Tuesday, January 28, 2014

የሚያስደንቅ ሞት




‹‹ሞታ ለማርያም የሃጽብ ለኩሉ››
(ጥር 21 አርኬ ዚቅ)
ቅዱሳን ሐዋርያት በአባታቸው በመምህራቸውና በመጋቢያቸው በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ዕርገትና መለየት ያዘኑና የተከዙ ቢሆንም አማናዊቷ ታቦት ሞገሳቸውና ክብራቸው ጽዮን በመካከላቸው ነበረችና ተጽናኑ ጽዮን ማለት አምባ መጠጊያ ማለት ነውና፡፡ ጽዮንን ተጠጉ ነቢዩ ዳዊትም ‹‹ዕግትዋ ለጽዮን›› ጽዮንን ክበቧት በዙሪያዋም ተመላለሱ ብሏልና ጽዮንን ከበው በመካከላቸው አድርገው ከጽዮን ተጠግተው አገልግሎታቸውን ወደ ዓለም ሁሉ አደረሱ፡፡





በተለይም የፍቅር ሐዋርያ ፍቅረ እግዚእ እየተባለ የሚጠራው ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ታማኝ ትሑትና የፍቅር ሰው ስለነበረ በቀራኒዮ ተራራ በመስቀሉ ግርጌ በቁርጥ ሰዓት ስለተገኘ ሰው በጠፋበት ሰዓት ሰው ሆኖ በመገኘቱ ወዳጅ በጠፋበት ሰዓት በጨለማና በክፉ ቀን ወዳጅ ስለሆነ ጽዮንን ድንግል ማርያምን በእናትነት በአደራ ለሐዋርያት ለመቶ ሃያው ቤተሰብ ለዓለም ሁሉ ተቀበለ (ዮሐ 19፡27) የምስጢር ጓዳ ናትና የራቀው ይቀረበለት የረቀቀው ይጎላለት የተሰወረውም ይገለጽለት ዘንድ የፀሐይን እናት ወደ ቤቱ ወሰዶ ለአስራ አምስት ዓመታትም በትህትናና በክብር እያገለገላት ኖረ ድንግል ማርያም ስድሳ አራት ዓመት ሆናት የባሕርያችን መመኪያ ከቅዱስ ኢያቄምና ከቅድስት ሐና የተወለደች የአዳም ዘር በመሆኗ ወደ ዓለም በአዳም ስህተት የገባውን የሞትን ጽዋ በሥጋ ተካፍላለች ይሁን እንጂ ሞታ ሥጋዋም በስብሶ አልቀረም በልጇ ፈቃድና ስልጣን በሦስተኛው ቀን ተነስታ አርጋለች ይህም ለሐዋርያት ተገልፃላቸው በቅዱሳት መጻሕፍት ተቀምጦ እናገኘዋለን፡፡
ወላዲተ አምላክ ሞተች ተብሎ ቋንቋው ሲነገር ቃሉ ይከብዳል ይልቅንስ አርፋለች ከዚህ ዓለም ውጣ ውረድ ቢባል ይቀላል የቤተክርስቲያናችን ዕንቁ የዜማ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በዚቅ ድርሰቱ (ጥር 21 አርኬ) ‹‹ሞት እሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የሃጽብ ለኩሉ። ሞት ለሙታን ሁሉ የተገባ ነው፣ የአምላክ እናት የድንግል ማርያም መሞት ግን በእጅጉ የሚያስደንቅ ነው›› በማለት የወላዲተ አምላክ ሞት ለመናገር የሚከብድ ለመስማትም የሚያስቸግር ብቻ ግሩምና ድንቅ እፁብ እፁብ የሚያሰኝ መሆኑን ገልጾታል፡፡
አዎ የፀሐይ እናት ሞተች የብርሃን እናት የትንሣኤ እናት ከዚህ ዓለም በሞት ተለየች ተብሎ ሲነገር ለህሊና ያስደንቃል ልጇ ወዳጇ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት ሲሆን እርሷም የሕይወት እናት ስትሆን ሕይወት የሆነውን አምላክ የወለደችልን ሞተች ሲባል ያስገርማል፣ ይከብዳልም ነገር ግን አረፈች ከዚህ ዓለም ውጣ ውረድ ከድካም ዓለም ዕረፍት አድርጋ ድካም ወደ ሌለባት ወደ ልጇ መንግስት አረገች፡፡
ወላዲተ አምላክ በ64 ዓመቷ ጥር 21 ቀን አርፋለች በድንግል ማርያም ዕረፍት ቅዱሳን መላዕክት ተደነቁ፣ አስራ ሁለቱ ሐዋርያት አዘኑ ሞገሳቸው መጠጊያቸው የምስጢር ጓዳቸው ነበረችና በተለይ ቅዱስ ዮሐንስ አብዝቶ አዘነ እናቱ መጽናኛው የዓይኑ ማረፊያ ነበረችና 36ቱ ቅዱሳን አንዕሳት አዘኑ አማካሪያቸው አክሊላቸው ነበረችና 72ቱ አርድዕት አዘኑ ታቦታቸው ክብራቸውና ነበረችና፣ ፍጥረታት ሁሉ አዘኑ ርህርህት አዛኝት እናት ነበረችና፣ የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች 5000 ምዕመናን አዘኑ ትሑት የጽናት መምህርት አርአያ ነበረችና     
ቅዱሳን ሐዋርያት የእመቤታችንን ሥጋ በጎልጎታ በጌታ መቃበር ጎን ቀብረዋታል በሞተች በሦስተኛው ቀን ተነስታ ስታርግ ለሐዋርያው ለቶማስ ተገልጻ መታጠቂያዋን ስሽነን ሰጥታ ተሰናበተችው የምስራቹ ለቅዱሳን ሐዋርያት ቢነግራቸው እንዴት አሉ፣ እርሱም እርሷስ አርጋለች ይኸው መግነዟ ስሽኒ አላቸው ሐዋርያትም ለቅዱስ ቶማስ እንደተገለጽሽ ለእኛም ተገለጭልን ብለው ሁለት ሱባኤ በመያዝ ከጾሙ ከጸለዩ በኋላ (ከነሐሴ 1-14) ድረስ ወላዲተ አምላክ በነሐሴ 16 ቀን ተገልጻ እርገቷን አይተዋል፡፡
ጌታም ድንግል ማርያምን መንበር ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስን ረዳት ካህን አድርጎ ቀድሶ አቁርቧቸዋል፡፡
እኛም የሐዋርያት ተከታዮች ኦርቶዶክሳውያን የእመቤታችንን ዕረፍትና ትንሳኤ በማሰብ አባቶቻችን ሐዋርያት እንደጸለዩትና እንደጾሙት በአበው እንደተገለጽሽ ለእኛም በረድኤት ተገልጸሸ ፍቅርሽን እናትነትሽን ትንሳኤሽን እንይ እያልን በቤተክርስቲያናችን ከነሐሴ 1-16 ድረስ ሱባኤ በመያዝ ንስሐ ገብተን ዕረፍቷን ትንሳኤዋን እያሰብን በየዓመቱ እናከብረዋለን፡፡
እመቤታችን የጽናትና የትዕግስት ምሣሌ በመሆኗ ጽናትና ትዕግስትን ከልጇ እንለምናለን የንጽሕና የቅድስና ምሳሌ ናትና እኛም ንስሐ እየገባን የጽድቅ ፍሬ እያፈራን በቅድስና እንምሰላት፡፡
ወላዲተ አምላክ በእምነቷ ጽኑና ብርቱ ‹‹ያመነች ብፅዕት›› የተባለላት ፍጹም እምነት ያላት እንደሆነች እኛም ሃይማኖታችንን እንድናጸና ኑፋቄን ጥርጥርን አለማመንን ከኅሊናችን እንድናስወግድ እግዚአብሔር ይርዳን አሜን፡፡


No comments:

Post a Comment