Saturday, April 9, 2016

ተዘጋጅታችሁ ኑሩ ፣(ማቴ ፳፬ ፣፵፪)

ደብረ ዘይት 


የዓብይ ጾም ፭ኛ ሳምንት

ትግሁ እንከ እስመ ኢተአምሩ በዓይ ሰዓት ይመጽእ እግዚእክሙ።(ማቴ ፳፬ ፣፵፪)
===============================================
ወእንዘ ይነብር እግዚእነ ውስተ ደብረ ዘይት ቀርቡ ኅቤሁ አርዳኢሁ ፤ ጌታችንና መድኃኒታችን በደብረዘይት ተቀምጦ ሳለ ደቀመዛሙርቱ ወደሱ ቀርበው ፤ ወይቤልዎ እንተ ባሕቲቶሙ ፤ለብቻቸው ጠየቁት ፡ ንገረነ ማዕዜ ይከውን ፡ -
1)ዝንቱ ወናሁ ይትኃደግ ለክሙ ቤትክሙ በድወ ብሎ ነበርና፤ህንፃ በህንፃ ላይ ሳይፈርስ አይቀርም
2) ወምንትኑ ተአምሪሁ ለምጽአትከ ፣ አማን እብለክሙ ኢትሬእዩኒ፣ የሰውን ልጅ በክብሩ ሲመጣ ታዩታላችሁ ብሎ ነበርና
3) የመምጫህስ ወለኀልፈተ ዓለም ፣ የኀልፈተ ዓለምስ ምልክቱ ምንድን ነው? አሉት።
ጌታችንም የዓለምን መጨረሻና የመምጣቱን ምልክት በዝርዝር አስተማራቸው ፣ ወአውሥአ ወይቤሎሙ 

፩) ዑቁ ኢያስሕቱክሙ።ኤፍ ፭፣፮
___________________________
እንዳያስቷችሁ አስተውሉ አላቸው፤
እስመብዙኀን ይመጽኡ በስምየ እንዘ ይብሉ አነ ውእቱ ክርስቶስ ፤ እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ ብዙ ሰዎች በስሜ ይነሳሉና ፣ በሀገራችን በአማራ ሳይንት እኔ ክርስቶስ ነኝ ብሎ፤ ሰባት መቶ የሚያክሉ ስዎችን ይዞ ተነስቶ ሰቅለው ገድለውታል እነሱንም አጥፍተዋቸዋል፤ ወያስሕትዎሙ ለብዙኃን ፣ እንዲህ ዓይነቶቹ ብዙዎችን ያስታሉ።ሌሎችም መናፍቃኑ ሃይማኖት ለዋጮች ይነሳሉ ሰይጣን የብርሃን መልእክ እንዲመስል እውነተኞችን መምህራን መስለው ወንጌል ይዘው ፤ጌታችን የበግ ለምድ ለብሰው እንዲል ፡ ወንጌላውያን መስለው ይመጣሉ ነገር ግን አሳቾች ናቸውና ከሐሳውያን መምህራን ተጠንቀቁ።
፪) ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ ዘንድ ግድ ነውና ፣ ዑቁ ኢትደንግጹ፤
___________________________________
ይህ በሆነ ጊዜ አትደንግጡ፣ የዜና ማሰራጫዎች ጋዜጣዎች ድህረ ገጾች ዛሬ መልካምን ወሬ አያሰሙም ይህ ምልክቱ ነው አስተውሉ፤
፫) ወይትነስኡ ሕዝብ ዲበ ሕዝብ፤
_________________________________
ሕዝብ በሕዝብ ላይ ይነሳል ወገን በወገኑ ላይ ይነሳል ብሔር በብሔር ላይ ይነሳል ተነጋግሮ መግባባት ተወያይቶ መስማማት ከሁሉም አስተዋይነት ይጠፋል ፣ ይህ ሁሉ ግን የምጥ ጣር መጀመሪያ ነው የሐሳዊው መሲህ መንገድ መጥረጊያ ነውና አስተውሉ፤
፬) በክርስቲያኖች ላይ ጽኑ ፈተናና መከራ ይመጣል ፤
___________________________________
አሜሃ ይትባጽሑክሙ ወይሜጥውክሙ ለምንዳቤ፣ ያን ጊዜ ለጸዋትዎ መከራ አሳልፈው ይሰጧችኋል ፣ ወይቀስፉክሙ ወይቀትሉክሙ ፤ ይገርፏችኋል ይገድሏችኋል። ወትከውኑ ጽሉዓነ በኀበ ኩሉ ሰብእ በእንተ ስሜ ፤
በእኔ ስም ስላመናችሁ ስለተማራችሁ በእኔ ስም ስለተጠራችሁ ማዕተብ አድርጋችሁ መስቀሌን ስለተሸከማችሁ በሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ። ትላንትና ወንድሞቻችን በሊቢያ ሰማዕት ሆነዋል።
፭)ወይእተ ዓሚረ የዓልው ብዙኃን ሃይማኖቶሙ፤ ብዙዎች ሃይማኖትን ይለውጣሉ።
_______________________________
በዚያን ጊዜ ብዙ ሰዎች ሃይማኖታቸውን ይለውጣሉ ፣ አንድም በክርስቲያኖች ላይ ከሚመጣው መከራ የተነሳ ፈርተው ሃይማኖታቸውን ይለውጣሉ አንድም ባለመጽናት ዓለምና ምኞቷን በመሻት
አንድም ከሐሰተኛ መምህራን ከክህደት ትምህርት የተነሳ ሃይማኖታቸውን ይለውጣሉ። እርስ በእርስ ይጣላሉ ፤ ይገዳደላሉ ፣ አንዱ አንዱን ይጠላዋል።
እናንተ ግን አስተውሉ ሃይማኖታችሁን አጽኑ ምግባራችሁን አቅኑ።(ዕብ፫፧፬)

፮) ወብዙኃን ሐሳውያን ነቢያት ይመጽኡ ፤ ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያት ይነሳሉ።
__________________________________
በመምህራን የሚያብሉ መምህራንን የሚያሳብሉ የሚያሳምጹ ብዙዎችንም የሚያስቱ ነቢያትና መምህራን ይነሳሉ ብዙዎችንም ያስታሉ። እናንተ ግን በተማራችሁበት ትምህርት ጸንታችሁ ቁሙ።
፯) ወእምብዝኃ ዓመፃ ወእከይ ተሐፅፅ ፍቅር እምብዙኃን። ከዓመፃ ብዛት የተነሳ ፍቅር ከብዙ ሰዎች ትቀዘቅዛለች።
__________________________________
ከኃጢያትና ከአመፃ የተነሳ ፍቅር ከቤተስብ ከሀገር ከቤተክርስቲያን አገልጋዮች ሳይቀር ትጠፋለች። ፍቅር የኃጢያትን ብዛት ትሸፍናለች ገመናን ትከድናለች ከሁሉ ጋር በሰላም ታኖራለች ። ዛሬ ፍቅር ስለሌለ ሰላም የለም እረፍት የለም ። ቤተሰብ እየተበተነ ነው አገልጋዮች ሳይቀር በአንድ ቤት ውስጥ ፣አርአያ በመሆን ፈንታ ይበላላሉ። በሀገር ፍቅር ስለሌለ ሕዝብ ከሕዝብ ይበላላል።
እናንተ ግን አስተውሉ ይህ ሁሉ ይሆን ዘንድ ግድ ነውና።
፰) ወይሰበክ ዝ ወንጌለ መንግሥት ውስተ ኩሉ ዓለም፤ -ይህ የመንግስት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል።
___________________________________
የመንግሥት ወንጌል ማለት ጌትነቱን የምትናገር ወንጌል በአራቱም ማዕዘን ትነገራለች። በእስላም ቤትም እንኳ ሳይቀር በአሕዛብ ምኩራብ ትገኛለች ።
ይህም ሆነ ያ ግን ጌታ የሚመጣባትን ያችን ቀን ግን የሚያውቃት የለም ፣ መጽሐፍ ወበእንተሰ ይእቲ ዕለት ወይእቲ ሰዓት አልቦ ዘየአምራ እንዲል፣ ዘመኑ ዘመነ ዮሐንስ ወርኁ ወርኅ መጋቢት ዕለቱ ዕለተ እሁድ ሰዓቱ መንፈቀ ሌሊት ከመሆኑ ውጪ ምንም አይታወቅም ፣ በኖህ ዘመን የጥፋት ውሃ እስኪመጣ እንዳላወቁ ወበ ከመ ኮነ በመዋዕሊሁ ለኖህ ከማሁ ይከውን ምጽአቱ ለወልደ እጓለ እመ ሕያው ፤ ብዙዎች ይበላሉ ፣ይጠጣሉ፣ ያገባሉ ይጋባሉ ፣ ኃጥዓንን ግብረሰዶማውያንን ያመነዝራሉ፣ ይሰስታሉ ይበላላሉ ፣ይክዳሉ፣ ክፋትን ተንኮልን ይሰራሉ
ክርስቶስ ግን ሳይዘጋጁ በድንገት ባላሰቡት ሰዓት ይመጣባቸዋል። እንግዲህ ይህንን እወቁ ባለቤት በየትኛው ሰዓት ሌባ እንዲመጣ ቢያውቅ ኖሮ ነቅቶ በጠበቀ ።
ወበእንተዝ አንትሙኒ ድልዋኒክሙ ሀልው (ንበሩ)፤
የሰው ልጅ የተባለ ክርስቶስ ባልጠረጠራችሁት ዕለት ባላወቃችኋት ሰዓት ይመጣልና ንስሐ ገብታችሁ ሃይማኖታችሁን አጽንታችሁ ምግባራችሁን አቅንታችሁ ለንስሐ የሚገባ ፍሬን እያፈራችሁ ቅዱስ ሥጋውን በልታችሁ ክቡር ደሙን ጠጥታችሁ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ።

No comments:

Post a Comment