Thursday, January 11, 2018

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን ልዩ የሚያደርጓት ምክንያቶች።



፩- የተመሠረተችው በሰባኪ ወይም በአሳማኝ ወይም በአስገዳጅ ወይም ጥሬ ሃብትና መልክዓ ምድርን በሚሹ ወራሪዎች አይደለም። በመንፈስ ቅዱስ እንጂ። የኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ጥምቀት በቀጥታ ከመንፈስ ቅዱስ የታዘዘ ነው። [የሐዋርያት ሥራ ፰፣ ፳]። ጃንደረባው ጥምቀትን እንደጠየቀ ሁሉ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እንዲጀመር ወደ ቅዱስ ማርቆስ መንበር የላኩ አብርሃና አጽብሃ ናቸው።
፪- አይሁድ የነበረች አንዲት አገር በመንግሥት አዋጅ ክርስቲያን የሆነች አገር ኢትዮጵያ ብቻ ስትሆን ይህን ሽግግር የፈጸመች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ናት።
፫- በአዋጅ፣ በእምቢልታና በእልልታ ኢየሱስ ክርስቶስ ንጉሠ ነገሥቴ ነው ብላ ያወጀች አገር በምድር ላይ ኢትዮጵያ ብቻ ስትሆን ይህን አዋጅ በቤተክርስቲያን ቡራኬ ያጸናች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ብቻ ናት።

፬- በምድር ላይ ካሉ ክርስቲያን ነን ከሚሉ አካሎች ተለይታ “የናንተ ክርስትና ልክ አይደለም፣ ክርስቶስ በናንተ ዘንድ የለም፣ ክርስቶስ እዚህ አለና የናንተን ተታችሁ ኑ” የሚል መመጻደቅ ያልታየባት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ብቻ ናት። በክርስቶስ እናምናለን የሚሉትን “የናንተ እምነት ልክ አይደለም” በማለት ምእመናቸውን በማስኮብለል ወይም ሌሎች ክርስቲያን ነን በሚሉ ድርጅቶች ውስጥ ሰርጎ ገቦችን በመትከል የሌሎችን ማህበሮች ለማፍረስ ተነስታ የማታውቅ፥ በበር እንጂ በመስኮት የማትገባ [ዮሐ ፲፡፩-2]የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ብቻ ናት።
፭- የጣሊያን ቅኝ ገዢ መንግሥት ኢትዮጵያውያንን ቅኝ ለመግዛት፣ ኢትዮጵያንም ለመውረስና ኃይማኖቷን ለመቀየር በመጣ ጊዜ ሁለቱንም ጊዜ በምህላና በጸሎት በእግዚአብሔር ኃይል ድል የነሳች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ናት።
፮- ምእራባውያን የተስማሙበትን የሊግ ኦፍ ኔሽንስ ሕግ ጥሰው ከጣሊያን ጋር በመዶለት ኢትዮጵያን ቅኝ ለማስገዛት የሚስጢር ውላቸውን በፈጸሙ ጊዜ፣ በከበቧትም ጊዜ፥ ጸሎቷንና ምህላዋን ሰምቶ እግዚአብሔር የተበቀለላት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ናት። ኢትዮጵያን ቅኝ ለማስገዛት ሲዶሉቱ በቅጽበት ቅኝ ገዢ በነሱ ላይ መጣባቸው። በዚህም ምክንያት የሁለተኛው ዓለም ጦርነት ተነሳ። በጦርነቱም ምእራባውያን ወደሙ፣ ድህነትም አጠቃቸው። ቅኝ መግዛትም ተሳናቸው። በዚህም ምክንያት የምእራባውያን የቀጥታ ቅኝ አገዛዝ አከተመ። የአፍሪካና የእስያ ሰዎች ከአስደንጋጩ መከራ ከቅኝ ግዛት ነጻ ወጡ።
፯- ጌታችን መድኃኔታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጨረሻው ቀን ንግሥተ ዓዜብ በክፉው ትውልድ ላይ ትፈርዳለች አለ። [ማቴ ፲፪፣ ፵፪] የሳባ ንግሥትን ንግሥተ ዓዜብ ብሎ ጠራት። ለምን? በምድር ላይ ከኢየሩሳሌም ደቡብ የምትገኝ አገር ከኬንያ በቀር ኢትዮጵያ ብቻ ናት። ኬንያም የኢትዮጵያ አካል ነበረች። በንግሥቷ የመሰላት ያልተቋረጠ መስዋእትን ለረጂም ዘመናት ያቀረበችለት እነሆ የመድኃኔታችን ቃል ምስክር የሆነላት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ናት።

፰- የሰሎሞንን ጥበብ ሰምታ ልትፈትነው የሄድችው የሳባ ንግሥት ለኢየሩሳሌም ሌላ ደቡብ የለምና ከኢትዮጵያ ተነስታ ነው። ጠቢቡ ሰሎሞንም በመሓልየ መሓልይ “ስድሳ ንግሥታት፣ ሰማንያም ቁባቶች፡ ቁጥር የሌላቸው ቆነጃጅት አሉ። ርግቤ መደምደሚያየም አንዲት ናት።” ብሎ በደቡቧ ንግሥት ስዕል በትንቢት የመሰከረላት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ናት።
፱- ነቢዩ ዳዊትም “ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች” ብሎ በትንቢት የመሰከረላት የኢትዮጵያ ኃይማኖት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ናት። የኛን “ክርስትና ተቀበሉ” እያሉ በመጨረሻው ዘመን የሚመጡ አሳቾች ይህ ትንቢት ለኛ ነው እያሉ እንዳያታልሉ ንጉሡ ዳዊት ዐረፍተ ነገሩን የጀመረው መኳንንት ከግብጽ ይመጣሉ በሚል ጠቋሚ ምልክት በመሆኑ ትንቢቱ ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ብቻ መሆኑን ያረጋግጣል።
፲- እንደገናም ነቢዩ ዳዊት በመዝሙር ፸፱ “ከግብጽ የወይን ግንድ አመጣህ፥ አህዛብን አባረርህ፥ እሷንም ተከልህ። በፊቷም መንገድን ጠረግህ፥ ሥሮቿንም ተከልህ፥ ምድርንም ሞላች። ጥላዋ ተራሮችን ከደነ፣ ጫፎቿም እንደ እግዚአብሔር ዝግባ ሆኑ። ቅርንጫፎቿንም እስከ ባህር፥ ቡቃያዋንም እስከ ወንዙ ዘረጋች። አጥሯን ለምን አፈረስህ? መንገድ አላፊም ሁሉ ይበላታል። የበረሃ እርያ አረከሳት። የዱር አውሬም ተሰማራባት። የሃያላን አምላክ ሆይ እባክህ ተመለስ። ከሰማይ ተመልከት፥ እይም፥ ይህችንም የወይን ግንድ ይቅር በላት። በሰው ልጅ ለአንተ ያጸናኻትን ቀኝህ የተከላትን አጽንተህ አነሣሣት። በእሳት ተቃጥላለች፣ ተነቅላማለች ከፊትህ ተግሳጽም የተነሳ ይጠፋሉ። … ፊትህንም አብራ እኛም እንድናለን።” ብሎ በትንቢት ለአሁኑ ዘመን የተማጸነላት ቅድስት ቤተክርስቲያን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ናት።
፲፩- “ገና ሌሊት ሳለ ትነሣለች ለቤትዋም ሰዎች ምግባቸውን ትሰጣለች። መብራትዋ በሌሊት አይጠፋም” ተብሎ በመጽሐፈ ምሳሌ እንደተጻፈላት በዓለም ላይ ካሉ እኛም አለን ከሚሉት ሁሉ ተለይታ በሌሊት መስዋእትን የምታቀርብ፣ መብራትዋ በሌሊት የማይጠፋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ናት።
፲፪- ትርንጎዎች መዓዛን ሰጡ፤ መልካሞች ፍሬዎች ሁሉ፥ አሮጌው ከአዲሱ ጋር፥ በደጃችን አሉ፤ ውዴ ሆይ፥ ሁሉን ለአንተ ጠበቅሁልህ። ተብሎ እንደተጻፈ ብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳንን በየዘመናቸው አሟልታ ከሁሉም ተለይታ በመከር የታጨደ የተሟላና ያልጎደለ መጽሐፍ ቅዱስን ይዛ የቆየች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ብቻ ናት።
፲፫- “ለእናትዋ አንዲት ናት ለወለደቻትም የተመረጠች ናት” ተብሎ እንደተጻፈ፥ ከንግሥታት፣ ከእቁባቶችና ከቆነጃጅት ተለይታ በእግዚአብሔር የተመረጠችና የታመነች፣ እግዚአብሔር ጽላቱን ያስቀመጠባት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ብቻ ናት።
፲፬- በምድር ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የመዝሙር ኖታዎችን (ምዕራባውያን የሙዚቃ ኖታ የሚሉት) ያቀረበች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ናት። የምእራባውያን የሙዚቃ ኖታ የቀረበው ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አቅርቦት አምስት መቶ አመት በኋላ ነበር። የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ሰዎች የራሳችን የሆነ ኖታ አለን ብለው ሊመኩ የሚችሉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በእግዚአብሔር ቸርነት ባቀረበችው ኖታ ብቻ ነው።

የህብረተሰብን ቁስአካላዊ እድገት በተመለከት
፲፭- በተፈጥሮ የሚታዩ የፍጥረታት፣ የእንስሳት፣ የአእዋፍ፣ የአትክልቶች፣ የዛፎች፣ የአፈር፣ የድንጋይ የግዑዛን ሁሉ ቀለማትን የተፈጥሮ ቀለማቸው ሳይዛባ ንጥረ ነገሮችን፣ አበቦችንና ቅጠላ ቅጠሎችን በመቀመም በቀለማት፣ በቅብ እና በሰዕል ማስፈር ብዙ ጥበብን ይጠይቃል። እንዲህ አይነቱን የስዕል ጥበብ በእግዚአብሔር ቸርነት ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ያበረከተች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ናት።
፲፮- ስነ ጽሁፍ፣ ቃል አገባብ፣ ትረካ፣ የታሪክ ምዝገባ፣ የታሪክ ቅርስ አያያዝ፣ ግጥም፣ ጥልቀትና ምጥቀት ያላቸው ቅኔዎችን በእግዚአብሔር ቸርነት ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ሆነ ለዓለም ያበረከተች፣ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ አፍሪካውያንም በስነጽሁፍ ስልጣኔ ሊመኩባት የሚችሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ብቻ ናት።
፲፯- ከዓለም አገሮች ሁሉ ቀድማ ህገ መንግሥትን በእግዚአብሔር ቸርነት ያበረከተች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ናት።
፲፰- ለኢትዮጵያ ህብረተሰብ መተዳደሪያ እንዲሆን በእግዚአብሔር ቸርነት የማህበረሰብ ህግ አርቅቃ ያበረከተች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ናት።
፲፱- ኢትዮጵያውያን በየትኛውም ቦታ ሄደው በበጎ ስነምግባር እንዲታወቁ ያደረጋቸውን ግብረ ገብነት በእግዚአብሔር ቸርነት ያነጸች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ናት።
፳- ከዓለማት ሁሉ ቀድማ የሚያስደንቅ የህንጻ ኪነ ጥበብን (አርኪቴክቸርን) ከሚያስደንቅ ምህንድስና አዋህዳ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም የሚያስደንቁ ህንጻዎችን በእግዚአብሔር ቸርነት የገነባች፥ አፍሪካውያንም ሊመኩባት የሚችሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ብቻ ናት።
፳፩- ኢትዮጵያውያን የሚታወቁበትን ልዩ አለባበስ፣ ያለባበስ ስርዓት፣ የልብስ አዘገጃጀት በእግዚአብሔር ቸርነት አዘጋጅታ ያቀረበች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ናት።

፳፪- ለረጂም ዘመናት በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የሥራ መስክ የፈጠረች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ናት።
፳፫- ለረጂም ዘመናት ኢትዮጵያውያንን ማንበብ፣ መጻፍ፣ የቀን ቆጠራ፣ የዘመናት ቆጠራ፣ ሒሳብ፣ ሙያ፣ ግብረ ገብነት፣ ምስጋና፣ ቅዳሴ ወዘተ ያስተማረች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ናት።
፳፬- ለረጂም ዘመናት ምርታማነትን ከልምላሜ ጋር ጠብቃ ያቆየች አሁንም ኢትዮጵያንም ጨምሮ ዓለም በዘመናዊ ጥፋት ልምላሜዋ ሲጠወልግ ልምላሜን ከትህትና ጋር ጠብቃ ያቆየች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ናት።
፳፭- ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ሰዎችም በጠቅላላ ከውጭ ሰዎች መሳለቂያነት የሚያወጣቸውን ሊመኩበት የሚችሉ የፊደልን ስልጣኔ በእግዚአብሔር ቸርነት ያበረከተች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ናት።
፳፮- አሁን ዓለም ማድነቅ የጀመረውን በዘመን ቆጠራ የእህል ዘርን በእርሻ የማፈራረቅ ጥበብን በእግዚአብሔር ቸርነት ያበረከተች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ናት።
፳፯- አሁን በዓለም አካባቢ እስልምና ከየመን አበረከተ እየተባሉ የሚነገርላቸው ቅመማና ሌሎች ብዙ ጥበቦችን ያበረከተቻቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ስትሆን ተራኪዎች እስልምና አበረከተ የሚሉት ዐረቦች የመንን ከኢትዮጵያ በመውሰድ ክርስትናን አጥፍተው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን አስተዋጽኦ የራሳቸው አስመስለው በማቅረባቸው ነው።
፳፰- የሃገር ፍቅር ጸንቶ የሚኖረው በእግዚአብሔር ፍቅር መሆኑን በማስተማር በእግዚአብሔር ፍቅር አገርን ጠብቃ ለረጅም ጊዜ ያቆየች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ናት።
በዓለም ሌሎች ያበረከቷቸው የማህበረሰብ ስልጣኔዎች ለሰው ክብር የቀረቡ ሲሆኑ ከላይ የተጠቀሱትን ሌሎችንም ያልተጠቀሱ ማህበራዊ ስልጣኔዎች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ያበረከተችው ለእግዚአብሔር ክብር ነው።

No comments:

Post a Comment