Thursday, November 12, 2020

 እኔ የምመርጠው ሳይሆን እግዚአብሔር የመረጠው ይሁን

በክርስቶስ የተወደድሽ እህቴ ሆይ መልካም የትዳር ሰው ትፈልጊያለሽ እንግዲያው ሀብትና ገንዘብ ያለው፣ውጫዊ መልኩ ቆንጆ የሆነ ፣ተክለ ስውነቱ ያማረ፣ወይም ሀብታም ፣የተማረ ድልቅቅ አርጎ የሚያኖርሽ አይሁን ምርጫሽ ይልቁንስ እግዚአብሔር ን የሚፈራ ሰውን የሚያከብር ቢሆን ይሻላል።
ምክምያቱም በጥንተ ፍጥረትም ሆነ በሐዲስ ተፈጥሮ ትዳርን የመሠረተ ጋብቻን ያጸና እግዚአብሔር ነው። (ዘፍ2፣18ና ዮሐ2፣1)
ትዳር በሀብት ብዛት የማትወሰን በመልክ ማማር የማትመካ ድንቅ የሕይወት መንገድ የእግዚአብሔር ስጦታ ናት ።
እህቴ ሆይ ! መልኩ ሳይሆን፤ስብእናው ቆንጆ የሆነውን፣ ልብሱ ሳይሆን ልቡ ንፁህ የሆነውን መሻት ነው።
ንፁህ የሆነውን የሕይወት አጋርሽን ከፈለግሽ የምትወጂውን ወንድ ከማንም ጋር አታወዳድሪው። ሃይማኖቱን ያጸና ምግባሩን ያቀና ባል እንዲሆን አስተምሪው።


በትዳርሽ ደስታ እንዲኖርሽ ከፈለግሽ ሕይወትሽን ከማንም ጋር አታወዳድሪው። ባልሽ ማለት የአባትሽ ምትክ ማለት ነው።
ተንከባከቢው እንጂ አትጨቃጨቂው ።ባልሽ የደስታ ምንጭሽ ነው። ከእቅፉ ውስጥ ገብተሽ ሌላ አለም ውስጥ የገባሽ እስኪመስልሽ የሚያስደስትሽ ባልሽ ነው።
ያንቺ ባል ላንች ውብና ቆንጆ ንጉስሽ ነው። አክብሪው በደካማ ጎኑ ገብተሽ አበርችው ኃይል ሁኚው፤ አጠንክሪው።
ከተሳሳተ አስርጂው አርሚው ደስታን ስጪው ፤ብርታት ሁኚው። ያኔ የሕይወት ጣእሙን ታውቂያለሽና።
“ለሁሉም በአምላኩ የሚፀና ወንድ ፈጣሪውን የሚፈራ ትዳሩን ያከብራልና።”
በክርስቶስ የተወደድክ ወንድሜ ሆይ መልክ፣ውጫዊ ውበት ተክለ ሰውነት ትዳር አሆንም፣ ቤትንም አያቆመውም። ወዳጄ ሆይ ልብ በል በጎ ስጦታ ሁሉ ከላይ ከሰማይ ነውና እግዚአብሔርን ደጅ ጥና ተንበርክከህ ጠይቀው። አስተውል ትዳር ማለት የሕይወትን ጣዕም የምታውቅበት የምትደጋገፍበት በሳል የምትሆንበት አባት የምትሆንበት ከብቸኛነት ወጥተህ ሁለተኛ እናት የምታገኛበት፣ ሃሳብህን የምትጋራልህ ፣ መፍትሄ የምትስጥህ የሕይወትህ ማጣፈጫ ደስታን የምትሰጥህ ሴት ከፈለክ መልኳን ሳይሆን ከአስተሳሰቧ፣ ከአለባበሷ ሳይሆን ፈጣሪ ፈሪነቷ ይሁን ምርጫህ።
በክፉው ዘመን ፈጣሪዋን የምትፈራ ሴት ማግኘት መታደል ነውና። መልካም ና እግዚአብሔርን የምትፈራ ሴት የምትፈተነው በክፉው ዘመን ነውና በታመምክ ጊዜ አልጋህን የምታነጥፍልህ ጎንበስ ቀና ብላ የምታስታምምህ፣ በተበሳጨህ ጊዜ የምትታገስህ፣ በሐዘንህ የምታዝን በደስታህ የምትደሰት በመከራህና ገንዘብ በሌለህ ጊዜ በጽናት አብራህ የምትቆይ ባንተ የምትተማመን ፣ተስፋ በቆረጥህ ሰዓት ከጎንህ ሆና የምታጽናናህ እርሷ ከላይ ከእግዚአብሔር የተሰጠች ስጦታ ናት።
ውጫዊ ውበቷን ሳይሆን ለአንተ ያላትን አመለካከት አስብ።
በእርግጥ ውጫዊ ሥነ-ምግባር ለውስጣዊ ማንነት አስተዋጽኦ ይኖረዋልና በዓለም ውስጥ እየኖርን በጥበብ መመላለስ ግድ ይለናል።
ወንድሜ ሆይ ለዘላለም አብሮህ የሚኖረው ንጹህ ልቡናዋና ስብእናዋ ለክርስቶስ ያላት ፍቅር እንጂ መልኳ አይደለም፣ ምክንያቱም እግዚአብሔር ን የምትፈራና ለአምላኳ ልዩ ፍቅር ያላት ሴት ለባሏ በፍቅር ትገዛለች።
ወዳጄ ሆይ ለሕይወትህ ስኬትን ከፈለግህ ዓይንህ ሳይሆን ልብህ ያረፈባትን ሴት አግባ።
ዓይን አዋጅ ነው እንዲሉ አበው ። ዓይን ብዙ ያምረዋልና ልብህን አዳምጥ። ያንተ ሚስት ላንተ ብቻ ቆንጆና ውብ ናት ያንተ ሚስት ላንተ ንግሥት ናት።
ባለቤትህን ከማንም ጋር አታወዳድራት። ራስን ሆኖ መኖር ጥበብ ነው።እንደ ራስ መኖር ብስለት ነው።
ሕይወትህን ከማንም ጋር አታወዳድር ( ትዳርህን) እንደራስህ ሆነህ ከኖርክ ራስህን ከማንም ጋር ሳይሆን ከራስህ ጋር ካወዳደርከው በሕይወትህ ደስተኛ ነው የምትሆነው።
መልክ ትዳር አይሆንም፣ ጎጆን አያቆምም። መጽሐፍ "መልክ ከንቱ ደም ግባትም ከንቱ እግዚአብሔርን የምትፈራ ሴት ግን የምትመሰገን ናት።" (ምሳ 30፤8) ይላልና።


No comments:

Post a Comment