Tuesday, March 25, 2014

ያዘዘን የትኛውን ነው? ከባድ ነው?



ያዘዘን የትኛውን ነው? ከባድ ነው?
እውን እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ለአዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች የሰጣቸው ትዕዛዛት ከባዶች ናቸው? በመጀመሪያ አንድ ነገር ማየት ጌታ ሲመጣ የማይጠይቀን ምድን ነው? ጌታ ሲመጣ በምድር ላይ ምን ያህል ቤት እንደሰራን አይጠይቀንም ግን በትንሽም ጎጇችን ብትሆን እንግዳ እንደተቀበልን ይጠይቀናል፡፡ በሞተ ሰው ቀብር ላይ እንደተገኘን ሳይሆን በሕመሙ ጊዜ እንደ ጎበኘነው ይመረምራል፡፡ በጓዳችን ስለሚሰራው የምግብ አይነት አይጠይቀንም የተራቡትን እንዳበላን ግን ይጠይቀናል፡፡ በየክሎዜታችን ስንት አይነት የአበሻ ልብስ እንዳለን አይመረምርም እርቃናቸውን የወደቁትን እንዳለበስን ግን ማወቅ ይፈልጋል፡፡ ከላይ ብቻ ነጭ ነጠላ ለብሰን ቤ/ክ መገኘታችን አይጠይቅም ግብዝነት እንዳለብን ግን ልብን ይመረምራል እንጂ…፡፡
በሌላ አንጻር ግን የታመመውን ጠይቁ አለን እንጂ እንድንፈውሰው ያለ ጸጋችን አልጠየቀንም፡፡ እንግዳን በቤታችን እንድንቀበለው አዘዘን እንጂ ያለአቅማችን ቤት ሰርታችሁ ካልሰጣችሁት አትጸድቁም እስከማለት ደርሶ አላስጨነቀንም፡፡ ለተቸገረውም ካለን ላይ ከፍለን እንድንሰጥ ነገረን እንጂ እኛ እንድንቸገር አይደለም፡፡ ደግሞ በሰማናት ቃል እንድንኖር እንጂ የመፀሐፍትን ሁሉ ቃል ካላወቃችሁ መንግስተ ሰማያት የእናንተ አይደለችም አላለንም፡፡ ሩህሩህ ሸክሙም ልዝብ ነውና በምንም በምንም እርሱ ትዕዛዙን አላከበደብንም፡፡ ኃጢዓት ብናደርግ ብንወድቅም ፈጥነን እንድንነሳ በልባችን እንድንመለስ ዳግም በምህረቱ እድል ሰጠን እንጂ ሁለተኛን ዕድል ነፍጎ አልተወንም፡፡ ትዕዛዛትን ብቻ ግን የሰጠን አይደለም የምንጠብቅበትን ጸጋ መንፈስ ቅዱስ እንዲያው ያለ ዋጋ ሰጥቶናል እምነት ብቻ ይጠይቃል በእርግጥ ሕጉን አክብደን ያየነው እኛው ነን፡፡ ተራመዱ ሲባል ሩጡ ታገሱ ሲባል አይሰጥም የተባልን እየመሰለን ይሆናል፡፡ መጽሐፍ ግን ምን አለ? ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እግዚአብሔር እንደሆነ ለሚያምኑ ሁሉ ‹‹ትዕዛዛቱም ከባዶች አይደሉም›› 1ዮሐ5::3
የክርስቶስን አካል ልታከብሩት ትወዳላችሁ?
መልሳችሁ አዎ ከሆነ ራቁቱን ሆኖ እያያችሁት አትለፉት በየመንገዱ ራቁቱን ሆኖ በብርድ እየተሰቃየ አለና፣ ራቁቱን ሆኖ በብርድ እየተሰቃየ አልፋችሁት መጥታችሁ እዚህ ከቤተ መቅደስ በብርና በወርቅ ላስጊጥህ አትበሉት፡፡ ‹‹ይህ ሥጋዬ ነው›› ብሎ የተናገረው ክርስቶስ ራሱ ‹‹ተርቤ አይታችሁኝ አላበላችሁኝም›› ያለው እንዲሁም ‹‹ከእነዚህ ከታናናሾች ወንድሞቹ ለአንዱ ያደረጋችሁት›› ያለውም ያው እርሱ ራሱ ነውና፡፡ ወንድምህ በረሃብ እየተሰቃየና እየሞተ ቅዱስ ደሙ የሚቀዳበት ጽዋ በወርቅ ቢለበጥና ቢንቆጠቆጥ ጥቅሙ ምን ላይ ነው? አስቀድመህ የወንድምህን ረሃብ በማጥገብና ጥሙን በማርካት ጀምር፡፡ ከዚያ በኋላ በተረፈህ ገንዘብ ቤተ መቅደሱንና ንዋያተ ቅዱሳትን እንዲህ ማስጌጥ ትችላለህ፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
‹‹ንጹሕ የሆነ ነውርም የሌለበት አምልኮ በእግዚአብሔር አብ ዘንድ ይህ ነው፣ ወላጆች የሌላቸውን ልጆች ባልቴቶችንም በመከራቸው መጠየቅ በዓለምም ከሚገኝ እድፍ ሰውነቱን መጠበቅ ነው››
 

No comments:

Post a Comment