Thursday, November 12, 2020

 ድምጽ በራማ ተሰማ

=============
“እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የዋይታና የመራራ ልቅሶ ድምፅ በራማ ተሰማ ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች የሉምና ስለ ልጆችዋ መጽናናትን እንቢ አለች ።” (ኤር. 31፡15)
ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች ። ይህች ራሔል የያዕቆብ ሚስት ራሔል ከሆነች እርስዋ በወሊድ ምክንያት ሞተች እንጂ ልጆችዋ ዮሴፍና ብንያም አልሞቱባትም ። በርግጥ በግብጽ ምድር የታነቁት ሕፃናት ትውልዶቿ ናቸውና ከቀኑ በፊት አዝናለች ፣ የፍቅር አንጀቷ ስለ እነርሱ ተላውሷል ማለት ይሆናል ። ይህች ራሔል በግብጽ የባርነት ዘመን የነበረች ከሆነች ድርስ እርጉዝ ሁና ጡብ የሚሠራበትን ጭቃ ስትረግጥ ልጇ ፈትለክ ብሎ ከማኅፀኗ ወጣ ። በዚህ ጊዜ ደንግጣ ብትቆም አስገባሪው፡- “እርገጭው ምን ይለዋል ፣ የሰው ደም እንደውም ያጠነክረዋል” አላት ። በዚህ ጊዜ “በዚህ ሰማይ የእስራኤል አምላክ የለምን!” ብላ እንባዋን ወደ ላይ ረጨችው ። የራሔልም እንባ መንበረ ጸባዖትን አራሰው ። እግዚአብሔርም ለፍርድ ና ለፍትሕ ተነሣ ፣ እስራኤልም ፈረኦንን ሰብሮ የበኩር ልጆችን ከግብጽ ባርነት ነጻ አወጣ።
ዛሬም ራሔል ስለ ልጆችዋ እያለቀሰች ነው። ይህች ራሔል የዘመናት አልቃሾችን ፣ በልጅ ሞት ፣በወገን ሞት የሚተክዙትን ወክላ የቆመች ናት ።
ያቺ ራሔል የዘመናትን የልጆች ሞት ሲገልጥ ይኖራል ። በባቢሎን ምርኮም የእስራኤል ሕፃናት እንደ ጎመን ሲቀረደዱ ፣ እንደ ዛፍ ሲቆረጡ ይህች ራሔል ታወሰች (ኤር. 31፡15) ። ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች ተባለ ። ሄሮድስም የቤተ ልሔም ሕፃናትን ሲፈጃቸው ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች በማለት ቅዱስ ማቴዎስ ያነሣታል (ማቴ. 2፡17) ። ወንጌላዊው ማቴዎስ ያነሣት የመጀመሪያው መራራ ኀዘን መሆኑን ስለመግለጥ ነው ። ሁለተኛ ታሪክ መደገሙን ለማንሣት ነው ። ክፉ ታሪክ ሲደገም ሰው ካለፈው አለመማሩን ያሳያልና ያሳምማል ። ካለፈው ትርፍ እንዳልተገኘ ተገንዝቦ አሁንም ትርፍ የሌለው ነገር መሥራቱ ያሳዝናል ።
ራሔል ዛሬም ያሉትን ፣ በመላው ዓለም በተለይም በኢትዮጵያ ስለ ልጆቻቸው የሚያለቅሱትን አባቶች እናቶች ትወክላለች ። በአገራችን በኢትዮጵያና በቤተክርስቲያን ራሔል ጠፍታም ፣ ልቅሶዋም ነጥፎ አያውቅም ። የዘመናት አልቃሽ ሁና ዛሬም ትጮኻለች ። የዋይታና የልቅሶ ድምፅ በአርያም እየተሰማ ነው ። ባለፉት አርባ ዓመታት እንኳ ስንት ወጣት ረገፈ ። ቀይ ሽብርና ነጭ ሽብር እየተባባለ ስንቱ እንደ ወጣ ቀረ ። ሬሣው የሚያነሣው ጠፍቶ በአደባባይ ዋለ ። እርጉዞች ተገደሉ ፣ ብዙ ወጣቶች የት እንደ ደረሱ ሳይታወቅ ደብዛቸው ጠፋ ። በመቀጠል ለ17 ዓመታት በዘለቀ ጦርነት በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ብዙ ወጣት ረግፎ ቀረ ። ይህም ምንም ትርፍ የሌለው የወንድማማቾች እልቂት ነበር ። በ1990 ዓ.ም. “የክፍለ ዘመኑ ኋላ ቀር ጦርነት” ተብሎ በተሰየመው በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል በተደረገ ጦርነት ትውልድ እንደ ወጣ ቀረ ። እነዚያ ወጣቶች እንዳጎደሉ የሚያውቀው ዛሬም ያ ቤተሰባቸው ብቻ ነው ። የእኛ የኢትዮጵያውያን ጸጋችን መርሳት ነውና ረስተናቸዋል ። ላለፉት አርባ ዓመታት ጥቁር ልብስ ያላወለቁ ፣ በኀዘን ምክንያት በሽተኛ የሆኑ ፣ አቅላቸውን ስተው ያበዱ ፣ ከኅዘን የተነሳካሉት በታች ከሞቱት በላይ ነዋሪ ሁነው የቀሩ ብዙ ራሔሎች አሉ ። በዚህ የደም ገንቦ ላይ እንጨምርበታለን ተብሎ አይታሰብም ነበር ። አሁንም እያትረፈረፍነው ነው ። አዎ ጣፋጩ ትረካችን “ኢትዮጵያ ማንንም ወርራ አታውቅም” የሚል ነው። ኢትዮጵያውያን ግን ሲተላለቁ የሚኖሩ ናቸው ። እስከ ሰባት ቤት ደም ከሚቃቡት ጀምሮ ያለ ምክንያት እስከሚፈጁት ወገኖች ድረስ የደም ጥምቀት በአገራችን የተለመደ ሁኗል ። ያለፈው ሳይካስ ሌላ ዕዳ እያመጣን ፣ የወለድናቸው ለአንድ ቀን እንኳ የሰላም ድምፅ እንዳይሰሙ አድርገን እያሸማቀቅናቸው ነው ።
ራሔል ኢትዮጵያ ስለ ልጆችዋ አለቀሰች ። በጠፍ ጨረቃ ፣ በውድቅት ሌሊት በራቸው ተንኳኩቶ ስለታረዱት ፣ በጎሣቸው ምክንያት ስለተፈጁት ምስኪኖች ልቅሶ በአርያም ተሰማ ። እግዚአብሔር ፍርድ ሲሰጥ ሰምተን እንዳልሰማን የሆነውን ፣ እኔን ካልነኩኝ ብለን ያለፍነውን ሁሉ የብይኑ በትር ያገኘናል ። ሁሉም ነገር ካለቀ በኋላ ወሬ ማሯሯጥ ጥቅም የለውም ። ንጹሕ ነኝ ብሎ ማሰብም ከንቱ ነው ። ማንን ነው የምንቀየመው ? ብለን ስንጠይቅ ገዳይም ሟችም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው ።
“የገደለው ባልሽ የሞተው ወንድምሽ ፣
ኀዘንሽ ቅጥ አጣ ከቤትሽ አልወጣ ፤”
ሌላም ግጥም ትዝ ይለናል፡-
“አንጀቴ ተቆርጦ ከሆዴ ከወጣ ፣
እንግዲህ ሐኪሙ ምን ሊቀጥል መጣ ?”
አዎ ሁለት ነገሮች ያስፈልጋሉ ። የእኛ አባት መገለጥ ቀላል አይደለም ። ፍርድና ትምህርት ያስፈልጋሉ ። ከተመከርንበት የሕንዱ የነጻነት ታጋይ የነበሩት ማኅተማ ጋንዲ እንዲህ ብለው ነበር፡- “በምድር ላይ ብቻህን ብትቀር እንኳ ከግፈኞች ጋር አትተባበር ።”
እግዚአብሔር የመጽናናትን መንፈስ ይላክልን ። ላዘኑት የሚያረጋጋ መልአክ ይላክልን ። ልብ ይስጠን ።
“ጎዳናው ሳይጠበን አመል እያጋፋን ፣
አካሄዱ ቀርቶ አቋቋሙ ጠፋን ፤”
(ሰባኪውና ጸሐፊው)
ሕዳር ፫፣፳፲፩፫


No comments:

Post a Comment