Tuesday, February 18, 2014

‹‹ቃል ኪዳኔን ልጠብቅልሽ በራሴ ማልሁልሽ››


‹‹መሃልኩ ለኪ በርዕስየ በከመ ኢይሔሱ ኪዳንየ››
‹‹ቃል ኪዳኔን ልጠብቅልሽ በራሴ ማልሁልሽ››
(ስንክሳር ዘየካቲት ፣ ተአ/ማር ገጽ 76)
  
እግዚአብሔር አምላክ ሰውን ከፈጠረ በኋላ ቦታ ለይቶ ህግ ሠርቶ አኖረው ህጉን ከተላለፈ ቅጣት እንደሚያገኘው አእምሮውን ዳኛ አድርጎ ሠየመለት ይሁን እንጂ ሰው የባሕርይው ደካማነት ይህን ፈተና እንዲያልፍ አላስቻለውም ካለመቻሉም የተነሳ ምክረ ከይሲን (የሰይጣን ምክር) ሰምቶ ዕፀ በለስን በልቶ ከፈጣሪው ተጣልቶ ከገነት ወጥቶ መንጸፈ ደይን (የጉስቁልና ቦታ) ወደቀ በሞተ ሥጋ ሞተ ነፍስ (በሥጋ ሞት ላይ የነፍስ ሞት) በርደተ መቃብር ርደተ ሲኦል (ወደ መቃብር በመውረዱ ላይ ሲኦል መውረድን) ፈረደበት፡፡

እግዚአብሔር በጥፋቱ ቢፈረደበትም ንስሐ ሲገባ ደግሞ ይቅር እንደሚለው አውቆ ንስሐ ገብቶ ፈጣሪውን ይቅርታ ጠየቀ (ኩፋ 5፡1) እግዚአብሔርም ዘመን ለይቶ ቀጠሮ ሰጥቶ ልቡን በተስፋ ሞልቶ እንዲቆይ አደረገው ቀደም ሲልም ‹‹ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሉአት›› ብሎ ነበርና በዚሁ መሠረት የሰው ዘር በምድር ላይ በብዛት እየጨመረ ሲሄድ ከሥጋ ወላጆቹ (አዳምና ሔዋን) ያገኘውን ኃጢዓት በግብር እየወለደ ያሳድግ ጀመር በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር ቅዱስ መንፈሱን ከሰው ላይ አነሳ ዕድሜውንም ቀነሰ ይህ ብቻ አልበቃም ‹‹ወነሰሐ እዘግዚአብሔር እስመ ገብሮ ለእጎለ እመ ሕያው ላዕለ ምድር›› ሰውን በምድር ላይ ስለፈጠረው እግዚአብሔር ተፀፀተ ይላል ንስሐ መግባቱ እንዳልሆነ ሁላችንም እንረዳለን ሰው በፈጸመው ወንጀል የሚከተለውን ቅጣት እየታየው ለሰው ለራሱ ተፀፀተበት እንጂ (ዘፍ 6፡3-6) ለወዳጁ ለኖህ ግን ከነቤተሰቡ እንሰሳቱንና አራዊቱን ጭምር በመርከቡ ውስጥ እንደሚጠብቀው ቃል ኪዳን ፈጸመለት (ዘፍ 6፡18) ለሚፈሩት ለሚያከብሩት ህጉን ለሚጠብቁት ትዕዛዙን ለሚያደርጉት ለወዳጆቹ (ጻድቃን) የመጀመሪያ የድኅነት ውል አደረገ፡፡
እንቢተኞች ግን በንፍር ውሃ ተቀጡ ከገጸ ምድር ተወገዱ የዋሆችና ቅኖች አዲሲቱን ምድር በሃላፊነት ተረከቡ ለአዲሱ ትውልድ መምህራን ሆነው ተሾሙ እግዚአብሔርም ቃል ኪዳኑን እንደገና አጸና እንዲህ ሲል ‹‹ለዘላለም የማደርገው የቃል ኪዳን ምልክት ይህ ነው ቀስቴን በደመና አድርጌአለሁ የቃል ኪዳኑም ምልክት በእኔና በምድር መካከል ይሆናል›› (ዘፍ 9፡12-17) በቅዱስ መጽሐፍ ተጽፎ እንደምናነበው እግዚአብሔር ለሌሎች ወዳጆቹም ቃል ኪዳን ገብቷል፡፡ ከወዳጆቹ አንዱ ለሆነው ለአብርሃም ‹‹እግዚአብሔር በራሴ ማልሁ ይላል ይህን ነገር አድርገሃልና አንድ ልጅህንም አልከለከልከኝምና በእውነት በረከትን እባርክሃለሁ ዘርህንም እንደሰማይ ከዋክብትና በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ አበዛዋለሁ በማለት ቃል ገብቶለታል›› (ዘፍ 22፡16-18)
 

ቅዱስ ዳዊት በገናውን እየደረደረ መሰንቆውን እየመታ ለእግዚአብሔር ክብር በሚያቀርብበት ዘመን እግዚአብሔር ከወዳጆቹ ከቅዱሳን ጋር የሚያደርገውን ቃል ኪዳን በተመለከተ ‹‹ኪዳንየ ተካየድኩ ምስለ ኅሩያንየ›› ቃል ኪዳኔን ከመረጥኳቸው ጋር አደረግሁ›› በማለት የጻፈ ሲሆን የገባውንም ቃል ኪዳን በመሐላ ሲያጸና ‹‹ኪዳኔንም አላፈርስም ከከንፈሬ የሚወጣውንም አልለውጥም›› (መዝ 88(89)፡3 ና ቁጥር 34) በማለት በዝማሬው አረጋግጦልናል፡፡
የእግዚአብሔር ወዳጆች እጅግ ብዙዎች ናቸው ከወዳጆቹ ሁሉ የምትበልጠው ግን እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም ነች እናት ደግሞ ወዳጅ ብቻ ሳትሆን እናት ናትና እንደ እናትነትዋም የተለየ ቃል ኪዳን ገብቶላታል ታሪኩን አበው በተአምረ ማርያምና በስንክሳር ላይ እንዲህ ይነግሩናል ‹‹መድኅኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም የመጣበትን የመስቀል ጉዞ በመስቀል ከደመደመ በኋላ በዚህ መስቀል አጠገብ እናቱ እመቤታችንን ለሚወደው ተማሪው ለዮሐንስ አደራ በማለት እንዲጠብቃት እንዲያገለግላት ነግሮት ወደ ቀደመ ክብሩና አኗኗሩ ተመለሰ›› (ዮሐ 19፡26)
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ግን ልጇ ወዳጇ ከሷ ተለይቶ በባሕርይ ክብሩ ከተመለሰ በኋላ ዘወትር በጌታ የመቃብር ሥፍራ (ጎልጎታ) ላይ እየተገኘች ትጸልይ ነበር አይሁድም ባዩአት ጊዜ ቅንዓትንና ቁጣን ተመልተው ከዚህም በኋላ በዚያ ትጸልይ ዘንድ ሁለተኛ እንዳትደርስ ውሳኔ አሳልፈው በልጇ መቃብር ላይ ጠባቆችን ሾሙ ለህጋቸው የማትገዛ ከሆነም በድንጋይ ወግረው እንዲገድሏት ለጠባቂዎች ጥብቅ ትዕዛዝ ሰጡ እርሷ ግን ሳታቋርጥ ዕለት ዕለት ወደ መቃብሩ እየሄደች ትጸልይ ነበር ጠባቂዎችም አያዩአትም ነበር ‹‹የልጇ የጌትነት መጋረጃ ይሰውራት ነበርና›› በዚያም መላዕክት እየመጡ ይላላኳት፣ ጌታም ዘወትር ይጎበኛት ነበርና ከዕለታት አንድ ቀን በወርሃ የካቲት በ16ኛው ቀን ቆማ ስትጸልይ መላዕክት አፋፍሰው ወደ ገነት ወሰዷት በዚያም ከአዳም ጀምሮ የነበሩትን ነፍሳተ-ጻድቃን እያዞሩ አሳዮአት፡፡
በገነት በአካለ ነፍስ ያሉ አበውም ከአጽማችን አንቺን አጽም ከሥጋችን አንቺን ሥጋ አድርጎ የፈጠረልን ወልደ አምላክ (የአምላክ ልጅ) ካንቺ ሰው በመሆኑ ከጥፋት የሕይወት ወደብ የሆንሽን ምክንያተ ድህነታችን ሆይ ሰላም ላንቺ ይሁን እያሉ ሰገዱላት
በድጋሚ መላዕክት መካነ ኩነኔ (የፍርድ ቦታ) ያሳዩአት ዘንድ ከዚያ ወስደው ለሰይጣንና ለሠራዊቱ በሱ መንገድ በሱ ሕግ ጸንተው ለሚኖሩ ሁሉ ወደ ተዘጋጀ የጨለማ ዳርቻ ወዳለበት አደረሷት የኃጥአንንም መከራና ስቃይ በጥልቅ ኃዘን ተመለከተች፡፡ እመቤታችን የኃጥአንን የሲኦል ውስጥ ሕይወት ካየች በኋላ ግን ለሰው ልጆች ይልቁንም ለኃጥአን አጥብቃ መለመንና ማማለድ ጀመረች ርህርህተ ልቦና ናትና በለቅሶና በሐዘን ወደ ልጇ ወደ ወዳጇ አሳሰበች እንደልማድዋ የካቲት 16 ቀን በጎልጎታ ቁማ ስትጸልይ ልጇ ወዳጇ ኢየሱስ ክርስቶስ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ሆኖ በዕልፍ አዕላፍ መላዕክት ታጅቦ ነቢያት በዝማሬ ሐዋርያት በይባቤ ሆነው ወደ ጎልጎታ መጥቶ እናቴ ሆይ ምን አደርግልሽ ዘንድ ትወጃለሽ ሲል ጠየቃት እሷም አሥራ አንድ ጥያቄዎችን በትህትና በአክብሮት ለጌታዋና ለአምላኳ አቀረበች፡፡
መታሰቢያዬን የሚያደርገውን፣ በስሜ ቤተ ክርስቲያን የሚያንጸውን ፣ የተራቆተ የሚያለብሰውን፣ በሽተኛ የሚጎበኘውን፣ የተራበ የሚያበላውን፣ የተጠማ የሚያጠጣውን፣ ያዘነን የሚያረጋጋውን የተበሳጨ የሚያስደስተውን፣ መመስገኛየን የጻፈና ያጻፈ ፣ ወንድ ወይም ሴት ልጁን በስሜ የሰየመውን፣ በምመሰገንበት ቀን ዝማሬ ያቀረበውን ዓይን ያላየውን ጆሮ ያልሰማውን የሰው ኅሊና ተመራምሮ ያልደረሰበትን መልካም ዋጋ ትሰጥልኝ ዘንድ እለምንሃለሁ የሚል ነበር፡፡
ጌታም ‹‹መሃልኩ ለኪ በርዕስየ በከመ ኢይሔሱ ኪዳንየ›› ያልሽውን ሁሉ ላደርግልሽ ቃል ኪዳኔንም ልጠብቅልሽ በራሴ ማልሁልሽ በማለት የምህረት ቃል ኪዳን ገብቶላት በይባቤ መላዕክት ተመለሰ፡፡
ከዚያን ጊዜ አንስቶ እመቤታችን እስካሁን ድረስ በተሰጣት ቃል ኪዳን ለኃጢዓተኞች ከእግዚአብሔር ዘንድ ምህረት ይቅርታን ታሰጣለች ለበጎ ሥራም ታነሳሳለች ይህንንም ወዳጆቿ ሁሉ ያምናሉ፡፡ ከዚህም የተነሳ ኢትዮጵያውያን እናቶችና አባቶች ለእመቤታችን ያላቸው አክብሮትና ፍቅር ከፍ ያለ ነው ይልቁንም ቃል ኪዳን በተቀበለችበት የካቲት 16 ቀን መላው ምዕመናን በተለይ የሀገር ቤቱ ሕዝብ ከላይ እመቤታችን የጠየቀቻቸውን መልካም ሥራዎች በመሥራት በዓሉን በታላቅ መንፈሳዊ ሥነሥርዓት ያከብራሉ የኔ ቢጠውም ከተዘጋጀው ጠበል ጸዲቅ (ድግስ) በልቶ ጠጥቶ እመብርሃን ትስጥልኝ እያለ እየመረቀ በደስታ ይውላል፡፡ ሕዝቡም ይህን በማድረጉ ከእመቤታችን ድንግል ማርያም ታላቅ በረከት እንደሚያገኝ ያምናል ዕለቱ ለራሱ የድኅነት ዋስትና ያገኘበት መሆኑንም ይገነዘባል፡፡
በዚህ ሁሉ እግዚአብሔር ከሰው ልጆች ጋር በሚያደርገው ቃል ኪዳን የምንረዳው እግዚአብሔር አምላካችን ሰውን በሰው ይቅር ሲለው ነው፡፡
ለኖህም ሆነ ለአብርሃም ቃል የገባላቸው ለራሳቸው ሳይሆን ለቀረው ዘራቸው መሆኑን ልናስተውል ይገባል እግዚአብሔር ራሱ ፊትለፊት ማድረግ የሚችለውን በተዘዋዋሪ በቅዱሳን ላይ አድሮ ሲያደርግ እናየዋለን፡፡ ይህም እንዲሁ አይደለም ምክንያት አለው ምክንያቱም አንደኛ የቅዱሳንን ክብር ለመግለጥ ሲሆን ሌላው ደግሞ የሰዎችን የመዳን መስመር በብዛትና በስፋት ለመዘርጋት ነው፡፡ ቅድስት ድንግል ማርያም በእግዚአብሔር ቀኝ ሆና የምትማልድልን መሆኗንና እኛም ልንለምናት የሚገባ መሆኑን ልበ አምላክ የተባለው ነብይ ቅዱስ ዳዊት በዝማሬው መዝ 44 (45)፡ 9-12  ላይ ግልጽ አድርጎ መግዝቦታል፡፡
አንዳንዶች ከምስጢር የተራቆቱ በንባብ የሞቱ ይህ አባባል የእግዚአብሔርን ክብር መጋፋት ይመስላቸዋል ነገር ግን እንዲያውም የበለጠ ክብር መስጠት ነው እንዴት ቢሉ እግዚአብሔር ኃያልና ገናና ክቡር ቅዱስ አምላክ ሲሆን (ኢሳ 2፡21) ሰው ደግሞ ደካማና ዝቅተኛ በሰይጣን የፈተና ወጥመድ በቀላሉ የሚጠመድ ነው፡፡ (ኢሳ 2፡22)
በመሆኑም በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ያለው ርቀት ይህን ያህል ሲሆን፣ በእግዚአብሔርና በጻድቃን መካከል ያለውን ቅርበት ለመለካት ደግሞ ወደ ኋላ የተጠቀሱትን መረጃዎች መመልከቱ በቂ ነው ፡፡ ከዚህም የተነሣ ኃጢዓተኛው ዓለም ከኃጢዓት ብዛት የተነሣ ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ባለመቻሉ በእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስ ያገኙትን ጻድቃን ይማልዳል እነሱም ከፈጣሪ ዘንድ ቀርበው ይለምኑታል፡፡ ለእግዚአብሔር ክብር መጨመር እንጂ ክብሩን መጋፋት አይደለም ያልነው ስለዚህ ነው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዮሐ 19፡26 ላይ እንደተጻፈው በፍቅረ እግዚእ በቅዱስ ዮሐንስ አማካኝነት ለዓለም ሁሉ የቃል ኪዳን እናት ትሆን ዘንድ በአደራነት የተሰጠች የመስቀል ስር ስጦታ መሸጋገሪያ ድልድይ መወጣጫ መሰላል ምዕራገ ፀሎት አቁራሪተ መዓት ነች፡፡
 

በመሆኑም ሁሉም እናትነቷን አምኖ በመቀበል በእናትነቷ መኩራት ይገባል እንጂ ተጠራጣሪዎች ሰዎች በእምነት ስም በሚያቀርቡለት አሉባልታና ወሬ ከፀጋ እናቱ መለየት የለበትም፡፡ ማንኛውም ሰው ከድንግል ማርያም በመለየቱ ክብር የሚያጣው ራሱ እንጂ ለርሷ ማንም ምንም ዓይነት ክብርን መጨመር ወይም መቀነስ የማይችል መሆኑን ማወቅ ያሻል ይልቁንም የተቀበለችውም የምህረት ቃል ኪዳን ለኛ ለኅጥአን መሆኑን በግልጽ መረዳት ያስፈልጋል፡፡
እመቤታችን ጌታ መድኃኔዓለምን ለመፀነስ በቅዱስ ገብርኤል ብሥራት ሰላምታ በቀረበላት ጊዜ ከተናገረችው ወይም ከጸለየችው ጸሎት መካከል ‹‹ትውልድ ሁሉ ወይም ቀጣዩ ትውልድ ብፅዕት (የተመሰገነች) እንደሚላት›› ነው፡፡ (ሉቃ 1፡48)
ይህ ትውልድ ግን አባቱን የሚያዋርድ እናቱን የሚሳደብ በመሆኑ አመስግኖ በረከትን ለመቀበል አልታደለም አለማስተዋል ነው እንጂ በእግዚአብሔር መንፈስ ከተቃኙት ከኤፍሬም ሦሪያዊ፣ ከሕርያቆስ ግብፃዊ (ሀገረ ብሕንሳ)፣ ከጊዮርጊስ ዘጋስጫ ኢትዮጵያዊ አልያም ከሊቁ ቅዱስ ያሬድ ኢትዮጵያዊ አንበልጥም የበለጠ ምስጢር ተረድተን አሊያም ተራቀን አይደለም፡ ነገር ግን የሉተር አባዜ፣ የንስጥሮስ ርኩስ መንፈስ የመቅደንዮስም ጥርጥር በዚህ ትውልድም በልቡናው እየነገሰ እንደ ነፋስ አፍገምግሞ ጥሎት እንጂ:: ባለንበት በመጨረሻው ዘመን ዋዜማ የሚሳደብ፣ የሚያፌዝና የሚዘብት ትውልድ ይነሳ ዘንድ ግድ ነው ከዚህም የተነሣ የእግዚአብሔር ረድኤትና በረከት ከትውልዱ እየራቀ ነው፡፡ ድንግል ማርያም እኛ ባናመሰግናት ቅዱሳን መላዕክት ያመሰግኗታል ‹‹ስለዚህ ማርያም ሆይ መላዕክት ከፍ ከፍ ያደርጉሻል ሱራፌልም ያመሰግኑሻል›› (ውዳሴ ማርያም ዘዓርብ) እኛም ብናመሰግናት ከፍ ከፍም ብናደርጋት እንመሰገናለን ከፍ ከፍም እንላለን፣ ብናዋርዳት ግን እርሷ አትዋረድም እኛ ግን እንዋረዳለን፡፡
ይህን ተገንዝበን አሁኑኑ እንመለስ ለመልካም ሥራ እንዘጋጅ በዚህ ቃል ኪዳን በተቀበለችበት ዕለት በስሟ ወደ ታነጸው አቢያተ ክርስቲያን በመሄድ ምስጋና እናቅርብላት ከተቻለን እርሷ ልጇን ወዳጇን ጥያቄ ይቃ መልስ ያገኘችባቸውን ቃል ኪዳን የተቀበለችባቸውን ሁሉ እናድርግ ምክንያቱም ‹‹የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ›› (ዮሐ 2፡6) ብላናለችና፡፡
በቃል ኪዳኑ ለተማጸኑት በስሟ በታነጸው አጸድ ተሰብስበው ማርያም ማርያም ብለው ለሚቃትቱት ሁሉ ከልጇ ከወዳጇ እያማለደች ከጭንቀት ከመከራ እየገላገለች ከቀሳፊው በሽታ እያላቀቀች የምህረት ኪዳንን ትዝታ በልባቸው እያተመች ታሰናብታለችና፡፡
እናትነቷን ሳናቃልል በቃል ኪደኗ ጸንተን በአማላጅነቷ እንታመን ልጇ ወዳጇ የሚለውንም እናድርግ ‹‹የሚወደኝ ቢኖር ትዕዛዜን ይጠብቅ›› ይላልና (ዮሐ 15፡14 ፣ ዮሐ 14፡15)  


No comments:

Post a Comment