Thursday, November 12, 2020

  ቁስቋም

---------

ኀዳር ፮ ቀን እመቤታችን ወደ ግብጽ አገር ተሰዳ ስትመለስ ቁስቋም በምትባል አገር ገብታ ያረፈችበት በዓል ነው፡፡ ከገነት የተሰደደውን አዳም ወደ ገነት ለመመለስ ሲል ወልደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናቱ ከድንግል ማርያም ከአረጋዊው ዮሴፍና ከሰሎሜ ጋር ወደ ግብጽ ተሰደደ፡፡ ጌታችን ከ፫ ዓመት ከ፮ ወር የግብጽ ስደት በኋላ ወደ እስራኤል እንደሚመለስ አስቀድሞ ነቢየ ልዑል ሆሴዕ በትንቢት መነጽርነት ተመልክቶ “ልጄንም ከግብጽ ጠራሁት ” ብሎ ተናግሯል ሆሴ ፲፩፥፩ በዚህም መሠረት ቅዱስ ዮሴፍ እመቤታችን ከተወዳጅ ልጇ ጋር ይዞ ወደ ገሊላ ተመልሷል ኅዳር ፮ ቀንም ሀገረ ቁስቋም ገብተው አርፈዋል።


መንበረ መንግስት ቁስቋም
ለእግዝአብሔር ካላቸው አክብሮትና ፍርሃት ለቤተ ክርስቲያንና በንግሥና ለሚያስተዳድሩት ህዝብ ካላቸው ፍቅር የተነሣ በህዝቡ “እምዬ” የሚል ስም የተሠጣቸው ንጉሠ ነገሥት አፄ ሚኒሊክ ከባለቤታቸው እቴጌ ጣይቱ ብጡል ጋር ሠራዊታቸውን አስከትለው ከእንጦጦ ቤተ መንግስታቸው ወደ ፍልውሃ እና ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ሲንቀሣቀሱ መንበረ ንግስት ቁስቋም ማርያም ቤተ ክርስቲያን በታነፀችበት ሥፍራ ላይ ድንኳናቸውን ተክለው ቆይታ ያደርጉበት ነበር፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን እረፍት ባደረጉበት ሥፍራ እንቅልፍ ሸለብ ያደርጋቸውና አንዲት እጅግ የተዋበች ሴት ልጅ አዝላ በእቴጌ ጣይቱ አማሣል “ይህንን ቦታ ልቀቁልኝ፤ ቤቴን ልስራበት !!” ስትላቸው ያያሉ፡፡ ንጉሡም ከእንቅልፋቸው በመንቃት ያዩትን ሁሉ ለባለቤታቸው ለእቴጌ ጣይቱ ብጡል ይነግሯቸዋል፤ በመቀጠልም በእቴጌ ጣይቱ አምሣል ስለታየቻቸው በስምሽ ሆስፒታል ትሰሪበት ዘንድ ፈቅጄልሻለሁ ብለው ቦታውን ለእቴጌ ጣይቱ ይሰጧቸዋል፤ ከግዜ በኃላ ንጉሠ ነገሥት አፄ ምኒሊክ ስለታመሙ እቴጌ ጣይቱ ባለቤታቸውን ማስታመም ይጀምራሉ፤ አብረዋቸው አባታቸውን ያስታምሙ ለነበሩት ንግሥተ ነገሥት ዘውዲቱ አፄ ምኒሊክ ንጉሡ ያዩትን ራዕይና ሀኪም ቤቱን ለመስራት ያለመቻላቸውን ጭምር ይነግሯቸዋል፡፡ ከጥቂት ዓመታት በኃላ ንጉሠ ነገሥት አፄ ምኒሊክ አርፈው እቴጌ ጣይቱም እንጦጦ በቤተመንግስት ተቀምጠው ከእምዬ ምኒሊክ ጋር ያሣለፉትን ህይወት በማስታወስ አዲስ አበባን ቁልቁል እየተመለከቱ “ነበር እንዲህ ቅርብ ነው ወይ አሉ ይባላል !!” ብዙም ዓመት ሳይቆዩ እቴጌም ባለቤታቸውን ተከትለው አረፉ፡፡
ልጅ ኢያሱ መሪነቱን ይዘው በነበሩበት ሠዓት ከመኳንንቱ፤ መሳፍንቱ እና ሹማምንቱ ጋር በአስተዳደር ባለመግባባታቸው ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ሚኒሊክን ንግሥናቸውን እንዲረከቡ ሲደረግ ራስ ተፈሪ መኰንን አልጋወራሽነትን እንዲረከቡ ተደረገ፡፡ የንግሥና ህይወታቸውን ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ሚኒሊክ በመባል በትረ መንግስታቸውን ከተረከቡ በኃላ እቴጌ ጣይቱ የነገሯቸውን አስታውሰው፤ ዛሬ መንበረ ንግስት ቁስቋም ማርያም ቤተ ክርስቲያን በተተከለችበት ቦታ ላይ ሆስፒታሉን ለመሥራት የመሠረት ቁፋሮ ይጀመራል፡፡ በቁፋሮውም ወቅት አስደናቂ ነገር ይከሠታል፤ ይኽውም “ታቦተ ቁስቋም የሚል ፅሑፍ ያለበት የንግሥት እሌኒ የመዳብ ወንበር እና የብረት መስቀል” ይገኛል፡፡ ንግሥት እሌኒ የአፄ ዘርዓያቆብ እህት ሲሆኑ በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበሩ ንግሥናቸውም በ1426 ዓ/ም እንደነበረ የኢትዮጵያ ታሪክ ያስረዳናል፡፡ የ492 ዓመት ዕድሜ ያለው ንብረት ከመሬት ተቀብሮ በጥበብ እግዚአብሔር ተጠብቆ ምንም ሳይበላሽ መገኘቱ ድንቅ የእግዝአብሔር ሥራን ያመላክተናል፡፡ በዚህም ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ተደንቀው ንዋየ ቅዱሣቱን መስቀል እና ሌሎቹንም የተገኙትን በታሪከ ነገሥታት በዓታ ለማርያም እንዲቀመጥ ያደርጋሉ፡፡ በቁፋሮው ግዜ በተገኘው ንዋየ ቅዱሣት ምክንያት ሥራው ወደ ተቋረጠው የሆስፒታል ቦታ በመሄድ ቤተክርስቲያን ይሠራ ዘንድ ሕዳር 6 ቀን 1918 ዓ.ም የመሠረት ድንጋይ አስቀመጡ፡፡ መቃኞውም በአስቸኳይ ይሠራ ዘንድ ለራስ ዳምጠው ትዕዛዝ ተሰጠ፡፡
በበጎ ሥራቸውና ካህናትን በመውደዳቸው ምክንያት ዘመነ ካህናት ተብሎ በሚጠራበት ግዜ በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ሚኒሊክ ዘመነ ንግሥና በግብፃዊው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ማቴዎስ ፍፃሜ ዘመን በሰሜን አዲስ አባባ ልዩ ስሙ እንጦጦ በተባለ ስፍራ በራስጌ ርዕሰ አድባራት እንጦጦ መንበረ ፀሐይ ቅድስት ማርያም እና ደብረ ኃይል ቅዱስ ዑራኤል ወቅዱስ ኤልያስ በግርጌ ሀመረ ኖህ ቅድስት ኪዳነ ምህረት እና ቀጨኔ ደብረ ሠላም መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያንን አዋሣኝ አድርጋ በመሐል ባለ ልዩ ጉብታ (መሶብ) በምትመስል በግማሽ አዲስ አባባን ሊያሣይ በሚችል ቦታ ላይ መቅደስና ቅኔ ማህሌት ያለው መቃኞ ቤተክርስቲያን ሠርተው በትእዛዙ መሠረት አሠርተው ታቦተ ቁስቋም ማርያምንና ታቦተ መድኃኔዓለም እየሱስን ሌሎችንም ንዋየ ቅዱሳት በእጨጌ ተድላና በዓቃቤ ሰዓት መምሬ አበበ ትዕዛዝ በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ሚኒሊክ ካህናትና ዲያቆናት በምዕመናንና ምዕመናት ታጅቦ ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ እና ታላላቅ ሹማምንት በተገኙበት በግብፃዊው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ማቴዎስ ባራኪነት ታቦቷ ኅዳር 6 ቀን 1919 ዓ.ም ገባች፡፡ ስያሜዋንም “መንበረ ንግሥት ቁስቋም ማርያም” ብለዋታል፤ የመጀመሪያው አስተዳዳሪም ቄስ ገበዝ ብሥራት ኃ/ማርያም ነበሩ፡፡

















No comments:

Post a Comment