Tuesday, April 5, 2016

ሞት ሆይ መውጊያህ የት አለ? (ሆሴ ፲፫፣፲፬)





ሞት ሆይ መውጊያህ የት አለ? (ሆሴ ፲፫፣፲፬)
===================================
ይህንን ቃል ነቢዩ ሆሴዕ የጌታችንን የመድኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ በትንቢት መነጸር እያየ በእምነት ሐሴት እያደረገ ሞት ሆይ መውጊያህ የት አለ? ሲዖል ሆይ ድል መንሳትህስ ወዴት ነው?በማለት ተናግሮታል፡፡
መጽሐፍ እግዚአብሔር ሞትን እንዳልፈጠረም ነገር ግን የሰው ልጆች ትዕዛዝን በመሻር ሕግን በመተላለፍ በአመጽ ምክንያት በሥራቸው ሞትን ወደ ሕይወታቸው እንዳስገቡ ይነግረናል፡፡ ይህንን ሲያጸና ሐዋርያው ጳውሎስም ኀጢዓት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ ካለ በኋላ በኀጢዓትም ሞት ገባ ይለናል፡(ሮሜ ፳፫) የኀጢዓት ደሞወዝ ሞት ነውና ከዚያን ጊዜ ጀምሮ  ሺህ  መቶ ዓመታት ሞት ገዥ ሆኖ : አሳዳጃችን በአንገታችን ላይ ነው ተብሎ እንደተጻፈ በሰው ልጆች ላይ ሁሉ ንጉሥ ሆኖ ኖረ  የአዳም ልጆችም ከሞት እርግማን የተነሣ አልቃሾች ሆነው ኖሩ ደስታ ከእነሱ ራቀ፣ ሞት ሁሉን እያሸነፈ ሁሉን እየማረከ ከተወደደችው ዓመት ደረሰ (ኢሳ ፷፩ )  በዚች ዓመት ግን ነገር ተገለበጠ የተቆጠረው ባዔ የተነገረው ትንቢት ጊዜ በደረሰ ጊዜ ሞት በእባብ ተሰውሮ ገዥ ሆኖ እንደኖረ ከሦስቱ ቅዱስ አንዱ ቅዱስ እግዚአብሔር ወልድ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከዙፋኑ ዝቅ ብሎ ከድንግል ማርያም ተወልዶ ሁለተኛው አዳም ሆነ እንደ እግዚአብሔርነቱ እየሰራ ሞትን በሞት ያጠፋ ዘንድ ሰው ሆነ ከሙላቱ ሳይጎድል በተለየ አካሉ ሰው ሆነ፤ ሰው ሆነው ተፈጥረው ሰው መሆን ያቃታቸውን፣ የሰው ልጆችን ሰው ያደረግ ዘንድ ሰው ሆነ ችግራችንን ይፈታ ዘንድ መርገማችን ይሽር ዘንድ ስድባችን ያስወግድ ዘንድ ሰው ሆነ በግዕዘ ሕፃናትም በሞገስና በጥበብ ቀስ በቀስ አደገ በ፴ዘመኑም በዮርዳኖስ ተጠመቀ ሳይውል ሳያድር ዳመ ቆሮንጦስ ጾመ ጸለየ ከዲያብሎስም ተፈተነ ከዚህም በኋላ ነበረ አሳሪውን ያስር ዘንድ ኀይለኛውን ያንበረክክ ዘንድ ከምድር ከፍ ከፍ አለ (ዮሐ፲፪፴፪) በመስቀል ላይም ተሰቀለ፣ ሁሉን ወደእርሱ ይስብ ዘንድ ሕዝቡን ይቤዣቸዋል ተብሎ በነቢያት ተነግሮ ነበረና ቃሉ ይፈጸም ዘንድ በመስቀል ላይ ተሰቀለ፣ በኃጢዓታችን ሙታን ነበርንና በክርስቶስ ሕይወትን ይሰጠን ዘንድ እስከ መስቀል ሞት ድረስ አከበረን መቃብራችንን ከፍቶ ከሞት ያወጣን ዘንድ ወደ መቃብር ወረደ፣ ሙታንን ሕያዋን ያደርግ ዘንድ ሞተ፣ ሁሉን ሕያው ያደርግ ዘንድ አንዱ ስለሁሉ ሞተ፣ የትንሣኤያችን በኩር ይሆን ዘንድ አንዱ ስለ ሁሉ ሞተ (፪ቆሮ )::

በሦስተኛው ቀን እንደተናገረ ተነሣ፣ መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል በኅይል ተነሣ፣ በክብር ተነሣ፣ ምስክሮቹን ነቢያቱን ሁሉ ምስክራቸውን እውነት ያደርግ ዘንድ ተነሣ ክርስትናን ይመሰርት ዘንድ ተነሣ የአልቃሾችን እንባ ያብስ ዘንድ ተነሣ፣ የታሰሩትን ሁሉ ይፈታ ዘንድ ተነሳ መቃብርን ሁሉ ባዶ ያደርግ ዘንድ ተነሳ፣ በዓለማችን ላይ ብዙ ኀያላን ተፈራርቀዋል ብዙ ነገስታት ዓለምን ገዝተዋል የብዙ እምነት ድርጅት መሥራቾችም ነገር ግን ሁሉም ሞተዋል፡፡ ገዥውን ያሸነፈ ሞትን ድል ያደረገ፣ መቃብርን ባዶ ያስቀረ ንጉሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ የሞትን መውጊያ የሰበረ የሲኦልን ድል መንሳት ያሸነፈ ኀያሉ የድንግል ማርያም ልጅ ብቻ ነው፡፡
የክርስቶስ የትንሣኤው ይል ልዩ ነበረ ምክንያቱም:-
--------------------------------------------------------------
      ፩. ክርስቶስ ከመቃብሩ የወጣው ሳይከፈት ነው፡፡ ከእመቤታችን ከድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ከተፀነሰ በኋላ ማኅተመ ድንግልናዋን ሳይፈታ ተወለደ፣ አስቀድሞ በነቢዩ ሕዝቅኤል ይህ በር ለዘላለም ተዘግቶ ይኖራል ተብሎ ተነግሮ ነበረና፣ (ሕዝ ፵፬  )  ከትንሣኤውም በኋላ ሐዋርያት ደጃፍ ዘግተው በተሰበሰቡበት እንደተዘጋ ገብቶ በመካከላቸው ተገኘ ሰላም ለእናንተ ይሁንም አላቸው (ዮሐ፲፱) በመሆኑም ከሞትም በተነሣ ጊዜ መቃብሩ ዝግ እንደሆነ ነበር የተነሣው ይህ ትንሣኤውን ኃያልነት ልዩነት የሚመሰክር ነው፡፡ 
 ፪.  በሌላው የክርስቶስን ትንሣኤ ኃያልነት ካረጋገጡት ምስክሮች መካከል እርሱ በኀይሉና በሥልጣኑ መነሣቱ ነው፡፡ ‹‹ከእርሱ አስቀድመው የተነሱት ሁሉ በእግዚአብሔር አስነሺነት ተነስተዋል፡፡ (ዮሐ ) እርሱ ግን እግዚአብሔር ስለሆነ ሞት በሱ ላይ ስልጣን ስለሌለው ሞትን ድል አድርጎ በኀይሉና በሥልጣኑ ተነስቷል፡፡
      ፫.  መቃብሩን የሚጠብቁ ብርቱ ወታደሮችና ከመቃብሩም ደጃፍ ተከድኖ የነበረው ድንጋይ እጅግ ትልቅና በአንድ ሰው ሊነሣ የማይችል ሆኖ ሳለ ክርስቶስ ግን በኀይሉ ይህንን ሁሉ አልፎ ተነስቷል፡፡ ዓለም ያለ የሌለ ኀይሏን ተጠቅማ እውነትን ልትደብቅ ብርሃንን ልታጠፋ ብትሞክርም እርሱ ግን ለእሁድ አጥቢያ ቅዳሜ ሌሊት ማንም ባላወቀው ቅጽበት ውስጥ ከመቃብሩ ወጥቷል መልአኩ መጥቶ ትልቁን ድንጋይ በማንከባለል መቃብሩን እስኪከፍተውና ትንሣኤውን እስከሚያበስር ድረስ ድንጋዩ ከቦታው አልተነቃነቀም ነበር፡፡ (ማቴ ፳፰:)

      ፬. ከትንሣኤው በፊትም ሆነ ከትንሣኤው በኋላ የተከናወኑት የኢየሱስ ክርስቶስ ሥራዎች የትንሣኤውን ኀያልነት ይመሰክራሉ፡፡ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞቱ በኋላ የሲዖልን መዝጊያ ከፍቶ በእስር ላይ ለነበሩት ነፍሳት ነፃነትን የሰበከላቸው በገዛ ራሱ ኀይል በሥልጣኑ ነው፡፡ በዚህ ኃይሉ ጥልቅ ወደ ሆኑት የምድር ክፍሎች ወርዶ ምርኮዎችን እንደራሱ መንጋ በመምራት ለሰዎች ሁሉ ድኅነትን አድሏል፡፡ ከትንሣኤው በኋላም በሙላት በኀይሉና በሥልጣኑ ከፍ ከፍ በማለት ወደ ሰማየ ሰማያት አርጓል፡፡ (ሉቃ ፳፬ ፶፩)
  .  መድኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በትንሣኤው ከሞት ይበልጥ ኀያል መሆኑን አረጋግጧል፡፡ ይህ በመሆኑም ሞቱና ለፍርድ ሲቀርብ የገለጠው ዝምታ በውስጡ ካለው ፍርሃት አለመሆኑን እንረዳለን፡፡ ቢናገር ኖሮ አፋቸውን


   ማስያዝ አድማጮቹን ማሳመን ይችል ነበር ነገር ግን ጌታችን መድኒታችን ሰው የሆነበት ዓላማ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት የተገለጠበት ጥበብ ይህ አልነበረምና፡፡ እንደ በግ ተጎተተ ከእስራት ይፈታን ዘንድ ታሰረ፣ ነፃ ያወጣን ዘንድ ነፃነቱን አሳልፎ ሰጠ፡፡ ስለነም ከመስቀል ላይ እንዲወርድ አይሁድ እየተሳለቁ በጠየቁት ጊዜ ኀይል እያለው እንደሌለው መውረድ ቢችልም እንኳ ኀይለኛውን ሳያስር የሞቱን መውጊያ ሳይሰብር መውረድ አልነበረበትምና ምንም መልስ አልሰጣቸውም፡፡ የክርስቶስ ብቸኛ ዓላማ ስለእኛ ሕማምን ተቀብሎ በመሞት የኀጢዓትን ዋጋ በእኛ ፈንታ መክፈል ለእኛ ስርየትና ድኅነት ማስገኘት ነበርና፡፡ ሞትን ሞቶ የሞትን መውጊያ ሰበረ፣ ሕይወትን ይሰጠን ዘንድ ሞቶ ተነሣ፣ የሲዖልን ድል መንሳት ያሸንፍ ዘንድ በኀይሉና በሥልጣኑ ምርኮን ማረከ የሲዖልን መዝጊያ ሰበረ፡፡ ክርስቶስ በእውነት ተነስቷል መቃብሩም ባዶ ሆኗል፣ የሞት ፍላጻ ተሰብሯል የሲዖል ድል መንሳት ተሸንፏል፡፡






No comments:

Post a Comment