Wednesday, February 12, 2014

ክልፍ 2‹‹መዳን በሌላ በማንም የለም›› (ሐዋ 4፡12)

 
                                             ‹‹መዳን በሌላ በማንም የለም›› (ሐዋ 4፡12)
                                                        ክልፍ 4



 






 

‹‹በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል ፣ ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል››(ዮሐ 14፡12)

ባለፈው ጽሑፋችን ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ መዳን ‹‹በሌላ በማንም የለም›› ብሎ ያስተማረበትን ኃይለ ቃል ርዕስ አንስተን የመዳንን ትርጉምና ዓይነት የመናፍቃን የሉተራውያን ዕይታና ስህተት በተዋሕዶ ሊቃውንት አስተምህሮ ሲተረጎምና ሲብራራ ምን እንደሚመስል ለማየት ጀምረን ነበር፡፡




በመሆኑም መዳን ብለን ስንል ሊቃውንት በሦስት መልኩ እንደሚተረጉሙት ጠቁመን ከዚያ መካከል፡-
   ፩ኛ፦  የመጀመሪያው መዳን እግዚአብሔር አምላክ ለሰው ልጅ ካለው ጥልቅ ፍቅር የተነሣ አዳምን ከወደቀበት አንስቶ ከተረሣበት አስታውሶ ጸጋውንና ክብሩን መልሶ በዕለተ አርብ ወደ ተፈጠረበት ወደ ጥንተ ተፈጥሮ ወደ ገነት የመለሰበት ወይም ለመመለስ ያደረገው ጉዞ ማዳን ይባላል፣ ይህ ማዳንም ፍጥረት የማይጋራው እግዚአብሔር በምህረቱና በቸርነቱ ለሰው ልጆች የሰጠው የጻጋ ስጦታ ነው (ኤፌ 2፡4-5)
ይህም ድህነት (ማዳን) የተፈፀመው በምስጢረ ሥጋዌ በነገረ ተዋሕዶ እንደሆነ አይተናል፡፡
   ፪ኛ፦ቅዱሳን መላዕክትና ቅዱሳን ጻድቃን ያድናሉ እግዚአብሔር ማዳን የባሕርይው ሲሆን መላዕክትና ቅዱሳን ሰዎች ደግሞ በጻጋ ከእግዚአብሔር በተሰጣቸው መሠረት
መላዕክት በጥበቃቸው፣ በምልጃቸው፣ በመመምራታቸው የሰው ልጆችን ያድናሉ፡፡ ጻድቃን ቅዱሳንም በተሰጣቸው ጸጋ በቃል ኪዳናቸውና በምልጃቸው ይታደጋሉ ብለን ማስነበባችን ይታወሳል በዚህ ጽሑፍም ካለፈው የቀጠለውን መዳንና የመዳን ትርም ነተዋሕዶ ሊቃውንት አስተምህሮ ሲገለጥ ምን እንደሚመስል ቀጣዩን ክፍል እነሆ
                                                           ፫ኛ፦ እግዚአብሔር በተለያየ ነገሮች ያድናል
በጸበል፣ በመስቀል፣ ገዳማትን በመሳለም ፣ በመጽሐፍ ቅዱስና; በቅዱስ አፈር (እምነት) በመተሻሸት ወዘተ እግዚአብሔር ብዙዎችን በብሉይ ኪዳንም  በሐዲስ ኪዳንም በጸበል አድኗል ለምሳሌም፡-
በ2ኛ ነገ 5፡8-19 ተጽፎ እንደምናነበው የሶሪያ ንጉሥ የሠራዊት አለቃ የሆነው ንዕማን በነቢዩ በኤልሳ ትዕዛዝ በዮርዳኖስ ወንዝ (በጸበል) ተጠምቆ ከለምጹ ነጽቷል፡፡
በሐዲስ ኪዳንም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመወለዱ ጀምሮ ዓይነ ስውር የነበረው ሰው ምራቁን በአፈር ቀላቅሎ ዓይኖቹን በጭቃ ከቀባው በኋላ ሂድና በሰሊሆም መጠመቂያ ተጠመቅ (ታጠብ) አለው (ዮሐ 9፡1-7) ሄዶም ተጠመቀ እያየም መጣ ሌሎቹም እንዲሁ ብዙዎች ተፈወሱ፣ ከላይ በተጠቀሱት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ላይ ቅዱስ አፈር (እምነትን) በተመለከተም የምንማረው ነገር አለ ‹‹ንዕማን በጸበል ከተፈወሰ በኋላ ከቅዱሳን መካናት ቅዱስ አፈር (እምነት) ለፈውስ ለድህንት ይጠቅማልና ይዞ ሄዷል›› (2ኛ ነገ 5፡17)

ኢየሱስ ክርስቶስም ዓይነ ስውሩን በአፈር፣ በጭቃ ነው የቀባው ይህ የቅዱስ አፈር (የእምነት) ምሳሌ ነው ታዲያ በጸበል መዳን፣ በቅዱስ አፈር (በእምነት) መዳን፣ በመስቀል መዳን ስንል ከሲኦል እስራት ነፃ ወጣህ ገነት ገባህ ማለታችን አይደለም፣ ነገር ግን እግዚአብሔር ተአምሩን የሚገልጽበት ለሰው ልጆች ያለውን ቸርነት የሚገልጽበት የማዳን ሥራው ነው፡፡ ምክንያቱም በኃይማኖት ውስጥ የሌሉ ወገኖች በእምነት ብቻ ፈውስ እናገኛለን ብለው ተጠምቀው ይድናሉ፣ ነገር ግን እነዚህ ወገኖች ጸድቀዋል ገነት ይገባሉ ማለት አይደለም፡፡ ይህ የሚያሳየው እግዚአብሔር ለእነሱ ያደረገውን ቸርነት ምህረት እንጂ የሰዎችን ንጽህና ቅድስና ጽድቅ አይደለም ብዙ ጊዜ ግን እግዚአብሔር ድንቅ ነገርን አድርጎላቸው ተአምራቱን ገልጾባቸው፣ ይህን ያደረገውን እግዚአብሔርን ከማድነቅና ከማመስገን ይልቅ ሰዎቹን ተጠምቀው የዳኑትን ወገኖች ለምስክርነት በአውደ ምህረት የምናቆም እንኖራለን፣ ከዚህም የተነሣ የሰዎቹ ሕይወት ሳይስተካከል ንስሐ ሳይገቡ፣ ወንጌል ሳይማሩ፣ ሥጋ ና ደሙን ሳይቀበሉ በዚያው ጠፍተው እንዲቀሩ እናደርጋቸዋለን፡፡
 

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በዘኅ 22፡22 የበላዕም አህያ የእግዚአብሔርን መልአክ ስላየች አህያዋ ጸድቃለች ማለት አይደለም ነገር ግን የእግዚአብሔር ምህረቱን ቸርነቱን ድንቅ ሥራውን ነው የሚያሳው፡፡ እንደዚሁ ሁሉ ሰዎች ኃጢዓተኛ ሆነው በጸበል፣ በእምነት፣ መስቀል በመሳለምና መካናትን በመሳለም ሊድኑ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ጸድቀዋል በቅተዋል ማለት ግን አይደለም ይህ የሚያሳየው የእግዚአብሔርን የምህረት ጊዜ ዛሬ እንዲህ ከዳንህ ከጊዜያዊ ቁስል ከሥጋ ቁስል ከተፈወስክ ከነፍስህሞ ቁስል እንድትፈወስ እምነትን ከምግባር አስተባብረህ ይዘህ ለንሰሐ የሚገባ ፍሬ አፍርተህ ወደ ዘላለም ድህንት ግባ ሲል ነው፡፡
በቅዱሳን መላዕክት፣ በቅዱሳን ጻድቃን ስም ስዕለት ተስለን ከጭንቀታችን ተረጋግተን፣ ከሐዘናችን ተጽናንተን ከደዌያችን ተፈውሰን መዳኑን እንድናለን ነገር ግን ይህ ከመጀመሪያው መዳን ጋር ግንኙነት የለውም ፡፡
ከጊዜያዊ መከራ፣ ሐዘን፣ ሥጋደዌ ዳንን ማለት ጸድቀን ገነት ገባን ማለት አይደለም፣ ያኛው መዳን በኢየሱስ ክርስቶስ መስዋዕትነት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍሶ አዳነን የምንለው ማዳን ሱታፌ ይጠይቃል፡፡ ይኸውም፡-
1.   የእግዚአብሔር ጸጋ
ጸጋ፡- እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ስላለው ፍቅር የሚሰጠው የቸርነት ስጦታ ነው ይህም ጸጋ የፍቅር አምላክነቱ መገለጫ፣ ያለጽድቅ ሥራ ያለ ዋጋ የሚሰጥ ነፃ ስጦታ ነው ሰዎች ሁሉ ኃጢዓትን ሰርተዋል የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሏቸዋል በምህረቱ ብዛት በጻጋው ስለታጠሩ ግን አልጠፉም ይህ ጸጋ ክብር ጎድሎን ጽድቅ ልምላሜ ተለይቶን ሳለ (ኢሳ 64፡5 ፣ ኤፌ 2፡5) በምህረቱ ባለጸጋ ስለሆነ በጸጋው አዳነን፡፡
ሌላው ይህ ጻጋ ያለ ዋጋ ያለ ክፍያ በነፃ ነው የተሰጠን ‹‹ብድራቱን ይመልስ ዘንድ ለእርሱ አስቀድሞ የሰጠን ማን ነው?›› ሮሜ 11፡35 እንዳለ ሐዋርያው ጳውሎስ (ሮሜ 3፡23) ይህ ጻጋ ዘላለማዊ ነው ሰዎች በኃጢዓታቸው ያልጠፉት የእግዚአብሔር ጻጋ ለዘላለም ስለሆነ ነው (ሰቆ ኤር 3፡22)
2.   እምነት (ማመን ያስፈልጋል)
‹‹ጸጋው በእምነት አድኗችኋልና›› (ኤፌ 2፡8) ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም የሁሉ ነገር መሠረት እምነት ነውና (ዕብ 11፡6)
እግዚአብሔርን ማመን የምንችለው ከእርሱ ጸጋ የተነሣ ነው (ዮሐ 6፡44) በጸጋ እናምናለን በእምነትም የእግዚአብሔርን ጸጋ እንቀበላለን ‹‹እንግዲህ ምህረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጻጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ›› (ዕብ 4፡16 ፣ ኤፌ 3፡12)
3.   የጽድቅ ሥራ
ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሰው ልጆች በደል በደለኛ ሆኖ በመስቀል ላይ የሞተው፣ የሰው ልጅ በሥጋ እንዳይሞት ሳይሆን በነፍሱ ዘላለማዊነት እንዳይሞት ነው እርግጥ ነው ገና ደካሞች ሳለን ክርስቶስ ዘመኑ ሲደርስ ስለ ኃጢዓተኞች ሞቷል፡፡ ኃጢዓት በሰው ልጆች ላይ ሲበዛ በኃጢዓት ላይ ሞት ነገሠ፣ ስለዚህ ከሞት ይልቅ ኃይል ያለውን ኃጢዓት ኢየሱስ በመስቀል ሞቶ ሲያስወግደው ፣ በሥልጣኑ የኃጢዓታችን እስራት ሲፈታ፣ በኃጢዓት ኃያልነት ላይ የነገሠው ሞት ኃጢዓት ሲደመሰስ ኃይሉን አጣ፣ ሞት ይቆምበት የነበረው ኃጢዓት ሥሩ ሲነቀል ይመካበት የነበረው ኃጢዓት በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ሲገሰስ ሞት ራሱን ችሎ መቆም አልቻለም፡፡ የጌታን የኃይል ድምፅ ሲሰማ ደነገጠ ‹‹ሞት ሆይ መውጊያህ የት አለ›› (1ቆሮ 15፡55)
የዲያብሎስ ሴራ የነበረው ኃጢዓት ሲፈርስ ሞት ፈረሰ (1ዮሐ 3፡9) ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል ከማድረጉ በፊት ኃጢዓትን ማሸነፍ ነበረበት፡፡
በመሆኑም ኢየሱስ ክርስቶስ ከኃጢዓት ማሠሪያ የፈታን ለኃጢዓት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር ነው እንጂ በጸጋው ብቻ እንድናለን ብለን ተመልሰን የኃጢዓት ባሪያ እንድንሆን አይደለም ጸጋ ከእግዚአብሔር የሚሰጥ ሲሆን እምነትና የጽድቅ ሥራ (ለንስሃ የሚገባ ፍሬ) ግን ከሰው ነው፡፡
ሉተራውያን ፕሮቴስንታንት ‹‹ጸጋው አድኖናል›› ጸጋው ካዳነን ደግሞ የጽድቅ ሥራ መስራት ጥሩ ነው ባንሰራም ምንም አይደለም ይላሉ፡፡ ነገር ግን ይህ ስህተትና መጻሕፍትን አለመረዳት የእግዚአብሔርን ኃይልም አለማወቅ ነው (ማቴ 22፡29) ጸጋው በእምነት አድኖናል ብለን ከጽድቅ መራቆትና ጽድቅን በቋሚነት አለመስራት ግን ለኃጢዓት መማረክ ከዚያም ከሞት ጋር መዛመድ ነው ኃጢዓት ከተሻረ ለጽድቅ መኖር እንዳለብን እንረዳለን፡፡
ካለበለዚያ ጽድቅ ላለመሥራት ምክንያት የለንም በሕይወት ዘመኑ የጽድቅ ሥራን የማይሠዘራ ክርስቲያን በመንፈሳዊ ሕወቱ እየፈረሰ ይሄዳል የዳንነው ከኃጢዓት ነው ካልን ተመልሰን ኃጢዓት መሥራት የለብንም ሐዋርያው ይህንን ሲያብራራ ‹‹እንግዲህ ምን ይሁን ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች ስላይደለን ኃጢዓትን እንሥራን?›› (ሮሜ 6፡15) በጸጋው ድነናል ብለን የጽድቅ ሥራን አለመሥራት የነፍስ ሞት ያስከትላል (ሮሜ 6፡23)
እምነት ያለ ጽድቅ ሥራ ከንቱ እንደሆነ ሐዋርያው ያዕቆብ ‹‹አንተ ከንቱ ሰው እምነት ከሥራ ተለይቶ የሞተ መሆኑን ልታውቅ ትወዳለህን?›› (ያዕ 2፡20) ብሎ ከጻፈ በኋላ ‹‹ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደሆነ እንዲሁ ደግሞ ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው›› (ያዕ 2፡26) በማለት እምነትን ያለ መልካም ስራ ማሳየት እንደማይቻል አስረግጦ ነግሮናል ስለዚህ ለመዳን የጽድቅ ስራ መሥራት ይገባናል ማለት ነው፡፡
4.   መጠመቅ ያስፈልጋል
ለመዳን በእግዚአብሔር ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት፣ የአብ የባሕርይ ልጅ መሆኑን በማመን፣ የዘመኑ ፍጻሜ ሲደርስም ከድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷ ነፍስን ነስቶ ከሁለት አካል አንድ አካል፣ ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ ሆኖ በተዋሕዶ የከበረ ፍጹም አምላክ ፈራጅ መሆኑን አምኖ በሥላሴ ስም መጠመቅ ያስፈልጋል፡፡
 




 
 

‹‹ሒዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ፣ በወልድ፣ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችሁ ደቀመዛሙርቴ አድርጓቸው›› (ማቴ 28፡19)
ይህንን በተመለከተ አምላካችን ክርስቶስ ራሱ በዘመነ ሥጋዌ በሚያስተምርበት ጊዜ ‹‹ያመነ የተጠመቀ ይድናል ያላመነ ያልተጠመቀ ግን ይፈረድበታል›› (ማር 16፡16) አንድም በእግዚአብሔር ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም አምላክነት አምኖ የልጅነት ጥምቀትን መጠመቅ ለድህነት ያበቃል፣ በሌላው በኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት አምነን በምድር ላይ ስለ ስሙ የሚመጣብን መከራ ሁሉ (ጥምቀት) ይባላልና፣ ያንን መከራውን ሳንፈራ ሳንሰቆቅ እስከ መጨረሻው ከፀናን እንድናለን፡፡ ‹‹ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ የተጠመቅን ሁላችን ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደተጠመቅን አታውቁምን?›› (ሮሜ 6፡3-5)
5.       ቅዱስ ሥጋውን መብላት ክቡር ደሙን መጠጣት
          ቅዱስ ሥጋውን መብላት ክቡር ደሙን መጠጣት ከኃጢዓት ነጽቶ ፍጹም ሥርየትን ለማግኘት ፣ ከሞት ለመዳን የዘላለም ሕይወትን ለመውረስ በኢየሱስ ክርስቶስም ለመኖር የሰውን ልጅ የአምላካችንን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ክቡር ደም ቅዱስ ሥጋ መጠጣትና መብላት ያስፈልጋል፡፡
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማይ ወረደ እንጀራ እኔ ነኝ በእኔ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፣ የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ ሰው ከዚህ ቢበላ ለዘላለም ይኖራል ከሰማይ ወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ እኔም ስለ ዓለም ሕይወት የምሰጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው›› (ዮሐ 6፡45-51)















 

አይሁድ በዚያን ጊዜ ተጠራጠሩ እንዴት ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር አስተካከለ ሁለተኛም እንዴት የሰውን ሥጋ መብላት መጠጣት ይቻላል? ሦስተኛ ይህ ሰው ሥጋውን ልንበላ ይሰጠን ዘንድ እንዴት ይችላል? ዛሬም ብዙዎች ይህንን ፍጹም ድህነት የተገኘበትን ሱታፌ በጥርጣሬ ባለማወቅ አቃለውታል ትተውታል፡፡ ነገር ግን ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹እውነት እውነት እላችኋለሁ የሰውን ልጅ ስጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሳዋለሁ ሥጋዬ እውነተኛ መብል ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ እኖራለሁ›› (ዮሐ 6፡52-57) በእርግጥም ሕያው ለመሆን ከሞት ወደ ሕይወት ለመሻገር የግድ ነው ‹‹ሕያው አብ እንደላከኝ እኔም ከአብ የተነሣ ሕያው እንደምሆን እንዲሁ የሚበላኝ ደግሞ ከእኔ የተነሣ ሕያው ይናል በማለት አስተምሮናል›› (ዮሐ 6፡58)
በመጽሐፍ ቅዱስ በተለያየ ቦታ ተጽፎ እንደምናነበው እግዚአብሔር በሐዋርያቱ እጅ የሚያስደንቅ ተአምራትን ወይም ድህነትን ከማድረጉም ባሻገር በጥላቸውና በልብሳቸው ቁራጭ በቀሚሳቸው ሳይቀር ሙት ያስነሱ ድውይ ይፈውሱ እውራን ያበሩ ነበረ ይህ የእግዚአብሔር በተለያዩ ነገሮች የማዳኑ ምሳሌ ነው ‹‹በሐዋርያትም እጅ ብዙ ምልክትና ድንቅ በሕዝብ መካከል ያደርግ ነበረ ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው በሰሎሞን ደጅ መመላለሻ ነበሩ ከሌሎችም አንድስኳ ሊተባበራቸው የሚደፍር አልነበረም ሕዝቡ ግን ያከብራቸው ነበር የሚያምኑትም ከበፊት ይልቅ ለጌታ ይጨመሩለት ነበር ወንዶችና ሴቶችም ብዙ ነበሩ ስለዚህም ጴጥሮስ ሲያልፍ ጥላውም ቢሆን ከእርሱ አንዱን ይጋርድ ዘንድ ድውያንን ወደ አደባባይ አውጥተው በአልጋና በወሳካ ያኖራቸው ነበር ደግሞም በኢየሩሳሌም ዙሪያ ካለችው ከተማ ድውያንን እና በእርኩሳት መናፍስት የሚሰቃዩትን እያመጡ ይሰበስቡ ነበር፣ ሁሉም ይፈወሱ ነበር›› (ሐዋ 5፡12-16)
‹‹እግዚአብሔርም በጳውሎስ እጅ የሚያስገርም ተአምራት ያደርግ ነበር ስለዚህም ከአካሉ ጨርቅ ወይም ልብስ ወደ ድውዮች ይወስዱ ነበር ደዌያቸውም ይለቃቸው ነበር ክፍዎች መናፍስትም ይወጡ ነበር›› (ሐዋ 19፡11) በወንጌል ተጽፎ እንደምናነበው ሕሙማን ዓይነስውራን፣ አንካሶች የልብሱን ጫፍ ብቻ ሊዳስሱ ይለምኑት ነበር የዳሰሱትም ሁሉ ዳኑ፣ (ማቴ 14፡36) ‹‹እንዲሁም አስራሁለት ዓመት ደም ሲፈሳት የነበረችው ሴት የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን የቀሚሱን ጫፍ በዳሰሰች ጊዜ ተፈውሳለች›› (ማር 5፡25-34) ይላል፣ ይህንን የጌታን የክርስቶስን መፈወስና ማዳን የጻፈው ወንጌል ቅዱስ ጴጥሮስና ጳውሎስ በጥላቸውና በቀሚሳቸው ወይም በልብሳቸው ቁራጭ አዳኑ ፈወሱ ይላል፡፡ ይህ ማለት እግዚአብሔር ማዳን የባሕርይውና ከማንም ያላገኘው ስለሆነ አዳናቸው ቅዱሳኑ ደግሞ በጻጋ ከእግዚአብሔር ያገኙት ስለሆነ ፈወሱ አዳኑ ምክንያቱም በዮሐ 14፡12 ‹‹በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል ፣ ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል››
ይህ  የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ነው፣ እግዚአብሔር ደግሞ በቃሉ የማይዋሽ ከተናገረ የማይክድ ከሰጠ የማይነሣ ጌታ ነው በመሆኑም ቃሉ ተአማኒና እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ የሐዋርያትን ገድል የአገልግሎታቸውን የሕይወት ታሪክ ማንበብ ነው፡፡
ከእኔ የሚበልጥ ይሠራል ተአምር ያደርጋል ማለት ጳውሎስ ወይም ጴጥሮስ ሙት ስላስነሱ ተአምርን ስላደረጉ ከአምላክ ከክርስቶስ ይበልጣል ማለት አይደለም፣ እኔ ለአርያነት በምሣሌነት በወንጌል ከሠራሁት ተአምር አብዝቶ ይሠራል ያደርጋል ማለት ነው፡፡ ይኸውም ጴጥሮስ በጥላው ጳውሎስም በቁራጭ ልብሱ ሳይቀር አዳኑ ብዙዎች የኢየሱስ ክርስቶስን ልብስ ዳሰሱና ዳኑ፣ የቅዱስ ጳውሎስን ግን ቆርጠው ሳይቀር በመውሰድ ተፈወሱ ይህንን የማዳን ጸጋ ለቅዱሳኑ የሰጠ እግዚአብሔር ነው ስለዚህም ስለ ቅዱስ ጳውሎስ ስለቅዱስ ጴጥሮስ ስንናገር ስለ እግዚአብሔር መናገራችን ነው፡፡ ‹‹መንክር እግዚአብሔር በላዕለ ቅዱሳኒሁ፣ እግዚአብሔር በቅዱሳኑ ላይ ግሩም ነው ድንቅ ነው›› ነው የምንለው ምክንያቱም እንዲህ አድርጎ የማዳንን ጸጋ ለቅዱሳኑ ለተክለሃይማኖት ለገብረ መንፈስ ቅዱስ ፣ ለአብነ አረጋዊ ፣ ለክርስቶስ ሰምራ፣ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ለቅድስት አርሴማ ወዘተ የሰጠ እግዚአብሔር ነውና፡፡ እንጂ ሰዎችን አይደለም የምናመሰግነው እግዚአብሔርን ነው ከፍ ከፍ የምናደርገው ለምሳሌ ሰው በአንገቱና፣ በእጁ ላይ ሐብልና ቀለበት ጌጥ ቢያደርግ እጁ ብቻውን አጌጠ ወይም አንገቱ አጌጠ ሳይሆን የምንለው ሰውየው (ሴትየዋ) አጊጣለች አምሮባታል ነው የምንለው ስለዚህ የተክለሃይማኖትን ፣ የቅድስ ጊዮርጊስን ቤተክርስቲያን አሳምረን ስንሰራ (ስናንጽ) እግዚአብሔርን ነው የምናከብረው ምክንያቱም እግዚአብሔር አካል ነው ቅዱሳኑ ብልቶች ናቸው፣ እርሱ ግንድ ነው እነርሱ ቅርንጫፎች ናቸውና፡፡
መጽሐፍ ቅዱስን ብንመለከት ከዘፍጥረት እስከ ራዕይ ከአዳም ጀምሮ ያሉትን ቅዱሳን አበው ታሪካቸውን ይተርካል ገድላቸውን ጽፎልናል፣ ነገር ግን የእግዚአብሔር መጽሐፍ ነው ካልን ለምን ሰዎችንና ታሪካቸውን መጻፍ አስፈለገ ብለን ብንመረምር እግዚአብሔርን ያወቅነው በፍጥረቱ ስለሆነ እንጂ እግዚአብሔርማ ግሩምና ድንቅ ከአእምሮ በላይ ነው በዚህ ዘመን ተወለደ አንል ለዘመኑ ጥንት ወይ ፍጻሜ የሌለው አልፋና ኦሜጋ ነው፣ እዚህ ቦታ ሠራ አንል በቦታ አይዋሰንም እዚህ ነው ወይም እዚያ ነው አይባልም፣ በዚህ ሰዓትና ጊዜ ይህን አደረገ አንል እርሱ ጊዜ የማይቆጠርለት ያለ ዕረፍት የሚሠራ ግሩም አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሔርን ያየው አንድስኳ የለም ተብሎ ነው የተጻፈው (ዮሐ 1፡18) ታዲያ ስላላየነው ነገር ምን ብለን እንጻፍ ምንስ እንናገር አብርሃም ባይኖር ይስሐቅ ባይኖር ያዕቆብ ባይኖር ሌሎችም ባይኖሩና ከእግዚአብሔር ጋር አካሄዳቸውን አድርገው በምግባር በሐይማኖት ሆነው ኖረው ገድላቸው ታሪካቸው ባይጻፍ ኖሮ ስለማናውቀው ስለ እግዚአብሔር ለመናገር ይከብደን ነበር ሰማያዊውን በምድራዊ ቋንቋ አሟልቶ መናገር አይቻልምና፡፡
አራቱን የወንጌል መጽሐፍ ስንጨርስ የሐዋርያት ሥራ ነው የሚቀጥለው፣ የሐዋርያት ሥራ ማለት ደግሞ የሐዋርያት ገድል ማለት ነው፣ እግዚአብሔር በሐዋርያት ላይ አድሮ የሠራው ሥራ ያደረገው ገቢር ተአምር ነው፡፡ እንደዚህ ሁሉ እግዚአብሔር በተለያዩ ቅዱሳን ላይ አድሮ የሠራው ሥራና ታሪካቸው ገድላቸው ተጽፎ ስናይ ከዚህ የተለየ አይደለም ቅዱሳን አዳኑ ስንልም እግዚአብሔርን ረስተን አይደለም፣ እግዚአብሔር በእነሱ ላይ አድሮ ሥራ ሰራ፣ በጸበሉ በእምነቱ (ቅዱስ አፈር) ላይ አድሮ ስራ ሠራ ማለታችን ነው፡፡
የእኛ የሰው ልጆች አእምሮ ስለ እግዚአብሔር መመራመር ማሰብ አትችልም በመሆኑም እግዚአብሔር በአቅማችን ልናስብ የምንችለውን ነው የሰጠን፡፡
ተክለሃይማኖት ገብረመንፈስ ቅዱስ ተነስተው በጽናት በመጋደል እግዚአብሔርን ባያሳዩን ኖሮ ብርታትን አግኝተን ተስፋን ሰንቀን መነሣት ይከብድ ነበር ለዚህም ነው ‹‹በነፍሳችሁ ዝላችሁ እንዳትወድቁ የጸኑትን አስቡ›› የተባለው (ዕብ 12፡3)
ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ሰማየ ሰማያት ተነጥቆ ምስጢርን ዓይቶ መጥቶ ሰማያዊውን በምድራዊ ቋንቋ መግለጥ ስላልቻለ ‹‹በዓይን ያልታየ በጆሮ ያልተሰማ በልብ ያልታሰበ እግዚአብሔር ለወዳጆቹ ያዘጋጃት›› (1ቆሮ 2፡9) አለ፡፡ በመሆኑም የእግዚአብሔር ነገር ከአእምሮ በላይ ስለሆነ እንደ እኔ መሆን ቢያቅታችሁ ብሎ እንደ እኛ የሚበሉ የሚጠጡ የሚያድኑ የሚሞቱ ሰዎችን አምጥቶ አበረታቸው ድንቅ ተአምሩን ገለጠባቸውና እናንተም እንደነዚህ ሁኑ፣ ወንጌል ከባድ ነው ሰው ሊፈጽመው አይችልም እንዳትሉ ይሔውላችሁ ሰዎች ሲፈጽሙ ተመልከቱ ለአመነ ሁሉ ይቻላልና፣ እናንተም በእምነት እነሱን አብነት አርአያ አድርጋችሁ ተጋደሉ ሲል ቅዱሳኑን ሰጠን፡፡
ስለዚህም ሚካኤል ገብርኤል፣ ተክለሃይማኖት ጊዮርጊስ አዳኑኝ ስንል እግዚአብሔር አዳነን ማለታችን ነው በእንጦጦ ጸበል፣ በሸንኮራ ጸበል ዳንን ስንል እግዚአብሔር አዳነን ማለታችን ነው በመስቀሉ በወንጌሉ ተሳልመን ተሻሽተን ዳንን ስንልም እግዚአብሔር አዳነን ማለታችን ነው፡፡

No comments:

Post a Comment