Wednesday, September 14, 2016

በዚች ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሰራለሁ የሲዖል ደጆችም አያናውጡአትም። ማቴ ፲፮፣ ፲፰



ሰኔ ፳ ቀን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፊሊጶስ ቂሳሪያ ከሦስት አዕባን (ዓለቶች ) ለእመቤታችን መታሰቢያ ይሆን ዘንድ በስሟ ቤተ ክርስቲያንን ካነጸ በኋላ ሰኔ ፳፩ ቀን ቅዳሴ ቤቷ የከበረበት ዕለት ነው። በማቴዎስ ወንጌል ፲፮ ፣፲፫ ኢየሱስም ወደ ፊሊጶስ ቂሳሪያ አገር በደረሰ ጊዜ ደቀመዛሙርቱን ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ይሉታል ? ጌታችን ስለራሱ ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ይሉታል አለ? ከእመቤታችን በነሳው ሥጋ፣ ከእኛ ከአዳም ልጆች በነሳው ሥጋ ራሱን የሰው ልጅ እያለ ይጠራልና። እምነ ፅዮን ይብል ኩሉ ሰብዕ፣ ወብእሲ ተወልደ በውስቴታ።(መዝ፹፮፣፭) 

እነርሱም አንዳንዶች መጥምቁ ዮሐንስ ሌሎችም ኤልያስ ሌሎችም ኤርሚያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ አሉት። እናንተስ እኔን ማን እንደሆንሁ ትላላችሁ አላቸው? ስምዓን ጴጥሮስም መልሶ አንተ ክርስቶስ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ ነህ።አለው። ኢየሱስም መልሶ የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ በሰማያት ያለው አባቴ እንጅ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ እኔም እልሃለሁ አንተ ጴጥሮስ ነህ በዚችም ዓለት ላይ ቤተክርስቲያኔን እሰራለሁ። እውነተኛ አምላክ አንተ ነህ የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅ ነህ ብሎ መሰከረ። ጌታችን የሰማይ አባቴ ገለጸ ማለቱ አንድም መንፈስ ቅዱስ በወደደው አድሮ ምስጢርን ያናግራልና ይህን የባህርይ ሕይወቴ መንፈስ ቅዱስ ገልጾልህ መሰከርክ ሲል ነው። አንድም ሰው ከላይ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ካልተሰጠው በቀር ምሥጢርን ገልጾ እይናገርም ፣አያስተምርም፣አይመሰክርምና።
ጴጥሮስ ቃሉ የግሪክ ሲሆን ትርጉሙም ዓለት ማለት ነው። ኬፋም ማለት ጽኑ ዓለት የማይናወጽ ማለት ነው። ጌታችን ጴጥሮስን ዓለት ያለው እንደ ዓለት የፀናና የማይናወጽ ምስክርነትን ስለሰጠ ነው።
የማይለወጥ የማይፈርስ ጽኑ ቃል ስለተናገረ አንተ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ ነህ ብሎ ስለመስከረ አንተ ዓለት ነህ በዚህ ዓለት ላይ ቤተክርስቲያኔን እሰራለሁ ፤የሲዖል ደጆችም አይችሉአትም።
በዚህም ምስክር ላይ ቤተክርስቲያን ታነጸች በዓለት ላይ በጽኑ ምስክር ላይ የማይናወጽ የማይናድ የማይፈርስ ምስክርነት ኢየሱስ ክርስቶስ ከባሕርይ አባቱ ከአብ የተስተካከለ የእግዚአብሔር ልጅ እግዚአብሔር ነው ብሎ ማመንና መመስከር። በወንጌለ ዮሐንስ " ነገር ግን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ታምኑ ዘንድ አምናችሁም በስሙ ሕይወት ይሆንላችሁ ዘንድ ይህ ተጽፏል " (ዮሐ፳፣ ፴፩) በዚህ ዓለት ላይ ቤተክርስቲያኔን እሰራለሁ የሲኦል ደጆችም አይችሉአትም። ዲያብሎስና ሰራዊቱ አላውያን ነገስታት አህዛብና መናፍቃን አይቋቋሟትም።
ቤተክርስቲያን የሚለው ቃል ስለሦስት ነገሮች የተነገረ ሲሆን፦
1ኛ. አንድም እያንዳንዱ ክርስቲያን ቤተክርስቲያን ነው።
___________________________________________
የተሰራንበት ዓለቱ ክርስቶስ ነው።ማቴ፯፣ ፳፬ ብዙዎች በዚህ ዓለት ላይ ስላልተሰሩ ተሰናከሉበት ተፍገምግመው ወደቁ ናቁት አቃለሉት።
ኢሳ፳፰፣ ፲፮ እነሆ በጽዮን ድንጋይን ለመሠረት አስቀምጣለሁ የተፈተነውን የከበረውን መሠረቱ የጸናውን የማዕዘን ድንጋይ የሚያምንም አያፍርም። ከጽዮን ከድንግል ማርያም የተወለደው የጸናው ዓለት ክርስቶስ የባህርይ አምላክ ፈጣሪ እንደሆነ የሚያምን ሁሉ በዚህ ዓለት ላይ ታንጿል መሠረቱም የጸና ነው። ቤተአይሁድ ተሰናከሉበት ብዙዎችም ዛሬ የባህርይ ክብሩን አቃለሉ ኃይሉን ካዱ አስቀድሞ በዳዊት የተነገረው ትንቢት ይደርስ ዘንድ" ግንበኞች የናቁት ድንጋይ እርሱ የማዕዘን ራስ ሆነ የእንቅፋትም ድንጋይ የማሰናከያም ዓለት ሆነ" መዝ ፻፲፯፣፳፪
ክርስቲያኖች የሕያው የእግዚአብሔር ቤተመቅደስ ነን ለዚያውም በመስቀሉ የተቀደስን በጥምቀት የከበርን በቤዛነት ቀን የታተምን በቅዱስ ደሙ የተዋጀን መቅደሶች ክርስቲያኖች ነን።
በጥንተ ፍጥረት ከምድር አፈር አበጅቶ የሕይወትን እስትንፋስ እፍ ብሎ የራሱ ቤተ መቅደስ ያደረገን እሱ ነው።ዘፍ ፩ ፣፳፯ ፤ዘፍ ፪ ፣፲፰
2ኛ. ህንፃ ቤተክርስቲያንን ቤተመቅደስን ፦
_____________________________________
ለእግዚአብሔር ክብር የምንዘምርበትን ስለተደረገልን ነገር ሁሉ ምስጋና የምናቀርብበትን ቅዳሴ የሚቀደስበትን ማህሌት የሚቆምበትን ሰዓታቱ የሚደረስበትን ስብሐተ እግዚአብሔር የሚፈስበትን ቃሉ የሚነገርበትን የተሰበረው ልባችን የሚጠገንበትን እንባችን የሚታበስበት ታሪካችን የሚቀየርበት የጸጋው ግምጃ ቤት ሐዘናችን ወደ ደስታ ለቅሶአችን ወደ ሳቅ የሚቀየርበት እንቆቅልሻችን የሚፈታበት የእግዚአሔሓር ቤት ቤተ ክርስቲያን ነው። (ዘጸ፳፭፣፰)
ቤተ ክርስቲያን የጸጋ ግምጃ ቤት የበረከት ማዕድ ናት።( መዝ ፷፬፣፬) ቤተ ክርስቲያን የእውነት አምድና መሠረት ጻድቃን የሚገቡባት የሕያው የእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን ናት። (መዝ ፻፲፯፣ ፳ ፤፩ኛጢሞ ፫ ፣፲፭)
በብሉይ ኪዳን የመጀመሪያዋ ቤተክርስቲያን ደብተራ ወይም ድንኳን ነበረች። ከዚያም ቤተመቅደስ በዘሩባቤል ዘመን ፵፮ ዘመን ፈጅቶ ተሰራ። በአዲስ ኪዳንም ሰኔ ፳ ቀን ጌታችን ከሦስት ድንጋዮች ቤተ መቅደስ አንጾ ሰኔ ፳፩ ቀን ቅዳሴ ቤቱ የከበረበት ዕለት ነው።
3ኛ. ቤተክርስቲያን የምዕመናን አንድነት የምዕመናን ሕብረት ነው
____________________________________________________
ሐዋርያት በሰበሰቧት በአንዲት ቅድስት ቤተክርስቲያን እናምናለን እንዲል ጸሎተ ሃይማኖት የመጀመሪያዎቹ ምዕመናን አስራሁለቱ ደቀመዛሙርት ፴፮ቱ ቅዱሳን አንዕስት ፸፪ አርድእት ነበሩ። በዕለተ ጰራቅሊጦስ መንፈስ ቅዱስ በወረደ ጊዜ ፫፼ የሚያህሉምዕመናን በቅዱስ ጴጥሮስ ስብከት አመኑ፣ ከዚያም በኋላ በሐዋርያት ስብከት ፭፼ የሚያሉ ተጨመሩ በአጠቃላይ ፰፼ የሚያህሉ ነበሩ ። ቤተ ክርስቲያን ማለት ማህበረ ምዕመናንን እንደሆነ በሚከተሉት የመጽሐፍ ማስረጃዎች እንረዳለን።
"በደረሱ ጊዜ ቤተክርስቲያንን ሰብስበው እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ያደረገውን ሁሉ ለአሕዛብም የሃይማኖትን ደጅ እንደከፈተላቸው ተናገሩ።" ሐዋ ፲፬ ፣፳፯
"አቢያተ ክርስቲያናትም በሃይማኖት ይበረቱ ነበር በቁጥርም ዕለት ዕለት ይበዙ ነበር።" ሐዋ ፲፮ ፣፭
በመሆኑም በሐዋርያትና በነቢያት መሠረትነት ላይ ታንጻችኋል የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው (ኤፌ ፪ ፣፪) እንዲል 
በዚህ ዓለት ላይ ታንጸን የማዕዘኑን ራስ ድንጋይ ክርስቶስን በፍቅርና በትህትና በቅድስናም ልንመስል ይገባል። በመጽሐፍ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ (፩ጴጥ ፪፣ ፭) ተብሎ እንደተጻፈ የሰላምና የትህትና የፍቅር ቅዱስ ህንፃ ሆነን እንሰራ ። ( ፩ኛ ቆሮ ፫ ፣፲፮)
_____________________________________________________
መምህር ዲ/ን ቸንነት ይግምረ
ሰኔ ፳ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም
ጎንደር፣ ኢትዮጵያ

No comments:

Post a Comment