Wednesday, September 14, 2016

የኢትዮጵያውያን እንቆቅልሽ መፍትሔ






ብዙዎቻችን በመንፈሳዊ ድርቀት ተይዘናል። ደስታና እረፍት ጥለው ከሸሹ ቀናት ተቆጥረዋል። ሁሉም ሰው ውስጡ ይቆዝማል። ለወዳጁ ቢያማክር እሱም የባሰ ውስጡ የኃዘን ትርምስምስ አለ። ባለን ገንዘብ ደስታ ይሰጡኛል ብለን ወደ ምናስባቸው አቅጣጫም ብናዘግም ዓለም የኛን ደስታ ሙሉ ለማድረግ አቅም የላትም። እናም ትርፍ አልባ ኪሳራ ሆነን ወደ መጣንበት እንመለሳለን። የሁሉንም ቤት እንደፈረኦን ዘመን የግብፃውያን ጓዳ ኃዘን አንኳኩቶታል።
ችግሮቻችን ደግሞ ህብረ ቀለማቸው መብዛቱ አንዱን ሳንወጣው ሌላው ይደረባል። ያለነው በሦስተኛው ዓለም ውስጥ ብቻ ሳይሆን በጨለማው የነፋስ ሌሊት ውስጥ ነው።
በውስጣችን ያለውን የኃዘን ጭጋግ የሚገፍ እስካሁን በምድር ላይ አልተገኘም። የብዙዎቻችን ጸሎት እንኳን ከጣራ ጋር እየተላተመ ይመለሳል እንጅ ብዙም አልፈይድ ብሏል። ዛሬ እግዚአብሔር ለምን ዝም አለ?የሚያስጨንቁንንስ ለምን ዝም ይላቸዋል? የሚለው አንደበት ኢትዮጵያ ውስጥ እልፍ ነው። እውነት እንቆቅልሹስ ምን ይሆን? መቼስ ነው የእንቆቅልሻችን መፍትሔ የሚገኘው?


በእርግጥም የደም እንባ ያስለቀሱንን ክፍሎች እግዚአብሔር ያላስታገሰልን እነርሱ ጻድቃን ስለሆኑ ወይም በደለኞች ስላልሆኑ አይደለም ፤በደላቸውንማ ከእኛ በላይ እግዚአብሔር ራሱ ያውቀዋል ። ከአሕዛብ የከፉ ከባዕድ ወራሪም የጨከኑ ጉበኛ ደም አፍሳሽ ስግብግብም ናቸው። አዎ ሰው የዘራውን ያጭዳልና የዘሯትን ማጨዳቸው አይቀርም። ገላ5፣6 የብዙዎቻችን ጥያቄ ታዲያ ለምን እግዚአብሔር ዝም አለ? እግዚአብሔር ኃጥዕን በሌላ ኃጥዕ የሚያስቀጣበት ጊዜ አለ። ወደድንም ጠላንም መረረንም ጣፈጠንም ማመን ያለብን አንድ ትልቅ እውነት አለ። ኃጢያት የማያመጣው መከራና ስደት ፍዳና እሮሮ የማያስመዝዘው የሰይፍ ዓይነት የለም። ማንኛውም ኢትዮጵያዊ መጀመሪያ ይህን አምኖ መቀበል መቻል አለበት።
መቼም እረኛ የሌለው ሕዝብ ጌታን ማሳዘኑ አይቀርም።እረ ለመሆኑ እኛስ የኃጢያታችንን ና የበደላችንን ብዛት ምን ያህል
አስበነው እናውቃለን? ሀገረ እግዚአብሔር የተባለችው ኢትዮጵያ ዛሬ ምን የማይሠራባት ኃጢአት አለ? 
እንኳንስ ሊሰርቁ ይቅርና ሌባ የሚለው ቃል ዲክሽነሪያቸው ላይ የሌለ አገሮች እንዳሉ የምናውቅ ስንቶቻችን ነን? ዛሬ በዝሙት ያልረከሰ ህሊና የማን ህሊና ነው? ማንስ ነው ትዳሩ ላይ ያልቆመረ?ስንቶቻችን ነን በእግዚአብሔር ስም ታምነን የተገኘን? የዝሙት መንፈስ ድሩን ያላደራበት ማን ነው? ዛሬ ሮጠው ማምለጥ የማይችሉ የአካል ጉዳተኞች ፣ህጻናት እንኳን ሳይቀሩ በሚዘገንን ሁኔታ የኃይል ጥቃት ይፈጸምባቸዋል። ተገደው ይነወራሉ።ተፈጥሮ የቸረቻቸው ስብራት አንሶ እኛ ደግሞ ይባስ ብለን ቅስማቸውን እንሰብራለን።ሀገሪቷ ውስጥ በጣም የሚዘገንኑ ኃጢያቶች ተንሰራፍተዋል።
ለመሆኑ የትኛው ኢትዮጵያዊ ነው ቂምና ጥላቻ ያላረገዘ ፤ በዘረኝነት በሽታ ያልታመመ ፤በጽንፈኝነት አባዜ ያልተያዘ?
የትኛውስ አገልጋይ ነው እግዚአብሔርን በመፍራት በመቅደሱ የቆመ? ማናችን ነን ቤተመቅደስ ሰውነታችንን ያላሳደፍን ?በጥንቆላና እሱን በመዳፈር በመዳራትና በውሸት አምላኩን ያላስመረረ ማን ነው?የቤት ሠራተኞቻችን እንኳ ከሰው ተርያ የምንቆጥር ስንቶቻችን እንሆን?እግዚአብሔር እንደኛ በቃሉ ያባበለውስ ማንን ነው?የመሥሪያ ቤት አለቃ በሆንን ማግስት ስንቶችን አስለቅሰናል?ዛሬ በየሆስፒታሉ መዳን እየቻሉ በአንዳንድ ግዴለሽ ሐኪሞች በአልጠግብ ባይ ባለሀብቶች ቸልተኝነት ብቻ የስንት ኢትዮጵዉዊ ሕይወት ነው እንደቅጠል የሚረግፈው? እንደኛ ወገኑ ላይ የሚጨክንስ ማን አለ? ከኢትዮጵያውያን ባለስልጣናትና ሹማምንትስ ፈሪሃ እግዚአብሔር ከመጥፋቱ የተነሳ እግዚአብሔርን መጥራት እንደነውር እየተቆጠረ አይደል እንዴ ?! ብቻ ማናችንም ብንሆን ከሊቅ እስከ ደቂቅ እግዚአብሔርን ተስተካክለን በድለናል።እርሱ ከእኛ የሚፈልገውን ክብር አልሰጠነውም። ኢሳ43፣7እናም የዘራነውን እያጨድን ነው።ኃጢያት ደግሞ ከልክ ሲያልፍ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል"በጨካኝ ጌታ እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ ጨካኝ ንጉሥም ይገዛችኋል ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር "ኡሳ19፣4 እውነታው ይሄ ነው አመንም አላመንንም ኢትዮጵያ ውስጥ የኃጢያታችን ጽዋ ሞልቶ ፈሷል ። እስራኤላውያን በኃጢያታቸው ለስደት ሲዳረጉ ምንም ያልበደሉ እነ ኤርሚያስን የመሰሉ የእግዚአብሔር ሰዎች የመከራው ገፈት ቀማሽ ሆነው ነበር። ዛሬም በሃገራችን በኢትዮጵያ በግፈኞች ምክንያት የንጹሃን ደም ይፈሳል ቅጥራቸው ይፈረሳል ደሃውና መበለቲቱ ይገፋሉ። እኛስ የበደላችን ውጤት ይሆናል ምንም የማያውቁ ንጹሐን ሰዎችና ህፃናት ደግሞ በዚህ መሃል ሲያልቁና ለእንግልት ሲዳረጉግን ልብ ያደማል።
ታዲያ የእንቆቅልሻችን መፍትሔ ምን ይሆን? 


የኢትዮጵያ መፍትሔ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ አይሆንም። ከላይ በጽሑፋችን እንዳየነው ይህ የኃጢያታችን ምላሽ ነው ብሎ ልባችን ከተስማማ ከዚህ በኋላ ያለው መፍትሔ ቀላል ነው የሚሆነው።ሉቃ23፣41 በክርስቶስ ቀኝ የተሰቀለው ሽፍታና ቋንጃ ቆራጭ እንደሆነ ያምናል።በግራ በኩል ያለው ሽፍታ ጌታችን ላይ ሲዘብት እርሱ ግን እንባው የዓይኖቹን ግድብ ጥሶ የገላውን እርቃን እያለፈ ቁልቁል መሬቱን ያርስ ነበር።በደሉ ተሰምቶት ሐዘን በተረተረው ማንነቱ "ስላደረግነው የሚገባንን እንቀበላለን በእኛስ እውነተኛ ፍርድ ነው "እያለ ንስሐ ገባ። ወዲያውም "ጌታ ሆይ በመንግስትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ አለው" ። ጌታችን ግን ገና በመንግስቱ እስኪመለስ ድረስ እንኳን አልጠበቀም። "ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር ትኖራለህ። " በሚል ፈጣን መልስና አባታዊ በሆነ ቃል ታሪኩን ቀየረለት።
እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ቃል ታሪካችን የሚቀየረው የኢትዮጵንና የሕዝቦቿ እንቆቅልሽ የሚፈታው በደላችን አምነን ወደ እግዚአብሔር ስንቀርብ ብቻ ነው። እኛስ ኃጢያታችን ነው፤ ምንም የማያውቁት ህፃናትና ንጹሓን ግን ምንም ክፉ አላደረጉም ብለን ስቅስቅ ብለን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉ አገር አቀፍ የሆነ ሥር ነቀል ንስሐ መግባት አለብን ።ከሊቅ እስከ ደቂቅ ፣ ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ሁሉም ልቡን ለንስሐ መስበር አለበት። ወገኖቼ። ኢትዮጵያውያን ሆይእውነት እላችኋለሁ ከእግዚአብሔር ተለይተን በኃጢያት የኖርንበት የባከነና የተረገምንበት ዘመን ነው። ኢትዮጵያ ያለ እግዚአብሔር ክብሯ አይመለስም። ኃጢያታችን ደግሞ ዛሬ የምናየውን ስቃይና እንግልት ሳንፈልግ ጎትቶ አምጥቶብናልና ስለዚህ ዛሬ አዲስ ሰው ለመሆን እንወስን።
ሽፍታውም ንስሐ ሲገባ ለእንቆቅልሹ ነገ እንኳን አላለውም።ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር ትኖራለህ አለው እንጅ።
እስኪ ለቅድስት ሀገር ለኢትዮጵያ በአዋጅ ሕዝቡ ሁሉ ንስሐ ይግባ። ያኔ እግዚአብሔር ለዚች ሀገር የተስፋ ደወል ያሰማል፣እግዚአብሔር እኮ የታመነ ነው። ይልቅንስ ነገ ዛሬ አንበል ከሞት ለማምለጥ ቀጠሮው ምንድን ነው? ሐዋ22፣16 አሁንስ ለምን ትዘገያለህ? ተነሳና ስሙን እየጠራህ ተጠመቅ ከኃጢያትም ታጠብ" እንዲል መጽሐፍ ቅዱስ " ወደ እኔ ዘወር በሉ ትድኑማላችሁ ነው የተባልነው።ኢሳ 45፣22 እንጅ በኃጢያት ላይ ኃጢያት ጨምሩ አልተባልንም። የሚገርመው እግዚአብሔር እየቀጣን እንኳ ኃጢያትን አልተውንም።ለመሆኑ በርካታ ኢትዮጵያውያን ምን ደልቷቸው በዚህ ዘመን ጭፈራ ቤት እንደሚያድሩ አልገባኝም።እርሱ ግን ዓመፃን እየጨመራችሁ ለምን ገና ትቀሰፋላችሁ?"ይለናል።ኢሳ1፣5 ተመስገን እንዲያውም እንደ ኃጢያትችን ክብደት አልጠፋንም። አምላክ ዛሬም በቃሉ ያባብለናል። እኛ ግን ደንደሳቸውን አዞሩ እንጅ መስማትን እንቢ አሉ።እንዳይሰሙም ጆሮአቸውን አደነቆሩ ። ተብሎ እንደተጻፈ ዘካ 7፣11 ዛሬም እንኳን ይህ ሁሉ ትርምስ በምድራችን እየሆነ ለድምጹ ውስጣችንን አደንቁናረል።
እስቲ እናስበው የክርስትና መዲና በሆነችው ሀገር ወንድም ወንድሙን በጥይት አረር እያነደደ ፣በአልሞ ተኳሽ እያቆሰለ
አካሉን እያጐደለ ነፍስ እያጠፋ እስከ መቼ? ሰላም የሚጠፋው በፃድቃን ከተማ ይመስልሃል? መጽሐፍ ለክፉዋች ሰላም የላቸውም ነው የሚለው "ኢሳ 48፣22 አዎ ክፋት በበዛበት ሀገር ሁከትና ብጥብጥ ይሆናል።ሕዝቅኤልም ሁከት በኢትዮጵያ ይሆናል ያለው ለዚህ ነው።ሕዝ30፣4
ክፋታችን ሰማይ ስለደረሰ ታዲያ እንቆቅልሻችን እንዴት ይፈታል?
እንቆቅልሽ ሊፈታ የሚችለው ከንስሐ በኋላ ነው። ከንስሐ በኋላ እግዚአብሔር ከሐዘንህና ከመከራህ ከተገዛህበትም ጽኑ ባርነት ያሳርሃህል።ኢሳ14 ፣3-4
ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እግዚአብርሔን ማማረር አበሳን አይቀንስም፤ ደግሞም ማጉረምረም የአሕዛብ ሥራ ነው። ብዙ ህዝባችን የእግአእብሔርን ዝምታ በማየት እግዚአብሔር
ለምን ዝም አለ? ግን እርሱ አለ ? ይላሉ። አዎ እግዚአሔሓር አለ በመንግስቱ ፣በዝምታ ውስጥም ይሰራል። ሰነፍ በልቡ አምላክ የለም ይላል እና ስንፍናችን እናስወግድ። አሁንም ለኢትዮጵያ መፍትሔ በግራ በኩል እንዳውለ ወንበዴ ማጉረምረም ሳይሆን በእምነት ሆኖ በንስሐ መመለስና መጮህ ነው። እርሱ እግዚብአሔር የትኛውንም የመከራ ባሕር ተርትሮ ያሻግራል። የትኛውንም ተራራ የሚያንሳፍፍና እሳትን የሚያጠፋ ግሩም አምላክ ነው። ኢሳ 43፣2
በርግጥ ጊዜው የጥያቄ ጊዜ ነው ነገር ግን የጸሎት አጀንዳዎቻችን ሁሉ በሥጋዊ ነገር ላይ ከሚታጨቁ ይልቅ ለእንቆቅልሻችን መፍትሔው ቅድሚያ ንስሐ መግባት ነው።ምድራችንም እንድትፈወስ ብሔራዊ እርቅ ያስፈልገናል።
እኛነታችን ምድረ በዳ መሆኑ ቀርቶ በሊባኖስ ዳርስ ዳርቻ እንደተተከለ ዝግባ የለመለም እንዲሆን ከእንባ ጋር እንጸልይ። ያኔ እርሱ የሚያስጨንቁንን ያዋርዳቸዋል።መዝ59፣12
ለነገ ድፈንልን ያልነውን ቀዳዳ እርሱ እግዚአብሔር ዛሬ ላይ ሲደፍንልን እናየዋለን። እግዚአብሔር እንደገና ያየናል።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ የሚል ቃል ከባለስልጣኖች አንደበት ይሰማል ሕዝብ ሁሉ ያርፋል። ነገራችን ይገለበጣል እቆቅልሻችን ይፈታል ታሪካችን ይቀየራል ።
አዎ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ ሕዝቦቿን ያሳርፍ አሜን።

No comments:

Post a Comment