Tuesday, March 25, 2014

ዘወትር ይህንን አስታውስ




·         ደካማነትህን አስታውስ ጠንቃቃ እንድትሆንና አንተን ከሚያጠፋህ ከትዕቢትና ከሐሰት ክብር እንድትጠበቅ ያደርግሃል፡፡
·         እግዚአብሔር ለአንተ ያለውን ፍቅር አስታውስ የምስጋና ሕይወት እንድትኖርና እምነት በልብህ እንዲያድግ በእግዚአብሔር ሥራና ፍቅርም እንድትመካ ያደርግሃልና፡፡

·         የሰዎችን ፍቅርና ያለፈ መልካም ትዝታዎቻቸውን አስታውስ ኋላ ታማኝነታቸውን ብትጠራጠርና መጥፎ ነገር ቢያደርሱብህም እንኳ የቀድሞ ፍቅራቸውና መልካምነታቸው አማላጅ ሆኖ ይመጣብህና ቁጣህ በርዶ ይቅር ትላቸዋለህና፡፡
·         ሞትን አስታውስ የዚህ ዓለም ፈታኝ ውበቶችና ብልጭልጮች ይጠፋሉ፡፡ እናም አንተም እንደዚህ ትላለህ ‹‹ከፀሃይ በታች የተሰራውን ሁሉ አየሁ እነሆም ሁሉ ከንቱ ነው ነፋስም እንደመከተል ነው›› መክ 1፡14
·         በእግዚአብሔር ፊት እንዳለህና እሱም ሁሌ እንደሚያይህ አስታውስ እናም ኃጢዓትን አትሰራም፡፡ ምክንያቱም አንተም ታየዋለህና፡፡
·         የእግዚአብሔር ቃል ኪዳኖች አስታውስ እናም በችግርህ ጊዜ ሁሉ እረፍት ይሰማሃል፡፡
·         ስለአንተ የፈሰሰውን የክርስቶስን ደም አስታውስ በእርግጥም የሕይወትህ ዋጋ ምን ያህል ውድ እንደሆነ ታውቃለህ፡፡ እናም የባከነ ሕይወት እየኖርህ ሕይወትህን እንዳታባክናት ትሆናለህ፡፡ ‹‹በዋጋ ተገዝታችኋልና›› 1ቆሮ 6፡20
·         በዚህች ምድር መጻተኛ (እንግዳ) እንደሆንክና ወደ ሰማያዊ ቤትህ መሔድህ እንደማይቀር አስታውስ እናም ሃሳብህና እቅድህ ሁሉ በዚች ምድርና በምቾቶቿ ላይ የተወሰነ እንዳይሆን ያደርጋልና፡፡
·         ወደ ሕይወት የሚወስደው ደጅ የጠበበ መንገዱም የቀጠነ መሆኑን አስታውስ ሰፊ ደጅና ትልቅ መንገድ ፊትህ ባጋጠመህ ጊዜ ሸሽተህ እንድታመልጥና ከዚያ እንድትርቅ ያደርግሃልና፡፡ በሰፊው ደጅ የሚሄዱ ግን…ሁሉም ይጠፋሉ፡፡
·         ዘላለማዊነትህን አስታውስ ለዛ እንድትተጋ ትሆናለህና፡፡
·         የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆንክና እርሱን መምሰል እንዳለብህ አስታውስ ለእግዚአብሔር ልጅነት የሚመች አካሄድ እንዲኖርህ ትሆናለህና፡፡ የእግዚአብሔር ልጆች ደግሞ በግልጽ የሚታዩ ናቸው፡፡
·         የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደሆንክ አስታውስ ባንተ ያለውን የእግዚአብሔርን መንፈስ ቅዱስ አታሳዝነውምና፡፡ ሁል ጊዜም ቅዱስ መቅደስ ሁን፡፡

(አቡነ ሺኖዳ 3ኛ በመንበረ ማርቆስ ግብጽ ኦርቶዶክስ ቤ/ክ 117ኛ ፓትርያርክ)
‹‹ማደግህ በነገር ሁሉ እንዲገለጥ ይህን አስብ ይህንም አዘውትር›› 1ኛ ጢሞ 4፡15

No comments:

Post a Comment