Thursday, December 26, 2013

"እነሱ በእምነት የእሳትን ኃይል አጠፉ" (ዕብ 11÷33)





የጽድቅ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ ለቤዛነት ቀን ለታተሙት በሜሮን ለከበሩት በልጅነት ክብር ለተጠሩት በወልድ ውሉድ በክርስቶስ ክርስቲያን ለተሰኙ ለዕብራውያን ሰዎች በሃይማኖት እንዲቆሙ በክርስቶስ ደም በተዋጀችው በሐዋርያትና በነቢያት መሠረትነት ላይ በታነጸችው በመጀመሪያ እምነታቸው እንዲፀኑ ሲያስተምር ይህንን ቃለ ተናግሮታል፡፡ እምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው አለ ሐዋርያው፤ አዎ እምነት የማይታየው እንደሚታይ የማይቻለው እንደሚቻል የማይገፋው እንደሚገፋ የሚያስረዳ ረቂቅ መሣሪያ ነው፡፡ እምነት የረቀቀውን የሚያጎላ የተሰወረውን የሚገልጽ የራቀውን የሚያቀርብ እጉሊ መነጽር ነው፡፡



ለዚህም ነበር አምላችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዘመነ ሥጋዌ በሚያስተምርበት ዘመን ለሚያምን ሁሉ ይቻላል ያለው (ማር 9÷23) ለሽማግሌዎች ለአበው፣ ለነቢያት የተመሰከረላቸው በእምነት ነው፣ ምክንያቱም እነርሱ ዓለሞች በእግዚአብሔር ቃል እንደተዘጋጁ የሚታየው ነገር ከማይታየውና ከረቂቁ ከእግዚአብሔር እንደሆነ በእምነት አስተውለዋልና እንዲሁም በግዙፉ በኃላፊውና በጠፊው ዓለም ውስጥ እየኖሩ የማያልፈውንና ዘላለማዊውን ዓለም በእምነት መነጽር ለማየት ችለዋልና ተመሰከረላቸው ያለ እምነትም እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና ተብሎ እንደተጻፈ ሐዋርያው እነሱ ያላቸው ሰማያዊውንና የሚበልጠውን ሀገር ናፍቀው ዓለምን ንቀው ከሀገራቸው ወጥተው የተሰደዱትን ብድራቱን ትኩር ብለው ስለተመለከቱ የሚገለብጠውን ወንበር የሚሻረውን ስልጣን በወረት የሚቀረውን ዝና የሚሻግተውን የሚበሰብሰውን እንጀራ በእምነት የተውትን ቅዱሳን ነው፡፡ እነሱ ገና ስለማይታየው ነገር ተረድተው እግዚአብሔርን እየፈሩ ቤተሰቦቻቸውን ለማዳን በእምነት መርከብን ያዘጋጁትን ዓለምን፣ በዓለም ያለው የዓይን አምሮትና ክፋት በመሆኑ ዓለምን የኮነኑትን፣ መሠረት ያላትን እግዚአብሔር የሠራትንና የፈጠራትን ከተማ በእምነት አሻግረው ያዩትን፣ ተስፋ የሰጠው የታመነ እንደሆነ ያስተዋሉትን ከምንምና ከማንም በላይ በእግዚአብሔር ፍቅር ተቃጥለው ዓለምን ተትው የመነኑትን ፀበ-አጋንንቱን የታገሱትን፣ ጤዛ ልሰው ድንጋይ ተንተርሰው በዱር በገደል በሸንተረር በዋሻና በበረሃ የተንከራተቱትን፣ እንዲሁም በዓለም እየኖሩ ጽድቅ ያደረጉትን ዓለምንና ዓላማውያንን የናቁትን ኃጢዓትን የተጸየፉትን አላውያንን አሕዛብ መንግስታትን ድል የነሱትን ስለአምላካቸው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም በመነቀፍ እንገታቸውን ለሰይፍ ጀርባቸውን ለግርፋት ሥጋቸውን ለመከራ አሳልፈው የሰጡትን በእምነት የአንበሶቹን አፍ የዘጉትን ከሰይፍ ስለት ያመለጡትን ከድካማቸው የበረቱትን በጦርነት ኃይለኞች ሆነው የባዕድ ጭፍሮችን ያባረሩትን የእሳቱን ኃይል አጥፍተው በእሳት መካከል የተመላለሱትን ሁሉ ሐዋሪያው በእምነት ተመሰከረላቸው አለ፡፡

ዓለምን የሚያሸንፈው እምነታችን ነው እንዲል የፍቅር ሐዋርያ ቅዱስ ዮሐንስ በእምነታቸው ከተመሠከረላቸው የእሳትን ኃይል ካጠፉት የእምነት አርበኞች መካከል በየዓመቱ ታህሳስ 19 ቀን መታሰቢያ በዓላቸውን የምናከብረው አናኒያ፣ አዛርያና ሚሳኤል ሰማዕታት ወራዙት ከዋክብተ ቤተ ክርስቲያን የተዋህዶ እንቁዎቻችን ናቸው፡፡ ዘመኑ እስራኤል በአንድነት እግዚአብሔርን የበደሉበት ፍርድ አጓድለው ደግ በድለው በነቢያቱና በካህናቱ በማፌዛቸው ለንስሐ ልባቸውን በማደንደናቸው እንደ ድንጋይም በማጠንከራቸው ነቢዩ ኤርሚያስ "በደላችሁ እነዚህን አስቀርታለች ኃጢዓታችሁም መልካም ነገርን ከለከለቻችሁ" (ኤር 5÷25) እንዳለ በበረከት ፈንታ መርገምን፣ በጥጋብ ፈንታ ርሃብን፣ በሰላም ፈንታም ሰይፍን በቅጣት ተቀበሉ፣ የቅድስት ሀገራቸው የኢየሩሳሌምም ቅጥር ፈረሰ ለጨካኝ ጠላት ለከለዳውያን ተላልፈው ተሰጡ ብዙዎችም ተማረኩ ወደ አሕዛብ ምድር ፋርስ በቢሎንም ወረዱ፣ ከምርከኞች መካከል የቀና መንፈስ ያላቸው ሶስት ወጣቶች ብልህና አስተዋዮች ነበሩ ቅዱስ ዳዊት "ኢየሩሳሌም ሆይ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ" እንዲል የእግዚአብሔር ሕዝብ መሆናቸውን ያስተዋሉ ስማቸው ተቀይሮ ሲድራቅ፣ ሚሳቅ፣ አብድናጎ ቢባልም እነርሱ ግን መልካቸውን ያልቀየሩ ምግባርን ከሃይማኖት አስተባብረው የያዙ ሆነው ተገኙ "መልካም ስም በጎ ምግባር ከመልካም ሽቶ ይበልጣል እንዲል (መክ 7÷1) መልካም ስም የተባለውን ክርስቲያንነታቸውን አልቀየሩም ምክንያቱም ስም ከመቃብር በላይ ይውላል፣ ቅዱሳን ከብዙ ዘመን በፊት አንቀላፍተው ዛሬም በስማቸው በመልካቸው፣ በሥራቸው ይናገራሉ በእምነታቸው ይመሰክራሉ"

ብዙዎቻችን ወጣቶች ሀገር ስንቀይር መልካችን ይቀየራል በጎውን ምግባራችን በክፉው፣ እግዚአብሔርን መፍራታችን፣ ትህትናችን፣ ቅድስናችን፣ ንጽህናችን፣ ሃይማኖትን ከምግባር አስተባብሮ መያዛችን እንደ ስም ቀልጦ ይጠፋል፡፡ ብልጭልጩ ዓለም ያታልለናል ዘመናዊነት ሁሉን ያስረሳናል ክብራችን አውልቀን ጥለን ዳንኪራ የምንረግጥ በተለያዩ ሱሶች ተጠምደን ስልጣኔ መስሎን ኃጢዓትን የሙጥኝ ብለን ስማችንን የቀየርን ታሪካችን ያበላሸን ብዙ ነን፡፡

በዘመኑ የነበረው ንጉሥ ናብከደነጾር እግዚአብሔርን የማይፈራ ጣዖትን የሚያመልክ ነበረና ቁመቱ ስድስት ክንድ የሆነ ጣዖትን ምስልን አሰርቶ በከተማው ዱራ በሚባለው ሜዳ አስተካከለ አዋጅንም አስነገረ ለተሰራውም ምስል ሁሉ እንዲሰግድ ትዕዛዝን አስተላለፈ ያልሰገደ ያልተንበረከከም ወደ እቶን እሳት እንደሚጣል መልዕክት ተላለፈ፣ ሁሉ ተንበረከከ ሁሉ ሰገደ አናንያ አዛርያ ሚሳኤል ግን በጽናት ቆሙ ጣዖትን ረገሙ ኃጢዓትን ተፀየፉ፡፡

እኛ በዚህ ዘመን ለስንት ነገር ሰገድን፣ ለስንት ነገር ተገዛን፣ እስካሁን እግዚአብሔርን በደባል ቤት የምናኖር ጠንቋይ የምናመልክ፣ አስማተኛ የምንከታተል፣ ከመጽሐፍ ገላጭ ከመዳፍ አንባቢ የምንመላለስ ብዙ ነን፡፡ "በእስራኤል ላይ ሟርት በያዕቆብ ላይ አስማት አይሰራምና" ዛሬ ንስሐ ገብተን እንመለስ (ዘኁ 23÷23)

አናኒያ አዛርያ ሚሳኤል በንጉሱ ፊት ተከሰው ቀረቡ ለምን አትሰግዱም ተብለው ተጠየቁ "ጻድቅ ልቡ እንደ አንበሳ ጽኑ ነው" እንዲል መጽሐፍ "እኛ የፈጠረን እግዚአብሔር ነው አምላካችን አንክድም አንተ ላቆምከው ምስል አንሰግድም" አሉት ንጉሱ ተቆጣ በክፉም ተነሳባቸው "ካልሰገዳችሁ ወደ እቶን እሳት ትጣላላችሁ" አላቸው፡፡" እነሱ ግን ዳዊት በመዝሙሩ "እኔስ ንጉሴን በልቤ ሾምኩ" (መዝ 2÷7) እንዲል በልባቸው የነገሰው እግዚአብሔር አበረታቸውና "እግዚአብሔር አምላካችን ያድነናል፣ ባያድነንም እንኳ እሱ አምላካችን ነውና አንተ ላቆምከም ምስል አንሰግድም" አሉት፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ "ሥጋን ብቻ የሚገድሉትን በነፍስ ላይ ስልጣን የሌላቸውንም ሥጋ ለባሾችን አትፍሩ ይላልና (ማቴ 10÷28) ወጣቶቹ በእምነት ዳኑ ፍጹም ፍቅር ፍርሃትን አውጥቶ ይጥላልና በፍቅር በርቱ፡፡ (1 ዮሐ 4÷17)

ከዚህ በኋላ መጽናታቸውን ያየ ንጉሥ ናቡከደነጾር ወጣቶችን ወደ እቶን እሳት ውስጥ አስጣላቸው ነገር ግን እግዚአብሔር ቅድመ ተራዳኢውን መልአክ ቅዱስ ገብርኤልን ላከ "በእሳትና በውሃ መካከል አሳልፍከን" "በእሳት በሄድክ ጊዜ አትቃጠልም" (መዝ 66÷12 ኢሳ 43÷2) ተብሎ እንደተጻፈ ዝማሬ ከእሳቱ ውስጥ ተሰማ አናኒያ አዛርያ ሚሳኤል ከብርሃናዊ መልአክ ከቅዱስ ገብርኤል ጋር በእሳቱ ውስጥ እየተመላለሱ እግዚአብሔርን አመሰገኑ፡፡

"ይትባረክ አምላክ አግዚአብሔር አበዊነ ስቡሕኒ ውዕቱ ወልዑልኒ ውዕቱ ለዓለም"

የእሳቱን ኃይል በእምነት አጠፉ ይህንን ያየ ንጉሥ ናቡከደነጾር "እናንተ የልዑል አምላክ ባሪያዎች ውጡ" በእናንተም አምላክ አምናለሁ፣ በእግዚአብሔርም የማያምን በዕቶን እሳት ይጣላል በማለት አዋጅ አስነገረ ነገር ተገለበጠ ታሪክ ተቀየረ ሶስት ወጣቶች በእምነታቸው ለቡዙዎች መዳን ምክንያት ሆኑ (ዳን 3÷28)

ዛሬ በዘመናችን እግዚአብሔር በእምነት ጸንቶ የሚያጸና ለቡዙዎች መዳን ምክንያት የሚሆን ሰው ይሻል ኢትዮጵያውያን ወጣቶች እሳት መለያየት፣ ዘረኝነት፣ መናፍቅነት በሀገራችን ሰፍኗልና ታምነን እንሰማራ ከመቃቃር መፈቃቀር፣ ከመተቻቸት መተራረም፣ ከመራራቅ መቀራረብ፣ ከጥል ከክርክር ፍቅርን እናስቀድም፡፡


ኢትዮጵያዊነት መልካችንን የቀየርን ሃይማኖታችንን የጣልን ምግባራችንን ያበላሸን ዘረኝነት የተጠናወተን በእሳት ተከበናልና ፈጥነን ንስሐ እንግባ የእምነትን ጋሻ እናንሳ ለእርቅ ለሰላም ልባችንና እጃችንን እናንሳ፡፡

No comments:

Post a Comment