Sunday, April 10, 2016

ሰሙነ ሕማማት --(ክፍል-ሁለት)


ነስአ ደዌነ ወፆረ ሕማመነ
-------------------------
እናት የወለደችው ልጇን እንደምታዝል አምላካችን እኛን ፍጥረቶቹን በተለይም በአርአያውና በአምሳሉ የፈጠረንን ልጆቹን ከልጅነት እስከ እውቀት ከነኃጢያታችን በማይዝል ትከሻው ተሸክሞ የሚያኖረንን መጋቢና ኤልሻዳይ አምላክ አይሁድ በእለተ አርብ መከራ አጸኑበት ተዘባበቱበት ። የአዳም ዘር ክብር ጎድሎት ጸጋው ተገፎ ከሰውነት ተራ ቢወጣ እሱ ሥግው ሆኖ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተገለጠ እንደሰው እየተመላለሰ እንደ እግዚአብሔር ሰራ የሰውን ስብዕና ይመልስ ዘንድ ድውያኖቻቸውን ቢፈውስ እውራኖቻቸውን ቢያበራ እነሱ ግን ሰንበትን ሻረ ብለው ክስ መሰረቱበት ፣ ችግራቸውን ይፈታ ዘንድ መናን አበርክቶ በመገባቸው ግፈኞች አይሁድ ግን የበሉበትን ወጪት ሰበሩ በጠላትነት ተነስተው ንጹህ ደም አፈሰሱ( መዝ ፵ ፣፱) ። ስለ በደላችንና ስለ ኃጢያታችን አስራ ሦስት ሕማማተ መስቀልን ተቀበለ። መከራ መቀበሉስ እንዴት ነው ቢሉ በአባቱ ፈቃድ በራሱ ፈቃድ በባሕሪ ሕይወቱ በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ፍቅር አገብሮት የፍጥረቱ የአዳም ነገር ግድ ስለሆነበት እንጅ እሱ የልዑላን ልዑል የማይገሰስ የማይደፈር ነው ።

ሠ) ተቀስፎ ዘባን ( ጀርባውን፣ትከሻውን ተገረፈ)
-----------------------------------------------
ስለ አዳምና ስለ ልጆቹ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁለተኛው አዳም ጀርባው እስኪላጥ ያለርኅራኄ በክፉዎች በአይሁድ ተገረፈ። በአይሁድ ህግ የተገረፈ አይሰቀልም፣ የሚሰቀል ደግሞ አይገረፍም ነበር ጲላጦስ ግን ኢየሱስ ክርስቶስን አስገረፈው ፣ይሰቀልም ዘንድ ከደሙ ንጹህ ነኝ ብሎ እጁን ከታጠበ በኋላ ንጹሀ ባህሪ ክርስቶስን ያለኃጢያቱ ለአይሁድ አሳልፎ ሰጠው ። (ማቴ፳፯ ፣፳፮ ማር ፲፭ ፣፲፭ ዮሐ ፲፱፣ ፩) ክብር ይግባውና ኢየሱስ ክርስቶስ በመንፀፈ ደይን ወድቆ በእግረ አጋንንት እየተጠቀጠቀ በእሳት አለንጋ የሚገረፈውን የሰውን ልጅ ለማዳን ሲል ጀርባውን ለግርፋት ሰጠ። ሥጋው አልቆ አጥንቱ እስኪቆጠር ተገረፈ ። ትላንት መና አበርክቶ የመገባቸው ከደዌያቸው የፈወሳቸው ድውያነ ሥጋ የቃሉን ትምህርት የተማሩ የእጁን ተአምራት ያዩ ድውያነ ነፍሳት ሁሉም ውለታውን ረስተው ፤ በደንባቸው በየአመቱ አንድ እስረኛ ይፈታላቸው ነበረና ፣ ጲላጦስ ወንበዴና ቋንጃ ቆራጭ የነበረውን በርባንን ልፍታላችሁ ወይስ ኢየሱስን ቢላቸው በርባንን ፍታልን ኢየሱስን አስወግደው እሰረው ከዚያም ብሶ ፈጽመፍ በክፋት ይሰቀል ይሰቀል አሉ። ዳሩ መድኃኔዓለም ትንቢቱ ይፈጸም ዘንድ ለድኅነተ ዓለም መጥቷልና በዳዊት መዝሙር ዐገቱኒ ከለባት ብዙኃን ወአኃዙኒ ማኅበሮሙ ለእኩያን ተብሎ እንደተጻፈ (መዝ ፳፩፣ ፲፩)ሁሉ በእርሱ ሆነ። አይሁድ ችግራቸውን ሊያስወግድ ነውራቸውን ሊያንከባልል ከእስራታቸው ሊፈታ የእግዚአብሔር ልጅ ሥግው ሆኖ ቢመጣ ፣ራሱን ከወህኒ ማውጣት የማይችለውን ወንበዴው መርጠው መድኃኒትን ግን አሰሩ።አስቀድሞ በነቢዩ በኢሳይያስ "ጀርባዬን ለገራፊዎች ጉንጬንም ለጠጉር ነጪዎች ሰጠሁ" (ኢሳ፶ ፮) ተብሎ እንደተነገረ ጌታችን ጀርባውን ለገራፊዎች አሳልፎ ሰጠ ፤ ጽህሙንም ተነጨ። የሚገርመው ነገር እስከዛሬ ድረስ ዓለማችን በወንበዴዎችና በአሸባሪዎች እየተጨነቀች ያለችው በዚያን ዘመን፤ በተወደደችው ዓመት የሰው ልጅ ከሚያድነው አምላክ ይልቅ የሚገርፈውን የሚዘርፈውን ወንበዴ መርጦ ስለተገኘ ነው።





ረ) ተዐርቆተ ልብስ ፡- ( ልብሱን ተገፈፈ ተራቆተ)
--------------------------------------------------------
ተዐርቆት፣ልብስን መራቆት ዕርቃንን መሆን ማለት ሲሆን ፤ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጸጋ ሁሉ ምንጭ ሆኖ በአይሁድ እርቃኑን መዋሉ ከአስራ ሦስቱ ሕማማት አንዱ ነው። ግሩም ትዕግስት ፀሐይና ከዋክብትን ብርሃን አልብሶ የፈጠረ እርሱ ምንም ምን የማይቀርበው ብርሃን አምላክ ተራቆተ። ጸጋውን ለዕሩቃን የሚያለብስ አምላክ በደካማው ሰው ሥግው
ሆኖ ተገልጧልና ልብሱን ተገፈፈ። ምድርን በዕፅዋትና በውብ አበባዎች ያስጌጠ እርሱ ልብሱን ተገፎ ራቁቱን ቆመ። በኃጢያቱና በበደሉ ምክንያት ጨለማን ለብሶ በመንጸፈ ደይን በአጋንንት ጨልሞበት የነበረውን የአዳም ዘር መልሶ ብርሃን ያለብሰው ዘንድ የብርሃናት ጌታ የጸጋ ሁሉ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ተገፈፈ፣ ተራቆተ። መተርጉማነ መጽሐፍ ሊቃውንት እንደሚያስተምሩት የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰናፊሉ ፣እጀ ጠባቡ አንድ ወጥ የሆነ በግዕዘ ሕፃናት እንደ ለበሰው እሱ በሞገስና በጥበብ ሲያድግ አብሮ በይዘት እየጨመረ ለ፴፫ዓመት የቆየ ነው። ጲላጦስ ጌታችንን አሳልፎ በሰጠቸው ሰዓት የአይሁድ ወታደሮች ልብሱን ገፈፉት፣(ማቴ ፳፯ ፣፳፯) የሲኦል ወታደሮች ዲያብሎስና ሰራዊቱ የሰውን ልጅ ጸጋ ገፈውት ነበርና የተራቆተውን የአዳም ዘር ጸጋ ክብር ያለብስ ዘንድ እርሱ እርቃኑን ሆኖ ዋለ ተራቆተ።


ሰ) ርግዘተ ገቦ (ጎኑን በስለታም ጦር ተወግቷል)
------------------------------------------
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ከሰጠ በኋላ ጎኑን በስለታም ጦር ተወግቷል፣ ይህም ከአስራ ሦስቱ ሕማማት አንዱ ነው።አይሁድ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ አጠገብ በግራና በቀኙ ሁለት ወንበዴዎችን አብረው ሰቀሉ። እነዚህም ወንበዴዎች ጥጦስና ዳክርስ የሚባሉ ሲሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግማዊት ኪሩቤል በተባለችው በድንግል ማርያም ጀርባ ታዝሎ ወደ ግብፅና ኢትዮጵያ በተሰደደበት ወራት በበረሃ ውስጥ እየተዘዋወሩ በሚዘርፉበት ወራት ጌታችን ከእናቱ ጋር አግኝተውት እንደነበር የቤተክርስቲያን ታሪክ ይነግረናል። በስቅለቱ ዕለት የእነዚህ ወንበዴዎች ሥጋቸው በሰንበት በመስቀል ላይ እንዳይኖር ጭናቸው ተሰብሮ እንዲወርዱ አይሁድ ጲላጦስን በጠየቁት መሠረት ጭፍሮቹ የሁለቱን ወንበዴዎች ጭናቸውን ሰብረው ከመስቀል ካወረዱ በኋላ ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲመጡ ፈጽሞ እንደሞተ አይተው ጭኑን አልሰበሩም። ይህም ከአጥንቶቼ አንዳች አልተሰበረም የሚለው የዳዊት ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ነው። (ዮሐ ፲፱ ፣፳፮)
ነገር ግን ከጭፍሮቹ አንዱ ጎኑን በጦር ስለወጋው ወዲያው ከጎኑ ደምና ውሃ በአንድ ላይ በለ ፊደል ቅርጽ ፈሰሰ። ይህውም በውሃው ተጠምቀን ደሙንም ጠጥተን ፍጹም ድኅነት አግኝተን መንግስቱንና ርስቱን እንወርሳለንና። (ዮሐ ፲፱ ፣፴፫)
አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል ያደርገው ዘንድ ሞተ የሲዖልን ድል መንሳት ያሸንፍ ዘንድ በአካለ ነፍስም በዕለተ አርብ ወደ ሲኦል ወርዶ ምርኮን ማረከ። (፩ ጴጥ ፫፣ ፲፰)
የሰው ልጅ በዘላለማዊ ሞት ተይዞ ነበርና።
ትልቁ ሞት በኃጢያት ምክንያት ከእግዚአብሔር መለየት ነው። በጌታችን ሞት ሞት ድል ተነሣ ። የሞት መውጊያ በሆነ ኃጢያት የሞተውን ሰው ለማዳን ጎኑን በጦር ተወጋ በሰው ልቡና ተተክሎ የነበረውን ኃጢያት ከነስሩ ነቅሎ ስለጣለው ሞት ሆይ መውጊያህ የት አለ? ተብሎ የተፃፈው ትንቢት ተፈጸመ።የሞት መውጊያው የሲኦልም ድል መንሻው ኃጢያት ነበርና። (ኢሳ ፳፭፣ ፰ ፤ ሆሴ፲፫ ፣፲፬ ፤ ፩ ቆሮ፲፭ ፣፶፬)
ከተወጋው የጌታንችን ጎን ደምና ውሃ መፍሰሱም የእግዚአብሔርን ልጅነትና የዘላለም ሕይወት አጥቶ የነበረውን ሰው ልጅነቱንና ሕይወቱን እንደተመለሰለት የሚያረጋግጥ ነው።ምክንያቱም ከጎኑ በፈሰሰው ውሃ ተጠምቆ ልጅነትን ደሙንም ጠጥቶ የዘላለም ሕይወትን ያገኛልና። (ዮሐ፫፣ ፭ ዮሐ ፮ ፣፶፬)


ሸ) ተአሥሮተ ድኅሪት(እጆቹን ወደ ኋላ የፊጥኝ ታሰረ)
------------------------------------------------
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁለት እጆቹን እንደ ወንጀለኛ ወደ ኋላ የፊጥኝ ታሰረ። አሳሪውን አስሮ እስረኞችን ከወኅኒ ሊያወጣ የመጣው እሱ በደካሞች በአይሁድ እጆቹን ታሰረ ። (ኢሳ ፷፩ ፣፪) አዳምን በመዳፉ ቀርጾ በእጆቹ አበጅቶ ከምድር አፈር የሰራ እሱ እጆቹ በአመፀኞች ታሰሩ። መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጊዜው በደረሰ ሰዓት ራሱን ለአይሁድ አሳልፎ በሰጠባት ዕለት ሻለቃውና ጭፍሮች የአይሁድም ተላላኪ ሎሌዎች እጁን የኋሊት አስረው መሬት ለመሬት ጎተቱት። አዳምና ልጆቹን ከውድቀት ሊያነሳ ቢመጣ አይሁድ ከውድቀት የሚያነሳውን ጣሉት ተሳለቁበት አፍገመገሙት። (ዮሐ ፲፰ ፣፲፪) በኃጢያት ሰንሰለት የኋሊት ታሥሮ። ጠላት ዲያብሎስ ሲያፍገመግመው የኖረውን የሰውን ልጅ ለማዳን ሲል መድኃኔዓለም ክርስቶስ በጠላቶቹ አይሁድ እጅ የኋሊት ታሠረ ፤ የሰውን ልጆች ከኃጢያት እሥራት ይፈታ ዘንድ የማይታሠረው ታሠረ።


ቀ) አምስቱ ቅንዋተ መስቀል፦( እጅና እግሮቹን በአምስቱ ቅንዋተ መስቀል ሳዶር ፣አላዶር ፣ሮዳስ ፣ዳናት ፣አዴራ ተቸነከረ)
-------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
መድኃኒታችን በመስቀል ላይ የተቸነከረባቸው ጠንካራ የብረት ችንካሮች ምስማሮች ቅንዋተ መስቀል ይባላሉ ። ቀነወ ቸነከረ ከሚለው የግዕዝ ግስ የተገኘ ነው። አይሁድ ጌታችንን በተመሳቀለ እርጥብ ዕፅ -እንጨት ላይ እጅና እግሮቹን በአምስቱ ቅንዋተ መስቀል ሳዶር ፣አላዶር ፣ሮዳስ ፣ዳናት ፣አዴራ ቸነከሩት። የሃይማኖታችሁ መሠረት አምስቱን አዕማድ መሠረትኩላችሁ ሲል በአምስቱ ቅንዋት ተቸነከረ አንድም ፭ሺህ ፭መቶ ዘመን የሰው ልጆችን በሞት በሲኦል እየቀጠቀጠ ያኖረውን ዲያብሎስንና ሰራዊቱን 
በአምስቱ ቅንዋት ተቸንክሬ ስድስተኛም ስምንቱን ሕማማት ተቀብየ ከእግራችሁ በታች ቀጠቀጥኩላችሁ ሲል በአምስቱ ቅንዋት ተቸነከረ። በትንቢት ሰው ሁሉ በእጆችህ መካከል ያለው ቁስል ምንድን ነው ይለኛል? እሱም በወዳጆቼ ቤት ስለወዳጆቼ የቆሰልኩት ነው ይላቸዋል ተብሎ የተፃፈው ይፈጸም ዘንድ እጆቹን ና እግሮቹ የአዳምና የልጆቹ ፍቅር ግድ ብልሎት ተቸነከረ። እሱ ድኅ ያይደለ ባለጸጋ ጌታ ፍጡር ያይደለ የፈጠረውን ሥጋ ገንዘብ ያደረገ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ብሎ ተናቀ ። ነቢዩ ኢሳይያስ እንዳለ የሕማም ሰው ደዌንም የሚያውቅ ሆነ።በዚህ ሁሉ መከራ መስቀል ውስጥ በእውነት ደዌያችንን ተቀንበለ ሕማማችንንም ተሸከመ። የሰውን ልጅ ለማዳን ማለትም እኛን ከደዌ ሥጋ ከደዌ ነፍስ ይፈውሰንና ከሕማመ ሥጋ ከሕማመ ነፍስ ሥቃይ ያሳርፈን ዘንድ እርሱ ተሰቃየ።
ቁስለ ኃጢያታችን ያርቅልን ዘንድ ስለ መተላለፋችን ቆሰለ ።በእውነት በእርሱ ቁስል እኛ ተፈወስን።በደላችን ይደመስስ ዘንድ ስለ በደላችን ደቀቀ ።ሊያረጋጋን ተጨነቀ ሊያሳርፈን ተሰቃየ።አፉንም አልከፈተም፤ የእግዚአብሔር የመስዋዕቱ በግ ኢየሱስ ክርስቶስ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት በሸላቾቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ እንዲሁ አፉን አልከፈተም። መልካሙ እረኛ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከጽድቅ በቀር ነውር ነቀፋ ግፍና ኃጢያት አልተገኘበትም (ዮሐ፰፣ ፴፬)
ልብንና ኩላሊትን የሚመረምር አምላክ ወሰብዕ ወልድ ዋሕድ ኢየሱስ ክርስቶስ በጲላጦስ በተመረመረ ጊዜ በአፉም ተንኮል አልተገኘበትም።


--------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ኪሪያላሶን ፣ኪሪያላሶን ፣ኪሪያላሳን (፲፪×)

2 comments:

  1. አምስቱ ቅንዋተ መስቀል የተቸነከሩበት የሰውነት ክፍል ቢብራራ በተለይ አዴራ ና ሮዳስ በተለያዩ መጻሕፍት ልዩነት ስላለ

    ReplyDelete
  2. ለልጄ ሳዶር የሚል መጠሪያ ሰጠኋት። በኔ እይታ የጌታን ስቃይ ሁሌም በህሊናዬ በልጄ ለማስታወስ እንዲሁም ጌታ በቅንዋተ መስቀሉ እኔን ከሃጢአት እንዳነፃኝ ለማሰብ ብዬ ነው። ይሁንና ክርስትና አጥማቂው እንዴት ሳዶር ትላላችሁ ብሎ አሳጣኝ። በእውነት ጥፋቴ ምን ይሆን? ሳዶርስ ሌላ ድብቅ ትርጓሜ ይኖረው ይሆን???

    ReplyDelete