Sunday, December 11, 2016

መቅደስ እንተ ውስቴታ መቅደስ

በዓታ ለማርያም

ኦ መቅደስ ዘኮነ ለሊሁ እግዚአብሔር ሊቀ ካህናት ማኅየዊ ፤ ጌታ በማኅፀን ያደረብሽ አማናዊት መቅደስ አንቺ ነሽ።
ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ 
ኢያቄምና ሐና ከዘመናት በኋላ በስተርጅና እንደ ፀሐይ የምታበራ ልጅ በመውለዳቸው " ነያ ሠናይት እንተ ኅቤየ ነያ ሠናይት አዕይንትኪ ዘርግብ ሥዕርትኪ ከመ መርኤተ አጣሊ ፤ወዳጄ ሆይ እነሆ ውብ ነሽ እነሆ መልከ መልካም ነሽ ዓይኖችሽ እንደ ርግቦች ናቸው " (መኃ 4፣1) በማለት ሰሎሞን እንደ ዘመረላት ፤ በውስጥ በአፍአ ደም ግባቷ ያማረ 
"ኲለንታኪ ሠናይት እንተ ኅቤየ አልብኪ ነውር ወኢምንትኒ ላዕሌኪ" ተብሎ የተተነበየላትን ፣ፈጣሪዋን የምትመስል ንጽህት ቅድስት ልጅ ስለ ወለዱ አምላክን አመሰገኑ። ኢያቄምና ሐና ደስታቸው ያለምክንያት አልነበረም ፤ አንድም ለረጅም ዘመናት ልጅ ሳይወልዱ ሲያዝኑ ቆይተው" ጸኒሐ ጸናሕክዎ ለእግዚአብሔር ሰምዐኒ ወተመይጠኒ ወሰምዐኒ ቃለ ስእለትየ" እንዲል ነቢዩ ዳዊት፤ እግዚአብሔር ስዕለታቸውን መሻታቸውን አይቶ በእርግናቸው ይህችን ብላቴና በማግኘታቸው እንጅ ቀድሞ ሐና በጎረቤቶቿ ጽርፈት ነበረባት፣ የበቅሎ ዘመድ ኅፁተ- ማኅፀን፤ ማኅፀኗ የተዘጋ እየያተባለች ትሰደብ ነበር ኋላ ይህን ዘለፋ የምታስወግድ ልጅ ወለደች፤ ድንግል ማርያም እንባቸውን አበሰችላቸው ፤ ስድባቸውን አራቀችላቸው ፤በእመቤታችን ነቃፊዎቿን አሳፈረች። 


አንድም ይህቺ ብላቴና ከፅንሰቷ ጀምሮ ግሩምና ድንቅ ነበረችና ለአለሙ ሁሉ ምክንያተ ድኅነት የምትሆን ናትና አስቀድሞ ቅድመ አያቶቿ በህልም በተገለጸላቸው መሠረት ሰባተኛዋ ጨረቃ የተባለች ድንግል ማርያም ፣ፀሐይን(ክርስቶስን) ትወልዳለችና በእመቤታችን መወለድ ተደሰቱ። ድንግል ማርያም የሐና ና የኢያቄምን ብቻ ሳይሆን የዓለሙን ስድብ የምታርቅ ናትና ፤ ነቢዩ ኢሳይያስ ጽድቃችን እንደ መርገም ጨርቅ ሆነ ፣ ሀላችንም እንደ ቅጠልም ረገፈናል በደላችንም እንደ ነፋስ ወስዶናል ፣ ተፍገምግመንም ወደቅን ሁላችን ተሳሳትን እንዲል (አሳ 64 ፣5)። ዓለሙ ሁሉ ከጽድቅ ከልምላሜ መካን ሆኖ ከጸጋው ተራቁቶ ሲኖር በፍጻሜው ዘመን ተወልዳ የወደቁትን አንስታለችና ፣የረከሱት እንዲቀደሱ ምክንያተ ድኅነታችን ሆናለችና፣ ያዘኑትንም አጽንታለች። የአዳም ልጆች ሁሉ ከነቃፊያቸውና ከአሳዳጃቸው ከዲያብሎስ ነጻ የሚወጡበትን ልጅ ፣ ከድቅድቅ ጨለማ ወደብርሃን የሚሻገሩበትን አማናዊ ፀሐይ የጽድቅ ብርሃን ኢየሱስ ክርስቶስን ትወልዳለችና፣ ኢያቄምና ሐና ብቻ ሳይሆኑ ዓለሙ ሁሉ ደስ ተሰኝቷል። በዚህም ሊቁ ኢትዮጵያዊው ቄርሎስ ሙኅዘ ፍስሐ ፣ የደስታ መፍሰሻ በማለት ብላቴናዋን አመስግኗታል።
ሐና እና ኢያቄም ለሦስት ዓመት ያህል ከእነርሱ ዘንድ ከአቆዩዋት በኋላ የተሳሉትን ስዕለት አሰቡ ።በ ነገረ ማርያም ተመዝግቦ እንደምናነበው ሁለቱ ቅዱሳን እግዚአብሔርን " ልጅ ብትሰጠን ሴት ከሆነች ውሃ ቀድታ መሶብ ወርቅ ሰፍታና መጋረጃ ፈትላ ካህናትን አገልግላ እንድትኖር ለቤተ መቅደስ እንሰጣለን፣ ወንድ ከሆነ ተምሮ ቤተክርስቲያንን እንዲያገለግል እናረጋለን " ብለው ተስለው ነበር ።በ ኦሪት ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ስዕለት በተሳልህ ጊዜ ፣ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ ፈጽሞ ይሻዋልና ፣ኅጢአትም ይሆንብሃልና መክፈሉን አትዘግይ። ባትሳል ግን ኅጢአት የለብህም ። በአፍህ የተናገርኽውን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር በፈቃድህ ተስለሃልና ከከንፈርህ የወጣውን ታደርግ ዘንድ ጠብቅ። ( ዘዳ23፣ 21-23) የሚለውን ቃል በማሰብ ሐና ባለቤቷን ኢያቄምን አፏ እህል ሳይለምድ ሆዷ ዘመድ ሳይወድ እንደተሳልን ወስደን ለቤተ እግዚአብሔር እንስጥ " አለችው፤ ኢያቄምም በሃሳቧ ተስማማ። 
ሐና ና ኢያቄም ቤተ መቅደስ እንደ ደረሱ ወደ ሊቀ ካህናቱ ዘካርያስ ዘንድ ቀረቡ ፣ የተሳሉትን ነግረው የሦስት ዓመቷን ህፃን ድንግል ማርያምን ሰጡት። ልጃቸውን ለቤተ መቅደስ አቀረቡ። ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸው፣ የተዘጋ ማህፀንን የሚከፍት መካኖችን ወላድ የሚያደርግ እግዚአብሔር ነው። በመሆኑም ለእግዚአብሔር ዕጣን ጧፍ ብቻ ሳይሆን ልጅም ስጦታ ይሰጣል። ለዚያውም እንደ ሳሙኤል ያለ ዝናው ከዳን እስከ ቤርሳቤህ የገነነውን ፣ እንደ ድንግል ማርያም ያለ ክብሯ ከቅዱሳን ሁሉ የሚበልጠውን ልጅ ለእግዚአብሔር ስጦታ ይሰጣል።ቅዱስ ዳዊት ከእጅህ የወሰድነውን መልሰን ሰጠንህ " እንዳለ ከእጁ የተቀበልነውን ገንዘባችንን ብቻ ሳይሆን ልጅም ልንሰጥ ይገባል። 
በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እንዲያድግ በዝማሬ በስብከት ፣በዲቁና፣ በቅስና ማዕረግ እግዚአብሔርን እንዲያገለግል ልናበረክት ይገባል።በዘመናችን ለቤተ እግዚአብሔር ብዙ ገንዘብ የሚሰጡ መባዕ በማቅረብ የሚታወቁ ልጆቻቸውን ለእግዚአብሔር አልግሎት የማይሰጡ፣ መንፈሳዊ ሲሆኑም የማይደሰቱ ሊያስተውሉና ከዚህም ሊማሩ ይገባል።
ሊቀ ካህኑ ዘካርያስም ድንግል ማርያምን ከተቀበለ በኋላ የምግቧ ነገር ስለአሳሰበው ደወል አስደውሎ ሕዝቡንና ካህናቱን ጠርቶ በማማከር ላይ ሳለ ፤ ድንግል ማርያም በአምላክ ኅሊና ታስባ ትኖር ስለነበረ ፣መጋቤ ኅብስት ሊቀ መላዕክት ቅዱስ ፋኑኤል በአምላካዊ ጥበብ የተዘጋጀ ሰማያዊ ኅብስት ሰማያዊ ጽዋ ይዞ ረብቦ ታያቸው። ለእነሱ የመጣ መስሏቸው ሕዝቡም ካህናቱም ቢቀርቡ ሸሻቸው ራቃቸውም። በዚህንጊዜ ሊቀ ካህናት ዘካርያስ " ጥበበ እግዚአብሔር አይታወቅምና ለዚህች ብላቴና የመጣ ይሆናል ትታችኋት ፈቀቅ በሉ አላቸው። ሁሉም ትተዋት ራቁ መልአኩም ሁሉ ከራቀ በኋላ እመቤታችንን በአንድ ክንፉ አጎናጽፎ፣ በአንድ ክንፉ ጋርዶ ከምድር ከፍ አድርጎ ኅብስቱን ከመገባት ጽዋውን ከአጠጣት በኋላ ወደ ሰማይ ተመልሶ ዐረገ።
እግዚአብሔር ወዳጆቹን ሰማያዊ ኅብስትን ይመግባል ሰማያዊ ጽዋም ያጠጣል ። በብሉይ ኪንዳ ዕዝራ ሱቱኤልን ጥበብን የሚገልጽ ሰማያዊ መጠጥን አጠጥቶታል። በዘመነ ኦሪት እስራኤልን መና ከደመና እያወረደ መግቧቸዋል። (ዘዳ 16፣13) ነቢየ ኤልያስም በመንገድ ሲደክም መልአከ እግዚአብሔር ተገልጦ ኅብስት ሰማያዊ መግቦታል። (1ኛ ነገ 19፣4 ) ለእነዚህም ለቀደሙት በጨለማው ዘመን ለነበሩት ይህን ካደረገ ማህፀኗን ዓለም አድርጎ ድኅነተ ዓለምን ለሚፈጽምባት ለሐዲስ ኪዳን ኪሩቤል ለድንግል ማርያም ከዚህም በላይ ቢያደርግ የሚያስደንቅ አይሆንም። አንድም ዳግሚት ሰማይ ፣ ሁለተኛዋ ሰማይ ሆና መለኮትን በማህፀኗ ትሸከማለችና አንድም በንጽኅናዋ በቅድስናዋ ከሰማያውያን መላዕክት ትበልጣለችና ምግቧ መጠጧ ሰማያዊ ቢሆን ከአእምሮ በላይ ሆነ የሚያሰኝ አይሆንም።
ሊቀ ካህኑ ዘካርያስ የምግቧ ነገር መፍትሔ ካገኘ በቤተ መቅደስ ትቀመጥ ፈጣሪዋን እያገለገለች ትደግ ብሎ ተቀበላት። ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት የተናገረው ትንቢት እንዲፈጸም ከዘመዶቿ ተለይታ ቤተ መቅደስ ገባች። ነቢዩ ዳዊት ልጄ ሆይ ስሚ እዪ ጆሮሽንም አዘንብዪ ወገንሽን የአባትሽን ቤትም እርሺ ንጉስ (እግዚአብሔር) ውበትሽን (ንጽህናሽን) ወድዷልና(መዝ 44፣10 )ብሎ ትንቢት ተናግሯልና የእናትና የአባቷን ቤት እንድትረሳ እግዚአብሔር ስለወደዳት ለተዋህዶ ስለመረጣት ከእርሱ ጋር እንድትኖር ነግሯት ነበር ። እንደቃሉም ተፈጸመ። እመቤታችን ታኅሣሥ ሦስት ቀን ወደ ቤተ መቅደስ ገባች ። ከዚህች ዕለት 3 ዓመቷ ጀምሮ ጌታን እስከፀነሰችበት ጊዜ ድረስ በቤተ መቅደስ አደገች። ቀደሰ ማኅደሮ ልዑል ፤ ልዑል ማደሪያውን መቅደሱን አጸና ቀደሰ ይላልና በንጽኅና በቅድስና አጸናት። አባሕርያቆስም "ድንግል ሆይ አንገታቸውን እንደሚያገዝፉ እንደ ዕብራውያን ሴቶች ልጆች በዋዛ በፈዛዛ ያደግሽ አይደለሽም። በንጽሕና በቅድስና ኖርሽ እንጅ " እንዳለ በቤተ መቅደስ በንጽሕና በቅድስና ተሸልማ አደገች ።
በዓታ ለማርያም የእግዚአብሔር ማደሪያ አማናዊቷ ቤተ መቅደስ ድንግል ማርያም ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን ወደ ሠራው ቤተ መቅደስ የገባችበት ዕለት ነው። ቤተ መቅደሱ ቤተ መቅደስ የሆነችውን እናት የተቀበለበት ዕለት ነው።እኛም ቤተ መቅደስ የሆነው ሰውነታችንን በኅጢአት አፍርሰንና አስጸይፈን ታቦቱ ወዳለበት ቤተ መቅደስ መግባት እግዚአሔሓርን አያስደስተውምና ፣ ነውር ነቀፋችን በንስሐ እያስወገድን መቅደሱን ቀድሰን ወደ ቤተ መቅደስ እንግባ ያን ጊዜ የእመቤታችን ልጆች የበረከቱ ተካፋዮች እንሆናለን።


------------------------------------------------------------------------------
መምህር ዲ/ን ቸንነት ይግምረ
ታህሣሥ 3 2009 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment