Thursday, November 12, 2020

ሐኪሙ ወንጌላዊ(ቅዱስ ሉቃስ)

================
ሐኪሙ ወንጌላዊ በማለት ሊቃውንት የሚጠሩት ቅዱስ ሉቃስ ነው። ቅዱስ ሉቃስ ሀገሩ አንጾኪያ ነው፡፡ አስቀድሞ ከ፸፪/72ቱ አርድእት ወገን የተቆጠረ ሲሆን ከበዓለ ሃምሳ በኋላ ወደ አንጾኪያ ወርዶ ወንጌልን ሰብኳል ከሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎሰ ጋር የተገናኘውም በዚሁ ነው፡፡ ቅዱስ ሉቃስ የሕክምና ሙያ የነበረው ሲሆን ያጠናውም ከአቴናና እስክንድርያ ሊቃውንት መሆኑ ታውቋል፡፡ ከዚህ ሙያው በተጨማሪ የሥነ-ሥዕል ችሎታም እንደነበረው ይነገራል፡፡ይህንን ችሎታውንም በወንጌሉና በሐዋርያት ሥራ መጽሐፉ ላይ ባለው ሥዕላዊ አገላለጥ ከማንጸባረቁም ሌላ በእጁ የተሳሉ ሥዕሎች በተለያዩ ሀገሮች ይገኛሉ፡፡
የቅዱስ ሉቃስ ስዕሎች እመቤታችን ልጇን አቅፋ ( ምስለ ፍቁር ወልዳ) የሳላቸው ሲሆኑ በኢትዮጵያ በተድባ በማርያም ፤ በደብረ ዘመዶ ፤ በዋሸራ ፤በጅበላ ሲገኙ ተመሳሳዩም በስፔን ቅድስት ማርያም ካቴድራል እንደሚገኝ ይነገራል ፡፡
ቅዱስ ሉቃሰ የድንግልና ሕይወት የነበረው ወንጌላዊ ነው፡፡ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በሰማዕትነት እስካረፈበት ጊዜ ድረስ ደቀ መዝሙር በመሆን አገልግሎታል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በ67 ዓ.ም. በሮማ በሰማዕትነት ሲያርፍ ሉቃስ ወደ ድልማጥያ መጣ፡፡ በዚያም በሽምግልና ዘመኑ ወንጌልን በመስበክ ላይ እያለ አይሁድና ካህናተ ጣዖት ተባብረው ትምህርቱን በመቃወም ተነሡበት፡፡ መስከረም 20 ቀን 68 ዓ.ም. አይሁድና አረማውያን ጉባዔ አድርገው ነገር በመሥራት ለሮም ንጉሥ ከሰሱት፡፡ በዚያን ዘመን ኔሮን እብደቱ ያየለበት ጊዜ በመሆኑ የቅዱስ ሉቃስን ከሮሜ ማምለጥና ወደ ድልማጥያ መምጣት ሲሰማ 200 ወታደሮችን ላከበት ቅዱስ ሉቃስም የሰዎችን መምጣት በመንፈስ ቅዱስ ተረድቶ ያሰተምራቸው የነበሩትን ምእመናን ወደየቤታቸው ላከና በድልማጥያ አጠገብ
ወደሚገኘው ባሕር ተጠጋ፡፡
በባሕሩ አጠገብ አንድ ዓሣ አስጋሪ ቆሟል፡፡ ቅዱስ ሉቃስ ወደ ዓሣ አስጋሪው ቀረበና ጨዋታ ጀመሩ፡፡ ቀስ በቀስም ወንጌል ይሰብክለት ጀመር፡፡ ዓሣ አስጋሪውም ቅዱስ ሉቃሰ የሚነግረውን ሁሉ ሥራውን አቁሞ በደስታ ያዳምጠው ነበር፡፡ በመጨረሻ እንካ እነዚህ የሕወትን መገንድ ይመሩሃል አለና የያዛቸውን መጻሕፍት ሁሉ ሰጠው፡፡ ያም ዓሣ አስጋሪ እጅግ ተደስቶ ዕቃ በሚያስቀምጥበት ቦታ በክብር አኖራቸው፡፡
ቅዱስ ሉቃሰ መጽሐፉን ሰጥቶት ዘወር ሲል የኔሮን ወታደሮች ተረባረቡና ያዙት፡፡ ከዚያም ወደሮም ተወሰደና የኔሮን ፍርድ ቤት ቀረበ፡፡ ጥቅምት 22 ቀን አንገቱን ተሠይፎ በአሸዋ በተሞላ ከረጢት አስገብተው በተወለደ በ84 ዓመቱ ወደ ባሕር ወረወሩት፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍቱን ግን ያ ዓሣ አስጋሪ ለዚህ ትውልድ አትርፏቸዋል፡፡
የቅዱስ ሉቃስ ወንጌል ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃሰ በዓይኑ የተመለከተውን ከሐዋርያትም የሰማውን ጠንቅቆ በማሰብ 24 ምዕራፍ፣1149 ቁጥሮች የያዘ ወንጌል አበርክቶልናል፡፡ ወንጌሉን የጻፈው ከ58-60 ዓ.ም. ባው ጊዜ ውስጥ ቅዱስ ጳውሎስ በእሥር ላይ ባገኘው ዕረፍት መሆኑ ይነገራል፡፡ ወንጌሉ የተጻፈው በግሪክ ቋንቋ ነው።
የሐዋርያት ሥራ የሐዋርያት ሥራን የጻፈው ቅዱስ ሉቃስ ነው፡፡ ቅዱስ ሉቃስ በወንጌሉ ከ1-34 ዓ.ም. ያለውን የክርስትና ታሪክ ካሰፈረ በኋላ ቀጣዩንና ከ34-58 ዓ.ም. ያለውን ደግሞ
በሐዋርያት ሥራ መጽሐፉ ላይ ጽፏል፡፡
ከምዕራፍ 1-8 ያለው የቤተ ክርስቲያንን ታሪክ በኢየሩሳሌም የሚያሳይ ሲሆን ከምዕራፍ 9-12 ያለው ታሪክ ደግሞ በእስጢፋኖስ ሰማኝትነት በተነሣው ስደት የተበተኑት የኢየሩሳሌም ቤተክርስቲያን ልጆች በአካባቢው ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉዞ የሚያሳይ ነው፡፡ ከምዕራፍ 13
ጀምሮ እስከ ፍጻሜው ደግሞ የቅዱስ ጳውሎስን ጉዞዎች ተከትሎ የጻፈውና ክርስተና በታናሿ እኪያር በአውሮፓ እንዴት እንደተሰበከ የሚያሳየው ክፍል ነው፡፡ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በመጀመሪያው የሮም እሥራቱ በቁም እሥር ላይ ሆኖ ወንጌልን እንዲሰብክ ተፈቅዶለት በነበረ ሰዓት በሮም ከሚኖሩ አይሁድ ጋር በ58 ዓ.ም ስለሃይማኖት ያደረገውን ውይይት ተርኮ ያጠናቅቃል፡፡ ወንጌላዊው ሉቃስ የሐዋርያት ሥራን የጻፈው በ58/በ59 ዓ.ም/ ነው፡፡
ጥቅምት ፳፪ ቀን የበዓሉ መታሰቢያ ነው።
የቅዱሱ በረከት በእጥፍ ይደርብን።


No comments:

Post a Comment