልታወቀም ነበር በሐዲስ ኪዳን ግን የሥላሴ አንድነትና ሦስትነት ግልጥ ሆኖ ታወቀ መሠረቱ ይህ ነው፣ እግዚአብሔር ወልድ በፈለገ ዮርዳኖስ በዮሐንስ እጅ ተጠመቀ፣ እግዚአብሔር አብ ከሰማያት ሆኖ የምወደው ልጄ ይህ ነው አለ፣ መንፈስ ቅዱስ በአምሳለ ርግብ ወርዶ በራሱ ላይ ተቀመጠ፡፡
ቅዱስ ዮሀንስ ይህንን ምስጢር እንዲህ አስተምሮታል ‹‹በሮማ አቆጣጠር በ8ኛው ሰዓት አስቀድሞ በግዕዝ ጥር 11 ቀን 10 ሠዓት ሌሊት ሁለቱ ጌታችን ኢየሱስና ቅዱስ ዮሐንስ ወደ ማዕዶተ ዮርዳኖስ ሄዱ ውኃዎችም እንደ ሞቀ ውኃ ፈሉ፣ ጌታም ገብቶ በዮሐንስ እጅ ተጠመቀ፡፡ ከተጠመቀም በኋላ ሰማይ ተከፈተ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ በላዩ ላይ ተቀመጠ ከሰማይም እንደመብረቅና ነጎድጓድ ድምጽ ያለ ቃል ተሰማ ቃሉም እንዲህ የሚል ነው፡፡



‹‹የምወደው ልጄ ይህ ነው ይህ ክርስቶስ ነው 30 ዘመን ከዮሐንስ የተጠመቀው ብሎ ሉቃስ እንደተናገረ››
ይህን ካልን ዘንድ የጌታችንን የመድኃኒታችን የኢየሱስን ከገሊላ ወደ ማዕዶተ ዮርዳኖስ መምጣትና መጠመቅ ስናስተምር ሌላ ምስጢርም ልንገልጽ ግድ ይለናል፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያናችን ዘወትር በዘመነ ጥምቀት ታቦታት ከመንበረ ክብራቸው ተነስተው ወደ ጥምቀተ ባሕር ይወርዳሉ፣ ይህም ባህል ወይም ልማድ ሳይሆን የጌታን ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መውረድ መሠረት ያደረገ ነው፡፡ ታቦታቱ የጌታ ምሳሌ ናቸው፣ ባሕረ ጥምቀቱ ወይም ሄደው የሚያድሩበት ሥፍራ የማዕዶተ ዮርዳኖስ ምሳሌ ነው በመሆኑም ጌታ ከገሊላ (ናዝሬት) በ10 ሰዓት ሌሊት ወደ ማዕዶተ ዮርዳኖስ እንደወረደ ዛሬም ካህናት ታቢታትን ይዘው ወደ ባሕረ ጥምቀት ይወርዳሉ፣ ታቦታቱም በውስጣቸው ባለው የእግዚአብሔር ስም በተጻፈበት ጽላት ሕዝቡንና ሀገሩን ይባርካሉ፡፡
አንድም እስራኤል ዘሥጋ ከግብፅ ባርነት ነጻ ወጥተው ፈርኦን አገዛዝ ተላቀው ማርና ወተት የሚፈልቅባትን ምድረ ርስት ከነዓንን ከመውረሳቸው በፊት ፈለገ ዮርዳኖስን (የዮርዳኖስን ወንዝ) መሻገር ነበረባቸው በመሆኑም ከግብፅ ተነስተው ባሕረ ኤርትራን ተሻግረው የሲና በረሃን አቋርጠው ዮርዳኖስ ሲደርሱ ግን ፈለገ ዮርዳኖስ (የዮርዳኖስ ወንዝ) ከአፍ እስከ ገደቡ ሞልቶ ለዓይን የሚያስፈራ ሥነልቡና የሚያደክም ተስፋ የሚያስቆርጥ ሆኖ አገኙት፣ ነገር ግን በመካከላቸው የቃል ኪዳኑ ታቦት ነበረና እያሱ ማልዶ ተነሣና ሕዝበ እስራኤልን ከጢስ ተነሥተው ወደ ዮርዳኖስ እንዲወርዱ አዘዘ ሳይሻገሩም ሦስት ቀን በዚያ አደሩ ከሦስት ቀን በኋላ አለቆችን በጢስ ሰፈር መካከል ልኮ ሕዝቡን የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት ሌዋውያን ካህናት ተሸክመው ባያችሁ ጊዜ ከሰፈር ተነስታችሁ ተከተሉት ፣ በእናንተና በታቦቱ መካከልም ያለው ርቀት በስፍር ሁለት ሺህ ክንድ ያህል ይሁን በዚህ መንገድ በፊት አልሄዳችሁበትምና የምትሄዱበትን መንገድ እንድታውቁ ወደ ታቦቱ አትቅረቡ ብለው አዘዙ፡፡

እያሱም ሕዝቡን ነገ እግዚአብሔር በመካከላችሁ ድንቅ ነገር ያደርጋልና ተቀደሱ አለ፣ ካህናቱንም የቃል ኪዳኑን ታቦት ተሸክማችሁ በሕዝቡ ፊት እለፍ ብሎ ተናገራቸው፣ የቃል ኪዳኑንም ታቦት ተሸክመው በሕዝቡ ፊት አለፉ፡፡
እግዚአብሔርም እያሱን ‹‹ከሙሴ ጋር እንደሆንሁ እንዲሁ ከአንተ ጋር መሆኔን ያውቁ ዘንድ በዚህ ቀን በእስራኤል ሁሉ ዓይን ከፍ ከፍ አደርግህ ዘንድ እጀምራለሁ አንተም የቃል ኪዳኑን ታቦት የሚሸከሙትን ካህናት በዮርዳኖስ ውኃ ዳር ስትደርሱ በዮርዳኖስ ውስጥ ቁሙ ብለህ እዘዝ›› አለው፡፡
ኢያሱም ሕዝቡን ወደዚህ ቀርባችሁ አምላካችሁን የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፣ ሕያው አምላክ በመካከላችሁ እንደሆነ እርሱም ከፊታችሁ ከነዓናዊውን ፣ ኬጢያዊውን፣ ኤዊያዊውን፣ ፌርዛውያንንም፣ ጌርጌሳዊውንም፣ አምራዊውንም፣ ኢያቡሳዊውንም (ሰባቱን የአሕዛብ ነገሥታት) ፈጽሞ እንዲያወጣ በዚህ ታውቃላችሁ እነሆ የምድር ሁሉ ጌታ ቃል ኪዳን ታቦት በፊታችሁ ወደ ዮርዳኖስ ያልፋል እናንተም ከእስራኤል ነገዶች አስራሁለት ሰዎች ምረጡ ከየነገዱ አንድ አንድ ሰው ይሁን
እንዲህም ይሆናል የምድርን ሁሉ ጌታ የእግዚአብሔርን ታቦት የተሸከሙ ካህናት እግር ጫማ በዮርዳኖስ ውኃ ውስጥ ሲቆም ከላይ የሚወርደው የዮርዳኖስ ውኃ ይቋረጣል እንደ ክምርም ሆኖ ይቆማል፡፡
እግዚአብሔርም በቃል ኪዳኑ ታቦት ሕዝቡን ታደገ፣ እስራኤል ዮርዳኖስን ሊሻገሩ ከየድንኳናቸው በወጡ ጊዜ የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙ ካህናት በሕዝቡ ፊት ይሄዱ ነበር እንደ መከር ወራት ሁሉ ዮርዳኖስ እጅግ ሞልቶ ነበርና ታቦት ተሸካሚዎች ወደ ዮርዳኖስ ሲደርሱ ታቦቱንም የተሸከሙት የካህናት እግሮች በውኃው ዳር ሲጠልቁ ከላይ የሚወርደው ውኃ ቆመ በዳርታን አጠገብ ባለችው አዳም በምትባል ከተማ በሩቅ ቆሞ በአንድ ክምር ተነሣ ወደ ዓረባ ባሕር ወደ ጨው ባሕር የሚወርደው ውኃ ፈጽሞ ተቋረጠ ሕዝቡም በኢያሪኮ ፊት ለፊት ተሻገሩ የእግዚአብሔርንም የቃል ኪዳን ታቦት የተሸከሙ ካህናት በዮርዳኖስ መካከል በደረቅ መሬት ጸንተው ቆመው ነበር ሕዝቡም ሁሉ ዮርዳኖስን ፈጽመው እስኪሻገሩ ድረስ እስራኤል ሁሉ በደረቅ መሬት ተሻገሩ፡፡ (ኢያሱ 3፡1-17)
ዛሬም አበው ካህናት የቃል ኪዳኑን ታቦት ከመንበረ ክብሩ በማውጣት ተሸክመው በሕዝቡ መካከል ባለፉ ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ በእልልታ በዝማሬ በጭብጨባ በልዩ ዜማ በክብር መሬት እየጠረጉ ምንጣፍ እያነጠፉ ከሰፈር ተነስተው ይከተሉት፣ እግዚአብሔርም ሕዝቡን በቃል ኪዳኑ ታቦት ላይ አድሮ ይባርካል ይቀድሳል፡፡
እንዲሁም የተመረጡት የአዲስ ኪዳን ካህናት የቃል ኪዳኑን ታቦት ይዘው ወጥተው በቆሙ ጊዜ እንደ ፈለገ ዮርዳኖስ ሞልቶ በመትረፍ ሕዝባችንን በማስጨነቅ ላይ ያለው መከራ የኑሮ ውድነት፣ ረሃብና ቸነፈር፣ በሽታና፣ ጸብና ክርክር ዘረኝነትና ጎጠኝነት መለያየትና መናፍቅነት ሁሉ ፀጥ ይላል ይቆማል፡፡








እያሱ እስራኤልን የቃል ኪዳኑ ታቦት በመካከላችሁ ይሁዳልና እግዚአብሔርም ሕዝቡን ይባርካልና ድንቅንም ያደርጋልና ተቀደሱ ብሎ እንዳዘዘ እኛም የተጣላን ታርቀን የተራራቅን ተቀራርበን ፍርድ ያጓደልን ደኃ የበደልን ፍጹም ካሣ ክሰን፣ የቀማን መልሰን በግብረሰዶም በዝሙት በርኩሰት ያለን በፍጹም ንስሐ ተመልሰን፣ በአድመኝነት፣ በዘረኝነት በመለያየት ውስጥ ያለን ስለሰላም በፍቅርና በአንድነት ሆነን የቃል ኪዳኑን ታቦታት አባቶች ካህናት ከገሊላ (ናዝሬት) ምሣሌ ከቤተክርስቲያን ከመንበረ ክብሩ አጅበን በመዝሙርና በእልልታ እየተከተልን ወደ ማዕዶተ ዮርዳኖስ ምሳሌ ወደ ጥምቀተ ባሕር እንሸኝ እግዚአብሔርም ሕዝባችንና ሀገራችንን በቃል ኪዳኑ ታቦት ይባርክ፣ መከራውን ፈተናውን ያቅልልን አሜን!



No comments:

Post a Comment