Tuesday, April 5, 2016

እግዚአብሔር በቅዱሳኑ አድሮ የሚሰራው ስራ እጹብ ድንቅ ነው:

 እግዚአብሔር በቅዱሳኑ አድሮ የሚሰራው ስራ እጹብ ድንቅ ነው:
====================================


የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሯችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ የኑሯቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በሃይማኖት ምሰሏቸው::እብ 13:7
እግዚአብሔር የጸጋ ሁሉ ባለቤት ነው ስለዚህ ለፍጥረቱ የሚሰጠው የጸጋ አይነት ውስን ስፍር ቁጥር ልናበጅለት አንችልም:: የምናውቅበት መንገድ ግን አለን ይህውም በየጊዜው ለሚነሱ ቅዱሳን የሚሰጠውን ጸጋ መመልከት ብቻ ነው:: እግዚአብሔር በቅዱሳኑ አድሮ የሚሰራው ስራ እጹብ ድንቅ ነው:: በመሆኑም በገድላቸውና በታምራቸው ለህሊና የሚያስደንቅ ነገሮችን እንመለከታለን:: በቅዱሳን ገድል ላይ ያሉት ቃል ኪዳኖች መረዳትና የነእርሱንም ስም በመጥራት እግዚአሔርን መማጸን በረከትን ያሰጣል::ለምሳሌ ነብየ እግዚአብሔር ኤልሳን ብንመለከት አምላከ ቅዱስ ኤልያስን በመጥራት በመጠምጠሚያው ባህር ተከፈሎለታል ከዚህ የምንረዳው የቅዱሳንን ስም በመጥራት አምላከ ቅዱሳንን ብንማጸነው የእነርሱን ዋጋ እንቀበላለን ማለት ነው::
በዚህም መሰረት የቅዱሳንን ገድል ጽፎ ማስቀመጥና ትውልድ ከእነርሱ ህይወት እንዲማር ማድረግ ከብሉይ ኪዳን ጀምሮ የነበረ በአዲስ ኪዳንም የነበሩ አበው ለኛ ያቆዩልን የቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ሃብት እንጂ ልብ ወለድ ድርሰት አይደለም::

መሆኑም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በውጭ የተጻፉትን ገድላት ተርጉማ በሃገር ውስጥ የነበሩትን ቅዱሳን ገድል ጽፋ ደጉሳ አስቀምጣለች እንግዲህ ቅዱሳን ሲነሱ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ስትነሳ ደግሞ ቅዱሳን መነሳታቸው ግድ ነው:: ለዚህም ነው ሃገረ ቅዱሳን የተሰኘችው::
ዛሬ በሃገራችን ኢትዮጵያ ያሉትን ተደጉሶ የተቀመጠውን ገድለ ቅዱሳን ስናገላብጥ እግዚብሔር በቅዱሳኑ አድሮ የሰራውን ድንቅ ነገሮች እንመለከታለን::
እስኪለዛሬ በጉብዝናው ወራት በለጋ እድሜው ከክርስቶስና ከመስቀሉ ጠላቶች ጎን አልቆምም በማለት በመከራ ብረት ምጣድ ላይ ተጥዶ በሞት ስለታማ ጥርስ ተፈጭቶ አንድ ጊዜ ለቅዱስን ፈጽሞ ስለተሰጠችው ሃይኖት የተጋደለውን የሰማእቱ ቅዱስ ጊዮርጊስን ገድል አና እግዚአብሔር ያደረገውን ድንቅ ስራ አብረን እንመለከታለን::
ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስንበ70ው መኳንንት ፊት ሰለ ክርስቶስ የባህሪ አምላክነት በመመስከሩ አያሌ ፈተናዎች ደርሰውበታል::ጣኦታትን በመናቅ የነገስታቱን ትእዛዝ ባለመቀበሉ የመከራ በር ተከፈተበት ዲዲያኖስ በሰማዕቱ ላይ የሞት አዋጅ አወጀበት መከራው ተጀመረ::
ቅዱስ ጊዮርጊስ በእንጨት ላይ ተሰቀለ ሰውነቱ እስከሚተለተል ድረስ ተገርፈው ወደ እስር አስገቡት በስቃይ መቀበያ አልጋ ላይም አስተኝተው አጥንቱ እስከሚሰባበር ሰውነቱ በደም እስኪጥለቀለቅ ድረስ በብረት አሰሩት ድድያኖስም ዳግመኛ በእንጨት መስቀል ሰቅለው አጥንቱ ከነስጋው እንዲያደቁት አደረገ ሰማዕቱ ግን ስለ ክርስቶስ ፍቅር ስቃዩን ታገሰ ከተሰቀለበትም አውርደው የችንካር ጫማ አጫሙት እንዲሄድም አዘዙት ሰማዕቱ ግን ችንካሮች የእግሩን ስሮች ስለበጣጠሱት ቆሞ መሄድ ተስኖት አጎንብሶ ሔደ ያጨካኝ ንጉስ ግን አሁንም ሳይራራለት በእንጨት ተሰቅ በሰባ ችንካሮች እንዲሰፋ አደረገ ከተሰቀለበትም እንጨት አውርደው የፈላ ውሃ ውስጥ ከተው አንጎሉ እስኪፈስ ድረስ በመዶሻ መቱት ከዚህ በኋላ ቢያዩት አልሞተም ከዛ አውጥተው ከትልቅ ድንጋይ ጋር አስረው ከድናጋዩ ጋር አንከባለሉት ዳግመኛ ጥርስ ባለው ብረት ሆዱ ተቀዶ የሆድ እቃው መሬት እስኪፈስ ድረስ ደበደቡት በቆሰለው ሰውነቱም ላይ መጻጻና ጨው አምጠተው በተተለተለው ሰውነቱ ላይ ከጸጉር በተሰራ ማቅ እያሹ መዘመዙትመከራውንም አበዙበት ቅዱስ ጊዮርጊስ ግን ስለክርስቶ ስ ፍቅር የህን ሁሉ መከራ በጸጋ ተቀበለ::
ይህም አልበቃ ብሎዋቸው በመንኮራኩር ተፈጭቶ ሞተ እነዚያ ክፉዎችም ሰው በማያገኘው ቦታ ቀበሩት ክብር ይግባውና ጌታችን አምላካችን መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን አጥንቱን ሰብስቦ እፍ አለበት ሰማዕቱ ነፍስ ዘራይህንንም ባየ ጊዜ ንጉሱ ዳግመኛ በመጋዝ ከጨንቅላቱ ጀምረው ለሁለት እንዲከፍሉ አደረገ ለሁለት ሰንጥቀው የወደቀውን የሰማዕቱን ስጋ በጋለ ብረት ምጣድ ላይ አድርገው እስኪያርና ከምጣዱ ጋር እስኪጣበቅ ድረስ አቃጥለው በታላቅ ጉድጓድ ውስጥ ከነ ምጣዱ ቀበሩት ጌታችን ግን ቅዱስ ሚካኤልን መቃብሩን እንዲከፍት አዞ የሰማዕቱን እራሪ አጽሙን ጠራው ቅዱስ ጊዮርጊስም ምንም እንዳላገኘው ህያው ሆኖ ተነሳ::
ዳግመኛ ያ ከሃዲ ንጉስ የሰማዕቱን መነሳት አይቶ ሰማዕቱን በግን አስረው እንዲሰነጥቁት ዝፍት በላዩ አፍስሰው እንዲቃጥሉት አደረገ ታሰረ ተሰባበረ ተቃጠለም ከስቃዩ ም ብዛት የተነሳ ነፍሱ ከስጋው ተለየች::አጥንቱና ስጋው አመድ እስኪሆን ድረስ አሳርረው አድቅቀው ጥር 18 ቀን ይድራስ በተባለ ተራራ ላይ በተኑት::ጌታችን ግንየሰማዕቱን መከራና ጽናት አይቶ የተበተነውን አጥንትና የሰጋውንብናኝ ሰብስቦ ነፍስ ዘራበት::እንዚያ ጨካኞች ባዩት ጊዜ የዚህሰው ምትሃቱ ሃይል አለው ብለው እንዲገደል ተያዘ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አማትቦ በድዲያኖስ ጭፍሮ ች አንገቱን ተቀላ ከሰማእቱም አንገት ደም ውሃ ወተት ፈሰሰ::
የሰማዕቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ ምልጃና ጸሎቱ ረድኤትና በረከቱ በኛ በምናምን ልጆቹ ጸንቶ ይኑር እኛም ዋኖ ቻችሁን አስቡ የተባልነው ለዚህ ነው ገድላቸውን በማንበብ በማድመጥ ከአባቶቻችን እግር ስር ቁጭ ብለን በመማር የቀደሙትን ስናስባቸው በስማቸው መንፈሳዊ የግባራትን ስንፈጽም የጻድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነው ሲል የተናገረው አምላከ ቅዱሳን ከነሱ በረከት ተሳታፊዎች ያደርገናል::የሰማነውን በልቦናችን አሳድሮ በቅዱሳኑ ቃል ኪዳን ይጠብቀን 
ለዚሁም የአባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር ይርዳን አሜን!

No comments:

Post a Comment