Saturday, January 2, 2021

ዓለምን የቀየረው የከበረው የክርስቶስ ልደት

 


ዓለም ካስተናገደቻቸው የታላላቅ ሰዎች፣ ነገሥታት ወይም ቅዱሳን ልደት ሁሉ የከበረው ልደት የትልቁ የክርስቶስ ልደት ነው።

የሁሉም ልደት የሚከበረው በተወሰኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ብቻ ሲሆን የክርስቶስ ልደት ግን በዓለም ሁሉ ውስጥ ባሉ አማኞችም ሆነ በፈላስፎችና በኢአማንያንም ዘንድ ሳይቀር ይታሰባል ይታወቃልም ።
ይህም የሆነበት ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደበት በተወደደችው ዓመት የዓለም ሚዛን በአማንያንም በኢአማንያንም ዘንድ የተዛባበት ወቅት ስለነበረ ነው። አማኞቹ አዳማውያን በመንፈሳዊው ሕይወት በዲያብሎስ ቅኝ ግዛት ጀርባቸው ጎብጦ ነፍሳቸው ዝሎ ግዞተኞች ሆነው ነበረ።
በአንጻሩ ዓለም በተለይ ከአባታቸው አብርሃም ወገን ክርስቶስ የተወለደው ዕብራውያን በተደጋጋሚ ጦርነትና በቅኝ ግዛት ተሰቃይተው በኢኮኖሚም ቢሆን ከስረው የነበረበት ዘመን ነበረ። ጥበብ ጠፍቶ ጠቢባን ዕውቀታቸው ለዛውን ባጣበት ወቅት የአብርሃም ተስፋ እንባን የሚያብሰው መንግስትን የሚመልሰው ጥበብ ክርስቶስ ተወለደ ከሚል የምስራች በላይ ምን ደስታ ይኖራልና።
ዓለም ሁሉ ጭው ብሎ ሰዎች ለመኖር ምንም ዋስትና ባላገኙበት በዚያ ዘመን ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለም ተስፋ ሆኖ በዓለም ላይ አዲስ ብርሃን ከማብራት በላይ ምን ትልቅ ዜና ይኖራል(ሉቃ ፪፥፲-፲፪)
የዓለምን ሚዛን የሚቀይረው ወንድ ልጅ ፣ ንጉሥ ተወለደ የሚለው ቃል ሙት የሚቀሰቅስ ድምጽ ነበር። እውነትም የሚታይ ነገር ባይኖር ሁሉም ነገር ተስፋ አስቆራጭ በሆነበት ዘመን ሁሉን አዲስ የሚያደርግ ንጉሥ የመወለዱ ዜና የተቆረጠ ተስፋን የሚቀጥል ነበር።
ዛሬም ጥያቄዎች የበዙበትና ሰዎች ለመኖር ምክንያት ያጡበት ዘመን ይመስላል። ራስ ወዳድነት ነግሷል ሰው ሠራሽ ደስታዎችም የቆርቆሮ ጩኽት ሆነዋል ሰው እንደ አበደ ውሻ እርካታን አጥቶ ይቅበዘበዛል፤ ስልቹነትም ወረተኛ አድርጎታል የመኖር ቁም ነገሩ ገንዘብ ሆኗል፣ ሕግ ሚዛናዊነትን አጥቶ ድሆችን ሲገዛ ባለጠጎች ግን ይገዙታል፤ ታማኝነት ጊዜ ያለፈበት ሆኗል፤ ትልቁ ተቋም ቤተሰብና ትዳር ፈርሷል ፣ አደንዛዥ ዕፅ ና ግብረ ሰዶማዊነት ብልጭልጩ ዓለም ትውልዱን ማርከውታል። ጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎች ፣ የተፈጥሮ አደጋዎች ፣ረሃብና ቸነፈር ሥጋት ሆነው ሳለ ሌላ የጦርነት ሥጋት ደም መፋሰስና እርስ በእርስ መጨካከን ትውልዱን አስጨንቆታል፣
ሕይወት ለብዙዎች ትርጉም የለሽ ሆኗል ብዙዎች እንደ ሸማኔ መወርወሪያ ቁም ነገርና ዝቅጠት ላይ ደርሰው ይመላለሳሉ። ብቻ ምን አለፋን ትውልዱ ለወንድሜ ከማለት ይልቅ የራስ ወዳድነት አባዜ ተጸናውቶት ከእናቱ መሃረብም ቢሆን ይሰርቃል፣ የእናቴ ልጆች ተጣሉኝ እንዳለ ዮሴፍ የእናቱን ልጅ ወንድሙን በግፍ እንደ ቃኤል ይገድላል።የረጋ ምንነት ሲጠፋ ሰው ራሱን ማግኘት በፍጹም አልቻለም።
ታዲያ ይህ ሁሉ ቢሆን እንኳ በጭራሽ ቀኑ አልጨለመም፣ እንዲያውም በጨለማ ለሄደው ሕዝብ ሁሉ ብርሃን ወጣ እንጅ (ኢሳ ፱፥፪) ፣የሰው እንጅ የእግዚአብሔር መልካምነት አላለቀም ፣ የተስፋችን የክርስቶስ ልደትም ሁልጊዜ አዲስ ነው ፣ የዓለምን ሚዛን የሚቀይረው ወንድ ልጅ ተወለደ የሚለው ዜና ዛሬም ትኩስ ዜና ነው፣አለቅነት በጫንቃው ላይ የሆነ ድንቅ መካር ኃያል የሰላም አለቃ ነውና (ኢሳ ፱፥፮)
ከሁኔታዎች በላይ የሆነው ታላቁ የምስራች፣ አእምሮን ሁሉ የሚያልፈው ሰላም ክርስቶስ ወወለዱ ነው። ታላቁ ኢትዮጵያዊው ቄርሎስ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በሰዓታት ድርሰቱ " ሞገድ የማይቀርበው መርከባችን ፣ ብል የማያበላሸው መዝገባችን የእግዚአብሔር ልጅ ነው"። እንዲል ጨለማ ያላሸነፈው ለሁላችን የወጣው የጽድቅ ፀሐያችን አማኑኤል ነው(ሚል፬፥፪)። ዓለም የሌላት ያለው ጥበብ እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በፈረሰው ግርግዳ በኩል የሚቆም ጉድለታችን የሚሞላ ሙላታችን መሲሑ ነው። ዛሬ ሁላችን የሰው ልጆች በተለይ እኛ ኢትዮጵያውያን በዙሪያችን ያሉት የእኛ የሆኑት ወገኖቻችንም ሆኑ ክስተቶች ሁሉ በእጅጉ ያስፈራሉ ፣ ነገር ግን ከወደቅንበት ተነስተን በእምነት ሆነን ክርስቶስን ካየን ልደቱን ካስተዋልን በሁሉ ነገር ላይ እንደፍራለን እንጽናናለን። መድኃኔዓለም ክርስቶስ በሁሉ ነገር ላይ ስልጣን አለው። ረቂቃኑ ነፋሳትና የባህር ማዕበል እንኳ የሚታዘዙለት እርሱን ብናምነው ጌታችን ነው ፣ የማይታለፈውን እናልፋለን ፣ ክፉውን ዘመን እንሻገራለን። (ማቴ፰፥፳፯)


ከሰው ልጆች የሃይማኖት መጥፋት ዓለምን ሥርዓት የለሽ ቢያደርጋት የሕግ የበላይነት ቢጠፋ፤ መልካም ሰው በመብራት ተፈልጎ ቢታጣ ፤ ሰው ለሰው መድኃኒቱ መሆኑ ቀርቶ ፍርሃቱ ቢሆንም እንኳ በእምነት ከሆንን "መንግስትና ኃይል የእግዚአብሔር ናትና " በምንም አንፍራ አንሸበር ጸንተን እንቁም። (ማቴ፮፥፲፫) ሁኔታዎች ከምንጊዜውም በላይ አደጋ ያንዣበበት ጊዜ መሆኑን ቢያሳዩም በክርስቶስ ለሚያምን ግን በጽናት ይህን ያልፋል። በቤተክርስቲያናችን የኪዳን ጸሎት "መናፍስት ያመጡትን የጎርፉን ፈሳሽነት ፀጥ ያደረግህልን ፤ ከጥፋት አድነህ የሕይወት ወደብ የሆንከን ፣የዘላለም ድኅነት ያለበት መሸሻ የሆንከን ፣በማዕበል የተጨነቁትን የምታድን አንተ ነህ።" እንዲል ሁሉን መሻገሪያ ወደባችን ሰላማችን ክርስቶስ ነው።
የሰው ልጆች ከኖሩበት ብዙ የታሪክ ምእራፍ እንዲህ እንዳለንበት ዘመን ራሳቸውን በሥልጣኔና በቴክኖሎጅ የለወጡበት ዘመን የለም። ሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የዕውቀትና የመረጃ ዘመን ነው። አለም አንድ መንደር ሆናለች፣ አንድ ሰው ስለ ሰፈሩ ከሚያውቀው በላይ ስለ ዓለም በቂ ግንዛቤ አለው። ነገር ግን ዓለም በዘመናችን በብዙ ያልተመለሱ ጥያቄዎች ተሞልታለች። የነፍስን ባሕርይ የሚሞላ ዕውቀት እንጅ የመንፈስን ጥም የሚያረካ ነገር ጠፍቷል፣ ከትውልዱ ቅድስናና ፍቅር ርቋል (፪ጢሞ ፫፥፩-፱) ። ያለ እግዚአብሔር ጣልቃ ገብነት ሕይወት አስቸጋሪ መሆኗ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ እውን ሆኗል። እግዚአብሔር ግን ላለብን የሥጋና የነፍስ ጥያቄ ከልጁ የተሻለ መልስ አይሰጠንም። ለዛሬና ለወደፊት ጥያቄዎቻችን ሙሉ መልስ አድርጎ አንድያ ልጁን በዳግም ልደት ሰጥቶናልና ። ክርስቶስ ካለን ለጥያቄዎች ሁሉ መልስ አለን ፣ ክርስቶስ ከሌለን ሁሉ ነገር ጥያቄ ይሆንብናል።
እግዚአብሔር የሰው ልጆችን በእጆቹ አበጃጅቶ በመዳፉ ቀርጾ የፈጠረው ለውርደትና ለጥፋት ሳይሆን ለክብር ነው። ሰው ግን ክቡር ሆኖ ሳለ ክብሩን አላወቀም እንዲል ነቢዩ (መዝ፵፰፥፲፪) ከታሰበለት ደረጃ በመውረድ ማለቂያ ለሌለው ለዚህ ሁሉ ምስልቅል መዳረጉ የእምነት መጉደልና የኃጢአት ውጤት ነው። የእግዚአብሔር ሃሳብ አሰናካይነት የለውምና ዛሬ በእምነት በንስሐ ተመልሰን በልደቱ የምሥራች ሐሴት ካደረግን እርሱ ሁሉን አዲስ ሊያደርግ የታመነ ነው። (ራዕ ፳፩፥፭) በታማኝነትና በጽድቅ የተሞላች መንግስቱን ይመሠርታል (ኢሳ ፲፩፥፩-፱) ተብሎ እንደተጻፈ የጌታችን ልደት ላለፉት ፳፻ ፲፫ ዓመታት ቀስትና ጦርነትን ሽሯል፣ ፍትህን አጽንቷል፣
የታሰሩትን ፈቷል። የመጣው ለድሆች የምሥራችን ይሰብክ ዘንድ፣ልባቸው የተሰበረውን ይጠግን ዘንድ ፣ ለተማረኩት ነጻነትን ለታሰሩት መፈታትን የሚያለቅሱትንም ያጽናና ዘንድ ነውና (ኢሳ፷፩፥፩-፮)።
እንደ ንጉሥ ይነግሣልና እርሱ በፍቅር በትር የሚገዛ ገዥ ነው፣ የእግዚአብሔር መቅደስ በሰዎች መካከል ይሆን ዘንድ፣ ጸብና ክርክር እንዲወገድ የክርስቶስን የልደት ዜና እኛ በንስሐ ልደት ተወልደን እናክብር (ኢሳ፲፩፥፩-፬)።
ይህ ሲሆን ሰው ሰውን የማይጠግበው ይሆናል ፣ የታወከው የዛሬው ሥርዓት በእግዚአብሔር የሰላም ወንዝ ይለመልማል። የተበላሸው የሰው ልጆች የሞራል ልሽቀትና ግብረገብነት ይስተካከላል። በሰላም አገር በኢትዮጵያም ዘረኝነት ጦርነትና ደም መፋሰስ ያለፈ ሥርዓት ይሆናል (ኤር ፳፫፥፩-፭)። ሁላችንንም ለኃጢአት የሚፈትነን አሮጌውን ተፈጥሮ የፈሪሳውያን እርሾ በክርስቶስ ይለወጣል።(ሮሜ ፰፥፳፫፤ ፪ ቆሮ ፭፥፩፥፭) እርግማን ሁሉ በበረከት ይለወጥልናል፣ ሰላም መኖሪያችን ፍቅርም ምግባችን ይሆናል ፣ እንደ ሸማም የምንደርበው የዘወትር ኩታ ይሆንልናል።
በከብቶች በረት ራሱን ዝቅ አድርጎ በትህትና ለእኛ ክብር ከተገለጠው ጌታ ጋር በማያልፍ ሕይወት እንኖራለን።


No comments:

Post a Comment