Saturday, January 13, 2018

ነዋ በግዑ ለእግዚአብሔር ዘያአትት ወያሴስል ኃጢያተ ዓለም (እነሆ የዓለምን ኃጢያት የሚያስተሰርየው የእግዚአብሔር በግ: ዮሐ ፩፣ ፳፱)





            የጌታ መንገዱን የሚጠርግ መልዕክተኛ እንዳለው አስቀድሞ በነቢየ እግዚአብሔር በኢሳይያስ( ኢሳ ፵ ፣፫- ፭) ላይ የአዋጅ ነጋሪው ዮሐንስ ፴ ዘመን ሲሞላው ለጌታችን መንፈቅ ሲቀረው የንስሐ ስብከትን እየሰበከ የንስሐ ጥምቀትን በሳሌም አቅራቢያ በሄኖን ማዶ በዮርዳኖስ ወንዝ እያጠመቀ ሲመላለስ ዓለምን ሊቤዥ የመጣውን የቆሮንቶሱን ባህታዊ የዕለተ አርቡን ሙሽራ ዘመኑ ደርሶ ሲመጣ ተመልክቶ እንደሚዜነቱ ለራሱ ደቀመዛሙርት ነዋ በግዑ ለእግዚአብሔር ዘየአትት ኃጢያተ ዓለም ፤የእግዚአብሔር በግ ሙሽራው የዓለምን ኃጢያት የሚያስተሰርየው ፣ትውልደ አዳም ፭ሺህ ፭ መቶ ዘመን የጠበቀው መሲህ እርሱ ነው በማለት አስተዋወቃቸው።

ትህትናን ከእናትና ከአባቱ ከካህኑ ዘካርያስና ከቅድስት ኤልሳቤጥ ተምሯልና በስብከቱ እኔስ ለንስሐ በውሃ አጠምቃችኋለሁ ጫማውን እሸከም ዘንድ የማይገባኝ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ( በ፮ ወር ይቀድመዋልና) ግን ከእኔ ይልቅ ይበረታል እራሱም በመንፈስ ቅዱስ በእሳትም ያጠምቃችኋልና መንሹም በእጁ ነው ዐውድማውንም ፈጽሞ ያጠራል ስንዴውንም በጎተራው ይከልታ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል በማለት የኢየሱስ ክርስቶስን የባህርይ አምላክነት ገናንነት ይመሰክር ነበር። (ማቴ ፫ ፣፲፮-፲፯) 

እነጻ አይል ንጹህ እቀደስ አይል ቅዱስ የባህርይ አምላክ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነውር ነቀፋ ኖሮበት ሳይሆን
በጥምቀቱ ጥምቀታችን ይመሠርትልን ዘንድ "ያመነ የተጠመቀ ይድልና " (ማር፲፮ ፣፲፮)በማለት በቃሉ የተናገረውን በመዋዕለ ስብከቱም ያስተማረውን ይተገብር ዘንድ አንዲሁም ደቀመዛሙርቱን አህዛብን ሁሉ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀመዛሙርቴ አድርጒአቸው ብሎ በትዕዛዝ ያስተማረውን አርአያና ምሳሌ በመሆን በባርያው በዮሐንስ እጅ ተጠምቋል። ማቴ ፳፰ ፣፲፱
ዳግመኛም ጥምቀታችን በጥምቀቱ ለመቀደስ በፈለገ ዮርዳኖስ ተጠመቀ ። "ተጠምቀ በዮርዳኖስ በኢተጠምቀ ከመ ይኩን ንጹሐ አላ ዳእሙ ከመ የሀበነ ሱታፌ ንጽሕ፤ በዮርዳኖስ ተጠመቀ ነገር ግን ኃጢያት ኖሮበት ለመንጻት አልተጠመቀም በንጽሕ አንድ መሆንን ይሰጠን ዘንድ ነው እንጅ ተብሎ እንደተጻፈ ።(ሃይ.አበ.ቃለ ግንዘት ምዕ፻፲፯ ቁ ፭ ገጽ ፭፻፴፫)
ቅዱስ ሳዊሮስም "ወዝንቱ ዓዲ አስተርአየ በጊዜ ጥምቀቱ በማየ ዮርዳኖስ አኮ ፈቂዶ ለተጠምቆ፤ በዮርዳኖስ ውሃም በተጠመቀ ጊዜ ይህ ምስጢር ዳግመኛ ተገለጠ ጥምቀትንም ፈልጎ/ሽቶ አይደለም ጥምቀት ስለሚያስልፈገውም አልተጠመቀም አምላክ በሥጋ ተገልጦ ጥንተ ልደትን ዳግመኛ ይሰጠን ዘንድ ነው እንጅ እርሱስ ከእኛ ከሰዎች ዘንድ የሚሻው ነገር የለም።"




               
ከምንም በላይ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ የተጠመቀበት ምክንያት እርሱ ከዘመን አስቀድሞ ከባህርይ አባቱ ከአብ የተወለደ አምላክ ወልደ አምላክ ሆኖ ሳለ በዘመኑ ፍጻሜ ከድንግል ማርያም ተወልዶ በቃሉ ትምህርት እያስተማረ በእጁ ተአምራት እየፈወሰ ለድኅነተ ዓለም እንደመጣ ከምንም በላይ መርገምን ሊሽር ኃጢያትን ሊደመስስ ነውር ነቀፋን ሊያስወግድ እንደተገለጠ ቢነግራቸውም አይሁድ ግን የባህርይ አምላክነቱን የእግዚአብሔር ልጅ እግዚአብሔር መሆኑን መቀበል ስላልፈለጉ ስላላመኑበትም ፣የአብ የባህርይ ልጅነቱን ለማስመስከር የአንድነቱን የሦስትነቱን ምስጢር ለመግለጥ ነው፤ ይኽውም አብ በሰማይ የምወደው ልጄ ይህ ነው ሲል መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ በወልድ ራስ ላይ ሲቀመጥ አንድነቱ ሦስትነቱ ይገለጣልና ነው።( ማቴ ፫ ፣፲፮ -፲፯)    
          ይህንን ረቂቅ ምስጢር ኢትዮጵያዊው ቄርሎስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ "በምድር ላይ ባይመላለስ የመጠመቅን ፍለጋ ማን ያሳይ ነበር ?፤ አብስ የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት ብሎ በማን ላይ ምስክር ይሆን ነበር፣መንፈስ ቅዱስም በነጭ ርግብ አምሳል በማን ላይ ይወርድ ነበር? ፣የሥላሴ አካል ባይገለጥ በማን ስም እንጠመቅ ነበር ? ስለዚህም ደቀመዛሙርቱን ወደ ዓለም ዳርቻዎች ሄዳችሁ አስተምሩ ስታጠምቋቸውም በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቁ ብሎ አዘዘ።(ማቴ፳፰ ፣፲፱ ) አብ ማን ነው? ወልድስ ማን ነው? መንፈስ ቅዱስስ ማን ነው እንዳይሉ በፈለገ ዮርዳኖስ የሥላሴ አካላዊ ሦስትነት ተገለጠ በማለት በመጽሐፈ ምስጢር መጽሐፉ ገልጦታል።( መጽሐፈ ምስጢር ገጽ፷፱)
አንድም ወልደ እግዚአብሔር በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ እጅ የተጠመቀበት ምክንያት ትንቢቱ ይፈጸም ዘንድ ምሳሌውም ይደርስ ዘንድ ነው።
በነቢዩ በዳዊት "ባሕርኒ ርእየት ወዮርዳኖስኒ ገብአ ድኅሬሁ፤
ወአድባር አንፈርዐጹ ከመ ሐራጊት ወአውግርኒ ከመ መሓስአ አባግዕ፤ምንተ ኮንኪ ባሕር ወጒየይኪ፣ ወአንተኒ ዮርዳኖስ ዘገባእከ ድኅሬከ ፤ ባሕር አየች ሸሸችም ዮርዳኖስም ወደኋላው ተመለሰ ተራራዎች እንደኮርማዎች ኮረብታዎችም እንደ ጠቦቶች ዘለሉ አንቺ ባሕር የሸሸሽ አንቺም ዮድዳኖስ ወደ ኋላሽ የተመለሽ ምን ሆናችኋል። (መዝ ፻፲፫ ፣፫ -፭)
ተብሎ የተጻፈ ትንቢት ነበረና ።
           አንድም የዕዳ ደብዳቤያችን ለመደመሰስ ነው ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ የተጠመቀው ። ይኽውም ጥንተ ጠላታችን ዲብያሎስ አዳምና ሔዋን በደብር ቅዱስ ሳሉ መከራ አጽንቶ አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ ፣ሔዋን አመቱ ለዲያብሎስ ፤አዳም የዲያብሎስ ወንድ ባርያ፣ ሔዋን የዲያብሎስ ሴት ባርያ ብላችሁ ብትጽፉ መከራውን አቀልላችኋለሁ ብሎ አታሎ በዕብነ ሩካም /በበረድ ድንጋይ ላይ ካስፈረማቸው በኋላ አንዱን በጥልቁ በሲኦል አንዱንም በዮርዳኖስ ባሕር ጥሎት ነበርና በዮርዳኖስ ተጥሎ የነበረውን በሰውነቱ ረግጦ በአምላክነቱ አቅልጦ 
በኪደተ እግሩ ደምስሶልን ሲወጣ በሲኦል የተጣለውን ደግሞ በዕለተ አርብ በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወርዶ ነፍሳትን ሲያወጣ ደምስሶልናል። " ወደምሰሰለነ መጽሐፈ ዕዳነ በሥርዓቱ እምዕድውነ ወአእተቶ እማእከሌነ ወቀነዎ በመስቀሉ ፣ከባለጋራችን ተንኮል የተነሣ ሰው በመሆኑ የዕዳችን ደብዳቤ አጠፋልን ከመካከላችንም አራቀው በመስቀሉም ቸነከረው ።" ( ቆላ ፪፣ ፲፬) ብሎ ሐዋርያው ጳውሎስ እንደገለጸው። እንዲሁም የዮሐንስ ጥምቀት የንስሐ ጥምቀት በመሆኑ መርገመ ሥጋን መርምመ ነፍስን ለሚደመስሰውና ፍጹም ለሆነው ሊመጣ ላለው ለአማናዊው ጥምቀት ምሳሌ ነበርና ፤ክርስቶስ። ተጠምቆ መዳኛ የሆነውን የእኛን ጥምቀት ኃይል ሊሰጠውና አፍላጋትንም ሊባርክና ሊቀድስ በፈለገ ዮርዳኖስ ቆመ በባርያው በዮሐንስ እጅም ተጠመቀ።



Show more reactions

No comments:

Post a Comment