Wednesday, January 3, 2018

የእረኞች አለቃ ልደት


           ሰው መሆን ያቃታቸውን የሰው ልጆችን ሰው ያደርግ ዘንድ የእግዚአብሔር ልጅ የሰው ልጅ ሆነ
        

 ከምስራቃዊ ኢየሩሳሌም አቅጣጫ ከዳዊት ከተማ ከቤተልሔም መንደር የብርሃን አምድ ተተከለ በእኩለ ሌሊት ድምጽ ከራማ ከኢዮር ኤረር ሰማያትን ሰንጥቆ ምድርን ያንቀጠቀጠ የዝማሬና የእልልታ ድምጽ ተሰማ በቤተልሔም ከተማ በአለቃና በነገድ ተከፍለው በጨለማ ውስጥ መንጋቸውን የሚጠብቁ እረኞችን የቀሰቀሰ የእረኞች አለቃ ልደት ፤ሌሊቱ ማለፉን ሊያበስር ብርሃን ከብርሃን ወጥቶ በእኩለ ሌሊት ጨለማውን አጠፋው ። አስቀድሞ በነቢያቱ የተናገረውን ይፈጽም ዘንድ በእንስሳት መካከል በበረት ተወለደ "እግዚኦ ሰማዕኩ ድምፀከ ወፈራህኩ ርኢኩ ፤ አቤቱ ድምፅህን ሰምቼ ፈራሁ ሥራህንም አይቼ አደነቅሁ በሁለት እንስሳት መካከል አየሁህ (ዕንባ ፫፣፪) 

በሬ የገዥውን አህያም የጌታውን ጋጣ ዐወቀ እስራኤል ግን አላወቀም ( ኢሳ ፩፣ ፫)
             ፍጥረታት አምሃቸውን አቀረቡ እስትንፋሳቸውን ገበሩ የሰማያዊው ሰራዊትም የሌሊቱን ኪዳን ሲያደርሱ ስብሃተ ነግሁን ሲያቀርቡ እረኞችም የምስራቹን ዝማሬ አስተጋቡ ስብሐት ለእግዚአብሔር በአርያም ወሰላም በምድር ስምረቱ ለሰብዕ ፤ለእግዚአብሔር በሰማይ ምስጋና ይሁን በምድርም ለሰው ልጆች ሰላም ። ይህ የዝማሬ ድምጽ የጥል ግርግዳን የከፈለ ለዘመናት በምድርና በሰማይ መካከል ተጋርዶ የነበረውንም የልዩነት መጋረጃ የቀደደ ከመሆኑም ባሻገር በዘመኑ የቤተልሄም  ምድራዊ ገዥ በሄሮድስ ቤተመንግስት ግን ፍርሃትና ጭንቀትን የፈጠረ አዲስ ክስተት ሆልኗ።
በእረኞች አለቃ ልደት በክፋት ስልጣናትና ሠራዊትም ዘንድ ሽብር ሆነ።
በጨለማ ለነበሩት እረኞች ግን ፍርሃት ርቆላቸው ሰላም በዛላቸው በእረኞች አለቃም ልደት ታላቅ ደስታ ሆነ ለሕዝብ ሁሉ የሆነውን የምስራች ቃል ሰምተው በአዋጅ አሰሙ ። በዚያች ሰዓት በዚያች ሌሊት በተወደደችው ዓመት የነቢያት ናፍቆት የአብ ቀኝ የእግዚአብሔር ክንድ ወልደ እግዚአብሔር ከብላቴናዋ ከመዝገበ ጽድቅ ከርኅርኅተ ኅሊና ከእማማ ከድንግል በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወለደ።
ከህግ በታች ያሉትን ይዋጅ ዘንድ ከህግ በታች ሆኖ ከሴት ተወለደ ፣በደይንና በድቅድቅ ጨለማ የተጣሉትን ያነሳ ዘንድ በእኩለ ሌሊት ጨለማውን ገልጦ ብርሃን ሆኖ ተወለደ ፣ሰላማችንን የነሳንን የቀደመውን እባብ ራስ ራሱን ይቀጠቅጥ ዘንድ ድንቅ መካር ኃያል የሆነው ወንድ ልጅ ተወለደ።
ለህሙማን መድኃኒት ለቁስለኞች ወጌሻ ፣በሰቆቃ ለሚያለቅሱት እንባን የሚያብስ ለተጠሙትም የማይደርቅ ምንጭ ተገኘ። (ማቴ፱፣፲፪ ፤ ሆሴ ፮ ፣፩ ፤ ኢሳ፳፭ ፣፰)
          ህፃን ተወለደልን የእኛን የሰው ልጆችን ግብርና አርአያ ነስቶ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት መገለጡን ለመግለጽ ህፃን ተወለደልን ወንድ ልጅም ተሰጠን እንዲል ልዐለ ቃ ኢሳይያስ፤ ስሙም ድንቅ መካር ኃያል አምላክ የዘላለም አባት የሰላም አለቃ እግዚአብሔር የእግዚአብሔር ልጅ የዘመኑ ፍፃሜ ሲደርስ ረቁቁ መለኮት ግዙፉን ሥጋ ተዋህዶ የማይታዬው ታዬ የማይዳሰሰው ተዳሰሰ ከእኛ ዘንድ አርአያ ግብርን ነሳ።
ሁሉ ኃጢያትን ሰርቶ ጽድቅ ልምላሜ ስለጠፋ ጽድቃችን እንደመርገም ጨርቅም በመሆኑ ከአዳም እስከ ዘካርያስ ደማቸውን የሚያፈሱ አጥንታቸውን የሚከሰክሱ መስዋዕትን የሚያቀርቡ ቢነሱም የሚቤዥ ግን አልነበረም። መርገምን የሚሽር የዕዳ በልን የሚደመስስ ትውልደ አዳምን ከተቆራኘው የኃጢያት ድርቀት በሽታ የሚፈውስ መድኃኒት በመጥፋቱ ነቢያት "መኑ ይሁበነ መድኃኒተ እምጽዮን" ብለው በሚማፀኑበት በሰቆቃ ዘመን የተገኘ መድኃኒት ፤ ልባቸው የተሰበረ የሚጠገንበት ቀኑ ሲቀርብ ጊዜው ሲደርስ ጨለማው ሊገለጥ ብርሃን ሊያሸንፍ ነጋ። ፍጥረታት ለ፭ሺህ ፭ መቶ ዘመናት ጨለማው አይሎባቸው ብርሃንህን ና ጽድቅህን ላክልን ብለው ተማጽውነ ነበርና ጨለማ ያላሸነፈው ብርሃን ስውሩ እንዲገለጽ የተደበቀው እንዲታይ እንቅፋት እንዲወገድ ኃጢያት ሁሉ ሊሰረይ በቤተልሔም መንደር በከብቶች በረት በምሽት ነጋ የዘመናት የእንባ ጎርፍ ሊርደቅ ብርሃን ወጣ።
ሰው ግን ክቡር ሆኖ ሳለ ክብሩን አላወቀም እንዲል ነቢዩ ዳዊት ፣የሰው ልጅ በአርአያ ሥላሴ ተፈጥሮ እንደሚጠፉ እንስሶች በመምሰል በአመጻ ምክንያት ጸጋውን አጥቶ ነበር።
         ሰው መሆን ያቃታቸውን የሰው ልጆችን ሰው ያደርግ ዘንድ የእግዚአብሔር ልጅ የሰው ልጅ ሆነ እንዲል ሊቁ አትናቴዎስ፤ አምላክ ራሱ ለራሱ ባዘጋጀው ማህንፀ 
ተወስኖ ማንም ባልሰራው ማንም ባልገባበት ወደፊትም ማንም ሊገባበት በማይቻለውከተማ አደረ ( ሕዝ ፵፬ ፣፩ ፤ ኢሳ ፷፣ ፲፬)
ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም በሃይማኖት አበው ምዕ ፷፮ ቁ ፳፰ ላይ "ወቀዳሚኒ ለሐኮ ለአዳም እምነ ምድር ድንግል ወካዕበ እምነ አዳም እንበለ ብዕሲት አውፅአ ብዕሲተ ከማሁ ዮም ወለደት ድንግል ሰብአ እንበለ ብእሲ ፤ቀድሞም አዳም ካልታረሰች ድንግል ምድር ፈጠረው ዳግመኛ ሔዋንን ከአዳም ያለ እናት ፈጠረ ፣ አዳም ያለ እናት ሔዋንን እንዳስገኘ እንዲሁ ዛሬ ድንግል ማርያም ክርስቶስን ያለ አባት ወለደች "በማለት በድንግልና ተጸንሶ በድንግልና መወለዱን ያመሰጥል።
ቅዱሳን አበው ሊያዩት የተመኙት ነቢያት የናፈቁት በተስፋ ሰንቀው ያመኑት ከሩቅ አይተው እነሆ በኤፍራታ ሰማነው በዱር ውስጥ አገኘነው ወደ ማደሪያው እንገባለን እግሮቹ በሚቆሙበት ሥፍራ እንሰግዳለን። (መዝ ፻፴፩፣ ፮)
አንቺ ቤተልሔም ኤፍራታ ሆይ አንቺ በይሁዳ አዕላፋት መካከል ትሆኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ ከአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘላለም የሆነ በእስራኤልም ገዥ የሚሆን ይወጣልኛል። (ሚክ ፭ ፣፪)
እነሆ ጌታ ራሱ ምልክትን ይሰጣችኋል ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች ።(ኢሳ ፯ ፣፲፬) በማለት ትንቢት የተናገሩለት ዛሬ ተገለጠ።
          ለዘመኑ ጥንት ወይም ፍፃሜ የሌለው እርሱ በበሬዎችና በላሞች መካከል በግርግም ተኛ ፣ዓለሙን ሁሉ በአንድ እጁ የያዘ እርሱ በእማማ በድንግል እቅፍ ውስጥ አደረ ሰማይና ምድርን እንደ መጎናፀፊያ ጠቅልሎ የሚያሳልፍ እርሱ በመጎናፀፊያ በጨርቅ ተጠቀለለ። ኅደረ ውስተ ቤቱ ለሌዊ ዘይጠብልሎ ለሰማይ በአጽርቅት ተጠብለለ ወተወድየ ንጉሠ ነገሥት ውስተ ጎል ፤ ባለጠጋ እርሱ ከሌዊ ወገን በተወለደች በድንግል ማህፀን አደረ ፣ሰማይን በደመና የሚሸፍን እርሱ በጨርቅ ተጠልለለ የነገሥታት ንጉሥ። በበረት ተጣለ" በማለት በሃይ. አበ ምዕ ፰ ክፍል፲፩ ቁ ፭
በማለት ገልፃታል።



ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም ዘይነብር ዲበ መንበር ልዑል ተወድየ ውስተ ጒል ወወልድ ዋህድ ዘኢይትገሠሥ ዘሀሎ እንልለ ሥጋ ተገሠ ይእዜ በለቢሰ ሥጋ ዘይመትር ማዕሰረ ኃጢያት ተጠብለለ በአጽርቅት ምንተ እብል ወምንተ እነብብ አንሰ አነክር ወእዴመም እስመ ብሉዬ መዋዕል ኮነ ህፃነ ንዑሰ ፤ በልዑል ዙፋን ላይ ተምቀጦ ያለ እርሱ በበረት ተጣለ ሥጋ ሳይሆን የነበረ የማይዳሰስ ወልድ ዋህድ ዛሬ ሥንጋ በመዋሐድ ተዳሰሰ የኃጢአት ን ማሰሪያ የሚቆርጥ እርሱ በጨርቅ ተጠቀለለ ምን እላለሁ ምንስ እናገራለሁ ከዘመን አስቀድሞ የነበረ እርሱ ትንሽ ህንፃ ሆኗልና እኔ ፈጽሜ አደንቃለሁ።( ሃይ አበ ክፍ ፷፮ ቁ ፬ )

ቅዱስ ሉቃስም ወንጌሉን ሲጽፍ ወጠብለለቶ በአጽርቅት በመጠቅለያ በጨርቅም ጠቀለለችው ብሎ ጽፏል። (ሉቃ ፪፣ ፯)
ምትሐት እንዳይደለ በእውነት ሥጋን ተዋህዶ ሰው ሆኖ እንደተወለደ ለማጠየቅ አንድም በዕለተ አርብ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ቅዱሱን ሥጋህን እንዲህ አድርገው በአዲስ ጨርቅ ጠቅልለው ይገንዙሃል ስትል ጠቀለለችው
አንድም የሐዲስ ኪዳን ካህናት ዕለት ዕለት ሥጋህን በማህፈድ ይጠቀልሉታል ስትል በጨርቅ ጠቀለለችው።
በቤተልሔም የበራውን ብርሃን የጌታን ልደት ስናስብ እርሱ በተወደደችው ዓመት ለድሆች የምስራችን ይሰብክ ዘንድ መጥቶ ዛሬ ጥቂቶች ኃያላን ደሃዎችን ያደቅቃሉ (ኢሳ ፫፣ ፲፬)
       እርሱ ልባቸው የተሰበረውን ይጠግን ዘንድ ተገልጦ ባለጊዜዎች የሆኑ ግን ቀን ስለሰጣቸው ደካሞችን የሚያደክሙ ፍርድ የሚያጓድሉ ደሃ የሚበድሉ በቁስላቸው ላይ ጥዝጣዜን የሚጨምሩ ብዙ ናቸውና ልቡና ይሰጣቸው ዘንድ እንማልዳለን።
የርኅርኅተ ልቡና የአዛኝቱ የድንግል ፍሬ በባህርያችን የተገለጠው በግዕዘ ህፃናትም ያለቀሰው የአልቃሾችን እንባ ሊያብስ ነው (ኢሳ፳፭ ፣፰) ዛሬ ብዙዎች በስስትና በስግብግብነት ፍትህን አጥፍተው ድሃውን ቀምተው በዘረኝነትና በማንአለብኝነት የአብራኩን ክፋይ ከእቅፉ ነጥቀው እየገደሉ ሌላውንም ያለጥፋቱ በወህኒ እየወረወሩ የሚያስለቅሱትን ሁሉ ወደ ኅሊናቸው ይመለሱ ዘንድ እየማለድን መሆን አለበት።

No comments:

Post a Comment