ነስአ ደዌነ ወፆረ ሕማመነ
===============
የጌታችንን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን መከራ በትንቢት መነጽር እያየ ነቢዩ ኢሳይያስ መርገማችን ሊሽር ነውራችን ሊያንከባልል ፣ ስለ እኛ የከፈለውን ውለታ ሲዘክር ሕመማችን ታመመ መቅሰፍታችን ተሸከመ ስድባችንን ያስወግድ ዘንድ እሱ ተሰደበ አለ፤ ትውልዱ ግን አላስተዋለም፣ ከትውልዱ ማን አስተዋለ ፣ እርሱ ግን ያከብረን ዘንድ ተዋረደ ፣ ያነሳን ዘንድ ወደቀ
ከእስራታችን ይፈታን ዘንድ በገመድ ታሰረ
በአይሁድ ቀያፋ በስምንቱ ቤተ ጭፍራ ተዘለፈ ፣አስራ ሦስቱን ሕማማተ መስቀል ተቀበለ፡-
ሀ) ተኮርዖተ ርእስ፡-
_________________
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን በዘንግ መመታቱንና መቀጥቀጡን የሚገልጥ ነው።
አገረ ገዥው ጲላጦስ እኔ ከዚህ ጻድቅ ሰው ደም ንጹህ ነኝ ብሎ እጁን ከታጠበ በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ገርፎ ለካህናት አለቆችና ለሽማግሎች አሳልፎ ሰጥቶት ነበር። በአይሁድ ህግ ግን የተገረፈ አይሰቀለም ፤የሚሰቀል ደግሞ አይገረፍም።እርሱ ጲላጦስ ግን ከገረፈው በኋላ የበደል በደል እንዲሰቅሉት አሳልፎ ሰጣቸው። ማቴ 27፣24። ማር15፣15። ሉቃ23፣25። ዮሐ18፣39
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተላልፎ ከተሰጠ በኋላ የእሾህ አክሊል ጎንጉነው በራሱ ላይ ደፍተውበታል።ራሱንም በዘንግ መትተውታል ።ማር15፣19። የአዳም ዘር በጠላቱ በዲያብሎስ በተጎነጎነ የኃጢያት እሾህ ራሱ ተይዞ ነበርና። ነቢዩ ኤርሚያስ በሰቆቃው አሳዳጆቻችን በራሳችን ላይ ናቸው እንዲል(ሰ.ኤር 5፣5)ይህንን የመከራ አክሊል ያነሳልን ዘንድ የእሾህ አክሊል ደፋ ፤ አንድም ክብር ከአዳም ዘር ለቆ አክሊላችን ወድቆ ነበርና፣ የወደቀውን አክሊላችን ሊመልስልን በዲያብሎስ የግብር ልጆች በአይሁድ ተንኮል የተጎነጎነ የእሾህ አክሊል ደፍቶ ዋለ። ዳግማዊ አዳም የተባለ ክርስቶስ በሲኦል ወድቆ በዲያብሎስ ተረግጦ ራሱ የሚቀጠቀጠውን የሰውን ልጅ ለማዳን ራሱን በመቃ ተቀጠቀጠ። ከራሱ ላይ በሚወርደውም ደም ፊቱ ተሸፈነ።
የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የሕማሙ ነገር ከአእምሮ በላይ በመሆኑ እንኳን በሥፍራው ተገኝተው ለአዩትና ለተመለከቱ ለእመቤታችንና ለቅዱስ ዮሐንስ ቀርቶ ዛሬ በመንፈስ ለምንተርከው እንኳ እጅግ የሚያስደንቅ ነው። በዕለተ ዓርብ በተወደደችው ዓመት ቅዱሳን መላእክት ምግባቸው ምስጋናቸው ምስጋናቸው እረፍታቸው ነውና በተለመደው ሰዓት ሊያገለግሉት ና ሊያመሰግኑት በእኩለ ቀን ቢመጡ ፈጣሪያችን እጅና እግሩ ተቸንክሮ ተመለከቱ የመድኃኔዓለም የማዳን ሥራው ቢረቅባቸው እፁብ በማለት በትዕግስቱ ተደነቁ ፤ ከአእምሮ በላይ የሆነ ትዕግስት ፤ እንደምንስ ያለ ትህትና ነው ያሰኛልና፤
ቀንድ እያለው የማይዋጋ በግ ፣ ለመታረድ እንደሚነዳ. ጠቦት ፣ ለመሸለት እንደሚሄድ በግ ዝምታው እጅግ ያስደንቃል በመሆኑም አስራ ሦስቱን ሕማማተ መስቀል ተቀበለ፤ ሰው መሆን ላልቻልን ለሰው ልጆች ደዌያችንን ሁሉ በእሱ ላይ አደረገ::
ለ) ተፀፍዓ መልታሕት
---------------------------
ንጹሃ ባህሪ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ እጃቸው በደም ጣቶቻቸውም በበደል በረከሰ በአይሁድ እጅ በጥፊ መመታቱ ተፀፍዖ መልታሕት ይባላል። ጌታችን ለሊቀ ካህናት ቀያፋ እውነትን በመናገሩ እንደ ስድብ ተቆጥሮበት መላልሰው የብርሃን ፊቱን በጥፊ መትተውታል። ፊቱንም በጨርቅ ሸፍነው "ክርስቶስ ሆይ በጥፊ የመታህ ማን ነው ? ትንቢት ተናገርልን።" እያሉ ዘብተውበታል።በጠላት ዲያብሎስ እጅ ወድቆ በነፍሱ ይቀለድበትና ይንገላታ የነበረውን የሰው ልጅ ለማዳን ብሎ በጠላቶቹ በአይሁድ እጅ ወድቆ ተጎሰመ ፣ ዐገቱኒ አልሕምት ብዙኃን፣ ወአኃዙኒ አስዋር ስቡሐን
ወአብቀው አፉሆሙ ላዕሌየ። መዝ ፳፩ እንዲል በትንቢቱ በኃጢያት የሰቡ ክፉዎች አይሁድ ከበቡት አፋቸውንም ከፈቱበት ። አምላካችን ሊቤዣቸው ቢመጣ በጠላትነት ተነስተው አንገላቱት የብርሃን ፊቱን በጥፊም መቱት። ማቴ ፳፯ ፣ ፳፯
ጲላጦስ አሳልፎ ሰስጣቸው በኋላ አክሊለ ሦክ በራሱ ላይ አኑረው ቀይ ልብስ አልብሰው "የአይሁድ ንጉስ ሆይ ሰላም ላንተ ይሁን እያሉ እየተሳለቁበት በጥፊ መትተውታል "
ዮሐ ፲፱ ፣፪-፬ አላወቁትም እንጅ እሱስ በመንግስቱ ሽረት በባህሪው ሞት የሌለበት የዘላለም አምላክ ነው። ነቢዩ ኢሳይያስም በትንቢቱ ከትውልዱ ማን አስተዋለ የነገሥታት ንጉሥ መሆኑን ኢሳ፶፫፣ ፲፪ ቅዱስ ጳውሎስም አውቀውትስ ቢሆን የክብርን ጌታ ባልሰቀሉት ነበር እንዲል ፣ ምስጢር ተሰውሮባቸው ጌታችንን አንገላቱት።
ሐ) ወሪቀ ምራቅ
===========
እርሱ ምራቁ መድኃኒት የሆነ በአፈር ለውሶ ዓይነ ስውራቸውን የአበራላቸውን የብርሃን ጌታ ፤ ርኩሳን አይሁድ በብርሃናዊው የክርስቶስ ፊት ላይ በሚያጸይፍ ሁኔታ ምራቃቸውን ተፉበት። ለአስራ ሁለት ዓመታት ምራቅ እየተፉ የተሳለቁባትን ሴት ንጹሃ ባህሪ እርሱ ሳይጸየፍ ፈወሳት እነሱ ግን ኃጢያታቸው የሚሸትና የሚከረፋ አይሁድ በቅዱሱ ላይ ምራቃቸውን ተፉ። በነቢዩ ኢሳይያስ "ፊቴን ከትፋትና ከውርደት አልመለስኩም " ተብሎ እንደተፃፈ እየዘበቱበት ምራቃቸውን ተፉበት። ኢሳ፶፣ ፮
በኃጢያት የቆሸሸውን የሰው ሕይወት ያነጻ ዘንድ ንጹሃ ባህሪ እሱ ተተፋበት። ማቴ ፳፯ ፣ ፳፱ ና ማር ፲፭ ፣፲፱ በሥራው ከገነት ተተፍቶበት ተንቆ ተዋርዶ የነበረውን የሰው ልጅ ለማዳን ኃጢያትን ይቅር የሚል ሲሆን። እርሱ ጌታችን ያለ ኃጢያቱ ተተፋበት ተናቀ ተዋረደ። እንኳን በአምላክ ፊት በፍጥረታዊ ሰው ፊት እንኳ መትፋት እጅግ ያስነውራል፤ እርሱ ግን የኃጢያታችንን ነውር ከእኛ ሊያጠፋ ነውር የሆነውን ምራቅ ተቀበለ።
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፍጹም ትህትና የደቀ መዛሙርቱን እግር ካጠበ በኋላ የክርስትና ሕይወት ማኅተም የሆነውን ምስጢረ ቁርባንን መሠረተ ፣ ይህ ደሜ ስለ ብዙኃን የሚፈሰው ደሜ ነው ይህ ሥጋዬ ስለብዙኃን የሚቆረሰው ሥጋዬ ነው፣ ሥጋዬን በበላችሁ ደሜን በጠጣችሁ ጊዜ ሞቴን ሕማሜን መከራየን አስቡ አለ።ሕማም ሲባልም በሰው ሰውኛው ለእኛ የሚሰማንን ዓይነት ሕመም ማለትም የራስ ምታት የሆድ ቁርጠት የእጅ ወይም የእግር ቁርጥማት ሳይሆን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ዘር ሁሉ ከዲያብሎስ ቁራኝነት ለማላቀቅና ከሲኦል ባርነት ነፃ ለማውጣት ወዶ ፈቅዶ የተቀበላቸውን ጸዋትወ መከራ ነው። ፍቅር ሰሐቦ ለወልደ ኃያል እመንበሩ ወአብጽሖ እስከ ለሞት እንዲል ቅዳሴ ማርያም የእርሱ ሕማም ስለኃጢያታችን በፍቅር የሆነ መስዋዕትነት ነው። በመሆኑም አስራ ሦስቱን ሕማማተ መስቀል ተቀበለ።
መ) ሰትየ ሐሞት፦
=============
ይህ ሕማምና መከራ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በመልዕልተ መስቀል ላይ ሳለ ተጠማሁ ባለ ጊዜ መራራ ሐሞትና ከርቤን መጠጣቱን የሚያሳይ ክፍል ነው፤ መተርጉማነ መጽሐፍ እንደሚገልጹት ክርስቶስ መራውን ወይን በሰጡት ጊዜ ተጎንጭቶ ተፋው እንጅ አልጠጣውም እናንተም መራራ የሆነውን ኃጢያትን ርኩሰትን አትጠጡ በንስሐ አስወግዱት ትፋት፤ " ይልቁንስ አስጸያፊና የረከሰ ኃጢያትንም እንደውሃ የሚጠጣ ሰው ምንኛ ያንስ?(ኢዮ ፲፭ ፣፲፮) " ተብሎ እንደተፃፈ ፤አንድም ቂምን በቀልን አትያዙ ጸባችሁ ወይም ቁጣችሁ ፀሐይ እስኪገባ ይሁን ፤መራርነትና ቁጣን ትፉት አስወግዱት ሲል ለአብነት ነው። (ኤፌ፬፣፴) በሌላው ተጠማሁ ማለቱ አንድም የሚጠማ ሥጋን እንደተዋሐደ ሲያመለክት እንጅ በመለኮቱማ መጠማት የለበትም፤አንድም አዳምን ተገብቶ ነው ጽድቅን ልምላሜን ተጠምሁ ያለው ነቢዩ ኢሳይያስ "ጽድቃችን እንደ መርገም ጨርቅ ሆነ ሁላችን በድለናል ንፋስ ጠርጎ እንደሚወስደው ነፋስ ሆነናል" ኢሳ ፷፬፣ ፭ እንዲል። አስቀድሞ በመዝ ፷፰፣፳፩ ለመብሌ ሐሞት ሰጡኝ፡ ለጥማቴም ሆምጣጤ አጠጡኝ " ብሎ ነቢዩ ዳዊትን ትንቢት ያናገረ የነቢያት አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ የመጽሐፉ ቃል ይፈጸም ዘንድ ተጠማሁ ባለ ጊዜ አይሁድ ሆምጣጤ ተሞልቶበት ተቀምጦ ከነበረው ዕቃ ሆምጣ ጤውን በሰፈነግ አድርገው መራራ ሐሞት ሰጡት ወደ አፉም አቀረቡለት። ውሃ አጠጡኝ ቢላቸው በሐሞት የተደባለቀ የወይን ጠጅ ሊጠጣ አቀረቡለት ፣ሰይጣን በክርስቶስ ላይ ልባቸውን አከፋ ፣ ቀምሶም ሊጠጣው አልወደደም።(ማቴ፳፯ ፣፴፬)
ጌታችንም ሆምጣጤውን ከተቀበለ በኋላ ተፈፀመ አለ ። ራሱንም አዘንብሎ ነፍሱን አሳልፎ ሰጠ።ማቴ ፳፯ ፣፵፰ ። ማር፲፭ ፣፴፮። ሉቃ ፳፫ ፣፴፮።ዮሐ ፲፱ ፣፳፱
ቢጠጡት ለዘላለም የማያስጠማ የሕይወት ውኃ የሚሰጥ አምላክ ፣ የተጠማችውን ነፍስ የሚያረካ ጌታ ፣ ለዘላለም የሚፈልቅ የሕይወት ውሃ ምንጭ የሚያድል ፈጣሪ፣ አፍላጋትንና ውቅያኖስን በእፍኙ የሰፈረ ፣በተጠማ ጊዜ የፈጠረውን ውሃ እንኳ የሚያጠጣው የሚያቀምሰው አልተገኘም።
(ኢሳ ፵፮ ፣፲፬ ።ኢሳ ፶፭ ፣፩ ።መዝ ፳፪)
እስራኤል አርባ አመት ሙሉ በቃዴስ በረሃ ኳትነው ለነበሩ አባቶቻቸው። ከሰማይ መናን አውርዶ የመገበ ውሃን ከዓለት አመንጭቶ ያጠጣቸው ክርስቶስ ያ የሕይወት ውሃ ያፈለቀ ዓለት በተጠማ ጊዜ ቀዝቃዛ ውሃ ነፈጉት። (ዘዳ፲፮ ፣፩-፳ ።፩ኛ ቆሮ፲ ፣፫) ጠልን ለደመና ዝናማትን ለዘር ሰጥቶ ምድርን በዝናማት የሚያረሰርስ የባሕር ባለቤት ፈጣሪ በውሃ ጥም ተቃጠለ። መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሲኦል በረሃ ወድቀው በሕይወት ውሃ ጥም የተቃጠሉትን ነፍሳት ለማርካት ሲል እርሱ ተጠማ። በኃጢያት ወድቀው በበደል ረክሰው በነፍሳቸው ተጎሳቁለው መራራ መከራ የሚቀበሉትንና ምረ ረ ገሃነም አፉን ከፍቶ ሆዱን አስፍቶ የሚጠብቃቸውን ሁሉ ለማዳን መራራ ሐሞትን ቀመሰ ሆምጣጣውንም እንዲሁ። በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ ሕመማችንም ተሸከመ እንዲል ነቢዩ የመረረውን የሰው ልጆች ሕይወት ለማጣፈጥ እርሱ መራ ራውን ተጎነጨ ።
(ኢሳ ፶፫ ፣፭)
-----------------------------------------------------------------------------------------------------
ኪይሪያላይሶን ፣ኪይሪያላይሶን ፣ኪይሪያላይሶን (፲፪×)
ይቆየን
No comments:
Post a Comment