Monday, December 19, 2016

የድንግል ማርያም ክብር

Image result for mary ethiopia

የድንግል ማርያም ክብርና ነገረ ክርስቶስ በቅዱስ አትናቴዎስ ሊቀጳጳስ ዘአሌክሳንድርያ  ( d.373)
======================================================
የድንግል ማርያምን አስተምህሮ (Mariology) ንጽህና ቅድስና ዘላለማዊ ድንግልና እንዲሁም በነገረ ድኅነት ውስጥ ያላትን ሱታፌ አብራርተው ከጻፉትና ካስተማሩት አበው ሊቃውንት መካከል 20ኛው የአሌክሳንድርያው ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ አትናቴዎስ አንዱ ነው። ቅዱስ አትናቴዎስ ከመንፈሳዊ መልዕክቶቹ ጠጣርነት በተለይም በነገረ መለኮትና በነገረ ማርያም ትምህርቱ የተነሳ ታላቁ አትናቴዎስ ሐዋርያው አትናቴዎስ እየተባለ ይጠራል። ትክክለኛውን የተዋሕዶ ምስጢር በተለይም የጌታችንን የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን የባህርይ አምላክነት ለአርዮስና ለተከታዮቹ አስረግጦ በማስተማሩ የእንዚናዙ ቅዱስ ጎርጎርዮስ "የቤተክርስቲያን አምድ" የሚል ስያሜ ሰጥቶታል።
ቅዱስ አትናቴዎስ በአሌክሳንድርያ በ295 ዓ.ም. ተወለደ፣ ዕድሜው ከፍ ሲልም በ24 ዓመቱ (319 ዓ.ም) ከሊቀ ጳጳሱ ከብፁዕ አቡነ አሌክሳንደር ዲቁናን ተቀበለ፣ የሊቀጳጳሱም ጸሐፊ ሆኖ ተሾመ። ይህ አጋጣሚ ነበረ አትናቴዎስን ከሊቀጳጳሱ ጋር በ325 በተደረገው የኒቂያ ጉባኤ ላይ እንዲገኝ የረዳው።

በዚህ ጉባኤ ላይ ቅዱስ አትናቴዎስ አርዮሳውያንን በሃይማኖት ብስለቱና በበሳል የስብከት ብቃቱ በመከራከር ለርትዕት ክርስትና ሃይማኖቱ በተለይም የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት ግልፅ ባለ መልኩ አስረግጦ በማስረዳቱ ሊቀ ጳጳሱን ብፁዕ አቡነ አሌክሳንደርን እንዲተካ ዕጩ ሆነ።
ይህንን ያዩ አርዮሳውያን ብዙ ፈተና አደረሱበት ሕይወቱንም አመሰቃቀሉበት፣ በሚያገለግልበትም ቤተክርስቲያን ሆን ብለው የተወሰኑ ክፍሎችን በማስተባበር ተቃዋሚ አድርገው በጠላትነት አስነሱበት።ቅዱስ አትናቴዎስ ከሃዲው አርዮስ ወደ መቅደስ ገብቶ ምሥጢር እንዲሳተፍ የሚለውን የንጉሥ ቆስጠንጢኖስን ትዕዛዝ አጥብቆ ተቃወመ። ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ የሊቀጳጳሱን ሃሳብ ማስቀየር ባለመቻሉ ክስ መስርቶበት በግዞት በጎል ከተማ ወደ ምትገኘው ትርየር አስጋዘው ፤ሌሎች አትናቴዎስን ይቃወሙ የነበሩ ሊቃነጳጳሳት ከመንበሩ እንዲነሳ አደረጉት።
ምንም እንኳን ቆስጠንጢኖስ ከሞተ በኋላ በ337ዓ.ም. አትናቴዎስ በአሌክሳንድርያ ወደምትገኘው ቤተክርስቲያኑ ቢመለስም ወደ መንበሩ ግን ሊመለስ አልቻለም ነበር፣ በጠላቶቹ እኩይ ሴራ አምስት ጊዜያት ይህል ወደ ግዞት ተወስዷል፤ በመጨረሻ ግን በ336 ዓ.ም.ወደ መንበሩ ተመልሶ እስከ ዕለተ ሞቱ (376 ዓ.ም) ድረስ በፓትርያርክነት አገልግሏል።

ቅዱስ አትናቴዎስ ስለ እመቤታችን አስተምህሮ (Mariology or Marian Doctrine ) ያበረከታቸው አስተዋጽኦዎች ሁሉ ስለ ነገረ ክርስቶስ ( Christological) አስተምህሮዎች ከመናፍቃን ጋር ባደረጋቸው ጥልቅ ክርክሮችና ስለ ጌታችን ስለ መድኃኒታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የባህርይ አምላክነት ካለው ጠንካራ እምነትና አቋም የመነጩ እንደሆኑ የቤተክርስቲያን ጸሐፊያን ይመሰክራሉ። ነገር ግን ስለ እመቤታችን ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ንጽህና ና ቅድስና በሚያስተምራቸው ትምህርቶቹ በቀድሞው ሊቀ ጳጳስ አሌክሳንደር ዘንድ ሳይቀር ትልቅ ዝናን አትርፏል " ፀባይህና ክርስትና ሕይወትህ ልክ እንደ ቅድስት ድንግል ማርያም ለመንግስተ ሰማያት ብቁ የሆነ ነው " ብለው አመስግነውታል።
ቅዱስ አትናቴዎስ ድንግል ማርያም የአምላክ እናት ስለመሆኗ በስፋት ያስተማረ ፣የነገረ ማርያም አስተምህሮ (Mariology) ጠንካራ ተከላካይ ጠበቃ እንዲሁም አስተምህሮው በመስፋፋቱና በማደጉ ረገድ ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ያበረከተ ታላቅ የሃይማኖት አባት ነው።
በተለይም ከአርዮሳውያን በተለየ ጠንካራ አቋሙ ኢየሱስ ክርስቶስ ከባህርይ አባቱ ከአብ ከዘመናት በፊት የተወለደ የእግዚአብሔር ልጅ እግዚአብሔር በህልውና ና በባህርይ የተካከለ ነው ብሎ አስተምሯል። (መዝ2፣7 ፤ዮሐ1 ፣1-18)
በዚህም መሠረት በኋላ በጉባኤ ኤፌሶን በ431 ዓ.ም.በቃለ ጉባኤ የፀደቀውን ፤ ድንግል ማርያም የእግዚአብሔር እናት Mother of God ( Theotok'os) ተብላ ትጠራለች በማለት አስረግጦ አስተምሯል።
ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር ሆኖ ሳለ በረቂቅ ጥበቡ ከድንግል ማርያም፤ ከእግዚአብሔር እናት ሰው ሆኖ ተወልዶ
ከዲያብሎስ እስራት ከኅጢአት ቁራኝነት ነጻ አወጣን።
ቅዱስ አትናቴዎስ ምስጢረ ሥጋዌ ለነገረ ድኅነት ያለውን ሚና አጽንኦት ሰጥቶ ማስተማሩ ከእመቤታችን እናትነት ና ከሰው ልጆች የመርገም መንጻት ጋር ያለውን የምስጢር ግንኙነት አስረግጦ እንዲናገር ረድቶታል።
ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው የሆነው ከድንግል ማርያም ከእግዚአብሔር እናት ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስን የነሳው ለእኛ ለሰው ልጆች ጥቅምና ድኅነት ነው።
የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ ኅጢያትን ያስወግድ ዘንድ ከድንግል ማርያም ተወለደ ፣በመጽሐፍ ከህግ በታች ያሉትን ይዋጅ ዘንድ ከህግ በታች ከሴት የተወለደውን ልጁን ላከ ፣የሰውን ሥጋም ነሳ ሰው ሆኖም ተወለደ። (ገላ፬፣ ፬) ተብሎ እንደተጻፈ።
የተለያየ አመለካከት ያላቸው መናፍቃን ይህንን እውነት በብዙ መልኩ ይክዳሉ። አንዳንዶች ሥጋዋን ለማደሪያነት ብቻ ተጠቀመበት ፤ አንዳንዶችም ሰው ሁሉ በደልን ስለሠራ አንድስ እንኳ ጻድቅ ስለሌለ መለኮት ከሥጋ ጋር ይዋሐድ ዘንድ አልቻለም ብለው ሲጠራጠሩ ፤ ሌሎችም ኢየሱስ የተዋሐደው ሥጋ ሰማያዊ ና ከሰማይ ቀጥታ የወረደ ቀጥታም ወደ ማህፀኗ የገባ ከሷ ግን ምንም ያልነሳ ነው ሲሉ ፤አንዳንዶች ደግሞ ከድንግል ማርያም የተወለደው ኢየሱስ በመጀመሪያ ሰው ብቻ ሆኖ የተወለደ ኋላም በተአምር መለኮታዊ ባህርይ የለበሰ ነው ብለው የሚክዱም ነበሩ።
ቅዱስ አትናቴዎስ ግን ከዚህ ሁሉ በተለየ መልኩ የነገረ ክርስቶስን ነገር፤ የጌታችንን የመድኅኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ከድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስን ነስቶ የእኛን ሥጋ ለብሶ በፍጹም ተዋሕዶ በረቂቅ ጥበቡ ያለ ዘርአ ብዕሲ ተፀንሶ ሰው ሆኖ ተወለደ በማለት አስረግጦ አስተምሯል።
"የእግዚአሔር ልጅ በተለየ መልኩ መገለጥ ቢፈልግ ኖሮ ከእኛ ከሰው ልጆች በተለየ አካል በተገለጠ ነበር ፤ነገር ግን በሌላ ሳይሆን በእኛ በሰው ልጆች ሥጋ ተገለጠ ። ይህንንም ሥጋ ነውር ነቀፋ ከሌለባት ንጽህት ቅድስት ከሆነችው ከድንግል ማርያም ነሳ ፣ ይህም ሥጋ ያላደፈ በዘርአ ብእሲ(ከወንድ ዘር) ያልሆነ በግብረ መንፈስ ቅዱስ በአምላክነቱ በማይመረመር ጥበቡ ሰው ሆኖ ተወለደ ባጭር ቁመት በጠባብ ደረትም ተገለጠ ፣ " ሐዋርያው እንዳለ ነውርን ያንከባልል ዘንድ ኅጢያትን ያስወግድ ዘንድ የዲያብሎስን ስራ ያፈርስ ዘንድ የእግዚአብሔር ልጅ፤ እግዚአብሔር ተገለጠ። (፩ኛ ዮሐ፫፣ ፰)
ይቆየን።
ታህሣሥ ፰ ቀን፳፻፱ ዓ.ም.
-----------------------------------------------------------------------------
ትርጉም፦ በመምህር ቸርነት ይግረም( PhD Candidate)
Sources፦
1.Mary and Church Fathers
2.On the Incarnation of the Word
3.Against the Arians

No comments:

Post a Comment