Wednesday, February 17, 2016

ንሕነሰ ንሰብክ ክርስቶስሃ ዘተሰቅለ (1ቆሮ 1: 22)

                   

                     ንሕነሰ ንሰብክ ክርስቶስሃ ዘተሰቅለ (1ቆሮ 1: 22)
                     -------------------------------------------
ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ምእመናን በላከው መልእክት ውስጥ የእርሱና የሌሎች ቅዱሳን ሐዋርያት ተልእኮ ምን እንደ ሆነ ያስረዳበት ቃል ነው እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን የሚለው።
ሐዋርያት ወንጌልን ለማስተማር ወደ ዓለም በወጡበት ወቅት ከአይሁድ፣ ከሮማውያንና ከግሪካያውን የተለያዩ ፈተናዎች ገጥሟቸው ነበር። አይሁድ ወልደ አምላክ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የሰቀሉ ምእመናን ከኢየሩሳሌም ወደ ተለያዩ የአሕዛብ መንደሮችና ከተሞች እንዲበተኑ ያደረጉ ሐዋርያት በዋሉበት እንዳያድሩ ባደሩበት እንዳይዉሉ ሲያሳድዱ የነበሩ በእግዚአብሔር ለማመን ተአምራትን ይናፍቁ የነበሩ ናቸው። ሮማውያን በአምልኮ ጣዖት ዓይነ ልቡናቸው የታወረ ከመሆናቸው ባሻገር ነገሥታቶቻቸው ራሳቸውን እንደ ፈጣሪ ቆጥረው ምሥል አቁመው ሕዝቡ እነርሱን እንዲያመልክ የሚያስደርጉ ሲሆኑ ግሪካውያን ደግሞ በእነ ሶቆራጥስ፣ ፕሌቶና አሪስጣጣሊስ ፍልስፍና ተይዘው በነገር ሁሉ መጠበብን (መፈላሰፍን) ዋና ነገራቸው ያደረጉ ሕዝቦች ነበሩ።

እግዚአብሔር ለሕዝቡ ሁሉ መዳን ያዘጋጀውን ጸጋ በሐዋርያቱ በኩል ልኮ ወንጌሉን ሲያበሥራቸው ቃሉን በደስታ ሰምተው መቀበል አምነው መከተል ተሳናቸው። አይሁድ እንደ ሙሴ ባሕር ከፍላችሁ ጠላት አስጥማችሁ ሕዝቡን አሻግራችሁ ደመና ጋርዳችሁ መና አዝንማችሁ አሳዩን አሉ። ግሪካውያንም አምላክ መስቀል ተሸከመ ደከመ ተራበ ተጠማ በዕፀ መስቀል ተሰቀለ ቢሏቸው እንደ ሞኝነት ቆጠሩት። ሮማውያንም በክርስቶስ በተደረገልን ቸርነት ሕዝብና አሕዛብ፣ ጨዋና ባርያ ወንድና ሴት የሚሉ ልዩነቶች ተወግደው ባርያዎች እንደ ጌቶቻቸው ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ ክብር ያላቸው እንደ ማንኛዉም ሰው ሊከበሩ የሚገባቸው መመለክም መሰገድም የሚገባው የሁሉ ጌታ ለሆነው ለእግዚአብሔር መሆኑን ሲሰሙ ክርስትናን እንደ ጠላት ማየት ሐዋርያትንም ማሳደድ ጀመሩ።
በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች የተነሣ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “መቼም አይሁድ ምልክትን ይለምናሉ፤ የግሪክ ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ። እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን” አለ። ይኽም የሐዋርያት የስብከታቸው ዋና ዓላማና ማዕከል ተአምር ወይም ፍልስፍና ሳይሆን ነገረ ክርስቶስ መሆኑን ያመለክታል። ይኽ ማለት ግን ሐዋርያት ስለ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መውረድ መወለድ መጠመቅ ማስተማር ተአማራት ማድረግ መሰቀል መሞት መነሣት ማረግ ጌትነት አምላክነት ዳግም ምጽአት ብቻ አስተማሩ ማለት አይደለም።
ሐዋርያት ተልከው በሄዱባቸው ቦታዎች ሁሉ ነቢያት ትንቢት በተናገሩለት፣ ሱባኤ በተቆጠረለት፣ ምሳሌ በተመሰለለት አምላክ ወልደ አምላክ በሆነው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እንዲያምኑና በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ተጠምቀው ሥርየተ ኀጢአት ሀብተ ውልድና ስመ ክርስትና ሕይወተ ልቡና እንዲያገኙ አስተምረዋል። አያይዘውም በእምንትና በጥምቀት የጸጋ ልጅንትን ያገኙ ምእመናን ቅዱሳንን በሚመስል አኗኗር ክርስቶስን ወደ መምሰል እንዲያድጉ፣ ከአረማውያን ግብር እንዲጠበቁ፣ በቅዱስ ጋብቻ ተወስነው የእግዚአብሔር ማደርያ ሰውነታቸውን ከዝሙት እንዲጠብቁ፣ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን መንጋውን ሕዝበ ክርስቲያንን የሚጠብቁ በየደረጃው ካህናትን እንዲሾሙ፣ ካህናትን አበው ኤጲስ ቆጶሳትን እንዲያከብሩ፣ በጾም በጸሎት እንዲ ወሰኑና በመንፈሳዊ ተጋድሎ እንዲበረቱ በቃል አስተምረዋል፤ በየ መልዕክቶቻቸው አስረድተዋል።
ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችንም የሐዋርያትን ፈለግ ተከትላ ነገረ ክርስቶስን ስታስተምር ሁለት ሺህ ዓመታትን አስቆጥራለች፤ አሁንም በማስተማር ላይ ትገኛለች። ሐዋርያት ከእግዚአብሔር ርቀው በተስፋ መቁረጥ ለርኩሰትና ለጥፋት የተጣሉትን ሁሉ በቃለ ወንጌል አጽናንተው በእምነት አጽንተው በጥምቀት ለሰማያዊ ልደት አድርሰው ለክርስቶስ ሙሽራ አድርገው ምእመናንን ያጩ ያቀርቡ እንደ ነበረው ሁሉ ጥንታዊቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ሳትበርዝ ሳትከልስ ወንጌልን ለሰው ልጆች እያስተማረች ብዙ ምርኮ ለእግዚአብሔር ስታቀርብ ኖራለች፤ አሁንም በማቅረብ ላይ ትገኛለች።
ይሁን እንጂ በሐዋርያት በሊቃውንትና በቅዱሳን በኩል አክብራ የተቀበለችውን ወንጌል ጠብቃ ብታቆይም ሐዋርያትን መስላ ተልዕኮዋን ብትፈጽምም አሁን አሁን አግልግሎቷን የሚነቅፉ፣ ሥርዓተ አምልኮቷን ሥጋና ደም ባሳያቸው መንገድ ሊቀይሩ በሂደትም የእግዚአብሔርን መንጋ ሊያናጉና ለአውሬው አሳልፎ ለመስጠት የሚሹ ስሑታን ተነሥተዋል። በፍቅረ ንዋይና ዓለምን በመውደድ የታወረ ዓይነ ልቡናቸውን በወንጌል ብርሃንነት ማብራት ቢሳናቸው በኀጢአት የበለየ (ያረጀ) ሕይወታቸውን ማደስ ቢሳናቸው ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን እናድስ፣ ኦርቶዶክስ መታደስ አለባት በማለት በተዘራው ንጹሕ የስንዴ ማሳ (በቤተ ክርስቲያን) ላይ እንክርዳድ የሚዘሩ ተነሥተዋል። እነዚህ ስሑታን በሚገርም ሁኔታ ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ወንጌል አታስተምርም፤ ብታስተምርም ክርስቶስን አትሰብክም የሚል መሠረት የሌለው ትችት በመሰንዘር ላይ ይገኛሉ። ለመሆኑ ክርስቶስን መስበክ ማለት ምን ማለት ነው? ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችንስ ክርስቶስን እንዴት ትሰብካለች? ቀጥለን በጥቂቱ ለማየት እንሞክራለን።
ክርስቶስን መስበክ ማለት የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ባሕርይውን፣ ለምን ሰው እንደ ሆነና በጎ ፈቃዱ ምን እንደ ሆነ ማስተማር ነው። በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አስመልክታ የምታስተምረውን ትምህርት ከብዙ በጥቂቱ ቀጥለን እንመለከታለን።
1. ባሕርይው
ከጌታችን ዘመን ጀምሮ ስለ እርሱ በዓለማችን ውስጥ እጅግ ብዙና የተለያዩ አመለካከቶች ነበሩ፤ አሁንም አሉ። ስላሉም ነው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፊልጶስ ዘቂሣርያ ደቀ መዛሙርቱን “የሰውን ልጅ ሰዎች ማን ይሉታል?” በማለት የጠየቀው። ማቴ 16፣13። ይኽም ጌታችንን አምነን ስንከተለው ስለ ትክክለኛ ማንነቱ በቅዱሳት መጻሕፍት በተገለጠው መሠረት አምነንና ተቀብለን መሆን እንዳለበት ያስረዳናል።
የጌታችንን ትክክለኛ ማንነት ወይም ባሕርይ መረዳት ሁለት ዐበይት ጥቅሞችን ያሰገኝልናል። በመጀመርያ ከመሰናከል ያድነናል። ሁለተኛም ነገረ ድኅነታችን በማን ማለት በፍጡር ወይስ በፈጣሪ እንደ ተፈጸመልን እንድንረዳ ያደርገናል። ስለሆነም ነው ጌታ በክቡር ወንጌሉ “በእኔም የማይሰናከለው ሁሉ ብፁዕ ነው” ብሏል። ሉቃ 7፣ 23። ይኽም የተባለው ጌታችን በባሕርያችን ተገልጦ እየበላ እየጠጣ ከኀጢአት በስተቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ ሆኖ በዮሴፍ ቤት ማደጉን ተመልክቶ እንደ አይሁድ አምላክነቱን ተጠራጥሮ ክፉ ኅሊና የማያገኘው የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅነቱን የማይጠራጠር በባሕርይ አምላክነቱ የማይጠራጠር ብፁዕ ነው ማለት ነው።
ስለዚህ ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን በተቀበለቻቸው የሰማንያ አንዱ አሥራው ቅዱሳት መጻሕፍት አስተምህሮ ላይ ተመርኩዛ “ሰማይና ምድርን የፈጠረ የሚታየውንና የማይታየውን፤ ዓለም ሳይፈጠር ከእርሱ (ከአብ) ጋር በነበረ በአንድ የአብ ልጅ በሚሆን በአንድ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን” ብላ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንድምታምን ትመሰክራለች። ይኽም የምናምንበት ኢየሱስ ክርስቶስ በባሕርይው “ከብርሃን የተገኘ ብርሃን ከእውነተኛ አምላክ የተገኘ አምላክ የተወለደ እንጂ ያልተፈጠረ በባሕርይው ከአብ ጋር የሚተካከል ሁሉ በእርሱ የሆነ በሰማይ ካለው በምድርም ካለው ያለ እርሱ ምንም ምን የሆነ የለም” የሆነ አምላክ መሆኑን አምና ታስተምራለች። ይኽ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ደግሞ ከቅዱሳት መጻሕፍት የተረጋገጠ ነው።
ቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ በወንጌሉ መጀመርያ የሰጠው ምስክርነት ለዚህ ለቤተ ክርስቲያናችን ነገረ ክርስቶስ መሠረት ነው። እንዲህ እንዲል፦ “በመጀመርያ ቃል ነበረ፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። ይኽም በመጀመርያ በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። ሁሉም በእርሱ ሆነ፤ ከሆነውም ሁሉ ያለ እርሱ ምንም የሆነ የለም። ሕይወት በእርሱ ነበረ…….ያም ቃል ሥጋ ሆነ፤ በእኛም አደረ” ዮሐ 1፣ 1-14። ይኽ በመጀመርያ የነበረው እግዚአብሔር ነው የተባለው እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ ምክንያቱም ሐዋርያው ያም ቃል ሥጋ ሆነ ብሎ ምስክርነቱን እንደ ሰጠው ሰው የሆነው እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
ቃል ሥጋ የሆነበትንም ምሥጢር ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ቅዱሳን ሐዋርያውያን አበውን መሠረት አድርጋ እንዲህ ታምናለች፤ ታሰተምራለች። አካላዊው ቃል በግብረ መንፈስ ቅዱስ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ (ወስዶ) መለኮታዊ ባሕርይውን ከሥጋዊ ባሕርይ፣ መለኮታዊ አካሉን ከሥጋዊ አካል ጋር አዋሐደ። በተዋሕዶም አንድ አካል አንድ ባሕርይ ሆነ። መለኮትና ሥጋ ሲዋሐዱም አንዱ ሌላውን ሳያጠፋው ሳይውጠው፣ ወደ አንዱ ሳይቀላቀል ነው። ይኽም ያለ መቀላቀል፣ ያለ መለያየት፣ ያለ መጨመር፣ ያለ መጠፋፋት በተዓቅቦ የተፈጸመ ተዋሕዶ ነው። በዚህም ክርስቶስ አንድ አካል አንድ ባሕርይ መባል ይገባዋል። እንደ ንስጥሮስ ሁለት አካላት ሁለት ባሕርያት ሳንል፣ እንደ አውጣኪም መለኮት ሥጋን ዋጠው (መጠጠው) ክርስቶስ መለኮት ብቻ ነው ሳንል፣ እንደ ልዮና እንደ ምዕራባውያኑ አንድ አካል ሁለት ባሕርይ ሳንል አንድ አካል አንድ ባሕርይ ብለን ክርስቶስን እናምናለን።
በዚህ መሠረት በየዘመኑ የተነሡ መናፍቃን ትምህርት በቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ተቀባይነት የለውም። ክርስቶስ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ በክብር ከተገለጠና በክብር ካረገ በኋላ በዚህ ምድር በሥጋ እንደ ቆየባቸው ዘመናት አሁንም በአባቱ ቀኝ ባለበት ሆኖ ስለ እኛ ይማልዳል የሚሉ፣ ነቢይ ነው፣ ፍጡር ነው፣ የአምላክ ልጅ በማርያም ልጅ አደረበት፣ በምትሃት ሰው የሆነ መስሎ ታየ፣ በቅባተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ…. የሚሉ የክህደትና የስሕተት አስተምህሮዎች ሁሉ በእኛ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዘንድ የረከሱና የተወገዙ አስምህሮዎች ናቸው።
እንግዲህ ከላይ ከተገለጠው መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ ውጪ ወጥተን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ መናፍቃኑ የጌቶች ጌታ የሆነውን አምላክ አማላጅ ባለ ማለታችን “ክርስቶስን አልሰበካችሁም” የሚለን ካለ እርሱን እራሱን አንተ አስቀድመህ ስለ ክርስቶስ ተማር እንለዋለን።
እኛ ግን ከላይ ከብዙ በጥቂቱ ለማየት እንደ ሞከርነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የጌቶች ጌታ፣ የነገሥታት ንጉሥ፣ የአማልክት አምላክ ፈራጅና ገዢ ብለን ለዘላለሙ እናምናለን።
2. ለምን ሰው ሆነ?
ቤተ ክርስቲያናችን ስለ ክርስቶስ ከምትሰብካቸው ትምህርቶች መካከል አንዱ ለምን ሰው ሆነ የሚለው ነው። ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ አስቀድሞ ለሰዎች ልጆች የሚደረገውን ቸርነት፣ ያንንም ቸርነት ማን እንደሚያደርገው “በመልእክተኛም አይደለም፤ በመልአክም አይደለም፤ እርሱ ራሱ ያድናቸዋል እንጂ፤ እርሱ ይወዳቸዋልና፤ ይራራላቸዋልምና እርሱ ተቤዣቸው፤ ተቀበላቸውም፤ በዘመናቸውም ሁሉ ለዘለዓለም አከበራቸው” በማለት ተንብዮ ነበር። ኢሳ 63፣9 (ግእዙንና በ2000 ዓ.ም የታተመውን መጽሐፍ ቅዱስ ተመልከት)። ይኽም ጌታችን “ያመነበት ሁሉ ለዘለዓለም ሕያው ሆኖ እንዲኖር እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንዲያ ልጁን ቤዛ አድርጎ እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲህ ወድዶታልና” ካለው ጋር የተስማማ ነው። ዮሐ. 3፣15።
የባሕርይ አምላክ የሆነው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ በእኛ ባሕርይ ይወለድ ዘንድ፣ በዚህ ዓለምም ይመላለስ ዘንድ፣ በስተ መጨረሻም ሕማማተ መስቀልን ይቀበል ዘንድ የሆነው የሰውን ልጅ በአዳምና በሔዋን ምክንያት ካገኘው ከዘላለም ሞት ለማዳን ነው። በዚህም ኢሳይያስ “እርሱ ይወዳቸዋልና” ያለው ቃል ተፈጸመ። እኛን ለማዳን ሰው የሆነውም እንደ ነቢዩም ሆነ እንደ ሌሎች ቅዱሳት መጻሕፍት ቃል መልእክተኛ ወይም መልአክ ወይም ፍጡር ሳይሆን የእነዚህ ሁሉ ፈጣሪ የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሊቃውንትም የዚህን እውነታ “ፍጡራንን ያለ ፈጣሪያቸው ለማንሣት አልተቻለም፤ ብርሌ ቢሰበር ከሠራተኛው በቀር የሚገጥመው እንደ ሌለ” በማለት ሊያድነን ሰው የሆነው እርሱ የባሕርይ አምላክ እንደ ሆነ ያስተምራሉ። (መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል (1959)፣ መዝገበ ሃይማኖት. ገጽ 36፣ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት)።
ይኽን እግዚአብሔር ሊያድነን ያደረገውን ጉዞ ያሳየውን ፍጹም ትሕትና ቤተ ክርስቲያናችን በስፋት ትሰብካለች። በአዋልድ መጻሕፍቷ ሳይቀር ያድነን ዘንድ ወደዚህ ዓለም መምጣቱን “በእርሱ ፈቃድ በአባቱ ፈቃድ በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ መጥቶ አዳነን” እያለች ትመሠክራለች። ውዳሴ ማርያም ዘሠሉስ። በዚሁ ድርሰት በሰኞ ውዳሴ ማርያምም “ሰው ሆይ ፈጽመህ ደስ ይበልህ፤ እግዚአብሔር ዓለሙን ወዶታልና፤ አንድ ልጁንም የሚያምንበት ሁሉ እስከ ዘለዓለም ፈጽም ይድን ዘንድ አሳልፎ ሰጥቷልና ልዑል ክንዱን ሰደደልን” የክርስቶስ ሰው መሆን ለምን እንደ ሆነና ዓለሙም በዚህ ሊደሰትበት እንደሚገባ ትሰብካለች። ሰውን ለማዳን ሰው መሆኑንም ከነቢዩ ዳዊት ጋር ሆና በአንክሮ “ታስበው ዘንድ ሰው ምንድን ነው? ትጐበኘውም ዘንድ የሰው ልጅ ምንድን ነው? ከመላእክት እጅግ ጥቂት አሳነስኸው፤ በክብርና በምስጋና ዘውድ ከለልኸው” እያለች በማድነቅ ትመሠክራለች። ስለዚህ ክርስቶስ የሆነበትን ዐቢይ ምክንያት በማስረዳት ነገረ ክርስቶስን በስፋት እንሰብካለን።
3. በጎ ፈቃዱ ምን እንደ ሆነ በማስረዳት
የባሕርይ አምላክነቱን የተረዳነው ለምን ሰው እንደ ሆነ ያውቅነው ክርስቶስ በጎ ፈቃዱ ምን እንደ ሆነ በማስረዳት ለዓለም ክርስቶስን እንሰብካለን።
ጌታችን በእምነት ወደ እርሱ ለቀረቡትም ሆነ ከእርሱ ለራቁት በጐ ፈቃዱን በቅዱሳት መጻሕፍት አሳውቋል። ለቀረቡት “መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ” ብሏል። ማቴ. 5፣ 16። በዚህ ቃል መሠረት ቤተ ክርስቲያናችን አምነው ተጠምቀው ሀብተ ውልድና ጥምቀት ክርስትና ሕይወተ ልቡና ላገኙ ምእመናን በጌታ ፊት ብቻ ያይደለ በሰውም ፊት በጐ የሆነውን እንዲያስቡና እንዲሠሩ ትመሠክራለች። በዚህም ክርስቶስን እንዲመስሉ የእርሱን ሕይወት ወይም አኗኗር በስፋት ትሰብካለች።
ርቀው ላሉትም በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ የሚገኘውን ድኅነት ትሰብካለች። ድምጿን ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር ከፍ አድርጋ “መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና” ለዓለም ድኅነት መሠረቱና ቁልፉ በክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት ማመን መሆኑን ትሰብካለች። ሥራ 4፣12። እርሱ እውነተኛ አዳኛችን ስለ ሆነም መድኃኔዓለም ብላ ትጠራዋለች። ዮሐ. 4፣42።
በአጠቃላይ ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ክርስቶስ ማን እንደ ሆነ፣ ለምን ወደዚህ ዓለም እንደ መጣ፣ በማን በኩል እንደ መጣ፣ እንዴት እንደ ተወለደ፣ ከማን እንደ ተወለደ፣ መጠመቁን፣ መጾሙን፣ መራቡን፣ መፈተኑን፣ ዞሮ ማስተማሩን፣ ሐዋርያትን መምረጡን፣ እንዴት ሥልጣን እንደ ሰጣቸው፣ አጋንንትን ከሰው ልቡና ማውጣቱን፣ ሙት ማስነሣቱን፣ የተለያዩ ገቢረ ተአምራት ማድረጉን፣ በአይሁድ እጅ መያዙን፣ ሕማሙን፣ መሰቀሉን፣ በፈቃዱ መሞቱን፣ መነሣቱን፣ ለሐዋርያት መገለጡን፣ ማረጉን፣ ዳግም መምጣቱን፣ የባሕርይ ጌትነቱንና አምላክነቱን፣ እግዚአብሔርነቱን፣ ያስተማረውን ወንጌሉን ወዘተ ያለ መታከት ትሰብካለች።
እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነታዎችን ለትውልዱ በተለያዩ መንገዶች ታቀርባለች። በቅዱሳት በዓላት፣ በቅዱሳት ሥዕላት፣ በንዋያተ ቅድሳት በተለያዩ አዋልድ መጻሕፍት ነገረ ክርስቶስን ትሰብካለች። የገታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዘጠኑ ዐበይት በዓላትና ዘጠኙ ንዑሳት በዓላት ጽንሰቱ፣ ልደቱ፣ ግዝረቱ፣ ጥምቀቱ፣ ቃና ዘገሊላ፣ ደብረ ታቦር፣ ስቅለቱ፣ ትንሣኤው፣ ዕርገቱ ወዘተ ነገረ ክርስቶስን ቤተ ክርስቲያን የምትሰብክባቸው መንገዶች ናቸው። ቅዱሳት ሥዕላቱ ማንበብ ለማይችሉ እንዲሁም ለሕፃናት ቤተ ክርስቲያን የረቀቀውን ምሥጢር ቀለል አድርጋ የምታቀርብባቸው መንገዶች ናቸው። በከበሮው፣ በመቋሚያው፣ በመስቀሉ የክርስቶስን ሕማሙን ግርፋቱን መከራውን ትሰብካለች። በአዋልድ መጻሕፍትም ቢሆን የሚነገረው የክርስቶስ አምላክነት ቅዱሳን ለክርስቶስ ያላቸው ፍቅር ስለ ፍቅሩም ሲሉ የተቀበሉት ጸዋትወ መከራ.፣ ከመከራውም ጌታ እንዴት እንዳዳናቸው ነው።
እንግዲህ ከብዙ በጥቂቱ ለመግለጥ እንደ ተሞከረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንደ አይሁድ ምልክት (ተአምራት) ሳትሻ፣ እንደ ግሪኮችም ፍልስፍናን ሳትቀላቅል ወይም በዘመናችን አውሬው አፍ አድርጎ እንደሚጠቀምባቸው እንደ መናፍቃኑ ነገረ ጽርፈትን በክርስቶስ ላይ ሳትናገር እርሱ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክና የነገሥታት ንጉሥ እንደ ሆነ በሰማይም በምድርም ተስፋችን እርሱ እነደ ሆነ ታምናለች፤ ታስተምራለች። ከዚህ የእውነትና የእምነት መሠረት ወጥታ ግን ክርስቶስን ፍጡር፣ አማላጅ ነቢይ አትለውም። ይልቅ ጌታዬ አምላኬ ትለዋለች። ተውልዱ ሁሉ ወደዚህ እውነትና በዚህ እውነት የሚገኘውን በረከትና ድኅነት እንዲያገኙ አበክራ ትሰብካለች።
ስለዚህ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ክርስቶስን አትሰብክም የሚለው የመናፍቃኑና የሐራ ጥቃዎች ስም ማጥፋት “…ይሳደብ ዘንድ አፉን ከፈተ” ተብሎ የተነገረው የዲያብሎስ ጽርፈት ስለሆነ ምእመናን ባለንበት እንጽና። እናት ቤተ ክርስቲያችን የምታስተምረንን ቃል እንስማ። ለዚሁም የመድኃኔዓለም ቸርነትና የቅዱሳን ሁሉ አማላጅነት አይለየን፤ አሜን።
በቀሲስ ስንታየሁ አባተ

No comments:

Post a Comment