‹‹እነሱ በእምነት የእሳትን ኃይል
አጠፉ›› ዕብ 11፡33
የጽድቅ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ ለቤዛነት
ቀን ለታተሙት በሜሮን ለከበሩት በልጅነት ክብር ለተጠሩት በወልድ ውሉድ በክርስቶስ ክርስቲያን ለተሰኙት ለዕብራውያን ሰዎች በሃይማኖት
እንዲቆሙ በክርስቶስ ደም በተዋጀችው በሐዋርያትና በነቢያት መሠረትነት ላይ በታነጸችው በመጀመሪያ እምነታቸው እንዲፀኑ ሲያስተምር
ይህንን ቃል ተናግሮታል፡፡ እምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው አለ ሐዋርያው አዎ
እምነት የማይታየው እንደሚታይ የማይቻለው እንደሚቻል የማይገፋው እንደሚገፋ የሚያስራዳ ረቂቅ መሳሪያ ነው እምነት የረቀቀውን የሚያሳይ
የተሰወረውን የሚገልጽ የራቀውን የሚያቀርብ አጉሊ መነጽር ነው ለዚህም ነበር አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዘመነ ሥጋዌ በሚያስተምርበት
ዘመን ለሚያምን ሁሉ ይቻላል ያለው ማር 9፡23
ለሽማግሌዎች ለአበው ለነቢያት የተመሰከረላቸው
በእምነት ነው፤ ምክንያቱም እነርሱ ዓለሞች በእግዚአብሔር ቃል እንደተዘጋጁ የሚታየው ነገር ከማይታየውና ከረቂቅ ከእግዚአብሔር እንደሆነ
በእምነት አስተውለዋልና እንዲሁም በግዙፉ በኃላፊውና በጠፋው ዓለም ውስጥ እየኖሩ የማያልፈውንና ዘላለማዊውን ዓለም በእምነት መነጽር
ለማየት ችለዋልና ተመሰከረላቸው ያለ እምነትም እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ
ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና ተብሎ እንደተጻፈ ሐዋርያው እነሱ ያላቸው ሰማያዊውንና የሚበልጠውን ሀገር
ናፍቀው ዓለምን ንቀው ከሀገራቸው ወጥተው የተሰደዱትን ብድራቱን ትኩር ብለው ስለተመለከቱ የሚገለብጠውን ወንበር የሚሻረውን ስልጣን
በወረት የሚቀረውን ዝና የሚሻግተውን የሚበሰብሰውን እንጀራ በእምነት የተውትን ቅዱሳን ነው፡፡
እነሱ ገና ስለማይታየው ነገር ተረድተው
እግዚአብሔርን እየፈሩ ቤተሰቦቻቸውን ለማዳን በእምነት መርከብን ያዘጋጁትን ዓለምና በዓለም ያለው የዓይን አምሮትና ክፋት በመሆኑ
ዓለምን የኮነኑትን ፣ መሠረት ያላትን እግዚአብሔር የሠራትንና የፈጠራትን ከተማ በእምነት አሻግረው ያዩትን፣ ተስፋ የሰጠው የታመነ
እንደሆነ ያስተዋሉትን ከምንምና ከማንም በላይ በእግዚአብሔር ፍቅር ተቃጥለው ዓለምን ትተው የመነኑትን ፀበ አጋንንቱን የታገሱትን፣
ጤዛ ልሰው ድንጋይ ተንተርሰው በዱር በገደል በሸንተረር በዋሻና በበረሃ የተንከራተቱትን፣ እንዲሁም በዓለም እየኖሩ ጽድቅ ያደረጉትን
ዓለምንና ዓለማውያንን የናቁትን ኃጢዓትን የተጸየፉትን አላውያንን አሕዛብ መንግስታትን ድል የነሱትን ስለአምላካቸው ስለ ኢየሱስ
ክርስቶስ ስም በመነቀፍ አንገታቸውን ለሰየፍ ጀርባቸውን ለግርፋት ሥጋቸውን ለመከራ አሳልፈው የሰጡትን በእምነት የአንበሶቹን አፍ
የዘጉትን ከሰይፍ ስለት ያመለጡትን ከድካማቸው የበረቱትን በጦርነት ኃይለኞች ሆነው የባዕድ ጭፍሮችን ያባረሩትን የእሳቱን ኃይል
አጥፍተው በእሳት መካከል የተመላለሱትን ሁሉ ሐዋርያው በእምነት ተመሰከረላቸው አለ፡፡
ዓለምን የሚያሸንፈው እምነታችን ነው
እንዲል የፍቅር ሐዋርያ ቅዱስ ዮሐንስ በእምነታቸው ከተመሠከረላቸው የእሳትን ኃይል ከጠፉት የእምነት አርበኞች መካከል በየዓመቱ
ታህሣሥ 19 ቀን መታሰቢያ በዓላቸውን የምናከብረው አናኒያ፣ አዛርያና ሚሳኤል ሰማዕታተ ወራዙት ከዋክብቱ ቤተ ክርስቲያን የተዋህዶ
እንቁዎቻችን ናቸው፡፡
ዘመኑ እስራኤል በአንድነት እግዚአብሔርን
የበደሉበት ፍርድ አጓድለው ደኃ በድለው በነቢያቱና በካህናቱ በማፌዛቸው ለንሰሐ ልባቸውን በማደንደናቸው እንደ ድንጋይም በማጠንከራቸው
ነቢዩ ኤርሚያስ ‹‹በደላችሁ እንዚህን አስቀርታለች ኃጢዓታችሁም መልካም ነገርን ከለከለቻችሁ›› (ኤር 5፡25) እንዲል በበረከት
ፈንታ መርገምን፣ በጥጋብ ፈንታ ርሃብን፣ በሰላም ፈንታም ሰይፍን በቅጣት ተቀበሉ፣ የቅድስት ሀገራቸው የኢየሩሳሌምም ቅጥር ፈረሰ
ለጨካኝ ጠላት ለከለዳውያን ተላልፈው ተሠጡ ብዙዎችም ተማረኩ ወደ አሕዛብ ምድር ፋርስ ባቢሎንም ወረዱ፣ ከምርኮኞች መካከል የቀና
መንፈስ ያላቸው ሦስቱ ወጣቶች ብልህና አስተዋዮች ነበሩ ቅዱስ ዳዊት ‹‹ኢየሩሳሌም ሆይ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ›› እንዲል የእግዚአብሔር
ሕዝብ መሆናቸውን ያስተዋሉ ስማቸው ተቀይሮ ሲድራቅ፣ ሚሳቅ፣ አብድናጎ ቢባልም እነርሱ ግን መልካቸውን ያልቀየሩ ምግባርን ከኃይማኖት
አስተባብረው የያዙ ሆነው ተገኙ ‹‹መልካም ስም በጎ ምግባር ከመልካም ሽቶ ይበልጣል እንዲል›› (መክ7፡1) መልካም ስም የተባለውን
ክርስቲያንነታቸውን አልቀየሩም፣ ምክንያቱም ስም ከመቃብር በላይ ይውላልና ቅዱሳን ከብዙ ዘመን በፊት አንቀላፍተው ዛሬም በስማቸው
በመልካቸው በሥራቸው ይናገራሉ በእምነታቸው ይሰክራሉ፡፡
ብዙዎቻችን ወጣቶች ሀገር ስንቀይር
መልካችን ይቀየራል በጎው ምግባራችን በክፉው፣ እግዚአብሔርን መፍራታችን ትህትናችን ቅድስናችን ንጽሕናችን ኃይማኖትን ከምግባር አስተባብሮ
መያዛችን እንደ ሰም ቀልጦ ይጠፋል ብልጭልጩ ዓለም ያታልለናል ዘመናዊነት ሁሉን ያስረሳናል ክብራችን አውልቀን ጥለን ዳንኪራ የምንረግጥ
በተለያዩ ሱሶች ተጠምደን ስልጣኔ መሰሉን ኃጢዓትን የሙጥኝ ብለን ስማችንን የቀየርን ታሪካችንን ያበላሸን ብዙ ነን በዘመኑ የነበረው
ንጉሥ ናቡከደነፆር እግዚአብሔርን የማይፈራ ጣዖትን የሚያመልክ ነበረና ቁመቱ ስድሳ ክንድ የሆነ ጣዖትን ምስልን አሰርቶ በከተማው
ዱራ በሚባለው ሜዳ አስተከለ አዋጅንም አስነገረ ለተሰራውም ምስል ሁሉ እንዲሰግዱ ትዕዛዝን አስተላለፈ ያልሰገደ ያልተንበረከከም
ወደ እቶን እሳት እንደሚጣል መልዕክት ተላለፈ ፤ ሁሉ ተንበረከከ ሁሉ ሰገደ አናንያ አዛርያ ሚሳኤል ግን በጽናት ቆሙ ጣዖትን ረገሙ
ኃጢዓትን ተጸየፉ፡፡
እኛ በዚህ ዘመን ለስንት ነገር ሰገድን፣
ለስንት ነገር ተገዛን እስካሁን እግዚአብሔርን በደባል ቤት የምናኖር ጠንቋይ የምናመልክ፣ አስማተኛ የምንከተል፣ ከመጽሐፍ ገላጭ፣
ከመዳፍ አንባቢ የምንመላለስ ብዙ ነን ‹‹በእስራኤል ላይ ሟርት በያዕቆብ ላይ አስማት አይሰራምና›› ዛሬ ንስሐ ገብተን እንመለስ
(ዘኃ 23፡23)
አናኒያ አዛሪያ ሚሳኤል በንጉሡ ፊት
ተከሰው ቀረቡ ለምን አትሰግዱም ተብለው ተጠየቁ ‹‹ጻድቅ ልቡ እንደ አንበሳ ጽኑ ነው›› እንዲል መጽሐፍ ‹‹እኛ የፈጠረን እግዚአብሔር
ነው አምላካችን አንክድም አንተ ላቆምከው ምስል አንሰግድም›› አሉት ንጉሡ ተቆጣ በክፉም ተነሳባቸው ‹‹ካልሰገዳችሁ ወደ እቶን
እሳት ትጣላላችሁ አላቸው›› ‹‹እነሱ ግን ዳዊት በመዝሙሩ እኔስ ንጉሴን በልቤ ሾምኩ›› (መዝ 2፡7) እንዲል በልባቸው የነገሰው
እግዚአብሔር አበረታቸው ‹‹እግዚአብሔር አምላካችን ያድነናል፣ ባያድነንም እንኳ እሱ አምላካችን ነውና አንተ ላቆምከው ምስል አንሰግድም››
አሉት ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ሥጋን ብቻ የሚገድሉትን በነፍስ ላይ ስልጣን የሌላቸውን ሥጋ ለባሾችን አትፍሩ ይላልና›› (ማቴ 10፡28)
ወጣቶቹ በእምነት ጸኑ ፍጹም ፍቅር
ፍርሃትን አውጥቶ ይጥላልና በፍቅር በረቱ (1ኛ ዮሐ 4፡17) ከዚህ በኋላ መጽናታቸውን ያየ ንጉሥ ናቡከደነፆር ወጣቶቹን ወደ እቶን
እሳት ውስጥ አሰጣላቸው ነገር ግን እግዚአብሔር ቅደመ ተራዳኢውን መልአክ ቅዱስ ገብርኤልን ላከ ‹‹በእሳትና በውሃ መካከል አሳለፍከን››
‹‹በእሳት በሄድክ ጊዜ አትቃጠልም›› (መዝ 66፡12 ፣ ኢሳ 43፡2) ተብሎ እንደተጻፈ ዝማሬ ከእሳቱ ውስጥ ተሰማ አናኒያ አዛርያ
ሚሳኤል ከብርሃናዊ መልአክ ከቅዱስ ገብርኤል ጋር በእሳቱ ውስጥ እየተመላለሱ እግዚአብሔርን አመሰገኑ
‹‹ይትባረክ አምላክ እግዚአብሔር አበዊነ ሰቡሕኒ ውዕቱ ወልዑልኒ ውዕቱ
ለዓለም››
የእሳቱንም ኃይል በእምነት አጠፋ ይህንን
ያየ ንጉሥ ናቡከደነፆር ‹‹እናንተ የልዑል አምላክ ባሪያዎች ኑ ውጡ›› በእናንተም አምላክ አምናለሁ ፣ በእግዚአብሔርም የማያምን
በዕቶን እሳት ይጣላል በማለት አዋጅ አስነገረ ነገር ተገለበጠ ታሪክ ተቀየረ ሦስቱ ወጣቶች በእምነታቸው ለብዙዎች መዳን ምክንያት
ሆኑ (ዳን 3፡28)
ዛሬ በዘመናችን እግዚአብሔር በእምነት
ጸንቶ የሚያጸና ለብዙዎች መዳን ምክንያት የሚሆን ሰው ይሻል ኢትዮጵያውያን ወጣቶች እሳት መለያየት፣ ዘረኝነት፣ መናፍቅነት በሀገራችን
ሰፍኗልና ታምነን እንሰማራ ከመቃቃር መፈቃቀር ፣ ከመተቻቸት መተራረም፣ ከመራራቅ መቀራረብ፣ ከጥል ከክርክር ፍቅርን እናስቀድም፡፡
ኢትዮጵያውነት መልካችንን የቀየርን
ኃይማኖታችን የጣልን ምግባራችን ያበላሸን ዘረኝነት የተጠናወተን በእሳት ተከበናልና ፈጥነን ንስሐ እንግባ የእምነትን ጋሻ እናንሳ
ለእርቅ ለሰላም ልባችንና እጃችንን እናንሳ፡፡
No comments:
Post a Comment