Tuesday, January 28, 2014

የበግ ለምድ የለበሱ ተኩላዎች



 


‹‹ለኦርቶዶክሳውያን በሙሉ ጥብቅ ማሳሰቢያ››
በአሁኑ ሰዓት በቤተክርስቲያናችን ውስጥ አገልጋይ በመምሰል ምዕመን በመምሰል በተለያዩ ጉባኤያት አልፎ አልፎ በመምጣት በሰንበት ትምህርት ቤቶች ውስጥ አባል መስለው በመግባትና የሰንበት ትምህርት ቤት ዮኒፎርሞችን በመልበስ በበዓላት ላይ ተገኝተው በዓል አክባሪ መስለው በመቀላቀል በመመሳሰል መስቀል በአንገታቸው ላይ አድርገው ኦርቶዶክሳዊ መስለው ፎቶ በመነሳት፣





1.   በፌስ ቡክ (Face book) ላይ
-    በግለሰቦች ስም
-    በሕብረት ስም (Group)
-    Public figure
-    Community
በማድረግ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ስም አካውንት በመክፈት በመረጃ መረቦች (Internet) ላይ ብሎጎችን (blogs) በኦርቶዶክስ ተዋህዶ አባቶችና ቅዱሳን፣ ሊቃውንት፣ ጳጳሳት ስም የተለያዩ ድኅረ ገጾችን በመክፈት የመናፍቃንን የክህደት ትምህርት የሚያሰራጩ እንዳሉ በማስረጃ የተደረሰበት ከመሆኑም ባሻገር በመካከለኛው ምስራቅ በዱባይ አካባቢ በህብረት በመሆን ከፍተኛ የጥቃት ዘመቻ በቤተክርስቲያናች ላይ ከፍተዋል፡፡
በመሆኑም በዚህ አካባቢም ሆነ በሌሎች የመካከለኛው ምስራቅ ወይም በአረብ ሀገራት የምትኖሩ አገልጋዮች የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ልጆች ገበሬ ምርቱን ከገለባው በመንሽ እንደሚለይ ሁሉ እናንተም እነዚህን በግ የመሰሉ ነገር ግን የበግ ለምድ የለበሱ ተኩላዎች በጥንቃቄ እንድትከታተሉ እያሳሰብን ለመረጃ መረብ (Face book ፣ Blogs ፣ የተለያዩ ድኅረ ገጽ ተከታታዮች በሙሉ በኦርቶዶክስ ስም የሚጻፉት ሁሉ የቤተክርስቲያናችን ትምህርት አለመሆኑን አውቃችሁ ራሳችሁን ከኑፋቄ እንድትጠብቁና ከተለመደው አስተምህሮ ውጪ የሚከራከራችሁ ወይም አዲስ ነገር ይዘው የሚመጡ አካላት ካጋጠሟችሁ በቤተክርስቲያን የምታመንባቸው እውነተኞችን ሊቃውንትና መምህራን በመጠየቅ እንድትረዱ ለማስገንዘብ እንወዳለን፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ይሁዳ ‹‹ወዳጆች ሆይ ስለምንካፈለው ስለመዳናችን ልጽፍላችሁ እጅግ ተግቼ ሳለሁ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለተሰጠ ኃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኳችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ›› (ይሁ 1፡3-18)
እነዚህ ሰዎች መናፍቃኑና የበግ ለምድ የለበሱት ተኩላዎች እያለሙ ሥጋቸውን ያረክሳሉ ጌትነትንም ጥይላሉ ሥልጣን ያላቸውን ቅዱሳንን መላዕክትን፣ የአምላክን እናት ሊቃውንትን ካህናትን ይሰድባሉ አእምሮ እንደሌላቸው እንሰሶች በፍጥረታቸው በሚያውቁት ሁሉ በእርሱ ይጠፋሉ በቃየል መንገድ በመሄድ ወንድም እህታቸውን በኒፋቄ ይገድላሉ እነዚህ ከእናንተ ጋር ሲጋበዙ በፍቅር ግብዣችሁ እንደ እድፍ ናቸው፡፡ እንደ እረኞች ያለፍርሃት ራሳቸውን ይጠብቃሉ አስመሳይ እረኛ ናቸው በነፋስ የተወሰዱ ውሃ የሌለባቸው ደመናዎች መጻሕፍትን ያለትርጉም በንባብ የሚያጣምሙ ፍሬ የማያፈሩ ሁለት ጊዜ የሞቱ ከነሥራቸው የተነቀሉ በበጋ የደረቁ ዛፎች መሠረት የሌላቸው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹በብዙ መከራና ችግር የእግዚአብሔርን መንግስት እንወርሳለን›› ሐዋ14-21 እያለ በጻጋ ድነናል ምግባርን ከሃይማት አስተባብረን መያዝ አያስፈልገንም የሚሉ መንፈስ ቅዱስ ተሞላን እያሉ እየተዘረሩ የገዛ ነውራቸውን አረፋ እየደፈቁ ጨካኝ የባሕር (የሚወላውል ልብ) ማዕበል ድድቅ ጨለማ ለዘላለም የተቀበላቸው የሚንከራተቱ ከዋክብት ወይ ኦርቶዶክሳዊ አይደሉም ወይ ለይቶላቸው አልወጡም በመሀል ሆነው የሚዋዥቁ ተጠራጥረው የሚያጠራጥሩ የአምልኮት መልክ አላቸው ‹‹ኢየሱስ ጌታ ነው›› ይላሉ ነገር ግን ኃይሉን ክደዋል አማላጅ ይሉታል ወደ ቤቶች (ቤተክርስቲያን ጭምር) ሾልከው እየገቡ እየተመሳሰሉ ኃጢዓታቸው የተከመረባቸውን (አጫሽ ፣ ሰካራም ፣ ዘፋኝ ነገር ግን ኦርቶዶክሳዊ) የሆኑትን በልዩ ልዩ ምኞትንም የሚወሰዱትን ሁል ጊዜም እየተማሩ እውነትን ወደ ማወቅ ሊደርሱ ከቶ የማይችሉትን ሞኞችን ሴቶች የሚማርኩ ከነዚህ ውስጥ ናቸው›› 2ጤሞ 3፡6-8






 


ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እነዚህን የመሰሉትን አስመሳይ መናፍቃን በተመለከተ ‹‹የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውስጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኩላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ ከእሾህ ወይን ከኩርንችትስ በለስ ይለቀማልን? እንዲሁ መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያደርጋል ክፉም ዛፍ ክፉ ፍሬ ያደርጋል›› በማለት ከማስተማሩም ባሻገር በባዶ ጩኸት ብቻ ያለ ጽድቅ ሥራ ያለ መንፈሳዊ ተጋድሎ ያለ ጾም ያለ ጸሎት ያለትሩፋት መዳን ይቻላለሚሉት መናፍቃንም ‹‹በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደግር እንጂ ጌታ ሆይ የሚለኝ ሁሉ መንግስተ ሰማያት የሚገባ አይደለም›› ተአምራትን በማድረግ አጋንንትን በማውጣት ትንቢት በመናገር ነገር ግን ምግባርን ከሃይማኖት አስተባብረው የማይዙ እነሱ ባዶ ሆነው በጌታ ስም ብቻ የሚነግዱ ናቸውና ‹‹በዚህ ቀን ብዙዎች ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ በስምህ ትንቢት አልተናገርንም፣ በስምህስ አጋንንትን አላወጣንም በስምህስ ብዙ ተአምራት አላደረግንም ይሉኛል የዚያን ጊዜም ከቶ አላውቃችሁም እናንተ ዓመፀኞች ከእኔ ራቁ ብየ እመሰክርባቸዋለሁ›› (ማቴ 7፡15-23) በማለት አሳስቦናል፡፡






 


ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ከጌታ እግር ሥር የተማሩት ሐዋርያትም ‹‹ልጆች ሆይ መጨረሻው ሰዓት ነው ክርስቶስም ተቀዋሚ ይመጣ ዘንድ እንደሰማችሁ አሁን እንኳን ብዙዎች የክርስቶስ ተቋዎሚዎች ተነስተዋል ስለዚህም መጨረሻው ሰዓት እንደሆነ እናውቃለን፡፡ ከእኛ ዘንድ ውጡ ዳሩ ግን ከእኛ ወገን አልነበሩም ከእኛ ወገንስ ቢሆኑ ከእኛ ጋር ጸንተው በኖሩ ነበር ነገርግን ሁሉ ከእኛ ወገን እንዳልሆኑ ይገለጡ ዘንድ ውጡ›› (1ዮሐ 2፡18) በማለት የትንቢት መፈጸሚያ ሆነው እንደሚለዩ እንዲሁም ‹‹በእነዚያ ዘንድ ለማስተዋል የሚያስቸግር ነገር አለ ያልተማሩትና የማይጸኑትም ሰዎች ሌሎችን መጻሕፍት እንደሚያጣምሙ እነዚህ ደግሞ ለገዛ ጥፋታቸው ያጣምማሉ (ቀላል አማርኛ አዲስ ትርጉም በማለት) እንግዲህ እናንተ ወዳጆች ሆይ ይህን አስቀድማችሁ ስለምታውቁ በዓመፀኞች ስህተት ተስባችሁ ከራሳችሁ ጽናት እንዳትወድቁ ተጠንቀቁ ነገር ግን በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ዕውቀት እደጉ›› (2ጴጥ 3፡16)
‹‹እናንተ ግን ወዳጆች ሆይ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት ቀድሞ የተነገረውን ቃል አስቡ እነርሱ በመጨረሻው ዘመን በኃጢዓተኝነት እንደ ገዛ ምኞታቸው እየሄዱ ዘባቾች ይሆናሉ ብለው አስተምረዋችኋልና እነዚህ የሚለያዩ ሥጋውያንም የሆኑ መንፈስም የሌላቸው ሰዎች ናቸው እናንተ ግን ወዳጆች ሆይ ከሁሉ ይልቅ በተቀደሰው ኃይማኖታችሁ ራሳችሁን ለማነጽ እየተጋችሁ በመንፈስ ቅዱስም እየጸለያችሁ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚወስደውን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ምህረት ስትጠብቁ በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ አንዳንዶችንም ተከራካሪዎችን ውቀሱ ፣ የሚቻል ከሆነ አንዳንዶችን ከእሳት ከክህደት ከምንፍቅና ነጥቃችሁ አድኑ›› (ይሁ 1፡17)
እናንተም ሳትሰናከሉ እንዲጠብቃችሁ በክብሩም ፊት በደስታ ነውር የሌላችሁ አደርጎ እንዲያቆማችሁ ለሚችለው ብቻውን ለሆነ አምላክና መድኃኒታችን ክርስቶስ ከዘመን ሁሉ በፊት አሁንም እስከ ዘላለምም ድረስ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ክብርና ግርማ ኃይልም ስልጣንም ይሁን አሜን፡፡
‹‹ይህንን መልዕክት  "Share"  ና    "copy" በማድረግ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ከመናፍቃን ከከሃዲያን ከተኩላዎች እንድንታደግ ስል አሳስባለሁ››





No comments:

Post a Comment