Saturday, April 23, 2016

ሆሳዕና





እስራኤላውያን ጌታ የተቀመጠባት አህያ አከበሩ፡ ይህ ትውልድ ግን ጌታ የተቀመጠባት እመቤታችን ማክበር ተሳነው፡፡(ማቴ ፳፩፤ ፩፣ ፱)
============================================================================
• ጌታችን የታሰሩ አህዮች ለምን መረጠ?
•ሐዋርያት ለምን ልብሳቸው አነጠፉለት ?
• ጌታ ለምን በፈረስ ላይ አልተቀመጠም?
•ዘንባባ የምን ምሳሌ ነው?
• በሆሣዕና በእጃችን እደ ቀለበት ማሰራችን የምን ምሳሌ ነው?
---------------------------------------------------------------------

ቤተ ፋጌ የድሆች መንደር ናት፡- ጌታ የድሆች መንደር ወደደ፡፡እኛ ድሆቹን ባለ ፀጋ ሊያደርገን ስለኛ ብሎ ራሱን ድሃ ያደረገ አምላክ ነውና፡፡ቤተ ፋጌ ለእየሩሳሌም በጣም ቅርብ ናት፡፡እኛም ለቤተ ክርስትያን ቅርብ መሆን አለብን፡፡
እየሩ ሳሌም ቤተ ክርስትያን ናት እንቅረባት ፡፡እየሩ ሳሌም እመቤታችን ናት እንቅረባት ፡፡ጌታ ቤተሳጌ በደረሰ ጊዜ የተመሳቀለ መንገድ ቁሞ ሁለቱን ደቀ መዛሙርቱ ላከ "ሁሩ ሃገረ ቅድመክሙ" ወደ ፊታችሁ ላለው ሃገር ሂዱ ወደ መንደሪቱ ግቡ አላቸው፡፡
በተመሳቀለ ቦታ መቆሙ፡- ወደ ፊት በመስቀል ላይ እሰቀላለሁ ሲል ነው፡፡
ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ሲልካቸው በፊታችሁ ላለው ሃገር ሂዱ ያን ጊዜ አህያ ከውርንጭላዋ ጋር ታስራ ታገኛላችሁ ፈታችሁ አምጡልኝ አላቸው፡፡
ጌታችን ብዙ ያልታሰሩ አህዮች እያሉ ለምን የታሰሩትን መረጠ?
-------------------------------------------------------------------------
አህዮቹ የታሰሩት ሌባ ሰርቆ ነው ያሰራቸው፡፡ ወንበዴ ሰርቆ ነው ያሰራቸው
አህዮቹ ለጌታ ውለታ ሰርተዋል፡፡ ጌታ ሲወለድ አሙቀውታልና፡፡ ለጌታ ውለታ ልንመልስ ያልቻልነው እኛ ሰዎች ብቻ ነን፡፡
የታሰሩት እዲፈቱ የመረጠበት ሚስጥር፡-እኔ ከሃጥአታችሁ ልፈታችሁ የመጣሁ ነኝ ሲል ነው፡፡
ወንበዴው አህዮቹን ሰርቆ በመንደር እንዳሰራቸው ዲያብሎስም ለሰው ልጅ በሃጥአት ሰንሰለት ከሲኦል መንደር አስራቸው ነበርና፡፡
ሐዋርያቱ ሲልካቸው ምን ታደርጋላችሁ የሚላችሁ ሰው ቢኖር ጌታቸው ይሻቸዋል በልዋቸው አላቸው፡፡ የፈጠራቸው እሱ ነውና፡፡
ከአህያዋ ጀርባ ሃዋርያት ልብሳቸው አነጠፉለት ለምን?
ለምንስ ኮርቻ አላደረጉለትም? ለምንስ ልብሳቸው መረጡ?
---------------------------------------------------------------
ለስላሳ ህግ የሰራህልን አንተ አባት ነህ ሲሉ ነው፡፡ለስላሳ ህግ የተባለው ወንጌል ነው
ወንጌል ፍቅር ናት የሚረግማችሁ መርቁ ትላለችና፡፡ልብስ የሰውነት ነውር ይሸፍናል፡፡ ነውረ ሃጥአታችን የምትሸፍንልን አምላክ ነህ ሲሉ ነው፡፡ እሱ ልብሳችን ነውና፡፡ ነውራችን የሚሸፍንልን እሱ ነውና፡፡ችግሩ ግን ነውረ ሃጥአታችን የሚሸፍንልን ልብስ እርሱ መሆኑን አለማወቃችን ነው፡፡አብሮን እንዳለ አለማስተዋላችን ነው፡፡ስለዚ እንደ ሃዋርያት ሃጥአታችንን አስቀድመህም የሸፈንክልን ዛሬም የምትሸፍንልን ወደፊትም የምትሸፍንልን አምላክ አንተ ነህ ልንለው ይገባል፡፡ጌታችን በሁለቱ አህያዎች በጥበብ ተቀመጠ፡- በሰው የማይቻል በእግዚአብሔር ዘንድ ግን የሚቻል መሆኑ ጥበበኛ አባት ሁሉን የሚችል አባት መሆኑ የሚገልጽ ነው፡፡ አንድም ወንጌልን ኦሪትና ሃዲስን ሁለቱ አስታርቆ አስማምቶ አንዱን አንዱን እየመገበ የሚሄድ መሆኑ የሚያመለክት ነው፡፡
ጌታ ለምን በፈረስ ላይ አልተቀመጠም?
------------------------------------------
ትንቢትና ምሳሌውን ለመፈጸም ነው፡፡( ዘካ ፱፣ ፱) ” አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ፥ እጅግ ደስ ይበልሽ፤ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፥ እልል በዪ፤ እነሆ፥ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፤ ትሑትም ሆኖ በአህያም፥ በአህያይቱ ግልገል በውርጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል።”
በአህያ መቀመጡ
•ትህትናን ለማስተማር
•የሰላም ዘመን ነው ሲል
•ለፈለጉኝ ሁሉ የቅርብ አምላክ ነኝ ሲል በንጽህና በየዋህነት ለሚኖሩ መእመናን አድሬባቸው እኖራለሁ ሲል፡፡
•አህያዎች ትሁታን ናቸው ረጋ ብለው ነው የሚሄዱት፤በቀላሉ ትወጣበታለህ፤በቀላሉ ትይዘዋለህ፤እንደፈለክም ታዝዋለህ፤እኛ በትእቢት ተይዘን ነው እንጂ በየዋህነት ብንመላለስ እሱ ያድርብን ነበር፡፡ እኛ የእግዚአብሔር ማደርያ ነንና፡፡
ትልቅዋ አህያ የኦሪት ምሳሌ ነው
1.ትልቅዋ አህያ ሸክም የለመደች ናት ህገ ኦሪትም የተለመደች ህግ ናትና፡፡
2.የእስራኤል ምሳሌ ነው፡-ትልቅዋ አህያ ሸክም እንደለመደች ሁሉ እስራኤልም ህግ ለመፈጸም በህግ ለመራመድ የለመዱ ናቸው፡፡
3.የአዳም ምሳሌ ነው፡- አዳም ሸክም የበዛበት ነበርና
ውርጭላዋ
1.በህገ ወንጌል ትመሰላለች፡-ምክንያቱም ወንጌል ኢየሱስ ክርስቶስ የመሰረታት የሰራት አዲስዋ ህግ ናትና፡፡
2.በአህዛብ ትመሰላለች፡-ትንሽዋ አህያ ሸክም የለመደች አይደለችም እንዲሁም አህዛብም ህግህን የመቀበል የለመደ አይደሉም፡፡ ለህግህ አዲስ ናቸውና፡፡
3.የእመቤታችን ምሳሌ ናት፡- የዓለም ሸክም አቅልላለችና በእመቤታችን ትመሰለላለች፡፡ እመቤታችን ድህነተ ምክንያታችን ጌታን የተሸከመች ንጽህት እንከን የሌላት እናት ናትና፡፡
ህዝቡም ልብሳቸው እያወለቁ በጎዳና አነጡፉለት ለምን?
እንኳን አንተ የተቀመጥክባት አህያም ክብር ይገባታል ብለው ነው፡፡እስራኤላውያን ጌታ የተቀመጠባት አህያ አከበሩ፡፡ ይህ ትውልድ ግን ጌታ የተቀመጠባት እመቤታችን ማክበር ተሳነው፡፡ ልብሳቸው ማንጠፋቸው፡- ለክብሩ መግለጫ ነው፡፡
ሌሎችም ቅጠል አነጠፉለት፡ ሰስት አይነት ቅጠል አነጠፉለት ዝንባባ፤የቴመር ዛፍ፤የወይራ ዛፍ አነጠፉለት፡፡
ዘንባባ
=============
1.ዘንባባ፡- ይስሃቅ በተወለደ ጊዜ ደስ ብሎት አብርሃምን ዝንባባ ይዞ እግዚአብሔር አመስግነዋል፡፡
2.ዘንባባ ደርቆ እንደገና ሂወት ይዘራል፡- የደረቀ ሂወታችን የምታለመልም አምላክ ነህ ሲሉ ነው፡፡
3ዘንባባ የሰላም ምልክት ነው፡- የሰላም አምላክ ነህ ሲሉ ነው
4.ዘንባባ የደስታ መግለጫ ነው፡- አንተ ደስ የምታሰኝ ሃዘናችንም የምታርቅልን አምላክ ነህ ሲሉ ነው፡፡
5.ዘንባባ እሾሃማ ነው፡- አንተ ህያው አሸናፊ አምላክ ነህ ሲሉ ነው፡፡
6.ዘንባባ እሳት አይበላውም ለብልቦ ይተወዋል እንጂ፡፡ ጌታም አንተ ባህሪህን የማይመረመር ነው ሲሉ ነው፡፡
ሆሣዕና በእጃችን እደ ቀለበት ማሰራችን የምን ምሳሌ ነው?
----------------------------------------------------------------------
1.ጌታ ለአዳም የሰጠው ቃል ኪዳን ለማስታወስ፡-ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድነሃለሁ ያለውን የተስፋ ቃል ለማስታወስ፡፡
2.ጌታ ለእመቤታችን የገባላትን ቃል ኪዳን ተምሳሌት ነው
3.ጌታ ለእስራኤላውያን የሰጣቸው ቃል ኪዳን ተምሳሌት ነው
4.ጌታ ለአዳም ከሰይጣን ግዛት ነጻ እንዳወጣው ሁሉ እኛም ከሰይጣን ግዛት ከመከራ ስጋ ከመከራ ነፍስ ከክፋት ከሃጥአት አውጣን ማረን ለንስሃ ሞት አብቃን ከቤትህ አትለየን እንደ ቸርነትህ ይቅር በላን ስንል ከጌታ ደግመን ላናጠፋ ቃል የምንገባበት ነው፡፡
ስለዚ እንደ ታሰሩ አህዮች መፈታት አለብን፡፡ ሁላችን ታስረናልና ቤተ ክርስትያን በመሄድ እንድንፈታ እናድርግ፡፡ የታሰሩት ሁሉ በካህናት አባቶቻችን አማካኝነት እዲፈቱ ልናድርግ ይገባናል፡፡ ለምን ቢባል አምላካችን ይፈልገናል አባታችን አማላካችን ንጉሳችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይፈልገናል፡፡ ጌታ ጸጋውን አብዝቶ ለዘላለሙ ከቤቱ አይለየን የነጻነት አባት ካለን ሱስና ልማድ ሁሉ ነጻ አድርጎ ለሱ እንድንገዛ እርሱ ይርዳን
መልካም በዓል፡፡









No comments:

Post a Comment