Saturday, March 15, 2014

‹‹ለክፉው ዘመን የማምለጫ መርከብ››




ንዋየ ኅሩይ ቅዱስ ጳውሎስ ዘመኑን ዋጁ ይላል በተለይም ክርስቲያኖች የዓለም ብርሃን የዓለም ጨው ተብለናልና በውጭ ባሉት ዘንድ በጥበብ እየተመላለስን ዘመኑን ልንዋጅ ይገባል፡፡ ያለንበት ዘመን ደግሞ እውነት በሐሰት የተዋጠበት ግፈኞች ደም አፍሳሾች የበዙበት ፍርድ የተጓደለበት ግብረ ሰዶማዊነት በዓለም ላይ ያለ ዕፍረት የሚሠራበት፣ ትዕግስት ትህትና፣ ይቅርታ፣ ከሰዎች ጠፍቶ ትዕቢት፣ ጭካኔ ፣ ቂም በቀል የነገሠበት ክፉ ዘመን ነው ‹‹ለዚህም ነው ነቢየ እግዚአብሔር ሚክያስ በዚህ ወገን ላይ በክፉ አስባለሁ ከዚያም አንገታችሁን አታነሱም ዘመኑም ክፉ ነውና ቀጥ ብላችሁ አትሄዱም›› (ሚክ 2፡3) በማለት ስለዚህ ጉቦኛ፣ ግፈኛ፣ አመንዝራ አላስተዋይ ትውልድ ይናገራል፣



በመሆኑም ይህን ክፉ ዘመን እንዴት እንዋጅ ክቡር ዳዊት ‹‹በጎውን ዘመን ለማየት የሚወድ እርሱ አንደበቱን ከክፉ ይከልክል (መዝ 33፡12) ከንፈሮችህም ሽንገላ እንዳይናገሩ፣ ከክፉ ሽሽ መልካምም አድርግ›› ነው ያለን ክፉ ዘመን ጥንትም ነበር የኖኅ ዘመን የጥፋት ውኃ የሰዶምና የገሞራ እልቂት ይህን ያሣየናል በአባቶቻችንም ዘመን ክፉ ነበር ነበር ባለንትም ዘመን ክፉ ነገር አለ ሰው እስካልተመለሰ ድረስ ክፋት በቅቶኛል ብሎ በራሱ አይቆምም ሥራ እስካለ ደሞዝ ከፋይ እንዳለ ሁሉ ክፉ ነገርም የሥራችን ደሞዝ ሆኖ ይኖራል፡፡
ካለፉት ዘመናት ይልቅ ክፉ ነገር የበዛበት ዘመን የእኛ ዘመን ነው ክፉ ነገርን ከመልመዳችን የተነሣ አሁን ያለው ክፉ ነገር ሳይሆን የሚመጣው ነው የሚያስፈራን በዜና ማሰራጫዎች እለት እለት የምንሰማው ነገስታትና ሕዝቦች ምጥ ላይ መሆናቸውን ነው የእግዚአብሔር ቃል ትንቢቶችን ስናጠና ክፋት እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አይመጣም፡፡
ታዲያ በክፉ ዘመን የማምለጫው መርከብ ምንድን ነው? ስንል በተሰበረ ልብ የሚቀርብ ፀሎት ነው እነ ‹‹ኖህ ፣ እነ ሎጥ እንደ ዳኑ በክፉ ቀን ውስጥ እንዳለፉ እናነባለን›› ‹‹አድነኝ›› ብለን የምንጸልየው የሚያድነውን አምላክ ነው በአገራችን ከብትና አዝመራ የሚያጠፋ መቅሰፍት ሲመጣ ‹‹እግዚኦ›› ይባል ነበር መቅሰፍቱም ሲመለስ ደርቁም ሲርቅ እናውቃለን፡፡ ዛሬ ግን ይህ ሁሉ ወጣት በቅጠል ሲቀር ‹‹እግዚኦ›› የሚል መጥፋቱ ምን ያህል እምነት እንደ ራቀን ያሳያል፡፡ አዎ የእግዚአብሔር እጅ የምናውቀው ነው፡፡
ሞት ሰይፍ ይዞ በጎዳና በወጣበት፣ ሰው ለሰው አውሬ በሆነበት ከምንም በላይ ራሳችን ለራሳችን ጠላት በሆንበት ዘመን በንፁሕ ልብ የምትቀርብ ጸሎት ይህን ክፉ ነፍስ ትለውጣለች ጸሎት ክፉ ቀን ሳይመጣ ነው ክፉ ቀን ከመጣ በኋላ ግን እየተገረፉ እንደመጮህ ነው፡፡ አዎ በደግ ቀን ያልጸለዩት ጸሎት በክፉ ቀን አይረዳም በጦርነት በረሃብ እርስ በእርስ እልቂት ዘመን ሕዝቦችን ያዳኑ ታሪካዊ መርከቦች አሉ፡፡ ከዚያ ይልቅ በጸሎት መርከብ ባሕሩን የተሻገሩ ማዕበሉን ያለፉ ብዙ ምስክሮችን ምድር ተሸክማለች፡፡
እግዚአብሔር በክፉ ቀን መንገድ ይሰጣል ነገስታት በጦርነት ቀጠና ውስጥ ለቱሪስቶች የደኅንነት ዋስትና ለመስጠት አይደፍሩም እግዚአብሔር ግን በዐውሎና በወጀብ ውስጥ መንገድ አለው፡፡ (ኢሳ 43፡2 ፤ ናሆ 1፡3)





በአንድ ኩሬ ውስጥ የሚኖሩ እንቁራሪቶች ይዘላሉ ይጨፍራሉ ከመካከላቸው ግን አንዱ ጥግ ይዛ ‹‹አውጣኝ አውጣኝ›› እያለች ትጸልያለች ባልንጀሮቿም ወደ እርሷ መጥተው ከእኛ ጋር የማትደሰችው ጥግ ይዘሽ የምትጮሂው ለምንድን ነው?  አሏት እርሷም እዚያ ማዶ ቤት ሲቃጠል አያለሁ ስለዚህ አውጣኝ እላለሁ አለች እነርሱም ‹‹ቤት የሚቃጠለው እዚያ ማዶ ነው እኛ ያለነው ውኃ ውስጥ ነው ምን አስጨንቆሽ ነው?›› አሏት እርሷም እሳቱን ለማጥፋት በአቅራቢያቸው ያለውን ውኃ ተጠቅመው አልጠፋ ካላቸው ውኃ ለመቅዳት የሚመጡት ከዚህ ነውና አውጣኝ እላለሁ›› አለቻቸው እነርሱ ግን ዘብተውባት ዝላያቸውን ቀጠሉ እሳቱም እየጸና መጣ አቅራቢያው ባለው ውሃ ቅጠልና አፈር ቢሞከር አልጠፋ ስላለ የአካባቢው ሰው ባልዲውን እየያዘ ወደ ኩሬው መጉረፍ ጀመረ እነዚያ ይዘሉ የነበሩትን እንቁራሪቶች ዝቀው እሳት ውስጥ ሲጨምሯቸው ያች አውጣኝ የምትለው እንቁራሪት ግን ዳነች ‹‹አውጣኝ ያለም ወጣ ያላለም ተቀጣ››
በመሆኑም ‹‹ዳር ሲነካ መሐል ይሆናል›› እንደሚባለው ሩቅ የሚመስለው የሰዎች ጥፋት ካልተጠነቀቅነውና ካልጸለይን ወደ እኛም ይመጣል የጎረቤታችን ውድቀትና ሞት ለእኛ ማስጠንቀቂያ እንጂ የጨዋታ ርዕሳችን አይደለም፡፡ በባላገር ዳስ ጥለው ይዘፍናሉ ዳሱም ቶሎ ይፈርሳል በዚህ ምክንያት ‹‹የዘፈን ቤት ሳይፈርስ አይቀርም›› ይባላል እንዲሁም ጭፈራና ብዙ  ደስታ ልቅሶና ዋይታ ሳያመጣ በፍጹም አይቀርም ለሰዎች ማዘን ሲያለቅሱ ሳይሆን ዘፈን ዘፈን ሲላቸው ነው የሚቀጥለው ልቅሶ ነውና በእውነት በክፉ ዘመን የማምለጫው መርከብ መረጃ ሳይሆን ጸሎት ነው፡፡
አዎ ለመጸለይ ያለን ምክንያት ከምክንያቶች ሁሉ የሚልቅ ነው፡-
·         ጸሎት የማያቋርጥ አገልግሎት በመሆኑ
·         ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገሪያ ስለሆነ
·         ማንኛውም በጎ ነገር ያለ ጸሎት ኅይል ስለሌለው
·         በክፉ ዘመን የማምለጫ መርከብ ጸሎት በመሆኑ ነው
ጌታችንም ለዚህ ነበረ ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ ያለው (ማቴ 27፡40)
"ለመጀመር የሚያነቃቃ ለመፈጸም የሚያበቃ መድኀኔዓለም ኅይልና ብርታትን ሰጥቶ ለጸሎት ያቁመን"
ዋቢ:-
መጽሐፍ ቅዱስ(81)
በሃይማኖት ብትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ

No comments:

Post a Comment