Saturday, April 9, 2016

በጥቂቱ ታምነሃልና በብዙ እሾምሃለሁ፤ማቴ ፳፭ ፣፳፩

ገብርኄር 


የአብይ ጾም ስድስተኛ ሳምንት
 ገብርር ማለት ታማኝ አገልጋይ ማለት ነው።
ከመ እንግር ፈቃደከ መከርኩ አምላኪየ  
ወሕግከኒ በማዕከለ ከርስዬ 
 ዜኖኩ ጽድቀከ በማኅበረ ዐቢይ።
(መዝ፴፱፣ ፰)




 ወምዕመን ዘበኅዳጥ፣ ዘበውኁድ ምዕመነ ኮንከ ዲበ ብዙኅ እሰይመከ። ማቴ ፳፭ ፣፳፩
===============================================
ወደ ሩቅ ሀገር የሚሄድ ባለጸጋ ሰው አገልጋዮቹን ወደ እርሱ ጠርቶ ያለውን ገንዘብ ነግደው እንዲያተርፋበት ሰጣቸው ፣ ቦ ለዘወሀቦ ሃምስተ መክሊተ  አምስት መክሊት የሰጠው ሰው አለ፣ወቦ ለዘወሀቦ ክልኤተ መክሊተ ፡ሁለት መክሊት የሰጠው ሰው አለ፣ወቦ ለዘወሀቦ አሐደ መክሊተ ፡አንድ መክሊት የሰጠው ሰው አለ፤ ለእያንዳንዳቸው እንደአቅማቸው ሰጥቷቸው ሄደ፡ወነገደ በጊዜሃ።
፩) አምስት መክሊት የተቀበለው ወጥቶ ወርዶ አተረፈ ፣ወረብኃ ካልዓተ ኀምስተ መካልየ፤ አምስት አትርፎ አስር አድረገ።
፪) ወከማሁ ዘሂ ክልኤተ መካልየ ረብኃ ካልአተ መካልየ፣እንደዚሁ ሁሉ ሁለት መክሊት የተቀበለውም ወጥቶ ወርዶ አትርፎ አራት አደረገ።
፫) ወዘ አሐደሰ መክሊተ ነስአ ሖረ ወኃለፈ ወከረየ ምድረ ወኃብ ወርቀ እግዚኡ፣ አንድ መክሊት የተቀበለው ግን ሌባ ቢሰርቀኝ ወንበዴ ቢቀማኝ ቀጣፊ ቢያታልለኝ ብሎ ፈርቶ ሄዶ ምድር ቆፍሮ የጌታውን ወርቅ ቀበረ።
ወእምድኅረ ብዙኅ መዋዕል አተወ እግዚኦሙ ለእሉ አግብርት፣ ከብዙ ዓመት በኋላ የእነዚያ አገልጋዮች ጌታቸው መጣ
ወአኅዘ ይትሐሰቦሙ ፡ ተቆጣጠራቸውም።

ወጥተው ወርደው ነግደው አትርፈው ያቆዩትን ባለአምስትና ባለሁለት መክሊት በምስጋና ቃል ተናገራቸው ፣ወይቤሎ እግዚኡ ኦ ገብርሄር ወምዕመን ዘበውኁዱ ምዕመነ ኮንከ ዲበ ብዙኀ እሰይመከ ባእ ውስተ ፍስሓሁ ለእግዚእከ። አንተ በጎ አገልጋይ በጥቂቱ ስለታመንክ በብዙ ወገን እሾምሃለሁ ጌታህ ደስታ ግባ በማለት ተሾም ተሸለም በማለት አከበራቸው።
ባለ አንድ መክሊቱ ግን ወጥቶ ወርዶ በማትረፍ ፈንታ ሌባ ቢሰርቀኝ ወንበዴ ቢዘርፈኝ ብሎ ፈርቶ የተሰጠውን መክሊት መሬት ቆፍሮ ቀብሮ ስለቆየው ጌታው እንዲህ አለው፣ ወይቤሎ ኦ እኩይ ገብር ወሀካይ ተአምረኒኑ ከመ ብእሲ ድሩክ አነ አዓርር ዘኢዘራዕኩ ወአስተጋብዕ ዘኢዘረውኩ ፤ያልዘራሁትን የማጭድ ያልበተንኩትን የምሰበስብ ጽኑ ጨካኝ መሆኔን ታውቃለህን። ይህን ካወቅህ መክሊቴን ልትሰጠኝ በተገባህ ነበር ወጥቶ ወርዶ ለሚያተርፍልኝ በሰጠሁት ነበር አንድም እኔ ወጥቼ ወርጄ ባተረፍኩ ነበር። በዚያ ለቆሙትም ይህን መክሊት ከሱ ተቀብላችሁ ዓሥር መክሊት ላለው ስጡት ፣ ላለው ይሰጡታልና ወይዌስክዎ ይደርቡለታልና ፤ ወለዘሰ አልቦ ዘሂ ቦ የሀይድዎ ፣ የሌለውን ግን ያኑ ያለውን ይወስዱበታል። ያን ሐኬተኛ አገልጋይ ግን ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት ወደጽኑ ጨለማ አግዙት አለ።


ትርጉም፦
=======
የዚህ ትምህርት መሰረታዊ ዓላማ ክርስቲያኖች ሁላችን ከልሂቅ እስከ ደቂቅ ከካህን እስከ ምዕመን በታማኝነትና በቅንነት ሆነን በተሰጠን ጸጋ መክሊታችን እንድናተርፍበት ፴ ሰላሳ ፣፷ ስድሳ ና ፣ ፻መቶ ፍሬ እንድናፈራበት እንጅ ዘመናችንን በከንቱና ና በንዝህላልነት እናዳናሳልፍ መምከር ማስተማር ነው። ክርስትና የሚኖሩት ሕይወት ነው እንጅ የመጠሪያ ስም ብቻ አይደለም ፣ ብዙ ሰዎች ክርስቲያኖች ነን ይላሉ ነገር ግን ግብራቸው ከስራቸው ጋር አብሮ አይሄድም
ክፋትን ተንኮልን ቅሚያን ስስትን ዝሙትን ቅናትን ስድብን ክህደትን ራስ ወዳድነትን ገንዘብን መውደድን ቂምና በቀልን ሁሉ ካልተውን በክርስትናችን እያተረፍን አይደለም። ብዙ ወጣቶች ለእግዚአብሔር ክብር በሚቆሙበት ወጥተው ወርደው በሚያተርፉበት ተናግረው በሚያሳምኑበት ታግለው በሚያሸንፉበት በዕንቁ ዕድሜያቸው ጠጥተው ይሰክራሉ፤ በሥጋቸው ያመነዝራሉ በጫትና በአደንዛዥ እፅ እንዲሁም በተለያዩ ሱሶች ይናውዛሉ ፤ በመሆኑም ዘመናቸው ሳያተርፋበት ያልፋል።
፩) በሌላው ባለአምስት መክሊት የተባሉ ባለ ብዙ ጸጋዎች መምህራን ካህናት ናቸው። ወንበር ዘርግተው ጉባኤ አቁመው መንጋውን ወንጌልን ዝማሬዎችን መጻሕፍትን የሚያስተምሩ ፣ ፍጹም ትምህርት ተምረው መክረው አስተምረው ራሳቸውን አስመስለው የሚያወጡ፤ ቅዱስ ጳውሎስ ጢሞቴዎስን ና ቲቶን እንዳወጣ ፣ቅዱስ ጴጥሮስ ቀሌምንጦስን እንዳወጣ ማለት ነው።
፪) ባለአምስት መክሊት የተባሉት ባለትዳሮች ባለሕጎች ናቸው በትዳራቸው ሊያተርፉ ይገባልና ትዳር ማትረፊያ መክሊት ነው አንድ ከመሆን ሁለት መሆን ይሻላልና አንዱ ቢወድቅ ሁለተኛው ያነሳዋል ተደጋግፈው በመክሊታቸው ያተርፋሉና። አንድም በቅዱስ ጋብቻ በንጹህ መኝታ ካህናትን ነገስታትን ነቢያትን መምህራንን ይወልዳሉና።
፫) ባለ አምስት የተባሉ ባለ ሀብቶች የዚህ ዓለም ብዕል የሞላቸው ገንዘባቸውን ቢመጸውቱ ያላቸውን ሁሉ ለደሃ ሰጥተው ቢከተሉት በገንዘባቸው መንግስቱን ጽድቁን ያተርፉበታልና።
፬) ባለ አምስት የተባሉ በጵጵስና ማዕረግ ከፍ ያለው ማዕረግ ላይ ያሉ የሚያስተምሩ የሚያጠምቁ የሚቀድሱ ከምንም በላይ መንጋውን እንዲጠብቁ የተሾሙ። እነዚህ በትጋትና በታማኝነት ሆነው በጎችን
ከነጣቂዎች ከተኩላዎች ከሌቦች የመጠበቅ ግዴታ አለባቸው እንደዚያ ከሆነ በመክሊታቸው ያተርፋሉ (ሐዋ፳ ፣፳፰)
፬) ባለ ሁለት የተባሉ ቀሳውስት መምህራነ
ወንጌል መንጋውን ያገለግሉ ይጠብቁ ዘንድ የተለያየ መክሊት ጸጋ የተሰጣቸው በታማኝነትና በትጋት ፍጹም የሆነውን ትምህርት እያስተማሩ በመክሊታቸው ሊያተርፉ ይገባል። በተለይ ዛሬ ባለንበት ዘመን ወንጌልን የሚሸቅጡ ኑፋቄን አሹልከው ለማስገባት ተመሳስለው የሚንቀሳቀሱ የውስጥ መናፍቃን በበዙበት ዘመን በታማኝነትና በቅንነት መንጋውን ከነፍሳት ሌቦች የሚጠብቂ ታማኝ አገልጋዮች ለቤተክርስቲያን ያስፈልጋታል።
መጀመር ሁሉ ይጀምራል ነገር ግን አክሊል የሚቀበል በታማኝነትና በትጋት በቅንነትና በእውነት የሚፈጽም በጎ አገልጋይ ነው።
፭) ባለ አምስት የተባሉ የመስቀሉ ፍቅር ገብቷቸው የዓለምን ከንቱነት ተረድተው ዓለምን ትተው የመነኑ በዱር በገደል በዋሻና በሸንተረሩ ጸበ አጋንንቱን ታግሰው ዳዋ ጥሰው ቅጠል በልተው ድንጋይ ተንተርሰው በምናኔ የሚኖሩ ናቸው እነዚህ በተሰጣቸው መክሊት በርትተው ተጋድለው ለራሳቸው የክብር አክሊልን ተጎናጽፈው ለሌሎች ለደካሞች ለሀገርና ለወገን የሚጸልዩ ሊሆን ይገባልና። አንድም ባለ አምስት መነኮሳት ለዓለም የሞቱ ሚስቴን ልጄን ትዳሬን የማይሉ ለምድራዊ ብዕል ሳይሰስቱ መንግስቱንና ጽድቁን ብቻ በመሻት በእምነትና በምግባር በርትተው በሰጣቸው መክሊት አትርፈው የእንጦስን የመቃርስን ክብር ሊጎናጸፉ ይገባል በሕይወታቸው አርአያ ምሳሌ ሊሆኑ ይገባል በጸሎታቸው ለደካሞች ኅይል ሊሆኑ ግድ ነው።(ዕብ ፲፩ ፣፴፰)
፮)  ባለ አንድ የተባልን ዲያቆናት በንጽሕና በቅድስና ተላልከን አገልግለን ለሃይማኖት ጠበቃ በመሆን በፍጹም በመታመን እንደ ቀዳሚ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ በመክሊታችን ማትረፍ ይገባናል።
ባለ አንድ የተባልን ምዕመናን በተሰጠን ጸጋ ወጥተን ወርደን ጾመን ጸልየን ሃይማኖታችን አጽንተን ምግባራችን አቅንተን በመክሊታችን ልናተርፍ ይገባል። ይህን ካደረግን ወደ ሩቅ ሀገር ወደ ሰማየ ሰማያት በክብር ያረገው የድንግል ማርያም ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ በኋለኛው ዘመን ተመልሶ ዓለምን ለማሳለፍ ለእያንዳንዱ እንደሥራው ሊከፍል በክብር ሲመጣ ሁላችን በተሰጠን ጸጋና መክሊት ሲቆጣጠር በመክሊታችን አትርፈን እንድንገኝ እናንተ መልካም አገልጋዮች ወደ አባቴ መንግስት በሐሴት ግቡ የሚለውን የሕይወት ቃል እንድንሰማ ፣እሱ ባለቤቱ መድኃኔዓለም ይርዳን አሜን።

No comments:

Post a Comment