Thursday, November 12, 2020

ዳግሚት ሔዋን (አዲሲቱዋ ሔዋን )




ልዑለ ባሕርይ እግዚአብሔር << በአንተና በሴቲቱ በዘርህና በዘርዋ መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ : እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል አንተም ሰኮናውን ትነክሳለህ :: >> ( ዘፍ ፫፥፲፭ ) ሲል የተናገረው ይህ ተስፋ ትንቢት መፍቀሬ ስብእ የሆነው አምላክ ለሰው ልጆች ያለውን አምላካዊ የአድኅኖት ዕቅድና በጎ ፈቃድ የሚገልጥ መሪ የተስፋ ቃል ነው :: #በመሆኑም ይህ አምላካዊ ተስፋ ትንቢት በምክረ ከይሲ ተታለው በኃጢአት ተሰናክለው በመንጸፈ ደይን ወድቀው በእግረ አጋንንት ይጠቀጠቁ ለነበሩት ለአባታችን አዳምና ለእናታችን ሔዋን እንዲሁም ለልጆቻቸው ሁሉ የተሰጠ የመጀመሪያ አምላካዊ የድህነት ተስፋ ነው :: ስለሆነም መጽሐፍ <<ተፈጸመ ተስፋ አበው በማርያም ድንግል ወበቀራዮ ተተክለ መድኃኒት መስቀል ፤ የቅዱሳን አበው ተስፋ ድኅነት በቅድስት ድንግል ማርያም ተፈጸመ : የድኅነተ ዓለም ሥራ የተፈጸመበት መድኃኒት መስቀልም በቀራንዮ ተተከለ >> እንዳለው ወላዲተ አምላክ የዚህ ቃለ ትንቢት ፍጻሜ መሠረት መሆኑዋን የመለክቱዋል :: ከላይ የተጠቀሰው ምስጢረ ድኅነተ አለም ፣ቃለ ትንቢት ለጊዜው በቀዳሚነት ሔዋንና በጥንተ ጠላታችን በዲያቢሎስ መካከል ያለውን ጸብና ክርክር የሚያሳይ ሲሆን ፍጻሜ ምሥጢሩ ግን በዳግሚተ ሔዋን (አዲሲቱዋ ሔዋን ) በወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያምና ምክንያተ ስህተት በሆነው በሰይጣን መካከል የሚኖረውን ጠላትነት የሚገልጥ ነው :: (ራእ፲፪፥፩-፲፯) ከዚህም ሌላ የሴቲቱ (የድንግል ማርያም ) ዘር በሆነው በአምላካችን በመድኃኒታችን በፈጣሪያችን በኢየሱስ ክርስቶስና በሠራዊተ አጋንንት መካከል የሚኖረውን ጠላትነትም ያስረዳል :: ይህም ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት <<አንተም የዘንዶውን ራሶች ቀጠቀጥህ >> (መዝ ፸፫፥፲፬) ባለው መሠረት የድንግል ማርያም ልጅ መድኅነ ዓለም ክርስቶስ ጥንተ ጠላታችን የሆነውን የዲያቢሎስን ራስ በመስቀል ላይ ቀጥቅጧል :: በአንጻሩ ደግሞ << እጆቼንና እግሮቼን ቸነከሩኝ >>(መዝ ፳፩፥፲፮)ተብሎ እንደተጻፈ ጠላት ዲያቢሎስ በአይሁድ ልቡና አድሮ የአምላካችን የመድኃኒታችን የፈጣሪያችንን ቅዱሳት እግሮች በቀኖት አስቸንክሯል (ዮሐ ፲፱፥፳፫):: ታላቁ ሐዋርያ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስም ይህንን ድንቅ ምስጢረ ድኅነት አስመልክቶ ሲናገር <<ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ እግዚአብሔር ልጁን ላከ ከሴትም ተወለደ :: እንደ ልጆች እንሆን ዘንድ ከሕግ በታች ያሉትን ይዋጅ ዘንድ >> (ገላ፬፥፬-፭) በማለት መስክሯል :: በዚህም ሐዋርያዊ ቃል መሠረት ከላይ የገለጽነው የድኅነተ ዓለም ተስፋ በቅድስት ድንግል ማርያም እንደተፈጸመ ልብ ይሏል :: ዳግመኛም በቅዱስ ወንጌል እንደተጻፈው አምላካችን ጌታችን መድኃኒታችን ፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ እናቱ ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያምን የመጀመሪያውን ተአምር ባደረገበት በገሊላ ቃና ሠርግ ቤት በ(ዮሐ፪፥፬ 4) እንዲሁም የድኅነተ ዓለም ሥራን በፈጸመበት በቀራንዮ መስቀል ላይ (ዮሐ፲፱፥፳፮) "" አንቺ ሴት "" ሲል መጥራቱ አስቀድሞ ለሰው ልጆች የሰጠው የድህነት ተስፋ በእርዋ በኩል መፈጸሙን በምሥጢር ያጠይቃል :: በቀዳሚት ሔዋንና በዳግሚት ሔዋን በእመቤታችን መካከል ያለውን ምሥጢራዊ ንጽጽር በየዘመኑ የተነሡ የተለያዩ አበው ሊቃውንት መተርጉማን አምልተውና አስፍተው ገልጸዋል :: ይህውም ቀዳሚት ሔዋን ለፈቃደ እግዚአብሔር ባለመታዘዙዋ ምክንያት በመላው የሰው ዘር ላይ መርገምንና ሞትን አምጥታለች :: በአንጻሩ ደግሞ ዳግሚት ሔዋን የተባለችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለፈጣሪዋ ፈቃድ በመታመኑዋና በመታዘዙዋ ምክንያት በመርገምና በሞት ጥላ ሥር ወድቆ ለነበረው ዓለም በረከትንና ሕይወትን አስገኝታለች :: ይህንን አስመልክቶ ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴ ሲናገር "" በእንተ ሔዋን ተዐጽወ ኖኅተ ገነት ወበእንተ ማርያም ድንግል ተርኅወ ለነ ዳግመ : በቀዳሚት ሔዋን ምክንያት የገነት ደጃፍ ተዘጋብን ዳግመኛም ስለ ዳግሚት ሔዋን ስለ ድንግል ማርያም ተከፈተልን "" በማለት አስገንባል :: ከዚህም ሌላ ሰፊና ጥልቅ በሆነው የነገረ ማርያም አስተምህሮው የዜና አበው ሊቃውንት "" የነገረ ማርያም አባት "" እያሉ የሚጠሩት ታላቁ የቤተክርስቲያን ሊቅ ቅዱስ ሔኔሬዎስ ከላይ የገለጥነውን ኃይለ ቃል መሠረት በማድረግ እመቤታችን "" የሔዋን ጠበቃ አለኝታ "" ብሏታል :: በዜና አበው ክፍለ ትምህርት እንደሚታወቀው ይህ አባት የነበረበት ዘመን "" የነገረ ማርያም ዘመነ ልደት "" በመባል ይታወቃል ::
#እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለነገር ድኅነት መሠረት መሆኗን በመግለጥ የተአምሯ መጽሐፍ "" እግዝእትነ ማርያም ነበረት እምቅድመ ዓለም በኅሊና አምላክ "" ይላል :: ከዚህም ኃይለ ቃል ድኅነተ ሰብእ የሆነው እግዚአብሔር አምላክ አስቀድሞ የፈቀደውና ያሰበው የቸርነቱና የመግቦቱ ሥራ መሆኑን እንረዳለን : እንገነዘባለን :: ከዚህም ጋር ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ "" ወበእንተ ዝንቱ አስተርእየ ወልደ እግዚአብሔር ከመ ይስዐር ግብሮ ለጋኔን : ስለዚህ የዲያቢሎስን ሥራ እንዲያፈርስ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ "" (፩ኛ ዮሐ ፫፥፰) እንደመሰከረው ጥንተ ጠላታችን የሆነው ዳያቢሎስ በሥጋ ከይሲ ተሠውሮ አዳምንና ሔዋንን እንዳሳተ (ዘፍ ፫፥ ፩-፲፬) አካላዊ ቃል አምላካችን ፈጣሪያችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በሥጋ ብእሲ ተሠውሮ ወደ ቀደመው ጸግና ክብር መልሷቸዋል :: ይህንን ምስጢር ሊቃውንተ ቤተክርስቲና አሞንዮስና አውሳብዮስ በመቅደመ ወንጌል ሲገልጡ "" ወበከመ ተኃብእ ሰይጣን በጉሕሎቱ ውስተ ሥጋ ከይሲ ከማሁ ኮነ ድኅነትነ በሠውሮተ ቃለ እግዚአብሔር በዘመድነ :ሰይጣን በሥጋ ከይሲ ተሰውሮ አዳምን እንዳሳተው ጌታችን መድኃኒታችን ፈጣሪያችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስም በስጋ ብእሲ ተሰውሮ መጥቶ ዓለምን አዳነ "" በማለት ተናግረዋል :: በዚህም ትርጉዋሜ ምስጢር መሠረት የሰው ልጅ በምክረ ከይሲ ተታሎ ሕገ እግዚአብሔርን አፈረሰ በሀጢያቱም ምክንያት ከፈጣሪው አንድነት ተለየ ሲባል በአካለ ተደልሎ በልሳነ ከይሲ ተታሎ መሳቱን መናገር ነው :: ስለሆነም ጥንተ ጠላታችን ዲያቢሎስ አካለ ከይሲን መሰወሪያ ልሳነ ከይሲን መናገሪያ አድርጎ በማሳቱ በማኅደሩ ኃዳሪውን መናገሩ እንጂ ለሰው ልጅ ስሕተት ምንጩና መሠረቱ ራሱ ዲያቢሎስ መሆኑን መረዳት ያሻል ::
#ቤዛዊት ዓለም ድንግል ማርያም በዘመነ ብሉይ በተለአየ ኅብረ አምሳል መገለጧና በብዙ ዓይነት ኅብረ ትንቢት መነገሯም በነገረ ድኅነት ውስጥ ያላትን ሰፊ ድርሻ በጥልቀት ያስረዳል :: በዚህም መሠረት የነገረ ማርያም ትምህርት ከነገረ ድኅነት ትምህርት ጋር የተያያዘ ጥልቅ ምሥጢር እንዳለው ልብ ይሏል :: የመጋቤ ሐዲስ የቅዱስ ገብርኤል ዜና ብሥራትና የእመቤታችን ተአምኖና ተአዛዚተ እግዚአብሔር መሆን የመሲሕ ክርስቶስን ወደዚህ ዓለም መምጣትና የአዲስ ኪዳንን መጀመር ያበሥራል :: በአጠቃላይ ይህንን ታላቅና ድንቅ ምስጢር በተመለከት አራቱ ወንጌላውያን ይልቁንም ደግሞ ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ የእመቤታችንን ሁለንተናዊ ሕይወት በመግለጥ በልዑል እግዚአብሕሄር ፊት ያላትን ክብርና የባለሟልነት ሞገስ እንዲሁም ከመልአከ ብሥራቷ ከቅዱስ ገብርኤል ጋር ያደረገችውን ቃለ ምልልስ በሰፊው ተናግሮላታል ::
#በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የነገረ ማርያም አስተምህሮ አምላካዊ የድኅነት ዓለም ጉዞ በማህጸነ ድንግል እንዲጀምር ምክያትና መሠረት የሆነው የመልአከ ሰላም የቅዱስ ገብርኤል ዜና ብሥራት አስቀድሞ የሰው ልጆች በኃጢያት የወደቁበትን መርገምና ሞት ወደ ዓለም የገባበትን የመልአክ ጽልመት የዲያቢሎስን ተንኮል የሻረና ክፉ ምክሩንም ያፈረሰ የበረከትና የሕይወት መንገድ ነው :: በመሆኑም በእመቤታችን በድንግል ማርያም አማካይነት የተፈጸመው የሥጋዌ ምሥጢር መፍቀሬ ሰብእ የሆነው ቸሩ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለውን ጥልቅ ፍቅር የገለጠበት ታላቅ የድኅነት ምሥጢር ነው :: በቅዱስ መጽሐፍ እንደተገለጸው የመጀመሪያዪቱ ሔዋን በምክረ ከይሲ ተታልላ የጠላት ዲያቢሎስን ክፉ ምክር ሰምታ በመቀበሏ ምክንያት ለሰው ልጆች ድቀት (ውድቀት ) እንዲሁም የሞት ፍርድ ምክያት ሆናለች ( ዘፍ ፫ ፥፬-፮) :: በአንጻሩ ደግሞ ዳግሚት ሔዋን የተባለችው ቅድስት ድንግል እመቤታችን በልዑል እግዚአብሔር ፊት በባለሟልነት የሚቆመውን መልአከ ሰላም ቅዱስ ገብርኤልን ቃለ ብስራት ሰምታ "" ይኩነኒ በከመ ትቤለኒ : እንደቃልህ ይሁንልኝ ይደረግልኝ "" ብላ በእምነት በመቀበሏ ምክንያት ድኅነት ሆነችን :: ይህን ቃሏን ምክንያት አድርጎም አካላዊ ቃል እግዚአብሔር ወልድ ከሥጋዋ ሥጋ :ከነፍሷ ነፍስን ነሥቶ በማኅጸኗ አደረ :: በመሆኑም ቀዳሚት ሔዋንን ምክንያተ ስሕተት : ምክንያተ ሞት በመሆኗ ሲወቅሳትና ሲከሳት የነበረው የሰው ዘር በሙሉ ምክንያተ "" ድኅነት ምክንያተ በረከት ወሕይወት የሆነች ዳግሚት ሔዋን እመቤታችንን << ብፅዕት አንቲ እንተ ተአምኒ ከመ ይከውን ቃል ዘነገሩኪ እምኅበ እግዚአብሔር ፤ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልከው ከእግዚአብሔር ዘንድ አግኝተው የነገሩሽ ቃል እንዲፈጸም የምታምኚ አንቺ በእውነት ብጸዕት ነሽ ንዕድ ክብርት ነሽ >>(ሉቃ ፩፥ ፳፰-፴፰) እያለ የሚያመሰግናት ሆኗል :: ከላይ እንደተገለጠው ወላዲተ አምላክ የቅዱስ ገብርኤልን ዜና ብሥራት ሰምታ በማመኗ ምክንያት መድኅነ ዓለም ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም ስለመጣ ብሥራተ መልአክ የብሉይ ኪዳን አምሳልና ትንቢት ፍጻሜ ወይም መደምደሚያ ሆነ :: ይህንን ታላቅና ድንቅ ሚስጢር አስመልክቶ የቤተክርስቲያናችን የነገረ ማርያም መጽሐፍ ሲናገር "" ወቅዱስ ገብርኤል በቃለ ብሥራቱ ኅተመ ትንቢትዮሙ ለነቢያት :: ገብርኤል ውእቱ ዘአፈልፈለ ስቴ ፍሥሐ ለኩሉ ዓለም ወአብጠለ እማልባበ ሰብእ ኩሉ ስቴ ኃዘን መሪር ዘየአኪ እምሕምዘ አፍሀት ዘይቀትል "" ይላል :: ይህም ማለት "" ቅዱስ ገብርኤልም በምሥራቹ ቃል የቅዱሳን ነቢያትን ትንቢት አተመ :አጸና : ፈጸመ : ዘጋ : አረጋገጠ :: ለዓለም ሁሉ የደስታ መጠጥና ምንጭን ያፈለቀ : ያስገኘ : ያመነጨ : ገዳይ ከሆነ የእባብ (የአውሬ ) መርዝም የሚከፋ መራራ የኃዘን ውኃን (መጠጥን :ምንጭን ) ከሰው ሁሉ ልቡና ያስወገደ ያራቀ ይህ ቅዱስ ገብርኤል ነው "" ማለት ነው :: በዚህም መሠረት ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ የጻፈው የነገረ ብሥራት ምሥጢር ለኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን የንገረ ሥጋዌ ትምህርት ምንጭ ለሆነው የነገረ ማርያም ትምህርት ዐቢይ መሠረት ጥሏል :: ከዚህ በተጨማሪም ብሥራተ መልአክ የሰው ልጆችን አስከፊ የኃጢያትና የመርገም ታሪክ የቀየረ ታላቅ ክስተት በመሆኑ ለቤተክርስቲያናችን ጥልቅ የነገረ ድኅነት አስተምህሮ በቂ ማስረጃና ምስክር ነው :: እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለመልአኩ ዜና ብስራት በሰጠችው ቃለ ተአምንሮ ልዑለ ባሕርይ እግዚአብሔር ከጥንት ያሰበውና የፈቀደው ያድህነተ ዓለም ሥራ እንዲፈጸምና አማናዊ እንዲሆን አድርጋለች :: ይህም ወላዲተ አምላክ በነገረ ድኅነት ውስጥ ያላትን ታላቅ ሱታፌ በጉልህ ያሳያል :: ይህንን ምሥጢር በተመለከተ ኢትዮጵያዊው ሊቅ በድርሰቱ "" ዘበቃለ ጉሕሎቱ ለሰይጣን መልአክ ስሕተት ተሰፍሐ ግላ ጽልመት ውስተ ኩሉ ዓለም :ወበቃለ ብሥራቱ ለገብርኤል መልአክ ጽድቅ ተሰፍሐ ብርሀነ ሕይወት ውስተ ኩሉ ዓለም : የስሕተት አለቃ በሆነው በሰይጣን የክፋትና የጥፋት ቃል ምክንያት የጨለማ መጋረጃ በዓለም ሁሉ እንደተዘረጋ : የእውነት መልአክ በሆነው በቅዱስ ገብርኤል የምሥራች ቃል ደግሞ የሕይወት ብርሀን በዓለም ሁሉ ተዘረጋ በማለት መስክሯል :: ኢትዮጵያዊው የዜማ ሊቅ ቅዱስ ያሬድም እመቤታችን በነገረ ድህነት ውስጥ ያላትን ልዩ ሥፍራ ሲናገር "" በእንተ ተሠግዎቱ ለወልደ አምላክ እምኔኪ ቀሩባነ ኮነ እምድር ውስተ አርያም :ብኪ ወበከመ ወልድኪ "" ብሏል :: የዚህ ኃይለ ቃል ትርጉዋሜ ምሥጢርም ቃለ እግዚአብሔር ወልድ ከሥጋሽ ሥጋ :ከነፍሥሽ ነፍስን ነሥቶ ካንቺ ሰው በመሆኑ ከምድር ወደ ሰማይ :ከሞት ወደ ሕይወት : ከመርገም ወደ በረከት : ከኃሳር ወደ ክብር : ከሲኦል ወደ ገነት የተሸጋገርንብሽ ማለት ነው :: ከላይ የተጠቀሰውን በቃዲምት ሔዋንና በዳግሚተ ሔዋን መካከል ያለውን ምሥጢራዊ ንጽጽር አስመልክቶ
'' ኢትዮጵያዊው ቄርሎስ ""በመባል የሚታወቀው ሊቁ ቅዱስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ሲገልጽ "" ለእመ ኃሠሥላ ለሔዋን ትረክባ በህየ እንዘ ትትፌሣሕ በወለታ ዘእምጽአት ፈውሰ ለቁስሊሀ : ለእመ ኃሠሦኮ ለአዳም ረክቦ በህየ እንዘ ይትፌሣሕ ወይገብር በዓለ ምስለ ዳግማዊ አዳም "" በማለት በንጽጽሩ ውስጥ ያለውን ጥልቅና ረቂቅ ምሥጢረ ድህነት አስተምሯል :: እንደ ሊቁ አገላለጽ ዳግሚት ሔዋን የተባለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ፍሬ ሕይወት ወመድኃኒት የሆነው ጌታ የተገኘባት አማናዊት ዕጸ ሕይወት በመሆኗ የዕጸ በለስን ፍሬ በልታ ሞትን ላመጣችብን ለቀዳሚቷ ሔዋን ካሣ ናት :: ምክንያቱም ከዳግሚት ሔዋን ከድንግል ማርያም የተወለደው የማኅጸኗ ፍሬ ጌታችን መድኃኒታችን አምላካችን ፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ የሚያርቅ :በረከተ ሥጋ :በረከተ ነፍስን የሚያድል ሕይወተ ሥጋን ሕይወተ ነፍስን የሚሰጥ : ቀዳሴ ሥጋ ወነፍስ ወመንፈስ የሆነ ቡሩክ አምላክ ነውና ::
ወስብሀት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን ::


No comments:

Post a Comment