Friday, February 21, 2014

ሶምሶንንና ዴማስን የማረከችው ደሊላ



ሕይወታቸውን እስከ ሞት ድረስ ለወደዳቸው ለኢየሱስ ክርስቶስ ሰጥተው ፀበ-አጋንንቱን ታግሰው ፈተናንና እንቅፋትን በጥበብና በብዙ ትዕግስት በእግዚአብሔር አጋዥነት አልፈው አርአያና ምሳሌ በመሆን ክርስትናን ሕይወት አድርገው በንጽሕናና በቅድስና የኖሩት አበው፣ ክርስትና የመሰናክል ሩጫ ከመሆኑም ባሻገር፣ ክርስትና ተዘናግተው እንዳይኖሩ ተኝተው እንዳያድሩ ተደላድለው እንዳይቀመጡ ዕረፍት የሚነሳ ሰላምን የሚያውክ ሰይጣን ዲያብሎስን ያክል ክፉ ጠላትና የማይታረቁት ባለጋራ ያለበት ሕይወት እንደሆነ ያስተምሩናል በመሆኑም ክርስቲያን ዘወትር በመጠንና በጥንቃቄ መኖር ይገባዋል፡፡ ‹‹ባለጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሳ አንበሳ በዙሪያችሁ ይዞራል እንዲል የጽድቅ ሐዋርያ ጳውሎስ›› (1ጴጥ 5፡7)




ከዚህም በላይ በትዕግስትና በማስተዋል ሆኖ ልቦናን ለመንፈስ ቅዱስ ክፍት በማድረግ ዓይንን ከቀራኒዮ መስቀል ላይ ሳያነሱ የእግዚአብሔርን ድምፅ በመስማት ያለኝ ይበቃኛል በማለት ራስን በመግዛት ካልኖሩ የዲያብሎስን ሽንገላና ድለላ መቋቋምም ቢሆን አይቻልም፡፡
ሶምሶን በዘመነ መሳፍንት የነበረ ብርቱ አገልጋይ ነበረ ከኢያሱ ሞት በኋላ እስከ ሳዖል መንግስት ድረስ ለ450 ዓመታት ያህል እስራኤልን ያስተዳድሩ የነበሩ መሳፍንት ናቸው፡፡ (ሐዋ 13፡20) ከእነዚህ መሳፍንት መካከል አንዱ ሶምሶን ነበረ ሶምሶን በብሥራተመልአክ የተወለደ፣ ገና ከሕፃንነቱ የተለየ፣ ናዝራዊ ይሆናል በራሱም ምላጭ አይደርስበትም ተብሎ የተነገረለት፣ ከእግዚአብሔር በተሰጠው የኃይል ጸጋ እስራኤልን ከጠላቶቻቸው ከፍልስጤማውያን እየታደገ ይመራቸው የነበረ መስፍን ነው ሶምሶን የእግዚአብሔር መንፈስ በኃይል ስለነበረበት ፍልስጤማውያንን ለብቻው ታግሎ ያሸንፍ ነበር (መሳ 15፡5-15) የጸጋ ስጦታውም በፀጉሩ ላይ የሆነ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለመጠበቅ የተቀባ አገልጋይ ሆኖ ሳለ ከማያምኑት ጋር በማይመች አካሔድ ተጠመደ (2ቆሮ 6፡14) ከጠላቶቹ ወገን ከሆኑ ሴቶች ጋር በማይገባ አካሄድ እየተጠመደ ይመላለስ ጀመር (መሳ 14፡1-16) በመጨረሻም በሶሬቅ ሸለቆ ትኖር ከነበረችው ደሊላ ከተባለች ጋለሞታ ጋር በያዘው ፍቅር የልቦናው በር ቁልፍ ተከፍቶ ምስጢሩን አወጣ ጸጋው ያለበትን ፀጉሩንም ላጨችው የእግዚአብሔር መንፈስ ተለየው ኃይሉንም አጣ በጠላቶቹም እጅ ወደቀ ደሊላም በገንዘብ ተገዝታ አሳልፋ ሰጠችው (መሳ16፡4-22)
ዴማስ ደግሞ የአዲስ ኪዳንን አዋጅ እንዲነግር የተለየ አገልጋይ ነበረ፡፡ በእግዚአብሔር ፈቃድ በቅዱስ ጳውሎስ አማካኝነት ለአገልግሎት የተጠራ በእግዚአብሔር ቃል ዳግም ተወልዶ በመንፈስ ቅዱስ ያደገ የሐዋርያው የጳውሎስ የመንፈስ ልጅ ደቀመዝሙርም ነበረ:: ነገር ግን ‹‹ከእኛ ጋራ ተቆጥሮ ነበርና ለዚህም አገልግሎት ታድሎ ነበር›› (ሐዋ 1፡17) ተብሎ እንደተጻፈ የተጠራበትን ለብዙ ክብር የተመረጠበትን ኃላፊነት በልጅነት ክብር የከበረበትን ጸጋ መንፈስ ቅዱስ ችላ ብሎ ሄደ፡፡
የሠላምን መንገድ ያሳየውን ሕይወትና ትንሳኤ የሆነውን ክርስቶስን ያስታዋወቀውን መምህሩን ጳውሎስን ትቶ ክፉ ባልንጀርነት ጀመረ የዓለምን ታሪክ በሞቱ የቀየረውን ስብራትን የሚጠግነውን የአልቃሾቹን እንባ የሚያብሰውን በነፍሱ ተወራርዶ የተቤዥውን በኋላም ለዘላለም በደስታ መኖሪያ ይሆነው ዘንድ በዓይን ያልታየ በጆሮ ያልተሰማ ልዩና ማራኪ ሰማያዊ ከተማ ያዘጋጀለትን ኢየሱስ ክርስቶስን ረስቶ ደሊላ የተሰሎንቄ ከተማ ማረከችው፡፡
ደሊላ ሶምሶንን በውበቷ አታላ፣ በፍቅሯ አጥምዳ፣ በገንዘብ ተገዝታ አሳልፋ እንደሰጠችው ሁሉ ዴማስም ደሊላ የተሰሎንቄ ከተማ በውስጧ ባሉት ውብ ነገሮች አታላ በሥጋ አምሮት ማረከችው፡፡ አበው ወርቅ የሚመስል ነገር ሁሉ ወርቅ አይደለምና አስተውል በእሳት ነጥሮ ተፈትኖ ካልወጣ በስተቀር እንዲሉ ሶምሶንና ዴማስ የምዕመናን፣ ደሊላ የፈቃደ ሥጋ፣ የደሊላ ወገኖች የዲያብሎስ ምሳሌዎች ናቸው እንዴት ቢሉ ደሊላ ሶምሶንና ዴማስን አታላ ለጠላቶቻቸው እንደሰጠች ሁሉ ዛሬም ዓለም፣ ፍቅረ ነዋይ፣ ክፉ ምኞት፣ ሐሳውያን ረበናት መናፍቃን ወዘተ የመሳሰሉት ደላላዎች የሰውን ልጅ ሸንግለው ለዲያብሎስ አሳልፈው በመስጠት የእርሱ ተገዥ ያደርጉታልና፡፡ ዛሬ ብዙዎቻችን በጥምቀት ያገኘነውን የጸጋ ልጅነት እንደተሰበረ ዕቃ እያሸቀነጠርን ጥለን በሬ ለመታረድ እንደሚነዳ ራሳችንን ለሰይጣን አሳልፈን ስንሰጥ ይታያል፡፡
በዘመናችን ብዙዎችን ከማረኩት ደሊላዎች (ደላላዎች) መካከል ጥቂቶችን ለማየት እንሞክራለን፡፡
1.  ዓለም
ዓለም በኃላፊና በጠፋው ውበቷ ብዙዎችን ደልላ አስቀርታለች ይልቁንም ባለንበት በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ለዓይነ ሥጋ በሚያማምሩ በርካታ ብልጭልጭ ነገሮች ተሞልታለች የሚሰማው ዘፈን፣ የሚታዩት አልባሳት፣ በተለያየ ሁኔታ ጣፍጠው ተከሽነው የሚቀርቡት ምግቦች፣ ለስካርና ለሱስ የሚዳርጉት የአልኮል መጠጦችና የሚገኙባቸው መሸታ ቤቶች ፣ የመኖሪያ ቪላዎች የመንሸራሸሪያ መኪናዎች ወዘተ ካላወቅንባቸው የሥጋ አምሮታችንን ክፉኛ ቀስቅሰው ከሕገ እግዚአብሔር እንድንወጣና ስለምድራዊ ኑሯችን ብቻ እንድናስብ የሚያደርጉ ናቸው፡፡
ዓለም እስከፍጻሜዋ ዘማ ናት፣ የሚዳሯትን፣ በግብሯ የተማረኩትን ወዳጅ የሆንዋትን በደም ግባቷ ፍቅር የሳበቻቸውን ፍጹም በወጥመዷ ውስጥ ካስገባች በኋላ በቀላሉ አትለቃቸውም፡፡ ደሊላ ሶምሶንን ከአንበረከከችው በኋላ በብዙ ጭቅጨቃና ውትወታ የምስጢር በሩን ከፍታ እንደገባች ሁሉ ዓለምም በመላ ሰውነታችን በደም ሥራችን ሁሉ የኃጢዓት መርዟን ረጭታ በአፍዝ አደንግዝ አስማቷ እጅ እግራችንን ተብትባ ይዛ ለጠላታችን ዲያብሎስ አሳልፋ ትሰጠናለች፡፡
የጌታ ወዳጅ የፍቅር ሐዋርያ ቅዱስ ዮሐንስ በትምህርቱ ‹‹ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደድ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለገንዘብም መመካት ከዓለም ስለሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፣የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል›› (1ዮሐ 2፡15) በማለት የዓለምን አታላይነት ጽፎልናል ዓለምን እየወደደ የእግዚአብሔር የሆነ የለም አባቶቻችን ሐዋርያት ከዓለም ተመረጡ እንጂ ዓለማዊ አልነበሩም፣ ሁሉም ሲጠሩ ቤቴ ንብረቴ፣ ሚስቴ ፣ልጄ ሳይሉ ተከተሉት ዓለምንና ጣዕሟን ንቀው በዓለም ውስጥ ሆነው ከዓለም ተለዩ፡፡ (ዮሐ 17፡15)
ዓለምን መውደድ ከእግዚአብሔር ጋር መጣላት ነው ምክንያቱም የዓለም የሆነ ሁሉ የሰይጣን ነው፤ ሰይጣንና እግዚአብሔር ደግሞ ሕብረት የላቸውም ዴማስ፣ የተሰሎንቄ ከተማ ውበት የዓለም አምሮት ናፈቀውና ከጽድቅ ጎዳና አፈገፈገ ‹‹ዴማስ ይህን ዓለም ወዶ ትቶኛል›› (2ጢሞ 4፡10) እንዲል ሐዋርያው በዓለም ፍቅር የተነደፈ ጉዞ ቢጀምርም እንኳ ይቋረጣል ደላላዋን ደሊላን ዓለምን ከነስንኮፏ ነቅሎ በመጣል ቆርጦ መነሳት ይገባል፡፡ ብዙዎች ከዓለም ተለዩ ሲባሉ ‹‹እንዴት ይሆንልኛል›› በማለት ገና ለገና ከሩቅ ፍራቻ ብቻ ሲሸነፉ ይታያሉ አምላካችንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ትምህርቱ ‹‹በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ ነገር ግን አይዟችሁ እኔ ዓለሙን አሸንፌዋለሁ›› (ዮሐ 16፡33) ሲል ሐዋርያቱን ባጽናናበት አንቀጽ እኛንም ይመክረናል በዓለም እየኖሩ ከዓለም መለየት መከራ ነው ቢሆንም ግን ‹‹ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱን ግን ቢያጎድል ምን ይጠቅመዋል?›› (ማቴ 16፡27) ተብሎ ተጽፏልና ነፍሳችንን እንዳናጎድል ከዓለም መለየት ይገባናል፡፡
ሶምሶን ደሊላን ወድዶ ለጠላቶቹ እንደተዳረገ እኛም ዓለምን ወደን የዲያብሎስ ተገዥ ከመሆን እግዚአብሔር ይጠብቀን፡፡
2.  ፍቅረ ንዋይ
ገንዘብ :ንዋይ የሰው ልጆችን ሁለንተና ተቆጣጥሮ የመግዛት ኃይል ስላለው በመጽሐፍ ቅዱስ ጌታ ተብሏል፡፡ ‹‹ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም ወይም አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም ይወዳል ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይርቃል ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም›› (ማቴ 6፡24)
ፍቅረ ነዋይ ሌላው አዕይንተ አእምሮአችን በስግብግብነት መንጦላዕት ጋርዶ፣ እግሮቻችንን በምኞት ፈረስ እያስጋለበ ከእግዚአብሔር አንድነት ለይቶ ለዲያብሎስ ተገዥነት አሳልፎ የሚሰጠን ደላላ ነው፡፡ ‹‹ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነው›› (1ጢሞ 6፡10) የሚለው ቃለ እግዚአብሔር ተቀይሮ ‹‹ገንዘብ የደም ሥር ነው›› በሚለው ብሂል ከተተካ ውሎ አድሯል ዛሬ ብዙ እህቶቻችንና ወንድሞቻችን ‹‹እምነት በልብ ነው›› በሚል በተሳሳተ ፈሊጥ ስመ ክርስትናቸውን እየለወጡ ወደ ባዕድ ሀገር የሚነጉዱት ለዚሁ የገንዘብ ጉዳይ ነው፡፡
እነሱ እንደዚያ ይበሉ እንጂ ‹‹አንዳንዶች ይህንን ገንዘብ ሲመኙ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ስቃይ ራሳቸውን ወጉ›› (1ጢሞ 6፡10) የሚለው ቃል እየተፈፀመባቸው መሆኑን አላስተዋሉም፡፡ ዛሬ ከፍቅረ ንዋይ የተነሣ ነፍስ ሲጠፋ፣ እውነት ተደብቆ ሐሰት ሲነግስ ፍርድ ሲጓደል ደሀ ሲበደል ማየት አዲስ ነገር አይደለም፣ በእግርህ ከምትደክም በእጅህ ሄደህ ተገላገል በሚል ፈሊጥ ጉቦ እጅ መንሻ መስጠትም ሆነ መቀበል እንደ ባሕል ከተቆጠረም ቆይቷል፡፡፡
የበለፀጉ ሀገሮችም ግብረሰዶምን እንደ ሰብአዊ መብት ተቀብላችሁ ዝሙትን ካላወጃችሁ መዋዕለ ንዋያችን አናፈስም ፣ ዕርዳታ አንሰጥም፣ ገንዘብ አንለግስም በማለታቸው ታዳጊ ሀገሮች ነውሩን እንደ ክብር ኃጢዓቱን እንደ ጽድቅ በማየት በቸልተኝነት ሃይማኖትና አኩሪ ታሪክ ያለውን ጨዋና ምስጉን ሕዝብ በማበላሸት ላይ ያሉት ከፍቅረ ንዋይ የተነሣ ነው፡፡
‹‹በመጽሐፍ ርኩስንም አትንኩ ከመካከል ውጡ የተለያችሁም ሁኑ›› (2ቆሮ 6፡17-18) ተብሎ ስለተጻፈ ጻድቅ ያለ ነውር ይሄዳልና ትልቁ ሀብታችን ንጽህናችን ነው ልንል ይገባል ‹‹ብርን የሚወድ ሰው ብርን አይጠግብም ባለጠግነትንም የሚወድ ትርፍን አይጠግብም ይህም ደግሞ ከንቱ ነው›› (መክ 9፡10) ፍቅረ ንዋይ ያነሆለለው ሰው ስለ መንፈሳዊ ነገር የሚያስብበት ጊዜ አይኖረውም፡፡
አእምሮው ውስጥ ገንዘብ ደወል ስለሚደውል ቃለ እግዚአብሔር አይገባውም ባለጠጋም ስለንብረቱ ሲያወጣ ሲያወርድ እንቅልፍ አይወስደውም በወንጌል አንድ ሕግ አዋቂ ፈሪሳዊ የዘላለም ሕይወትን ሊያገኝ ፈቅዶ ጌታን ‹‹ምን መልካም ነገር ላድርግ አትግደል ፣ አታመንዝር ወዘተ የሚሉትን ሁሉ ፈጽሜያለሁ ብሎ የቀረበው ሰው ንብረትህን ሁሉ ሸጠህ ለድሆች ስጥ ተከተለኝም ባለው ጊዜ ፊቱን አዙሮ ኮበለለ ምክንያቱም ብዙ ሀብት ነበረውና›› (ማቴ 19፡16፡-22) ‹‹ኢየሱስ ክርስቶስም ባለጠጋ ወደ እግዚአብሔር መንግስት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል›› አለ፡፡ (ማቴ 19፡24) ገንዘብን ማምክ ፍጻሜው የዲያብሎስ ባሪያ መሆኑን አውቀን እንስራበት፡፡
ይህን ስንል ግን ገንዘብ አያስፈልግም ማለት አይደለም ነገር ግን ሐዋርያው እንዳለ ‹‹ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያው ነው›› (1ጢሞ 6፡6) ስለዚህ በደሊላ በፍቅረ ንዋይ ተማርከን ለጠላት ተላልፈን እንዳንሰጥ በመጠን እንኑር‹‹ኑሮዬ  ይበቃኛል›› ማለትን እንልመድ፡፡
3. ቢጽ ሐሳውያንና መናፍቃን
ግፈኛ ሰው ወዳጁን ያባብላል ጥሩ ወዳልሆነ መንገድም ይወስደዋል (ምሳ 16፡29) ተብሎ እንደተጻፈ የዘመናችን ደሊላዎች ሐሳውያን ረበናት መናፍቃን ናቸው እነሱ ተሳስተው ከሃይማኖት ወጥተው ከጽድቅ ተራቁተው ከምግባርም ጎድለው ነፃ እናውጣችሁ እያሉ በቀጥተኛው መንገድ ላይ ያሉትን በብዙ ውትወታና ድለላ ያስታሉ፣ በብርሃን ያሉትን ወደ ጨለማ ያግዛሉ፣ በጻጋና በብዙ በክብር ያሉትን ከጸጋ አራቁተው ወደ ባዶ አዳራሽ ወስደው ለጠላት ዲያብሎስ አሳልፈው ይሰጡታል ደሊላዎች ናቸው፡፡
‹‹ራሳቸው የጥፋት ባሪያዎች ሆነው አርነት ትወጣላችሁ እያሉ ተስፋ ይሰጡዋቸዋል›› (2ጴጥ 2፡19) ሃይማኖትን እንደ ፋሽን መቀያየር እንደ ዘመናዊነት በሚታይበት በዚህ ዘመን መርከብ በማዕበል እንደሚዋዥቅና አቅጣጫውን እንደሚስት ብዙዎች በሐሰት ትምህርትና በሐሳውያን መምህራን ስለ እምነት ስተዋል፡፡ ‹‹በውሸት ዕውቀት ከተባለ ለዓለም ከሚመች ከከንቱ መለፍለፍና መከራከር እየራቅህ የተሰጠህን አደራ ጠብቅ ዕውቀት አለን ብለው አንዳንዶች ስለ እምነት ስተዋልና›› (1ጢሞ 6፡21) ብዙዎች ባለማወቅ የሚያስቱ መናፍስትን አታላዮችን እየሰሙ ከሃይማኖት ወጡ፡፡
‹‹መንፈስ ግን በግልጥ በኋለኞች ዘመናት አንዳንዶች የሚያስቱ መናፍስትንና በውሸተኞች ግብዝነት የተሰጠውን አጋንንትን ትምህርት እያደመጡ ሃይማኖትን ይክዳሉ›› (1ጢሞ 4፡1) ልዩ ትምህርትን ይዘው ከሚመጡ ተሳስተው ከሚያስቱ በመራቅ ከእውነተኞቹ መምህራንና ሊቃውንት በመማርና በማወቅ በቀደመችውና በቀጥተኛዋ ሃይማኖት መጽናት እንደሚገባ ሲያስተምር ሐዋርያው ጳውሎስ ‹‹ማንም ልዩ ትምህርት የሚያስተምር ከጌታችንም ከኢየሱስ ክርስቶስ በሆነው ጤናማ ቃልና እግዚአብሔርን ለመምሰል በሚስማማ ትምህርት የማይጠጋ ቢሆን በትዕቢት ተነፍቶአል አንዳችም አያውቅም ነገር ግን ምርመራን በቃልም መዋጋትን እንደ በሽተኛ ይናፍቃል ከእነዚህም ቅናትና ክርክር ስድብም ክፉ አሳብም እርስ በእርስ መናደድም ይወጣሉ፣ አእምሮአቸውም በጠፋባቸው እውነትንም በተቀሙ እግዚአብሔርን መምሰል ማትረፊያ የሚሆን በመስላቸው ሰዎች ይገኛሉ እንደነዚህ ካሉት ራቁ›› (1ጢሞ 6፡3-5)
‹‹ነገር ግን ክፉዎች ሰዎችና አታላዮች እያሳቱና እየሳቱ በክፋት እየባሱ ይሄዳሉ አንተ ግን በተማርህበትና በተረዳህበት ነገር ጸንተህ ኑር ከማን እንደተማርከው ታውቃለህና ከሕፃንነትህም ጀምረህ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳት መጻሕፍትን አውቀሃልና›› (2ጢሞ 3፡13-15)
እንግዲህ ከላይ ለማየት እንደሞከርነው ልባችንን ከቤተ እግዚአብሔር አሸፍተው የዲያብሎስ አገልጋይ የሚያደርጉን ደሊላዎች ሦስት ብቻ ናቸው ማለት አይደለም ዋናዎቹን ለመጠቆም ያህል እንጂ ሶምሶንን ጠላቶቹ ከያዙት በኋላ ዐይኑን አውጥተው በሰንሰለት አስረው እህል እያስፈጩ እጅግ አስቃይተውታል እኛም በዲያብሎስ እጅ ከወደቅን የሚደርስብን ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ እንዳናይ ዓይናችንን ጋርዶ እንዳንራመድ እግራችንን አስሮ በንስሐ ሳንመለስ ሥጋውንና ደሙን ሳንቀበል ህልፈታችንን አቅርቦ በእሳት ሰንሰለት እየተገረፍን በሲኦል እንድንጣል ይፈልጋልና እንወቅበት ቀድመን መንገዱን እንዝጋ፡፡ ለጠላት አሳልፋ የምትሰጠን በሚያባብል ቃላት እያሳተች በፍቅሯ እየማረከች የምትደልለንን ደሊላን ከነክፋቷ ቆርጠን እንጣል ለዚህም እግዚአብሔር በምህረቱ አይለየን አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment