Thursday, January 11, 2018

ዘመነ አስተርዕዮ: ዝንቱ ውእቱ ወልድዬ ዘአፈቅር ዘቦቱ ሠመርኩ




     ይህንን ኃይለ ቃል እግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ በፈለገ ዮርዳኖስ ተጠምቆ ከወጣ በኋላ እንደ አባትነቱ እንደ እግዚአብሔርነቱ በሰማይ ሆኖ በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው በማለት ምስክርነቱን በሰጠበት ወቅት የተናገረው ሲሆን ፤የባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ ተቀመጠ ፣ርግብ እንቁላሏን ቢሰብሩ ከስፍራዋ ካላባረሯት ፣የፊቱን ረስታ እንደገና ሌላ እንቁላል ትጥላለች ለአዲስ ሕይወትም ትዘጋጃለች ፤መንፈስ ቅዱስም እንጅ የዋህና ኅዳጌ በቀል ስለሆነ ምን በደል ቢሰሩ በኃጢያትም ቢወድቁ ፈጽመው ካልካዱት ድረስ እንደማይተው ሲያጠይቅ ፤ ርግብ በኖህ ዘመን የጥፋት ውሃ ደረቀ ስትል የወይራ ዝንጣፊ ለምለም ይዛ እንደታየች መንፈስ ቅዱስም መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ መወገዱን በደልን ኃጢያት መደምሱን የ፭ሺህ ፭መቶ ዘመን ድርቀት መጥፋቱን የምስራች ይዞ ይገለጣልና ሲል በርግብ አምሳል ተገልጧል።


           ሥግው ቃል ክርስቶስም በጽንፈ ዮርዳኖስ በሄኖን ቆሞ ታይቷል። በምሥጢረ ሥላሴ ትምህርታችን እንደተረዳነው ከሰማይ ሆኖ የመሰከረው ክርስቶስ በቃልነት መንፈስ ቅዱስ በእስትንፋስነት ያሉበት( ሕልው የሆኑበት) አብ ነው፤ ወርዶ በእግዚአብሔር ወልድ ራስ በአምሳለ ርግብ የተቀመጠው አብ በልቡናነት ክርስቶስ በቃልነት ሕልው የሆኑበት መንፈስ ቅዱስ ነው፤ በጽንፈ ዮርዳኖስ ቆሞ የታየው አብ በልቡናነት መንፈስ ቅዱስ በእስትንፋስነት ሕልው የሆኑበት አካላዊ ቃል ክርስቶስ ነው፤ እንዲህ አድርገው የአካል ሦስትነታቸውን የፈቃድ አንድነታቸውን ለማስረዳት አብ በሰማይ ሆኖ ለባሕርይ ልጁ መሰከረ፤መንፈስ ቅዱስ በምአሳለ ርግብ ወርዶ ታየ፤ አካላዊ ቃል ክርስቶስ በጽንፈ ዮርዳኖስ ቆሞ ታየ ፤በዚህም የሥላሴ አንድነትና ሦስትነት በሚገባ ታወቀ በተጨማሪም በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው ብሎ በመመስከሩ ቅድመ አለም ከአብ ያለ እናት የተወለደው በኋለኛው ዘመን ከእመታትችን ያለ አባት በኅቱም ድንግልና የተወለደው እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ተቀዳሚና ተከታይ የሌለው አንድ አካል አንድ ባሕርይ ብቻ መሆኑ በሚገባ ተረጋግጧል ።

       ኢትዮጵያዊው ቄርሎስ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫም በሕማማት ሰላምታው ላይ "ለምህሮ ትሥልስት ሥላሴ በሌሊተ ጥምቀት ሐዲስ ዘአስተርአይክሙ በዮርዳኖስ በአምሳል ዘይሤለስ ግናይ ለክሙ" በአዲሲቱ ጥምቀት ሌሊት ሦስትነታችሁን ለማስተማር በሦስት አካላት በዮርዳኖስ የተገለጣችሁ ሥላሴ መገዛት ለእናንተ ይገባል" በማለት ገልጾታል።

እንደ ቤተክርስቲያናችን ሥርዓት ከልደተ ክርስቶስ እስከ ነነዌ ጾም መግቢያ ድረስ ያለው ጊዜ ዘመነ አስተርዕዮ ወይም የመገለጥ ዘመን እየተባለ ይጠራል። አስተርዕዮ የሚለው ቃል አስተርአየ =ታየ፣ ተገለጠ ከሚለው የግዕዝ ግስ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም መታየት ወይም መገለጥ ማለት ነው።

ዘመነ አስተርዕዮ የማይታየው የታየበት የማይዳሰሰው የተዳሰሰበት ፣ረቂቁ ግዙፍ የሆነበት ፣ሰማያት ተከፍተው ምስጢር የተገለጠበት ወቅት ነው።
በቀዳሚነት ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌሉን ሲጽፍ "እግዚአብሔር ን ያየው አንድስኳ የለም ነገር ግን በዘመኑ ፍጻሜ አንድ ልጁ ራሱ ተረከው" ዮሐ ፩ ፣፲፰ እንዲል ከሦስቱ አካል አንዱ አካል ወልደ እግዚአብሔር ሎጎስ አካላዊ ቃል በተለየ አካሉ ፀጋና እውነትን ተመልቶ በእኛ አደረ፣ከእመቤታችን ከድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነስፍን ነስቶ ሰው ሆነ (ዮሐ ፩ ፣፲፬ ፤ መዝ፹፮ ፣፭) በአጭር ቁመት በጠባብ ደረትም ተገለጠ። እምኛ ረቂቁ መለኮት ግዙፉን ሥጋ ስለተዋሐደ ዳሰስነው ጨበጥነው አየነው አብረነውም በላን ጠጣን።
         በሌላው የእግዚአብሔር የአንድነቱ የሦስት ነቱ ምስጢር ተገለጠ፤ በቅድሚያም ከሥላሴ አንዱ ወልደ እግዚአብሔር ከድንግል ማርምያ እንዲወለድ በቅዱስ ገብርኤል ከተበሠረበት ጊዜ አንስቶ ድንግል ማርያም የወልድ እናት ብቻ ሳይሆን የሥላሴ ማደሪያ ድንኳን ሆናለች ፣ለዚህም መልአኩ ሲያበስራት የልዑል ኃይል ይጸልልሻ ብሎ እግዚአብሔር አብን መንፈስ ቅዱስ ያነጻልሻ ይጠብቅሻልም ብሎ መንፈስ ቅዱስን ከአንቺ የሚወለደውም የእግዚአብሔር ልጅ እግዚአብሔር ነው ብሎ ወልደ እግዚአብሔርን በመጥቀስ አንድነታቸውን በሦስትነት ገልጧል።
እንዲሁም ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ በተጠመቀ ጊዜ ከላይ እንደለገጥነው አብ የምወደው ና በእርሱ ደስ የሚለኝ ልጄ እርሱ ነው ፣ ሲል ወልደ እግዚአብሔር በዮርዳኖስ ባህር ቆመ መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል ተገለጠ ሦስቱም በአንድነት ተገለጠ፤ አንድነቱ ሦስትነቱን ሳይጠልቀለው ፤ሦስትነቱም አንድነቱን ሳይከፍለው የተሰወረው ምስጢር ተገለጠ ፣ታየ።

No comments:

Post a Comment