ኒቆዲሞስ :
የአብይ ጾም ሰባተኛ ሳምንት
------------------------------------------
ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ መንግስተ ሰማይን አይወርስም::(ዮሐ ፫፣ ፫)
=======================================
ወሀሎ አሐዱ ብእሲ እምፈሪሳውያን ዘስሙ ኒቆድሞስ ። ብዙኃን አምኑ ቦቱ ብሎ ነበርና ብዙኃን ካላቸው ከፈሪሳውያን ወገን የሚሆን ኒቆዲሞስ የሚባል አንድ ሰው ነበር ። መጽሐፍ ይህን ሰው መልአኮሙ ለአይሁድ ይለዋል። መልአክ ማለት አለቃ ማለት ሲሆን ፤ ኒቆዲሞስ የአይሁድ አለቃ የተባለበት ምክንያት አንድም በትምህርቱ በዳኝነት ወንበር ላይ ተቀምጦ ይፈርድ ስለነበር፣ አንድም በሹመቱ የአይሁድ አለቃ ስለነበር፣
አንድም በሃብቱ በንብረቱ ባለጸጋ ስለነበር ነው።
ወውዕቱ መጽአ ኅበ እግዚእ ኢየሱስ ቀዲሙ ሌሊተ። አስቀድሞ በሌሊት በመከራ ሰዓት ወደ ጌታ የመጣ በኋላ የጌታን ሥጋ ከመስቀል አውርዶ የሚገንዝ እሱ ነውና፣ አንድም በሌሊት የመጣ ማለቱ በመዓልት ከሚመጡት አስቀድሞ ለማለት ነው። አንድም ሌሊት ወይም ጨለማ ያለማመን ምሳሌ ነውና ከማመን አስቀድሞ በሚጠራጠርበት ባላመነበት ዘመን ለማለት በሌሊት አለ፤ አንድም ውዳሴ ከንቱን ሽቶ የአይሁድ ህግ አዋቂ የኦሪት መምህርም ነበርና ፣ መምህር ነኝ እያለ እስከዛሬ ትምህርት ሳይከተትለት ኑሯል ይሉኛል ብሎ፤ አንድም አንድም የቀን ልቡና ባካና ነውና በጥዋት በሌሊት ትምህርት እንዲረዳው፣ በሌላው ግን ሌሊት እየመጣ ይማር የነበረው አሁድ እመቦ ዘአምነ ቦቱ ከመ ክርስቶስ ይሰደድ እምኩራብ ብለው አዋጅ ነግረው ነበርና መከራውን ስለፈራ ነበር።
ኒቆዲሞስም ጌታችንን ረቢ ነአምር ከመ እምኅበ እግዚአብሔር መጻእከ ከመ ትኩን መምህረ፤ አላመነም ብሎ መምህር ሆይ ከእግዚአብሔር ታዝዘህ ልታስተምር እንደመጣህ እናውቃለን። እስመ አልቦ ዘይክል ይግበር ዘንተ ተአምረ ዘአንተ ትገብር። አንተ የምታደርገውን ተአምራት ሊያደርግ የሚቻለው የለምና ፤ ኢይክል አሐዱሂ ይላል አንድስ እንኳ ሊያደርገው አይቻለውምና ። ዘእንበለ እግዚአብሔር ምስሌሁ እግዚአብሔር ካደረብህ ካንተ በቀር። አንድም አምኑዋል ብሎ መምህር ከእግዚአብሔር አካል ዘእምአካል ባሕርይ
ዘእምባሕርይ ተወልደህ ልታስተምር እንደመጣህ እናውቃለን፤ አንተ የምታደርገውን ተአምራት ሊያደርገው የሚቻለው የለምና ዘእንበለ ዘእግዚአብሔር በህልውናው ከርሱ ጋራ ካለህ ካንተ በቀር።
ጌታችንም መልሶ እንዲህ አለው አማን አማን ዕብለከ ዘኢተወልደ ዳግመ ኢይሬእያ ለመንግስተ እግዚአብሔር ። ዳግመኛ ያልተወለደ ሃይማኖትን አያውቃትም ብዬ እንዳያውቃት በእውነት እነግራችኋለሁ ። ሃይማኖት አይቀድምም ልጅነት አይከተልም ቢሉ ወአልቦ ዘይክል ብሂለ እግዚእ ኢየሱስ ዘእንበለ መንፈስ ቅዱስ ላዕሌሁ እንዲል፤ መጽናቱን መጉላቱን መገለጡን ሲያይ እንዲህ አለ እንጂ እውነት ነው ሃይማኖት ይቀድማል ልጅነት ይከተላል። ያመነ የተጠመቀ ይድናል ተብሎ በወንጌል እንደተጻፈ። ማር ፲፮ ፣፲፮
አንድም ዳግመኛ ካልተወለደ መንግስተ ሰማይ አይወርስም ብዬ እንዳይወርስ በእውነት እነግርሃለሁ ። ያልተካከለ ዳግመ ነው ለልደተ ሥጋው ልደተ ነፍሱን ዳግም አለው። በሌላው የተካከለ ዳግመ ልደተ ነፍሱን ለልደተ ነፍሱ ዳግመ አለው።ኒቆዲሞስ ግን ነገሩ ስላልገባው ምስጢሩ ስለረቀቀበት ፤ እፎ ይክል ብእሲ ዳግመ ተወልዶ እምድኅረ ልኅቀ ፤ካደገ ካረጀ ካፈጀ በኋላ ለሰው ሁለተኛ መወለድ እንደምን ይቻለዋልን? ሁለተኛስ ይወለድ ዘንድ ወደ አባቱ አብራክ ወደ እናቱ ማኅፀን መግባት ይቻለዋልን? አንድም ይገባዋልን?
ጌታችንም እንደገና መልሶ፤ አማን አማን ዕብለከ ዘኢተወልደ ዳግመ እማይ ወእመንፈስ ቅዱስ ኢይክል በዊዓ ውስተ መንግስተ እግዚአብሔር። ልደቱን ነግሮት መወለጃውን አልነገረውም ነበርና ሁለተኛ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማህፀነ ዮርዳኖስ ካልተወለደ መንግስተ ሰማያት መግባት አይቻለውም ብዬ እንዳይቻለው በእውነት እነግርሃለሁ። የሥላሴን አንድነት ሦስትነቱን በዚህ ነገረው
እማይ ብሎ ወልድን እመንፈስ ቅዱስ ብሎ መንፈስ ቅዱስን መንግስተ እግዚአብሔር ብሎ እግዚአብሔር አብን አምጥቶ አስተማረው። እስመ ዘተወልደ እምሥጋ ሥጋ ውዕቱ፤ ከግዙፉ ሥጋ የሚወለድ ግዙፍ ነውና ነገር ግን ወዘተወልደ እመንፈስ መንፈስ ውዕቱ ከረቂቅ መንፈስ ቅዱስ የምትወለድ ነፍስ ረቂቅ ናትና፤ ስለዚህም ወበእንተዝ ኢታንክር እስመ ዕቤለከ ሀለክሙ ትትወለዱ ዳግመ፤ ሁለተኛ ትወለዱ ዘንድ አላችሁ ስላልኩህ አታድንቅ ትወለዱ ዘንድ ግድ ነውና ምክንያቱም ነፋስ በወደደው እንሚነፍስ ነገር ግን በዓይነ ሥጋ እንደማይታይ ነገር ግን ባሕር ሲገሥፅ ዛፍ ሲናውጽ ድምጹን ብቻ ትሰማለህ፤ የሚመጣበትንም የሚሄድበትንም አታውቅም በምዕራብ ፮ በምስራቅ ፮ መስኮቶች አሉት በዚህ ይወጣል በዚህ ይገባል አትለውም ፤ከማሁኬ ውእቱ ኲሎ ዘይትወለድ እመንፈስ ቅዱስ ፤ ከማሕፀነ ዮርዳኖስ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ የሚወለዱት ልደት እንዲሁ ነው። መንፈሰ ረድኤት ፣የእግዚአብሔር መንፈስ በወደደው ያድራል ትንቢት ሲያናግር ሱባኤ ሲያስቆጥር ትሰማዋለህ ፤ ሀብተ ሙሴ በኢያሱ ሀብተ ኤልያስ በኤልሳዕ ሲያድር ግን አታውቅም። ከመንፈስ ቅዱስ የሚወለዱትም ልደት እንዲሁ ነው። አንድም መንፈስ ቅዱስ በወደደው ያድራል ቋንቋ ሲያናግር ምስጢር ሲያስተረጉም ትሰማዋለህ ነገር ግን ከወዲያ አለ ከወዲህ የለም ፣ ከወዲህ ወዲያ ይሄዳል አትለውም ከመንፈስ ቅዱስ የሚወለዱትም ልደት እንዲሁ ነው እልሃለሁ።
___________________________________
No comments:
Post a Comment