Monday, September 21, 2015

ጼዴንያ ማርያም


 
" ሰላም ለሥዕልኪ እንተ ሠዓላ በእዱ፡፡ ሉቃስ ጠቢብ እምወንጌላውያን አሐዱ፡፡ አመ ተቀብዑ ማርያም እምሐፈ ሥዕልኪ ቅብዐ ናርዱ፡፡ "
ጼዴንያ በምትባል ሀገር ማርታ የምትባል ደግ ሴት ነበረች፡፡ ይህች ደግ ሴት በቤቷ ትልቅ አዳራሽ ሰርታ እንግዶችን እንደ... አባታችን አብርሃም ተቀብላ አብለታ አጠጥታ ማደሪያ ቦታም ሰጥታ ታስተናግድ ነበር፡፡ አባ ቴዎድሮስ የሚባል ኢትዮጵያዊ መነኩሴ ወደ ኢየሩሳሌም ሲሔድ መሽቶበት ከማርታ ቤት በእንግድነት አድረ ጠዋት ሲሔድ ሲነሣ ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚሄድ ሲነግራት የእመቤታችንን ሥዕል ገዝተህ አምጣልኝ ዋጋውን ልስጥህ አለችው፡፡ ገንዘቡን ሥዕሉ ን ሳመጣልሽ ትሰጪኛለሽ ብሏት ሄደ፡፡
ቦታዎችን (መካናትን) ተሳልሞ ሥዕሉን ረስቶ ሳይገዛ ሲመለስ « አደራ ጥብቅ አይደለምን) ያቺ ሴት አደራ ያለችህን ለምን ረሳህ» የሚል ድምጽ ሰማ ተመልሶ ሄዶ ገዝቶ በረሃ በረሃውን መጓዝ ጀመረ፡፡ በመንገድም እየተጓዘ አንበሳ ሊበላው አየሮጠ ወደ እሱ ሲመጣበት አየ መነኩሴው አንበሳውን ከመፍራት የተነሣ ደነገጠ ተንቀጠቀጠ ደንግጦ ቁሞ ሳለ ያች ሥዕል ከአንበሳው ጩኸት ሰባት እጅ በሚበልጥ አስፈሪ ድምጽ ጩሃ ተናገረች፡፡ ያን ጊዜ አንበሳው ደንግጦ ፈጥኖ ሸሸ፡፡

መነኩሴውም መንገዱን ቀጠለ፡፡ በመንገዱም ከሚያስፈራ ዱር ውስጥ ወጥተው ወንበዴዎች ሊቀሙትና ሊገድሉት ከበቡት፡፡ ከሥዕለ ማርያሟም እንደ መብረቅ ያለ ታላቅ ቃል ወጣ ፡፡ ወንበደዎችም እጅግ ፈርተው ሸሽተው ከጫካው ውስጥ ገቡ፡፡
ያም መነኩሴ እኝህን የሚያስደንቁ ተአምራት በሰማና ባየ ጊዜ በልቡ « ለእኔ ረዳት ትሆነኝ ዘንድ ወደ ሀገሬ ይዣት እሄዳለሁ እንጂ ለላከችኝ ሴት አልሰጥም» ብሎ ወደ ሀገሩ ሊሄድ በመርከብ ተሳፈረ፡፡
በባሕር ላይም ሳለ ጽኑ ነፋስ ተነስቶ መርከቡን እየገፋ ማርታ ወዳለችበት ሀገር ወደ ጽዴንያ ዳርቻ አደረሰው፡፡ ማደሪያም ስለሌለው ወደ ደጓ ሴት ወደ ማርታ ቤት ከእንግዶች ጋር አብሮ ገብቶ አደረ፡፡ ሲነጋ ወጥቶ ሊሔድ ከደጃፍ ሲደርስ ደጃፉ ጠፍቶት ከአጥሩ ሲታገል ዋለ፡፡ ማርታም «አባቴ ያመመህ የደከመህ ትመስላለህ ዛሬ ደግሞ እዚህ እደርና ነገ ትሔዳለህ» አለችውና አደረ፡፡ በሁለኛውም ዕለት እንደ መጀመሪያሙ ቀን በሩን አልፎ መሄድ አቃተውና እዚያው ማርታ ቤት አደረ፡፡ በሦስተኛው ቀን መውጣት ፈልጐ ከአጥሩ ጋር ሲታገል አይታ «አባቴ የሆንከው ምንድነው እነሆ ዛሬ ሦስተኛ ቀንህ ነው፡፡» አለችው፡፡ መነኩሴውም « ይህችን ተአምረኛ ሥዕል አልሰጥም ብዬ ነው፡፡ እኔኮ ሥዕል ከኢየሩሳሌም ግዛልኝ ያልሽኝ መነኩሴ ነኝ» ብሎ ሥዕለ ማርያምን አውጥቶ ሰጣት፡፡ እርሷም እጅግ በጣም ተደስታ እግዚአብሔርን አመሰገነች፡፡ በሥዕሏም ፊት ሰግዳ ለእመቤታችን ለድንግል ማርያም ምስጋናን አቀረበች፡

ተቀብላም ሥዕል ቤት አሰርታ በክብር አስቀመጠቻት ይህችም ሥዕል ቅዱስ ሉቃስ የሳላት ናት ሥጋ የለበሰች ትመስላለች፡፡ ከፊቷም ወዝ ይንጠባጠባል፡፡ በዚህችም ሥዕለ ብዙ ተአምራት ተደረገ ሕሙማን ተፈወሱ ዓይነ ስውራን ማየት ቻሉ፡፡
በዚያ ዘመን የነበረው ሊቀ ጳጳስ ተአምሯን ሰምቶ ሥዕሏ ወደ ማርታ ቤት የገባችበት ዕለት መስከረም 10 ቀን እንዲከበር ሥርዓት ሠራ፡፡
ፍቅሯ፣በረከቷ ይደርብን፥ አሜን

No comments:

Post a Comment