Thursday, November 12, 2020

 አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን

አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን በ330 ዓ.ም በሐዋርያው ቅዱስ አትናቴዎስ እጅ ጵጵስና የተሾሙበት ዕለት ነው፡፡ ይኸውም ቅዱስ ጌታችን ‹‹ኢትዮጵያን ከጨለማ አውጥተህ በሃይማኖት ስለ አበራሃት ከፍ ያሉ ክብራትንና ማዕረጋትን ፈጽሜ ሰጠሁህ›› በማለት ታላቅ ቃልኪዳን የሰጣቸው እጅግ የከበሩ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያናችን እንደሚገባቸው መጠን ያላከበረቻቸው የመጀመሪያው አባታችን ናቸው፡፡

አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን፡- ቅዱስ አባታችን አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በኋላ በ245 ዓ.ም በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ህዳር 26 ቀን ሲወለዱ ታላቅ ብርሃን ከሰማይ ወርዶ ለ7 ቀናት አብርቷል፡፡ ቅዱሳን መላእክትም ወደ ምድር ወርደው በመወለዳቸው ታላቅ ደስታን አድርገዋል፡፡ በተወለዱም ጊዜ ‹‹ለአብ ስግለት ለወልድ ስግደት ለመንፈስ ቅዱስ ስግደት ይገባል፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን ለአወጡኝ ቅድመ ዓለም ለነበሩ ዛሬም ላሉ ዓለምን አሳልፈው ለሚኖሩ ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይገባል ብለው ዳግመኛም አሐዱ አብ ቅዱስ አሐዱ ወልድ ቅዱስ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ›› ብለው ፈጣሪያቸውን በአንድነት በሦስትነት አመስግነዋል፡፡
ቅዱስ አባታችን በሌላኛው ስማቸው ፍሬምናጦስ እየተባሉ ይጠራሉ፡፡ በ40 ቀናቸው ጌታ በተጠመቀበት በዮርዳኖስ ያጠመቋቸውና ስመ ክርስትና የሰጧቸው ሊቀ ጳጳስ ‹‹ይህ ሕፃን ለኢትዮጵያውን ሁሉ ብርሃን ይሆንላቸዋል›› በማለት ትንቢት ተናግረዋል፡፡ በሊቀ ጳጳሱ በቅዱስ አትናቴዎስ በሚገባ ተምረው ካደጉ በኋላ በ257 ዓ.ም ከኢየሩሳሌም ወደ ኢትዮጵያ ስሙ ሜርጵዮስ ከሚባል ከአንድ ነጋዴ ጋር መጡ፡፡ ከእነሱም ጋር አድስዮስ የሚባል ልጅ ነበር፡፡ ወደ ሀገራችንም ሊመጡ የቻሉት እንዴት ነው? ቢሉ መጀመሪያ ለሰባት ወር በአንድ ሌላ አገር ኖረው ወደ ኢየሩሳሌም ሊመለሱ ሲሉ የበረሃ ሽፍቶች ሜርጵዮስንና ሌሎች መንገደኞችን ገደሏቸውና ሁለቱን ልጆች ማርከው ወስደው ስሙ አልአሜዳ ለሚባል ለአክሱም ንጉሥ ሰጡት፡፡ እርሱም አድስዮስን የቤተክርስቲያን የአልባሳትና የዕቃ ቤት ጠባቂ አድርጎ ሲሾመው ፍሬምናጦስን ደግሞ የቤተክርስቲያንና የሕግ ጠባቂ አደረገው የቤተክርስቲያንን ሥርዓቷንና አገልግሎቷን ጠንቅቆ ያውቅ ነበርና፡፡
በአክሱምም በተጋድሎና በትጋት ኖረ፡፡ ቅዳሜና እሁድ የዛፍ ቅጠሎችን ከመመገብ በቀር ሌላ ምግብ አይቀምስም ነበር፡፡ በየቀኑም አምስት ሺህ ስግደትን ይሰግድ ነበር፡፡ በእርሱም የተጋድሎ ዘመን ደጋግ የሆኑ ነገሥታት አብርሃና አጽብሓ ነገሡ፡፡ እነርሱም ሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍሬምናጦስን በጣም ይወዱት ነበር፡፡ አንድ ቀን ፍሬምናጦስ የአክሱሙን ኤጲስ ቆጶስ ቅዱስ ሚናስን ‹‹ግዝረትና እምነት በእናንተ ዘንድ አለ ነገር ግን ጥምቀትና ሥጋ ወደሙ መቀበል በእናንተ ዘንድ የለም›› አለው፡፡ ቅዱስ ሚናስም ‹‹ግዝረትንስ አባቶቻችን ሌዋውያን አመጡ፣ በክርስቶስ ማመንን ሕንኬ የተባለች የኢትዮጵያ ንግሥት ጃንደረባ አመጣልን፡፡ ስለ ጥምቀትና ሥጋ ወደሙ ሐዋርያ ወደ እኛ አልተላከም ነገር ግን ያልከውን ሁሉ የሚያደርግልን የሚባርከንና የሚቀድሰን ጳጳስን ታመጣልን ዘንድ ሊቀ ጳጳሱ ወዳለበት ወደ እስክንድሪያ አገር አንተ ሂድ›› አለው፡፡ ጥምቀትስ በጃንደረባው በኩል አገራችን ገብቶ ነበር ነገር ግን ገና ስላልተጠናከና ብዙ ሕዝብም አልተጠመቀም ነበርና አባታችን ፍሬምናጦስ አጠናክሮ ያልተጠመቀውን ሁሉ አጥምቆአል፡፡
ፍሬምናጦስም ወደ እስክንድሪያ ለመሄድ አስቦ ሳለ እንደተኛ ድንግል ማርያም ተገልጣለት ‹‹ዲቁናና ቅስናን መቀበል ይገባሃል፣ ለጵጵስና ተዘጋጅ፣ እግዚአብሔር ይህችን ከፍ ያለችውን ማዕረግ ሰጥተሃልና የልጄ ወዳጅ ሆይ በጸሎትህና በልመናህ በስብከትህም የኢትዮጵያ ሰዎች ሁሉ ይድናሉ፣ በእጅህ ጥምቀትንና ሥጋ ወደሙን ይቀበላሉ›› አለችው፡፡ ጌታችንም እንዲሁ ተገልጦለት ‹‹ወደ ሊቀ ጳጳሳት ወደ አትናቴዎስ ሄደህ ከፍ ያችውን ማዕረግ ተቀብለህ የኢትዮጵያን ሰዎች አጥምቅልኝ፣ ነቢዩ ዳዊት ስለ እነርሱ ‹ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች› ብሎ ተናግሯልና›› አለው፡፡ እርሱም ቅዱሳኑን ነገሥታት አብርሃንና አጽብሓን አግኝቶ ከእነርሱም ጋር ተማክሮ ወደ እስክንድሪያ ሄዶ በቅዱስ አትናቴዎስ እጅ በአገራችን ላይ ሊቀ ጳጳስ ሆኖ ታኅሳስ 18 ቀን ተሾመ፡፡ ስሙንም ሰላማ ከሣቴ ብርሃን አለው፡፡ ሰላማ ማለት እግዚአብሔርንና ሰውን የሚያስታርቅ ማለት ነው፡፡ ከሣቴ ብርሃን ማለትም ሃይማኖትን ገልጦ የሚያስተምር ማለት ነው፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስም ከሾመው በኋላ ታቦትና በጣም ብዙ ንዋያተ ቅድሳትንና መገልገያ ዕቃዎችን ሰጥቶ መርቆ በሰላም ወደ ኢትዮጵያ ላከው፡፡
ቅዱሳን የሚሆኑ ሁለቱ ነገሥታትም መምጣቱን በሰሙ ጊዜ ‹‹ኢትዮጵያ ሰዎች ሁላችሁ እስከ 40 ቀን ተሰብሰቡ›› ብለው አዋጅ አስነገሩ፡፡ በደብረ ሲናም ሄደው ተገኛኙትና ከዚያች ቀን ጀምሮ ሕዝቡም ሁሉ እስከ 40 ቀን ድረስ ተጠመቁ፡፡ በዚያችም ዕለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚያች በደብረ ሲና አገር ላይ ወረደና ሕዝቡን ሁሉ ባረኮ ተመልሶ ሲያርግ ከአባ ሰላማ በቀር ያየው አልነበረም፡፡ ወደ አክሱምም ሄደው ነገሥታቱም የአድባራት ሁሉ የበላይ የምትሆን የቅድስት ጽዮንን ቤተክርስቲያን በወርቅና በዕንቊ ሠሩና አባ ሰላማ ባርኮ ቀደሳት፡፡ ታቦተ ጽዮንም ከድንኳን ወጥታ ማንም ካህን ሳይሸከማት አብርሃና አጽብሓ ወዳሠሩላት ቤተ መቅደስ ራሷ በመንፈስ ቅዱስ ገብታ ተገኘች፡፡ አባታችንም በእመቤታችንም በዓለ ዕረፍት ቀን ጥር 21 ቀን በውስጧ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲቀድስ ሚካኤልና ገብርኤል በግራ በቀኝ እየተራዱት እርሱም ከምድር ሦስት ክንድ ከፍ ብሎ ሥርዓተ ቅዳሴውን ፈጽሞ ለነገሥታቱና ለሕዝቡም ሁሉ አቆረባቸው፡፡ የዚያን ዕለትም እጅግ ታላቅ በዓልን አደረጉ፡፡
ከዚያም ሌሎችን እየሾመ ወደ ሌላ አገር ካሰማራ በኋላ እርሱም በየሀገሩ በአራቱም አቅጣጫ እየዞረ እያጠመቀና እያስተማረ አብያተ ክርስቲያናትንም እየሠራ ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ታላቅ ብርሃን ሆነ፡፡ በየቀኑም እስከ ማታ ድረስ የሚጠመቀው ሕዝብ የሦስት ገበያ ሕዝብ ይሆናል፡፡ በመሸም ጊዜ እንደ ኢያሱ ፀሐይን እያቆመ ሕዝቡን ያጠምቅ ነበር፡፡ መድኃኔዓለምም በየጊዜው በአካል እየተገለጠለት አገልግሎቱን ያፋጥንለት ይባርከውና ቃልኪዳን ይሰጠው ነበር፡፡
አባታችንም በድፍን ኢትዮጵያ በአራቱ አቅጣጫ እየዞረ በተአምራቱ ድውያንን እየፈወሰ፣ ሙታንን እያስነሳ፣ ወንጌልን እያስተማረ፣ እያጠመቀ፣ አብያተ ክርስቲያናትን እየሠራና አገልጋይ የሚሆኑ ቀሳውስትን እየሾመ በሀገራችን ላይ ብርሃንን የፈነጠቀ ለኢትዮጵያ መግለጽ ከሚቻለው በላይ ታላቅ ባለውለታዋ ነው፡፡ ከአባ ሰላማ በፊት እኛ ኢትዮጵያውያን ክርስቶስን ከማመን በቀር ጥምቀትና ሥጋ ወደሙ የመቀበል ልማድ አልነበረንም፡፡ በድንኳን ካለችው ታቦተ ጽዮን በቀርም ታቦታትና አብያተ ክርስቲያናትም አልነበሩንም፡፡ ይሄ ሁሉ ሲታሰብ ከአባ ሰላማ ውለታ አንጻር እንደዋለላት ውለታና እንደሠራላት እጅግ ታላቅ ሥራ ቅድስት ቤተክርስቲያናችን እንደሚገባው መጠን አላከበረችውም ማለት ይቻላል፡፡ ጌታም በመጨረሻ ቃልኪዳን ሲሰጠው ‹‹ስለ ትምህርትህና ስለ ስብከትህ ኢትዮጵያን ከጨለማ አውጥተህ በሃይማኖት ስለ አበራሃት ከፍ ያሉ ክብራትንና ማዕረጋትን ፈጽሜ ሰጠሁህ›› ነው ያለው፡፡ ‹‹ነቢያትና ሐዋርያት ፊቴን አይተው ስለእኔ መረዳት ያቻሉትን አንተ ግን ፊቴን አይተህ ስለ እኔ እንድትረዳ አደረግሁህ፣ ለቅዱሳንም ሁሉ ብርሃናቸው አድርጌሃለሁ›› ተብሎ በጌታችን አንደበት የተነገረለትን ቅዱስ፣ ጻዲቅ፣ መናኝ፣ ሐዋርያ፣ ጳጳስ… ቤተክርስቲያናችን አሁን እያከበረችው ባለው መልኩ ብቻ አልነበረም ማከበርና መዘከር የነበረባት፡፡
በተንቤን ምድር ብቻ በብሕትውናና በጽሙና ሲቀመጥ ቋጥኝ ፈልፍሎ በሠራው ቤተክርስቲያን ላይ የብርሃን መሰላል ተተክሎለት በእርሱም ወደ ሰማይ ወጥቶ ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ጋር የሥሉስ ቅዱስን መንበር አጥኗል፡፡ የተንቤንንም ምድር ቡሩካን በሆኑ እጆቹ አንስቶ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ መንበር ፊት አቅርቦ አስባርኳታል፡፡ መልአክም ሰማያዊ መናና ኅብስት እያመጣ ይመግበው ነበር፡፡ ወንጌልንም ካዳረሰ በኋላ በዋሻ ገብቶ በበዓት ተወስኖ ሰውነቱን በመከራ ይቀጣ ነበር፡፡ በጎጃም ክፍለ ሀገር በሞጣ ዓባይ በኩል በምትገኝ ቦታ እያስተማረና ሐዋርያዊ ተልዕኮውን እየተወጣ ሳለ ጊዜው መሽቶ ፀሐይ ልትጠልቅ ስትል እንደ ኢያሱ ገዝቶ ያቆማት ሲሆን ጌታ ግዝቱን እንዲፈታ ከነገረው በኋላ ነው ግትዙን አንስቶላት የጠለቀችው፡፡ በታዘዘውም መሠረት ከጎጃም ወደ ትግራይ ሲሄድ የዓባይን ባሕር በመጠምጠሚያው ለሁለት ክፍሎ ከእርሱም ጋር የነበሩትን አሻግሯቸዋል፡፡ በደመናም ተጭኖ ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ሄዶ አይሁድ ቀብረው በደፈኑት በክርስቶስ መስቀል ላይ ጸሎት አድርጎ ሰግዷል፡፡ ከጌታችንና ከእመቤታችንም መካነ መቃብር አፈር ዘግኖ ወደ ሀገራችን በማምጣት በሚያንጻቸው አብያተ ክርስቲያናት ላይ ነስንሶታል፡፡
አባታችን አባ ሰላማ ሐምሌ 26 ቀን ሲያርፍ ነፍሱን መላእክት ያይደሉ ራሱ መድኃኔዓለም ክርስቶስ ተቀብሎ ከእርሱ ጋር አሳርጓታል፡፡ መላእክትም ሥጋውን ከጌታችንና ከእመቤታችን መቃብር አድርሰው ወደ ደብረ መድኃኒት የመለሱት ሲሆን በመቃብሩም ላይ ብርሃን ወርዶ ለሁሉም ታይቷል፡፡ ነገሥታቱም ከዐረፈ በኋላ ወደ ደብረ መድኃኒት መጥተው ለመካነ መቃብሩ ሲሰግዱ አባ ሰላማም ተገልጦላቸው ከነሠራዊታቸው ባርኳቸዋል፡፡ የሰላማ ከሣቴ ብርሃን በረከታቸው ይደርብን፡፡
ለልዑል እግዚአብሔር ምስጋና ይሁን! እኛንም በአማላጅነታቸው የምንታመን የተዋሕዶ ልጆች የሆንን ሁላችንን የአቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃንን ረድኤት በረከታቸውን ያሳድርብን፣ በጸሎታቸው ይማረን፡፡
(ምንጭ፡- ገድለ አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን፣ የመስከረም፣ የግንቦትና የሐምሌ ወር ስንክሳር


No comments:

Post a Comment