Monday, November 9, 2020


እመቤታችንን በተመለከተ ለዘመናት በመናፍቃን ለሚነሱ ጥያቄዎች የማያዳግም መልስ 

ለዘመናት የእናታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ዘለዓለማዊ ድንግልና ለመቃወም ዲያቢሎስ ያዘመታቸው
መናፍቃን ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች ሁሉ የማያዳግም መልስ በዝርዝር እና በአንድምታ ቀርቧል ፡፡ ከጌታ ውጭ
ከቅዱስ ዮሴፍ ልጅ ወልዳለች ብለው ለተሰናከሉ ሁሉ በዚሁ አጋጣሚ ስለ ዮሴፍ ማንነት ጭምር ትምህርቱ
በጥቂቱ ይዳስሳል መልካም ንባብ፡-‹‹‹ አረጋዊው ዮሴፍ ማነው ? መናፍቃን ድንግል ማርያም ከጌታ ውጭ ከዮሴፍ
እንደወለደች ሲናገሩ እንሰማለን ማስረጃ ባይኖረውም። ነገር ግን የዮሴፍን ማንነት በጥቂቱም ቢሆን መረዳት
ለስህተታቸው ማሰታገሻ መድኃኒት ነውና እነሆ፡- አረጋዊው ቅዱስ ዮሴፍ ሀገሩ ናዝሬት ሲሆን ሐናፂም ነጋዴም ነበር።
ዘሩ ከዳዊት ወገን ነው። ሦሰት ሴቶች እና አምሥት ወንዶች ልጆች ነበሩ። ልጆቹ ገሚሶቹ ከ12ቱ
ሐዋርያት ገሚሶቹ ደግሞ ከ72ቱ አርድዕት ውስጥ የነበሩ ሲሆን ከሚስቱ ጋር 52 ዓመት፤ሚስቱ ከሞተች በኋላ
ደግሞ 40 ዓመት ኖሯል። በድምሩ 92 ዓመት ከኖረ በኋላ ለእመቤታች ጠባቂ ሆኖ ተመረጠ። 
ከእመቤታችን እና ከጌታ ጋር ደግሞ በስደት ፣ በመከራ 22 ዓመታትን አሳልፏል። ሊጠብቃትም 
ሲመረጥ ከ1,985 ሽማግሌዎች ውስጥ ዕጣ ደርሶት ነው።
በፈቃደ እግዚአብሔርም የከተሰበሰቡት ሁሉ የርሱ በትር ለሦስት ጊዜ ያህል በተደጋጋሚ አብባና ለምልማ ተገኘ።
አረጋዊ ዮሴፍ በ114 ዓመቱ ሐምሌ 26 ቀን አርፏል። ከማረፉ በፊት ግን ጌታችንን ‹‹ ሥጋዬን በዚህ ምድር
አታስቀረው ›› ብሎ ለምኖት ነበርና ዛሬም ድረስ ዮሴፍ መቀበሩን እንጂ ቅዱስ ሥጋው የት እንዳለ የሚያውቅ
የለም ጌታ ስለ ጸሎቱ (ስለልመናው) ሰውሮታልና። ‹‹‹ አረጋዊው ዮሴፍ ለምን ተመረጠ? 
*ይህ ጻድቅና ንጹሕ አረጋዊ ዮሴፍ ድንግል ማርያምን ሊጠብቅ ስለተመረጠበት ምክንያን አስረጋጭ ማስረጃዎች
እነሆ።
1ኛ) አገልጋይዋ ተላላኪዋ ሆኖ ሊጠብቃት።
2ኛ) መከራዋን እንዲጋራ። አንድም ዮሴፍ ዘመዷ ነው
መከራን ለብቻ አይዘልቁምና በልጇ አማካኝነት የሚደርስባትን ስደት እና መከራ አብሯት እንዲካለፈል
ነው። ዝምድናቸው ሲዘረዘር የሚከተለውን ሃቅ ያስረዳናል፡- ግንዱ ‹‹ አልዓዛር ›› በሁለት ወገን የሚከተሉትን
ወልዷል ፡- 1)* ማታን = * ቅስራ* 2) * ያዕቆብ = * ኢያቄም * 3)* ዮሴፍ = * ድንግል ማርያም
(የነዚህ የዘር ሐረጋት ግንዱ ከላይ እንዳየነው * አልዓዛር* ነው ስለዚህ የዘር ሐረጋቸው አንድ ነውና ሊጠብቃት
እንጂ ሊያገባት አይችልም)

3ኛ) ከመደብደብ ሊያድናት። በኦሪ.ዘኁ 5፥19 በተጠቀሰው መሠረት አንዲት ሴት ከባልዋ ውጭ ጸንሳ
ብትገኝ ማየ ዘለፋ ያጠጥዋት ነበር። እንዲሁም አንዲት ሴት ባል ሳታገባ ብትጸንስ በሙሴ ሕግ መሠረት
ደብድበው ይገድሉአት ነበር። ስለዚህ እመቤታችን ለዮሴፍ ሳትታጭ ቀርታ ቢሆን ለድብደባ ባበቁአት ነበር።
4ኛ) ትንቢቱ እንዲፈጸም ነው። ጌታ ከዳዊት ቤት እና ወገን እንዲወለድ ኢሳ 11፥1 ፣ 10 ላይ ትንቢት ነበር።
ዮሴፍም የዳዊት ዘር ነውና ክርስቶስ በዮሴፍ የዳዊት ልጅ ተብሎ እንዲቆጠር ነው። ምነው በእናቱ የዳዊት ልጅ
አይባልምን? ቢባል አይሁድ ሴትን ከትውልድ ቁጥር አግብተው አይቆጥሩምና ነው።

5ኛ) ኃይለ አርያማዊት (ከሰማይ ወረደች እንጂ ምድራዊት አይደለችም) የሚሉ ወገኖች ነበሩና
ምድራዊት መሆኑኗን ለማጠየቅ ነው። ሆኖም ከምድር መገኘቷን ለመግለጽ እንጂ ድንግል ማርያም በክብሯ ሰማያዊት
ናት። የባሕርያችን መመኪያ መባሏም ከሰው ዘር መገኘቷን ልብ እንዲሉ ነው። ስለዚህ ድንግል ማርያም ለዮሴፍ
መታጨቷ ስለዚህ እና ይህን ለመሰለ ምክንያት ነው እንጂ ለሚስትነት አልነበረም። አንድም ዮሴፍ እመቤታችን
ሊጠብቃት በተመረጠ ጊዜ ጀርባው ጎብጦ ፣ ጉልበቱ ዝሎ ፣ ዓይኑ ሞጭሙጮ ነበር 92 ዓመት አልፎት ነበር አረጋዊ
(ሽማግሌ) መባሉም ለዚህ ነው። በመሆኑም አረጋዊ ዮሴፍ ስለነዚህ ምክንያት ድንግል ማርያም ሊጠብቃት
ተመረጠ እንጂ ሊያገባት አይደለም። ሊያገባት የተመረጠ ቢሆን ኖሮ ድንግል ማርያምን መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል
ሊያበሥራት ሲመጣ ‹‹ ወንድ ስለማላውቅ እንዴት ይሆናል›› ባላለችውም ነበር ። ሊያበሥራት የተላከው
ለዮሴፍ ከታጨች በኋላ ነውና። በዚህም ንግግሯ ለዮሴፍ የታጨችው ሊጠብቃት እንጂ ሊያገባት እንዳልሆነ አረጋግጣለች።
ዛሬ የተነሱ መናፍቀን ምሥጢር ይጎድላቸዋልና ዮሴፍን እንደወጣት ሰው ቆጥረው ድንግል ማርያምን ሊያገባ
እንደታጨ በደካማ ጎናቸው ያስባሉ እውነቱ ግን ይሄ ነው።

 1) የእጮኛ ትርጉም 

እጮኛ የሚለው ቃል ጠባቂ ማለት ነው ሌላ ከሰው ልብ የፈለቀ ትርጉም ሊሰጠው አይችልም። ለምሳሌ ‹‹እናንተን
ለዘለዓለም ለእኔ እንድትሆኑ አጭቻችኋለሁ ›› ሆሴ 2፥21 ማለት ለጋብቻ ነውን? ያሳዝና አጣመው ለተረጎሙት።
አሁንም ሐዋርያው ከጌታችን ጋር ስላዋሐዳቸው ‹‹ ለእርሱ አጭቻችኋለሁ ›› 2ኛ ቆሮ 11፥3 ማለቱን አስተውል።
እንደገናም ምእመናንን የከበረች ማደርያው ስላደረጋቸው ‹‹ ለሰማያዊው ክብር አጭቻችኋለሁ ›› ኤፌ 5፥26 ታዲያ
እንዲህ ሲል ላጋባችሁ ነው ማለት ይሆን(ሎቱ ስብሐት)። እመቤታችን ንግሥተ ሰማይ ወምድር ነችና በ15 ዓመቷ
መለኮት ተዋሐዳት። ሲዋሐዳትም ለዮሴፍ ታጨች ሉቃ 1፥26። እንግዲህ እጮኛ ማለት ትርጉሙን ያላወቁ ይወቁ
እንላለን። ነገር ግን ሰው በራሱ ፍቃድ አይተርጉም ! ሌላው እጅግ የሚደንቀው ነገር ደግሞ ድንግል ማርያም
ክርስቶስን ከመውለዷ በፊት እንጂ ከወለደች በኋላ ዮሴፍ ‹‹ እጮኛ ›› ተብሎ በአንድም ስፍራ አለመጠቀሱ ነው
ማስረጃ ‹‹ ሕጻንና እናቱን ይዘህ ወደ ግብጽ ሽሽ ›› ማቴ 2፥3 እንዲሁም በግብጽ 3 ዓመት ከ3ወር በስደት ከቆዩ
በኋላ ይህንኑ ቃል ለዮሴፍ በህልም ተነግሮት ‹‹ ሕጻኑን የሚፈልጉት ሞተዋልና ሕጻንና እናቱን ይዘህ ወደ ናዝሬት
ተመለስ ›› አለው እንጂ እጮኛህን(ሚስትህን) ይዘህ ተመለስ አላለውም (ማቴ 2፥20)።



2) የበኩር ትርጉም 
የበኩር ልጇን ወለደች የሚለው ቃል ብዙዎችን አሳስቷል። ይህም ሊሆን የቻለው በተለምዶ የበኩር ልጅ የሚባሉ
የግድ ተከታይ ያላቸው መሆን አለባቸው የሚል አስተሳሰብ በመናፍቃን ክፉ ልቦና ስለሰረጸነው። ነገር ግን በተለምዶ
የሚባል ነገር መጽሐፍ ቅዱስ ጋር አይሰራምና እንዲህ ይታረማል ፡- ‹‹ እግዚአብሔር ሙሴን ከእስራኤል ልጆች
ዘንድ ከሰውም ከእንስሳትም ማኅጸንን የሚከፍት በኩር ሁሉ ለእኔ ቀድስልኝ አለው ›› ዘጸ 13፥1-2
ይህ ቃል እንደሚገልጸው በኩር የሚባሉት ለመጀመርያ ጊዜ ከእናታቸው ማኅጸን የሚወጡ መሆናቸውን እንጂ
ግዴታ ተከታይ ሊኖራቸው እንደማይገባ ያረጋግጣ። አንድም ብቻ ቢሆን የእናቱም ማኅጸን ለመጀመርያ ጊዜ ከፍቶ
ከወጣ ተከታይም ባይኖረው በኩር ነው። ይሄ የበኩር ትርጉም ካልገባን ወደ ሌላ ፤ ይልቁን ወደ ማንወጣው
አዘቅት መዘፈቃችን አይቀሬ ነው። ለምሳሌ ቆላስየስ 1፥7 ላይ ስለ ክርስቶስ ሲናገር ‹‹ ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኩር ነው ›› 
ይላል እዚህ ጋር በኩር የሚለው ቃል ተወዳዳሪ ላላቸው ነገሮች የሚጠቀስ ሆኖ ከቀረበ ጌታን ፍጡር አድርጎ ከፍጡራን ጋር አነጻጽሮ
እርሱ ከፍጥረታት በፊት ቀደም ብሎ የተፈጠረ ፍጡር ነው እንደማለት ይሆናልና(ሎቱ ስብሐት)። እንደገናም በኩር
የሚለውን ቃል በሥጋዊ ደማዊ ሃሳብ ከተረጎምነው ዕብ1፥6 ላይ ‹‹ በኩርን ወደ ዓለም ሲያገባ ›› የሚል ቃል
አለ እዚህ ላይ የክርስቶስ በኩር ተብሎ መጠራት አብ ቀዳሚ ተከታይ የሌለውን የባሕርይ ልጁን ወደ መሬት ሂድ፣ ውረድ
 ተወለድ ፣ ሙት ተሰቀል ብሎ እንደላከው ለመግለጽ ነው ። ታድያ አብ በኩርን ወደ ዓለም ሲልክ በኩር የሚለው ቃል
ተጠቅሷልና አብም ከክርስቶስ ሌላ ልጅ አለው ማለት ነውን? እናንት ግብዞች መናፍቃን የመጽሐፍን ቃል
በግርድፍ መረዳት ምን ያህል እንደሚያስት ተረዳችሁ? ድንግል ማርያምን የነካችሁ እየመሰላችሁ ባለቤቱን
ነቀፋችሁ ያሳፍራል !!! እርሷስ ክብር ይግባትና በእናንተ አፍ አትረክስም እርሱ ባለቤቱ አንዴ አክብሯታልና።
ለምትሰሙኝ ግን እላችኋለሁ ‹‹ የበኩር ልጇን ወለደች ›› መባሉ መጀመርያና መጨረሻ የሌለውን አምላከ አዶናይ ፣
ልዑለ ባሕርይን ወለደች ማለቱ ነው። 

3) የ-እስከ-ትርጉም

ሥጋውያኑ(መናፍቃን) ‹‹ እስከን ›› ተገን አድርገው ‹‹እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም ›› የሚለውን ቃል ፍጻሜ
ላለው ነገር በማስገባት ደግመው ደጋግመው ተሰናክለውበታል። ትርጉሙ(ፍቺው) ግን ይህ አይደለም
ለምሳሌ፡- 1ኛ) የሣኦል ልጅ ሜልኮል ‹‹ እስከሞተችበት ›› ቀን ድረስ ልጅ አልወለደችም (2ኛ ሳሙ6፥23)። ይህም ማለት
እስከመጨረሻው ልጅ አልወለደችም ማለት እንጂ ከሞተች በኋላ ወለደች ለማለት አለመሆኑ የታወቀ ነው።
2ኛ) ይህም ነገር በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ጆሮ ተሰማ ‹‹ እስከሞቱ ›› ድረስ ይህ በደል በእውነት
አየሰረይላቸውም ኢሳ 22፥14 ታዲያ የዚህ ትርጉም ከሞቱ በኋላ ይሰረይላቸዋል ማለት ነውን? እስከዘለዓለም
አይሰረይላቸውም ለማለት እንጂ። 3ኛ) ከአዳም ጀምሮ ‹‹ እስከሙሴ ›› ድረስ ሞት ነገሠ (ሮሜ 5፥14)   
ታድያ ከሙሴ በኋላ ሞት ቀረ ማለት ነውን? 4ኛ) እግዚአብሐየር ጌታዬን ጠላቶችህ ለእግህ መረገጫ
‹‹ እስካደርግልህ ›› ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው መዝ101፥1 ታዲያ ጌታችን ጠላቶቹን(አይሁደን) በሥልጣኑ
ከረታ በኋላ በአብ ቀኝ መቀመጡ ቀረ ማለት ነው? 5ኛ) እነሆም እኔ ‹‹ እስከ ዓለም ፍጻሜ ›› ድረስ ከእናተ
ጋር ነኝ ማቴ28፥20 ከዓለም ፍጻሜ በኋላ ከእናንተ ጋር አይደለሀም ማለት ነውን ? 6ኛ) ቁራውንም ሰደደው እርሱም 
ወጣ ውሃውም ከምድር  ‹‹ እስከሚደርቅ ›› ድረስ ወዲያና ወዲህ ይል ነበር ዘፍ 8፥7 ሲል ውሃው ከደረቀ በኋላ ወዲያና ወዲህ ማለቱን
ተወ ማለት ነውን? እንግዲህ ከላይ በተዘረዘረው የእስከ ትርጉም መሠረት በማቴ1፥25 የተጠቀሰው ፍጻሜ
የሌለው ‹‹ እስከ ›› መሆኑን ያስረዳል ስለዚህ ዮሴፍ እመቤታችንን እስከ ፍጻሜው ድረስ በግብር አላወቃትም
ነበር ማለትነው፡፡ ከዚህ ውጭ በራሱ ፍቃድ የሚረተጉም ሁሉ የረተገመ ይሁን::

4) የወንድሞች ትርጉም 

አዲስ ኪዳን በተለያዩ ቦታዎች ላይ ጌታችንን ‹‹ወንድሞቹ›› እንደሆኑ ከሐዋርያት ወገን የሚጠቅሳቸው
አሉ። ይህን በመያዝ ብዙ ጥራዝ ነጠቅ አንባቢያን (መናፍቃን) ጌታ ወንድሞች እንዳሉት እና ድንግል
ማርያም ከጌታ ውጭ ልጅ እንዳላት በማውራት አነስተኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ዕውቀታቸውን ለማንጸባረቅ ይሞክራሉ ፡፡
 ነገር ግን ማንም የራሱን ግላዊ ሃሳብ ከማንጸባረቁ በፊት የመጽሐፍ ቅዱስን የአጻጻፍ ዘይቤ መረዳት ያስፈልገዋል እንላለን።
መጽሐፍ ቅዱስ 1ኛ) በምን ቋንቋ እንደተጻፈ ፣ 2ኛ) በማን ባሕልና ዘይቤ እንደተጻፈ ፣ 3ኛ) በየትኛው ዘመን እንደተጻፈ 
አስቀድሞ ማወቅ ለማነበብና ለመረዳት ያስችላል ምክንያቱም ሃይማኖት መሠረታዊ ጉዳይ ነውና !!! መጽሐፍ ቅዱስን የጻፉት
ከ40 በላይ ቅዱሳን ሲሆኑ ከእነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ ዕብራውያን ናቸው ፡፡ ስለዚህም መጽሐፍ ቅዱስን አንብቦ
ለመረዳት የዕብራውያንን ባሕል በከፊልም ቢሆን መረዳት ያስፈልጋል። ስለዚህም በዕብራውያን ባሕል ፡- 1ኛ) አብሮ
 አደግና ዘመዶችን በሥጋ እንኳ ከአንድ እናትና አባት ባይወለዱም ‹‹ ወንድም ›› ይባላሉ (ዘፍ 13፥11) 2ኛ) በሃይማኖት 
የሚመሳሰሉም ‹‹ ወንድሞች ›› ይባላሉ (ገላ4፥1) ‹‹ ወንድሞቼ ይህን ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ ›› 3ኛ) በሕብረት በአንድ 
(ማህበር) የሚቀመጡ ‹‹ወንድሞች ›› ይባላሉ ‹‹ ወንድሞች በሕብረት ቢቀመጡ እነሆ መልካም ነው እነሆም ያማረ ነው›› መዝ 133፥1።
በተጨማሪም ሐዋርያት እርስ በርስ ‹‹ ወንድሞች›› ይባባሉ ነበር። ከዚህ በመነሳት ለጌታ ‹‹ ወንድሞቹ ››
ተደርገው የተጠቀሱት ሦስቱ ሐዋርያት በሥጋ የተወለዱ አይደሉም። ድንግል ማርያምም ከጌታ ውጭ ምንም
ዓይነት ልጅ የላትም !!! ልጅ ብቻም ሳይሆን ልጅ የመውለድ ሃሳብም የላትም አልነበራትምም !!! በተጨማሪም 
ወንድሞቹ ተብለው የተጠቀሱት ‹‹ ያዕቆብ›› እና ‹‹ ይሁዳ ›› መልዕክቶቻቸውን ሲጽፉ ‹‹የጌታ ባሪያ›› እያሉ 
ጻፉ እንጂ ‹‹ የጌታ ወንድሞች ›› ነን ብለው አልጻፉም ማስረጃ ፡- የያዕቆብ መልእክት 1፥1 ‹‹ የጌታ የኢየሱስ 
ክርስቶስ ባሪያ ያዕቆብ ›› የይሁዳመልእክት 1፥1 ‹‹ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ የያዕቆብም ወንድም የሆነ ይሁዳ ›› ስለዚህ እነዚህ
ሐዋርያት ዮሴፍ ከሟች ሚስቶቹ የወለዳቸውና አብረውት ያደጉ እንጂ ከድንግል ማርያም የተወለዱ አይደሉም።
‹‹‹እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም የሚለው ትርጉም ››› ይህን ቃል በመጥቀስ ድንግል ማርያም ክርስቶስን
ከወለደች በኋላ ዮሴፍ በግብር አውቋታል የሚሉ መናፍቃን አሉ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከወለደች በኋላ ልጅ
ወልዳለች የሚል ቃል አልተጻፈም እንጂ !!! ይህን ቃል መነሻ አድርጎ ለመጀመርያ ጌዜ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅን
የጠየቀው በ3ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረው ንጉሥ አርቃድዮስ ሲሆን ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ አምሥት
ነገሮችን ግልጽ አድርጎለታል። አርቃድዮስም መልሱን በሚገባ አምኗል ተረድቷል። ዛሬም ጥያቄውን በድርቅና ሳይሆን
 ልክ እንደ አርቃድዮስ በየዋህነት ለጠየቀ ሁሉ መልስ የማያስፈልገው ጥያቄ ነው። ሆኖም ለዚህ ስህተታቸው መልስ 
መስጠቱ ተገቢ ነውና አነሆ ፡- ‹‹የበኩር ልጇን እስክትወልድ ድረስ ዮሴፍ ድንግል ማርያምን አላወቃትም›› ማለት፡- ዮሴፍ ድንግል
ማርያም ጌታን እስከምትወልድበት ቀን ድረስ ማን እንደሆነች አላወቃትም(ማንነቷን) አልተረዳም ነበርለማለት ነው።
ኋላ ግን ጌታን በወለደች ጊዜ በቤተልሔም እረኞች (ኖሎት) እና መላእክት በአንድነት ሲዘምሩ ፣ የሩቅ ምሥራቅ ነገሥታት(ሰብዓ ሰገል) 
እጅ መንሻ ይዘው መጥተው ሲሰግዱለት ፣ እንዲሁም ቤተልሔም ላይ የብርሃን ድንኳን ከምድር እስከ ሰማይ
ተተክሎ ሲመለከት ድንግል ማርያም የአምላክ እናት መሆኗን አወቀ(ተረዳ) እስከዚያች ቀን ድረስ ግን ማለትም
ጌታን እስከምትወልድበት ቀን ድረስ ዮሴፍ ድንግል ማርያም የአምላክ እናት መሆኗን አላወቀም ፣ አልተረዳም
ነበር ለማለት ነው። አወቀ ማለት በግብር ተገናኘ ማለት አይደለም!!! እንዲህ ከታሰበ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንዲህ የሚል ቃል አለ፡-
‹‹ ከእነርሱም ጋር በማዕድ ተቀምጦ ሳለ እንጀራውን አንሥቶ ባረከው፥ ቈርሶም ሰጣቸው፤ ዓይናቸውም
ተከፈተ፥አወቁትም›› (ሉቃ 24፥30-31) ይህም ማለት ጌታችን መሆኑን አወቁ (ተረዱ) ከማለት
ውጪ ሌላ ምን ዓይነት ትርጉም ሊኖረው ይችላል ? (ማዕዱን ቆርሶ እስከሚሰጣቸው ድረስ ግን ጌታን
አላወቁትም ነበር)ስለዚህ ማወቅ ማለት መረዳት እንጂ የግድ በግብር መገናኘት ዓይደለም !!! ለምሳሌ ‹‹ ቃየል
ሚስቱን አወቀ ጸነሰችም ›› ዘፍጥረት 4፥17 የሚለው ቃል በግብር እንደቀረባት(እንደተገናኛት) የታወቀ ነው
ምክንያቱም አወቃት ብቻ ብሎ አላቆመም ‹‹ ጸነሰችም ›› ይላልና :: ነገር ግን ዮሴፍ ድንግል ማርያምን እስክትወልድ ደረስ
አላወቃትም ካለ በኋላ ሌላ ምንም ዓይነት ተቀጽላ ቃል የለውም። መናፍቃን በግድ እናጋባ እናዋልድ ካላላችሁ
በቀር ጸነሰችም ወለደችም አላለም አዚያው ላያ ያበቃል አራት ነጥብ። ‹ድንግል ማርያም ከክርስቶስ ውጪ ልጅ የላትም!›
ተጨማሪ ማስረጃዎች እነሆ ፡- ሲጀመር መጽሐፍ ቅደስ በአንድም ቦታ ድንግል ማርያም ከክርስቶስ ውጪ ልጅ
አላት አይልም ብሎም አያውቅም ! መጽሐፍ ቅዱስ እውነቱን እውነት ሐሰቱንም ሐሰት የሚል መጽሐፍ ስለሆነ
ያልሆነውን ሆነ አይልም የሆነውንም አይደብቅም! ወንጌልን ለዓለም የሰበኩ ቅዱሳን ሐዋርያትም ድንግል
ማርያምን ማዕከል አድርገው አስተምረዋልና ከክርስቶስ በኋላ ልጅ ወልዳ ቢሆን ኖሮ ለምን ደበቁን ? ለምሳሌ
ጌታችን ሲሰቀል በመስቀል ሥር ሆና ስማልቀሷ ፣ ለዮሐንስ ስለመሰጠቷና መንፈስ ቅዱስ በወረደ ጊዜ እርሷ
በመሃከላቸው እንደነበረች ሲጽፉ ለምን ከጌታ ሌላ ልጅ መውለዷን አልነገሩንም? ለምንስ ደበቁን? አሁንም በዚህ
አቋም ለጸናችሁ መናፍቃን አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ እውን መለኮት ባደረበት ማኅጸን ሰው ያድርበት ይሆን?
አዎ የምትል ከሆነ ያንተ ኢየሱስ ፍጡር እና ተራ ሰው እንጂ አምላክ አይደለም !!! የኛ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ
ባደረበት ማኅጸን ግን ማንም….. ማንም…. ማንም….  አያድርበትም። በድጋሚ ልምጣባችሁ እውን ድንግል 
ማርያም ከክርስቶስ ውጪ ሌላ ልጅ ያስፈልጋት ይሆን ከዚያ በኋላ ብትወልድም ሰው አምላክ አይሆን? አበው እንኳ ‹‹ሃምሳ
ቢወለድ …… ከተባረከ ይበቃል አንዱ›› ብለው የለ ታዲያ ድንግል ማርያም ከአንዱ ከብሩክ ልጇ ከክርስቶስ ሌላ
ምን ሽታ ትወልድ ይሆን ? መጽሐፍ ቅዱስ ዘለዓለማዊ ድንግልናዋን እንዴት እንዳስቀመጠ ተመልከት ፡-
 1) “እቴ ሙሽራዬ የተቆለፈች ገነት የተዘጋ ምንጭ የታተመች ፈሳሽ ናት” መኃ.ዘሰ 4÷12 (ዳዊት የመንፈስ
አባቷ ነውና ልጄ ይላት ነበር ሰሎሞን ደግሞ የዳዊት ልጅ ነውና እህቴ ያላታል የመንፈስ ወንድሟ ነውና)
2) “የምስራቁም በር ለዘለዓለም ተዘግቶ ይኖራል ሰውም አይገባበትም እግዚአብሔር አንዴ ገብቶበታልና” .ሕዝ
44÷1-2 (ምሥራቅ የተሰኘች ድንግል ማርያም ናት በእርሷ ሰማይነት ክርስቶስ ፀሐይ ሆኖ ወጥቷልና) ይህን ቃል
ለቤተ መቅደስ ነው ብለህ የምትከራከር ካለህ ‹‹ለዘለዓለም የተዘጋ ቤ/መ በዚህ ምድር ላይ የለምና
እራስህን አታታል! 3) “ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆንልኛል” ሉቃ 1÷34 (ይህ የእመቤታችን አስደናቂ ንግግር ለወደፊትም
እራሷን አቅባ እንደምትኖር የሚያረጋግጥ ቃል ነው። አንድም ኃላፊ ግስ ነው የወደፊት ዓላማዋንም
ያረጋግጣል) ‹ እርሱ ብቻ ልጇ እንደሆነ የክርስቶስ ምስክርነት › 1ኛ) አይሁድ በምቀኝነት ክርስቶስን ሲሰቅሉት ከእግረ
መስቀሉ ሥር የተገኘው ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስና ድንግል ማርያም ብቻ ነበሩ። እመቤታችን ሌሎች ልጆች
ቢኖሯት ኖሮ ‹‹ እነሆ ልጅሽ ›› ብሎ ዮሐንስን ጠብቃት ባላለውም ነበር። በዚህ ላይ ዮሐንስም እኮ እናት
ነበረችው። ነገር ግን ድንግል ማርያም አንድያ ልጇ በመሆኑ ጌታችን ለዮሐንስ አደራ ሰጥቶአታል።
2ኛ) የኢየሩሳሌም ሴቶች ጌታችን መስቀል ተሸክሞ ሲያልፍ ተመልክተው አዝነው ሲያለቅሱ ‹‹ ለራሳችሁ እና
ለልጆቻችሁ አልቅሱ ›› ተብለዋል እመቤታችንም መስቀል ሥር ሆና ታለቅስ ነበር ታዲያ ለምን ‹‹ ሄደሽ ለልጆችሽ
አልቅሺ አላላትም ? ‹ትልቅ እርምት የሚሻው የመናፍቃን ስህተት› ‹ ይህ የጸራቢ ልጅ አይደለምን? እናቱስ ማርያም ትባል
የለምን? ወንድሞቹስ ያዕቆብና ዮሳ ስምዖንም ይሁዳም አይደሉምን? እኅቶቹስ ሁሉ በእኛ ዘንድ ያሉ አይደሉምን?
እንኪያስ ይህን ሁሉ ከወዴት አገኘው? ተሰናከሉበትም››(ማቴ13÷56) የሚለውን ቃል ለማን እንደተነገረ እንኳ
ሳያስተውሉ ጭራሽ ድንግል ማርያም ከክርስቶስ ሌላ ልጅ እንዳላት አድርገው ይህን አሳፋሪ ቃል ሲጠቀሙበት አይቼ
እኔም አፈርኩበት !!! የዚህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል ዓላማ አይሁድ ክርስቶስን ወንድሞች አሉት ፤ዮሴፍ ከሟች
ሚስቱ የወለዳቸውን ሁሉ ከድንግል ማርያም ነው ብለው በማሰባቸው ወይም በመናገራቸው ተሰናከሉ(ተሳሳቱ)
ማለት ነው። ታዲያ እነርሱ ክርስቶስ የዮሴፍ ልጅ ነው ፤ድንግል ማርያምም ሌሎች ልጆች አሏት ብለው በማሰባቸው
ተሳሳቱ ከተባለ ለምን አንተ ደግመህ ትሰናከላለህ? ይህን ስህተታቸውን ሲያስረግጥ ትንሽ ወረድ ብሎ ‹በአለማመናቸውም
 ምክንያት በዚያ ብዙ ተአምራት አላደረገም › ይላል ። ‹ስለ ዘለዓለማዊ ድንግልናዋ ማጠቃለያ› እመቤታችን እንደማንኛውም
 ሴት አይደለችም! ክርስቶስን የጸነሰችው ቅዱስ ገብርኤል መጥቶ ሲያበሥራት ነው ፡፡ ‹ወንድ ስለማላውቅ ይህ 
እንዴት ይሆንልኛል › በማለት እንደተናገረችው እንደሌሎች ሴቶች በዘር በሩካቤ አይደለምና ነው። ቅድስት
ኤልሳቤጥም ‹‹አንቺ ከሴቶች ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ ›› (ሉቃ 13÷9) በማለት እንደተናገረችው። ቅዱስ ዳዊትም
‹‹ነኪር ነገሩ በእንቲአኪ ኦ ሀገረ እግዚአብሔር›› (የእግዚአብሔር ከተማ ሆይ ባንቺ የተደረገው ምንኛ ድንቅ ነው)
 አንዳለ በእመቤታችን የተደረገው ልዩ ነው። ለዚህ ዘለዓለማዊ ድንግልናዋ አንክሮ(ምሥጋና) ይገባል::
አሜን

ወስብሀት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን-ይቆየን


No comments:

Post a Comment