Thursday, March 17, 2016

‹‹ንጹም ጾመ ወናፍቅር ቢጸነ››

 


እንኳን ዓብይ ጾም አደረሳችሁ

ምን  እንጹም ባልንጀራችን እንውደድ

‹‹እስመ ጾም እማ ለጸሎት ወእኀታ ለአርምሞ ወነቅዓ ለአንብዕ ወጥንተ ኩሉ ገድል ሠናይት››
 ጾም የጸሎት እናት የአርምሞ እህት የዕንባ ምንጭና የመልካም ገድል ሁሉ ጥንተ መሠረት ናት

ባሕረ ጥበባትና ስንዱ እመቤት የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ልዩ ከሚያደርጓት ነገሮች መካከል አንዱ የሒሳብ ስሌት ሰርታ የዘመን መቁጠሪያ ሳይንስን (ባሕረ ሐሳብን) ቀምራ አበቅቴና መጥቅን ለይታ የአማትና የበዓላትን ዕለታት ወስና ለትውልድ ማስተለለፏ ነው፡፡ በመሆኑ ዘወትር በየዓመቱ ሰባቱን የአዋጅ አጽዋማት ታውጃለች፣ ከነዚህም መካከል አንዱና ርዕሰ አጽዋማት ሆነው የዓይ ጾም (የጌታ ጾም) ነው፡፡ በቤተከርስቲያናችን ቀኖና መሠረት እምነት ጾም ጸሎትና ምጽዋት የማይለያዩ አንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ከመሆናቸውም ባሻገር ጾም ጸሎትና ምጽዋት እንደ ጣራና ግርግዳ የመልካም ሥራ አበጋዞች ናቸው፡፡ እምነት በመሠረትነቱ እንዲጸና እንዲያድግና ሥራ እንዲሠራ ጾም ጸሎትና ምጽዋት ያስፈልጋሉ፡፡ ጾምም ከእምነትና ከጸሎት ጋር ሲሆን ድንቅ ሥራ ያሰራል ይህ ከሆነ ዘንድ ደግሞ በጎ ሥራን ሳይሰሩ ፍቅርን ሳይዙ ምህረትንና ይቅርታን ሳያደርጉ እጾማለሁ ማለት የረሃብ አድማ እንጂ ክርስቲያናዊ ጾም አይደለም፡፡
አበው በምሳሌ ሲያስተምሩ ቂም ይዞ ጸሎት የለም እንዲሉ ጌታችንም መድኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አይሁድን ጻሐት ፈሪሳውያንን በገሰጸበት አንቀጽም ሆነ በተራራው ስብከቱ እንደ ግብዞች አትጹሙ ነው ያለው፣ እነሱ የጾምን ትርጉም ባለመረዳት ክፋትን ተንኮልን፣ ቅሚያንና ስስትን እየሰሩ ባልንጀራቸውን በእግዚአብሔር አርአያና ምሳሌ የተሰራውን ሰው እያስቀየሙ ሕግና ሥርዓትን እናከብራለን እንጾማለን ይላሉና፣ ክርስቲያኖች ግን ከእንዲህ ዓይነቱ ፍሬ ከሌለው ጾም ራሳችን ልናር ይገባል፣ የሰማይ አባታችንም ምህረቱን ቸርነቱን እንዲያበዛልን በጾማችን ወቅት የበደሉንን ይቅር እንበል (ማቴ 6፡14 ና 16፣ ማቴ 23፡1) ከተራራ የሚከብድ ከሰይጣን ፆር የሚከፋ ነገር የለም፣ ተራራ ሲወጡት ያደክማል፣ ተነስ ብሎ ማዘዝና ከዚህ ወደዚያ ዕለፍ ማለት ደግሞ የበለጠ ይከብዳል በአካላዊ እንቅስቃሴ ብቻ የኅሊና አቀበትም ነው፡፡  በልቡና ይከብዳል ነገር ግን በእምነት፣ በጾምና በጸሎት ሁሉም ይቻላል፡፡ ጌታችንም ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው ይህንን አስረግጦ ሲያስተምር ‹‹ለሚያምኑ ሁሉ ይቻላል›› እምነት ከባዱን ያቀላልና እምነት የራቀውን የሚያቀርብ የረቀቀውን ሚያጎላ የተሰወረውን የሚገልጽ የማይቻለውንና የማይገፋውን የሚያስችል ክፉ ቀንን ለመሻገር ተስፋን ለመሰነቅ የሚረዳ ረቂቅ መሳሪያ ነው፡፡ ታዲያ እምነትን ደግሞ ኀይል የሚሰጡት እንደ ጣሪያና ግድግዳ ሆነው የሚያስውቡት ጾም ጸሎትና ምጽዋት ናቸው፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት ተራራውን ማስወገድ አጋንንትን ማውጣት በተሳናቸው ጊዜ እረኛቸውን መድኀኔዓለምን ቀርበው ‹‹ይህን ማድረግ የተሳነን፣ ልናወጣውስ ያልቻልነው ስለምንድን ነው?›› ቢሉት ጌታችንም ክብር ምስጋና ይግባውና ስለእምነታችሁ ማነስ ነው? እውነት እላችኋለሁ የሰናፍጭ ቅንጣት ያህል እምነት ቢኖራችሁ ይህንን ተራራ ከዚህ ተነስተህ ወደዚያ ዕለፍ ብትሉት ያልፋል የሚሳናችሁ ነገር አይኖርም ካላቸው በኋላ በማከልም ይህ ዓይነት ግን ከጾምና ከጸሎት በቀር አይወጣም አላቸው›› (ማቴ 17፡14-21) ለመሆኑ ጾም ምንድን ነው? ጾም ማለት ሰውነት ከሚያስፈልጋቸው ነገሮች ሁሉ መከልከል መወሰን ማለት ነው ወይም ለሰውነት የሚያምረውን የሚያስጎመጀውን ነገር መተው ማለት ነው፡፡ ጾም ከሃይማኖት ጋር ዘላዓለማዊ ዝምድና ስላለው ሃይማኖት ባለበት ቦታ ሁሉ ጾም አለ ይልቁንም በብሉይ ኪዳን ጾም ከፍተኛ ቦታ አለው የብሉይ ኪዳን ነቢያት ከእግዚአብሔር ጋር በሚገናኙበት ወራት እህል ውሃ ባፋቸው አይገባም ነበር፡፡ (ዘፀ 34፡28) በኃጢዓት ብዛት የታዘዘው የእግዚአብሔር መቅሰፍት መዓት የሚመለሰው ሕዝቡ በጾም ሲለምኑትና ሲማልዱት ነበር (ዮና 3፡5-8)
በሐዲስ ኪዳንም ጾም ሰው ሰራሽ ሕግ ሳይሆን፣ ራሱ መድኀኒታችን በመዋዕለ ሥጋዌው የሥራ መጀመሪያ አድርጎ የሰራው ሕግ ነው (ማቴ 4፡2 ፣ ሉቃ 4፡2) ከዚያ በኋላም ቤተክርስቲያን እንዲያገለግሉ የታዘዙ ሐዋርያትም ከመንፈስ ቅዱስ በየጊዜው ትዕዛዝ የሚቀበሉት በጾምና በጸሎት ላይ እንዳሉ ነበር (ሐዋ 13፡2) ለስብከተ ወንጌል የሚያገለግሉ ዲያቆናትና ቀሳውስት የሚሾሙትም በጾምና በጸሎት ነበር፡፡ (ሐዋ 13፡3 ፣ ሐዋ 14፡23) እነ ቆርኔሌዎስና ሌሎችም የአዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች ያላሰቡትን ጸጋ ያገኙት በጾም በጸሎት ፈጣሪያቸውን ማልደው ነው፡፡ (ሐዋ 10፡30)
የጾም ሃይማኖታዊ ትርጉም ፈጣሪን መለመኛ ከኀጢዓት ቁራኛ መላቀቂያ መሣሪያ ስለሆነ፣ በጾም ወራት ላምሮት ለቅንጦት የሚበሉ ወይም ለመንፈሳዊ ኀይል የሆነሥጋዊ ፍትወትን የሚያበረታቱ የአልኮል መጠጦችን ፣ ሥጋንና ቅቤን ወተትና እንቁላል ማራቅ ታዟል፡፡ (ዳን 10፡3 ፣ መዝ 118፡24) ከመብላት ከመጠጣቱና ከሌላው ደስታ ጋር ባልና ሚስት በምንጣፍ አልጋ አይገናኙም (1ቆሮ 7፡5) ይህም በትዳር ላይ ላለን በእግዚአብሔር የተከለከለውን ሰው ሰራሽ ወሊድ ቁጥጥር ዘርን ውጪ ከማፍሰስ (ዘፍ 38፡9-10) ወይም ማንኛውንም ዘመናዊ ቁጥጥር ከመጠቀም ሊጠበቅ የሚችል የመከላከል ሥርዓት ነው፡፡
ጾም  በትምህርተ ሐዋርያትም ሆነ በሊቃውንት ስብከት በአጽንኦት ከመነገሩም ባሻገር ቅዱሳን ሐዋርያት ጾምን የስራቸው መጀመሪያ የአገልግሎታቸው ስኬት መንፈሳዊ መሳሪያ ሆኗቸው እንደነበር በመጽሐፍ ተጽፎ እናነባለን ቅዱሳን ሊቃውንትም ቢሆን ‹‹እስመ ጾም እማ ለጸሎት ወእኀታ ለአርምሞ ወነቅዓ ለአንብዕ ወጥንተ ኩሉ ገድል ሠናይት›› ጾም የጸሎት እናት የአርምሞ እህት የዕንባ ምንጭና የመልካም ገድል ሁሉ ጥንተ መሠረት ናት በማለት አስተምረዋል፡፡
በሌላው ጾምና ምጽዋት የማይለያዩ እንደሆነ ሲያስተምሩ ‹‹ነዳያንን ለመመገብ የሚጾም ንዑድ ነው›› ይህም እንዴት ይሆናል ቢሉ ከፍቅረ ቢጽ የሚደመር ከአስርቱ ትዕዛዛት የሚቆጠር በጎ ሥራን መሥራት ተገቢ ነውና ነው፡፡ ጾመኛው ቢያንስ በቀን ውስጥ ቁርሱን ስለማይበላ ያንን የቁርሱን ወጪ ችግረኞች እንዲረዱበት ለመረዳጃ ማኅበር ወይም በቤተክርስቲያን አካባቢ ለሚገኙ ነዳያን ቢሰጥ ጾሙን የበለጠ ክርስቲያናዊ ያደርገዋል፡፡ (ኢሳ 58፡6) እንዲሁም ከቁርሱ በተጨማሪ በፍስኩ ወራት የነበሩት የወተቱ፣ የእንቁላሉ፣ የሥጋው. የቅቤው ሁሉ ወጪ በጾሙ ወቅት ስለሚቀርለት ጾመኛው ለመመጽወት ያለው ዕድል በጣም የሰፋ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ማንኛውም ክርስቲያን ሲጾም የማይመጸወት ከሆነ ቁጠባ አደረገ እንጂ ጾመ አይባልም በመሆኑም ጾም በቅዱሳት መጻሕፍት የተገለጹትን ምክሮች እያስታወሱ ከኀጢዓት ለመንጻት፣ ስለራስ የታሰበውን ለነዲያን በመስጠት የሚጾም ከመሆኑም ባሻገር ጾም ለራስ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም፣ ለወዳጅ ብቻ ሳይሆን ለጠላትም የሚሰራ መንፈሳዊ ሥራ ስለሆነ ፍቅረ ቢጽን የሚያስተገብር በጎ ምግባር ነው፡፡ ‹‹ለሚያሳድዱህ ጹምላቸው ›› (ዲ.ድ 1፡3) እንዲል ጌታችንም በወንጌል ‹‹ለሚያሳድዷችሁ ጹሙ ጸልዩ›› ብሎ አስተምሯል (ማቴ 5፡44-48) እንዲሁም በደዌ ዳኛ በአልጋ ቁራኛ የተያዙትን በስደትና በምርኮ ያሉትንም በጾም ወራት በማስታወስ መጸለይ ይገባል፡፡ በሌላው በጾም ወራት ከመብልና ከመጠጥ መወሰን ብቻ ሳይሆን ዓይን ክፉ ከማየት፣ አንደበት ክፉ ከመናገር መቆጠብ ግድ ይላል፡፡ ሊቁ ቅዱስ ያሬድም ይህን ሲያጸና በጾመ ድጓ ድርሰቱ ላይ ‹‹ይጹም ዓይን፣ ይጹም ልሳን እዝንኒ ይጹም እምሰሚዓ ሕሡም በተፋቅሮ›› በማለት አስተምሯል፡፡
በአጠቃላይ የጾም ጊዜ ፈጣሪን መለመኛ፣ የኀጢዓት ማስተሰሪያ ፣ ሕወት ለእግዚአብሔር ሕግ እንዲገዛ ማሰልጠኛ ነው፡፡ ክፉ መንፈስን ጦርና ፍላጻ ማስወገጃም ስለሆነ ጾም በጥንቃቄ ሊጠብቁትና ሊፈጽሙት የሚገባው ሃይማኖታዊ ግዴታ ነው፡፡ በመብል ምክንያት ድል የሆነውና ለኀጢዓት መግቢያ በር የከፈተው ሕይወት በጾም ኀይልና ጽናት እንደሚኖረው ያሳያል፡፡ (ዘፍ 2፡26-27) ፣ (ዘፍ 3፡6-8) ፣(መቃብያን ሳልስ 4፡24-34)
ጾም ሕይወት በእግዚአብሔር ፊት ትሁትና ታዛዥ እንዲሆን ያደርጋል (መዝ 34፡13) ፣ ሰውነትን በመንፈሳዊ መንገድ ለመምራት ይረዳል (መዝ 68፡10) ፣ የመልካም ሥራና የመንፈሳዊ ኀይል ተቃራኒ የሆኑ እንደ ስስት ትዕቢትና ፍቅረ ነዋይና ሐሰት የመሳሰሉ የኀጢዓት አውራዎችን ያርቃል፣ በመንፈሳዊ ሕይወት ላይ የሚዘምቱ የኀጢዓት ሠራዊትን ድል ለመንሳት ያበቃል፣ ሕይወትን ወደ ጽድቅ መንገድ ይመራል ለጸሎት፣ ለምጽዋት ፣ ሰውና እግዚአብሔር ደስ የሚሰኙበትን ሥራ ለመሥራት ያተጋል›› (2ኛሳሙ 12፡16-23 ፣ ማቴ 4፡1-11) ፣ እንዲሁም በኀጢዓት ምክንያት የሚታዘዝ መቅሰፍት የሚመለሰው ሕዝቡ ወደ እግዚአብሔር ተመልሶ በጾም በጸሎት ፈጣሪውን ሲለምንና ሲማልድ ነው፡፡ (ዮና 3፡5-10)
ጾም ከሃይማኖት ጋር የማይለያይ ቁርኝት ስላለው ሥርዓቱና የአፈጻጸሙ መንገዱ ይለያይ እንጂ በሃይማኖት ለሚኖር ሁሉ ጾም መንፈሳዊ ትዕዛዝ ነው፡፡ ጾም በብሉይ ኪዳን ታላቅ ሥፍራ እንደነበረውና ነቢያተ እግዚአብሔርም ታላላቅ የኃይልና የተአምራት ሥራ ይሰሩ የነበሩት በጾምና በጸሎት እንደሆነ ከእግዚአብሔር ጋራም ቃል በቃል የተነገሩት እህልና ውሃ በአፋቸው ሳይገባ በመጾም እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል፡፡ (ዘጸ 34-28)
በብሉይ ኪዳን ከአንድ ቀን ጀምሮ እንደየ ጊዜው ሁኔታ ሦስት  ሰባት ፣ አስራ አራት፣ ሃያ አንድ ና አርባ ቀናት የጾሙ ብዙዎች ነበሩ፡፡ ፈሪሳውያን ሳይቀሩ በየሳምንቱ ማክሰኞና ሐሙስ ሁለት ቀን በዓመት መቶ አራት ቀን ይጾሙ ነበር (ሉቃ 18:9-14) በሀገርና በወገን ላይ ለሚመጣ መቅሰፍት ሳይቀር መፍትሔው ወደ እግዚአብሔር በመመለስ በጾምና በጸሎት መለመን እንደሆነ ከቀደሙት ነገስታትና እግዚአብሔር ሰዎች መጽሐፍ ቅዱን መሠረት አድርገን እንማራለን፡፡ የእሴይ ልጅ ንጉስ ዳዊት የሳልና የልጁ የዮናታን ሞት፣ የብዙ እስራኤል ሠራዊትን እልቂትና የጦርን ግንባር መፍታት በሰማ ጊዜ ለእግዚአብሔር ሕዝብ ለእስራኤል ወገን እንባ በማፍሰስ የአንድ ቀን ጾም ጾሟል፣ (2ሳሙ 1፡11-12)
እንዲሁም ንጉሥ ዳዊት እግዚአብሔር ያደረገለትን ውለታ በመዘንጋት ኦርዮንን በግፍ አስገድሎ ከኦርዮን ሚስት ጋር በዝሙት የወለደው ሕፃን በታመመ ጊዜ፣ ከዙፋኑ ወርዶ ራሱን ተከናንቢ ፣ ጫማውን አውልቆ አመድና ትቢያ በራሱ ላይ በመነስነስ ወደ ደብረዘይት ተራራ በመውጣት ለሰባት ዕለታት እንደጾመ ልጁ ቢሞትበትም በምትኩ ግን ሰሎሞንን ያህል ጥበበኛ ልጅ እንደሰጠው ሰላሙም እንደተመለሰለት በመጽሐፍ ተመዝግቦልናል፡፡ (2ሳሙ 12፡12)
አስቴርም ከኢትዮጵያ ጀምሮ እስከ ሕንድ ድረስ ተበትነው ለነበሩት ሕዝቦች ግፍና ጭቆናቸውን ተመልክታ መርዶክዮስን ከሞት ወገኖቿን ከጥፋት ለማዳን ሁሉም ለሦስት ቀንና ሌሊት እህል ውሃ ሳይቀምሱ እንዲጾሙ አሳውጃ እሷም ከደንገጡሮቿ ጋር በመጾም ከእግዚአብሔር ዘንድ መልስ በማግኘት በክፉ አድራጊዎች ላይ ድልን ለመቀዳጀት በቅታለች እስ 4፡13-16 ፣ 7፡10
ነቢየ እግዚአብሔር ዳንኤልም ስለተገለጠለት አስደናቂ ምስጢርና ስለተሰጠው ሃብተ ትንበያ ሃያ አንድ ቀን የጣመ የላመ ምግብ ሳይበላ ወይንና የሚያሰክር መጠጥ ሳይጠጣ እንደጾመና፣ በጾሙ ፍጻሜም መላዕክተ እግዚአብሔር ተገልጠው እንዳረጋጉት ለሕይወት ደስ የሚያሰኘውንም መልካም ዜና እንደነገሩት ተጽፎ እናነባለን፡፡ (ዳን 10፡3-19) ሌሎችም አበይት ነቢያት ሙሴ፣ ኢያሱና ኤልያስ እያንዳንዳቸው አርባ መዓልትና አርባ ሌሊት ጾመዋል በተለይ ሊቀ ነቢያት ሙሴ በሲና ተራራ ላይ ከእግዚአብሔር ጋር ቃል በቃል ሲነገጋር ቆይቶ ዐሥርቱ ትዕዛዛት የተጻፈባቸውን ጽላቶች ተቀብሎ ሲመለስ ሕዝበ እስራኤል ግን እግዚአብሔር ካዘዛቸው መንገድ ወጥተው የጥጃ ምስልን ጣዖት ሰርተው በማምለክ ፈጣሪያቸውን በማስቆጣት ለቅጣትና ለጥፋት ተዘጋጅተው ባገኛቸው ጊዜ ‹‹ስለሰራችሁት ኀጢዓት እርሱንም ለማስቆጣት በእግዚአብሔር ፊት ክፉ የሆነውን ነገር ሁሉ ስላደረጋችሁ እግዚአብሔር ሊያጠፋችሁ ከተቆጣባቸሁ ከቁጣውና ከመዓቱ የተነሳ ስለፈራሁ እንደ ፊተኛው በእግዚአብሔር ፊት ዓርባ ቀንና ሌሊት ወደቅሁ፣ እንጀራ አልበላሁም ውኃም አልጠጣሁም እግዚአብሔርም ሰማኝ›› በማለት በሚመራው ሕዝብ ላይ ስለመጣው መቅሰፍት መጾሙን ይናገራል፡፡ (ዘዳ 9፡5 ፣ዘዳ 9፡25-29፣ ዘዳ 10፡10 ፣ ዘፀ 24፡13-18 ፣ ዘፀ 32፡15-17)
የሁልም የጾማቸው አፈጻጸምና ከጾማቸው ጋር ያቀረቡት የጸሎት ዓይነትም ለትምህርታችን ይሆን ዘንድ ተመዝግቧል፡፡

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ብሉይ ኪዳኑን ሕግና ሥርዓተ ጾም ለመፈጸም ዓርባ ቀንና ሌሊት የጾመው አበይት ነቢያት የጾሙትን ጾም ለማጽደቅ ነው፡፡ (ማቴ 4፡1-11፣ ማቴ 5፡17) ጾም በጎውን ነገር ሁሉ ከእግዚአብሔር ለማግኘት የሚረዳ መሣሪያ ነው፡፡ ጾም ፈቃደ ሥጋን ድል ይነሣል፣ የነፍስን ደዌ ይፈውሳል ከእግዚአብሔር ተልኮ የሚመጣውን በትረ መዓት ይመልሳል ጾም የሥራ መጀመሪያ መሆኑን ሲያስተምር መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በ ፴ ሰላሳ ዘመኑ በፈለገ ዮርዳኖስ ፣ በእደ ዮሐንስ ተጠምቆ ልጅነቱን አስመስክሮ ዕለቱን ወደ ገዳመ ቆሮንጦስ ነው የሄደው፣ በዚያም ከዘረጋ ሳያጥፍ፣ ከቆመ ሳይቀመጥ፣ ዓርባ መዓልትና ዓርባ ሌሊት በመጾም  ጾምን የሥራ መጀመሪያ አድርጎታል፡፡ (ማቴ 4፡1-11) ይህንን ለመግለጽ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ‹‹ጾመ እግዚእነ በእንቲአነ አርአያሁ ከመ የሀበነ›  ጌታችን ስለ እኛ ጾመ አርአያውን ይሰጠን ዘንድ በማለት ዘምሯል፣ እርሱ የጾመው ለእኛ አርአያና አብነት ለመሆን ነው እንጂ በደል ኖሮበት አይደለም፡፡ ኢሳ 53፡4 ፣ 1ኛጤጥ 2፡21 ብዙ ሰዎች ሕገ ጾምን እንደልጓም አውልቀው እየጣሉ እንብላ እንጠጣ ነገ እንሞታለን›› በማለት ለሚያልፈው ዓለም ሲጨነቁለትና ለመቃብር ቀለብ ሥጋን ሲያወፍሩለት ይታያሉ፡፡ ያዕ 5፡5 ፣ ፊልጵ 3፡18-21 ሌሎች ደግሞ ጾም ሕግ አይደለም፣ የመጾም ግዴታ የለም ጌታ ጾሞልናል እኛ መጾም አያስፈልገንም ይላሉ ይህ ሁሉ ከኅሊና ድካም የሚመነጭ ከንቱ አስተሳሰብ ነው፡፡ ጌታ የጾመው ጾም በቂ ሆኖ ከሱ በኋል መጾም መጸለይ የማያስፈልግ ቢሆን ኖሮ ግልጽ ሆኖ ይጻፍ ነበር፡፡
ነገር ግን ጾም እስከመጨረሻው ከክርስቲያኖች ሕይወት የማይለይ ሕግ መሆኑን ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለዮሐንስ ደቀመዛሙርት በሰጠው መልስ እናረጋግጣለን፡፡ የዮሐንስ ደቀመዛሙርት ወደ ጌታ ቀርበው እኛና ፈሪሳውያን አብዝተን እንጾማለን ያንተ ደቀመዛሙርት ግን ለምን አይጾሙም?›› ብለው በጠየቁት ጊዜ ክብር ይግባውና መድኀኔዓለም የሰጣቸው መልስ የሙሽራው ሜዜዎች ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ መጾም አይችሉም፣ ነገር ግን ሙሽራው ከመካከላቸው የሚወሰድበት ጊዜ አለ ያን ጊዜ ይጾማሉ›› በማለት መልሶላቸዋል፡፡
አምላካችን ጾም የማያስፈልግና እርሱ የጾመልን ጾም እኛ እንዳንጾም ቢሆን ኖሮ ከዚህ በኋላ መጾም የለባቸውም እኔ የጾሙኩት በቂ ነው ብሎ በመለሰ ነበር፣ ነገር ግን እርሱ የጾመው ለአርአያ ለአብነት እንደሆነና እኛም ከዚያ በኋላ የተነሳነውም ሆነ እስከ ዓለም ፍጻሜ የሚነሱት የእሱን ፈለግ ተከትለን መጾም እንዳለብን ያስረግጣል፡፡ በመሆኑም በሚዜዎች የተመሰሉት ቅዱሳን ሐዋርያት ሙሽራው ክርስቶስ ከእነሱ ከተወሰደ በኋላ ጾምን የሥራቸው መጀመሪያ አድርገው ጾመዋል፡፡ እኛም ከእነሱ ተቀብለን ከጌታ ተምረን ስንጾመው እንኖራለን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንም ብሉይ ኪዳንን ከሐዲስ ኪዳን አስተባብራ ይዛ፣ ሥርዓተ አበውን ጠንቅቃ ጠብቃ የምትመራ በመሆኗ ክርስቶስ እንደተጠመቀ አጥምቃ፣ እንደጾመ ጹሙ ብላ ታስተምራለች፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ይቆየን

No comments:

Post a Comment