Monday, December 15, 2014

ጻድቅ አባ ተክለ-ሃይማኖት


አባታችን ተክለ-ሃይማኖት ስለ አንዲት ሃይማኖት ስለ አንድ አምላካችን በስሙ ስላደረጉት ተዓምር መንፈሳዊ ተጋድሎ አጭር የህይወት ታሪክ ፡-
የኢትዮጵያ ብርሃን የእግዚ/ር አብ ምሩጥ አባታችን ተክለ-ሃይማኖት የኢትዮ ቤተ- መንግስት ከአክሱም ወደ ላስታ የተዛወረበት ዘመን ላይ በዮዲት ወረራ ወቅት ተደናግጦ የነበርው ህዝበ ክርስቲያኑ ተረጋግተው በሃይማኖታቸው እየበረቱና እየጸለዩ አምላካቸውንና አምላካችንን እያመሰገኑ የነበሩበት ዘመን ነበረ በወቅቱ የነበሩት ነገስታት እየመነኮሱና ምንኩስና እየተስፋፋ የነበረበት ወቅት ነው፡፡
እግዚአብሔር  ኢትዮጵያን እንዲባርካት በምህረቱ እንዲያት በቅድስና የተመረጠ ጻድቅ ሰው የሚያማልድ ሃዋርያ ያገኘችበት ዘመን ነው፡፡ በብሉይ ህዝቡን ሁሉ ከአምልኮተ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር  የሚመራ በእግዚአብሔር  የተመረጠ የእስራኤል ነብይ ሙሴ እንደሆነ ሁሉ ኢትዮጵያን ከአምልኮተ ሰይጣን አላቆ ህዝቡን ወደ አምልኮታ  እግዚአብሔር የሚመራ ወንጌልን የሚያስፋፋ ጻድቅ ሰው በእግዚአብሔር  አብ የተመረጠ ኢትዮጵያ ያገኘችበት ዘመን ነበር፡፡ ከከተታ ወፊት፣ ከወፊት ዳሞት፣ ከዳሞት ወላይታ፣ አማራ ሳይንት ከአማራ ሳይንት ሃይቅ እስጢፋኖስ፣ ከሃይቅ እስጢፋኖስ ወሎ ደብረ ዳሞ ከደብረ ዳሞ ወደ ትግራይ እየተመላለሱ የእግዚአብሔር  አብ ክብሩን የሚመሰክሩ ወንጌልን የሚያስፋፉ የኢትዮጵያን አብያተ ቤተ-ክርስቲያንን በትምህርት እያስተማሩ ምዕመናኑን ለእግዚዓብሔር እንዲገዙ በእርሱም እንዲታመኑ የሚያደርጉ ኢትዮጵያ ጻድቅ አባት ያገኘችበት ዘመን ነበር፡፡ በቀን በጸሃይ ፊታቸው የጠቆረ በለሊት በቆራ በብርድ ሰውነታቸው የተጎሳቆለ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ለሰከንድ ሳያቋርጡ ስለህዝቡና ስለ ሃገራችን ሌት ተቀን ሲጸልዩ አጥንታቸውን ከሰውነታቸው ክፍል ያጡ ፍጹም የእግዚ/ር አገልጋይ አባታችን ተክለ ሃይማኖት፡-
በሸዋ ቡልጋ አከባቢ ደብረ ጸላልሽ ዞረሬ የምትገኘው አከባቢ የቅዱስ ሚካዔል ደብር ውስጥ በካህንነት የእግዚአብሔርን ህግ የሚያስፈጽሙ እግዚአብሔርን የሚያገለግሉ ካህን ፀጋ ዘኣብ የሚባሉ ነበሩ አከባቢው በደን የተሸፈነ ጥቂት የሚባሉ ጎጆዎች ብቻ የነበረበት አከባቢ ነው፡፡ አከባቢው ኢቲሳ ይባላል፡፡ በዚህ አከባቢ የፀጋ ዘኣብ ባሌቤት የነበሩ እግዚኣርያ የሚባሉ ቅን ደግ እግዚአብሔርን የሚፈሩ በአከባቢው የተመሰገኑ በማህበራዊ ኑሮ የተከበሩ ናቸው፡፡ እኚህ ካህን አባትና እናት በየወሩ የቅዱስ ሚካዔልን ዝክር እየዘከሩ በአሉን ያከብራሉ ልጅም አልነበራቸውም ነበር ሃድያ  እግዚአብሔርን በካህንነት የሚያገለግሉ አባት ጸጋ ዘአብ ልጅ እግዚዓብሄር እንዲሰጣቸው ቅዱስ ሚካኤል እንዲያማልዳቸው አጥብቀው እየጸልዩ የተቸገረን እየረዱ ያላቸውን እየመፀወቱ ይለምኑ ነበር፡፡ መጋቢት 24 ቀን በቅዱስ ሚካዔል ምልጃ አባታችን ተክለሃይማኖት ተጸነሱ በእዚሁ እለት እናት እግዚኣርያ እራዕይ አዩ እራዕዩም የብርሃን ምሰሶ ከቤታቸው ቆሞ የምሶሶው እራስ ከሰማይ ደርሶ በአለም ያለ ህዝብ ሁሉ ነገስታት ጳጳሳት ሁሉ በዙሪያው ቁመው እኩሌቶቹ ሲሰግዱለት እኩሌቶቹ ደሞ እርሱን ጥግ አድርገውት ተቀምጠው አዩ፡፡ እናት ይህን እራዕይ ባዩበት ለሊት ካህኑ አባት ጸጋ ዘኣብም እራዕይ አይቶዓል፡፡ እራዕዩም ከሚተኙበት ስር ፀሐይ ሲወጣ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ከዋክብቶች በክንፉ ላይ ተቀምጠው ለአለም ሁሉ ሲያበራ አየ ሲነጋ ከባለቤቱ ጋር ስላዩት እራዕይ ተነጋገሩ፡፡ በዚህ ወራት ምን እንደሚገጥማቸው ለማወቅ አልቻሉም በሌላኛው ለሊት ቅዱስ ሚካዔል ተገልጾላቸው ወንድ ልጅን እንደሚወልዱ እርሱም በእግዚአብሔር  የተመረጠ በእናታችን በቅድስት ማርይም ዘንድ የተወደደ በቅዱሳን መላዕክት ዘንድ የከበረ እንደ ሆነ አበሰራቸው፡፡ እናትና አባት በእግዚአብሔር  ድንቅ ስራ ያላቸውን እየመጸወቱ በእርሱ ደስ እየተሰኙ እያመሰገኑ ይኖሩ ነበር፡፡ ከዘጠኝ ወር ቡኋላ ታህሳስ 24 ቀን 1197 ዓ.ም የኢትዮጵያ ብርሃን የምዕመናኑ ማረፊያ ሃዋርያ መነኩሴ አባታችን ተክለ ሃይማኖት ተወለዱ፡፡ በእዚህ እለት አይወልዱም መካን ናቸው የተባሉት እግዚኣርያና ኣባት ልጅ በእጃቸው  እግዚአብሔር  አሳቀፋቸው፡፡ አባታችን ተክለ ሃይማኖት በተወለዱ በሶስተኛው ቀን በእለተ ሰንበት ከእናታቸው እቅፍ ወርደው በታዓምራትና በእግዚአብሔር  መንፈስ አንዱ አብ ቅዱስ ነው አንዱ ወልድ ቅዱስ ነው አንዱ መንፈስ ቅዱስ ቅዱስ ነው እያሉ አመሰገኑ፡፡ ገና በተወለደ በሶስተ ቀኑ እንደ ካህን አባቱ  እግዚአብሔርን የሚያመሰግን ይህ ምን አይነት ተዓምር ነው አሉ በሶስት ቀኑ እንደምን ለምስጋና ተነሳ ብለው ተደመሙ አባቱ ጸጋ ዘአባ ተገረመ ይህም ቅዱስ ዳዊት ከህጻናትና ገና ከሚጠቡ ምስጋናን አዘጋጀህ ያለውን አስበው ሌሎችም ተገረሙ፡፡ ከዚህም ቡኋላ በተወለዱ በአርባኛው ቀን ስርዓተ ጥምቀትን ወሰዱ የክርስትና አርማቸውን በሰውነታቸው ላይ አተሙ፡፡ ስማቸውንም ፍሰሃ ጺዮን ብለው አወጡላቸው፡፡ የጺዮን ደስታዋ ነውና በወንጌለ ትምህርታቸው ቤተ-ክርስቲያንን ደስ ያሰኟታልና ነው፡፡ አባታችን ተክለሃይማኖት በአባትና በእናታቸው ቤት አደጉ፡፡
አባታችን አንድ አመት ከሶስት ወር እንደ ሆናቸው በሸዋ አከባቢ እርሃብ ገብቶ የሚላስ የሚቀመስ ጠፍቶ ከሰማይ ደመና ጠፍቶ ዝናብ ተከልክሎ ነበር በየወሩ የሚዘክሩት የቅዱስ ሚካዔል በዓል በሚበላና በሚጠጣ መጥፋት ዝክሩ ሊስተጓገል መሆኑን ሲያስቡ እናትና አባት አዘኑ፡፡ ጸጋ ዘአብ በሚያገለግልበት ቤተ-መቅደስ ገብቶ አቤቱ ጌታ ሆይ በእጄ ምንም የለም የሚካዔል በአል ሊስተጓጎልብኝ ነው እያለ ከመንበሩ ተደፍቶ እያለቀሰ ይጸልያል ሚስቱ እግዚአርያ በቤቷ ደጃፍ ህና ታዝን ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ጡት በመጥባት ላይ ያሉ ፍሰሃ ፂዮን እናታቸውን የዱቄቱን እቃ እንድታመጣው ጠየቁ እቃውም መጣላቸው አባታችን የመጣው እቃ ላይ እጃቸውን ሲያሳርፉ እንቅቡ በዱቄት ተሞላ አስራ ሁለት ቅርጫት ዱቄት ተገኘ፡፡  እግዚአብሔር ወልድ በእኔ የሚያምን እኔ ከማረገው ይበልጥ ያደርጋል ብሎ እንደተናገረ፡፡ የዘይቱ እቃም በታዓምራት ሞሉ፡፡ በዚህም የቅዱስ ሚካዔል ዝክር ሳይስተጓጎል ተዘከረ፡፡ አባታችን ሰባት አመት እስኪሞላቸው ድረስ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ከአባታቸው ከጸጋ ዘአብ በአግባቡ እየተማሩ አደጉ ከእግዚአብሔር  መንፈስ የተነሳ የተማሩትንም ፈጥነው ይይዛሉ፡፡ አባታችን ህጉንና ትዕዛዙን በመጠበቅ ያማሩና ያጌጡ ሆነው አደጉ የአጋንንትን ወጊያ ለማሸነፍ ጸሞን መጾም ጀመሩ፡፡
አባታችን አስራ አምስት አመት በሆናቸው ወቅት ብጹዕ አቡነ ቄርሎስ ከግብጽ ከመምጣታቸው በኢትዮጵያ ጳጳስ ሆነው የነበሩበት ወቅት አባታችን ድቁናን ተቀበሉ በመንፈስ ቅዱስ ታነጹ፡፡ እንደ አከባቢያቸው አውሬን ያድኑ ስለነበር ከሰፍር ሎጆች ጋር ሁነው በማደን ላይ ሳሉ ቅዱስ ሚካዔል ተገለጸላቸው አባታችንም ተደናገጡ እርሱም ከእንግዲህ አውሬ አዳኝ አትሆንም ወንጌልን እያስተማርክ ህዝቡን የምታድን ትሆናለህ ሙት የማስነሳት ድውያንን የመፈወስ አጋንንትን የማውጣት ፀጋ ተሸፅጥቶሃል ስምህም ፍሰሃ ጺዮን አይሆንም ተክለ ሃይማኖት ይሁን እንጂ አላቸው፡፡ ተክለ ሃይማኖት ማለት የአብ ተክል የወልድ ተክል የመንፈስ ቅዱስ ተክል ማለት ነው፡፡ አምላካችን እየሱስ ክርስቶስም ተገለጸላቸው ወደ አህዛብ በመምህርነት እልክህ ዘንድ በመላዕኬ አፍ አዲስ ስም አወጣውልህ አዲስ ሃዋርያ አድርጌሃለሁ አላቸው፡፡ ጳውሎስን ከአሳዳጅነት ጠርቶ ሃዋርያ እንዳደረገው አባታችንን አዲስ ወንጌልን የሚሰብክ አንዲት ሃይማኖትን የሚጠብቅ አርጎ በቅድስናው መርጦ አዲስ ሃዋርያ አደረጋቸው፡፡ አባታችንም ይህን አለም ሳይመስሉ በሃይማኖት የታነጹ ፍጹም ሰው ሆኑ  እግዚአብሔርን በመፍራትና በማምለክ ኖሩ፡፡ አባታችን ተክለ ሃይማኖት በ22 አመታቸው ቅስናን ተቀበሉ አባታቸው ጸጋ ዘኣብ በሚያገለግሉበት ደብር በእርጋታ ማገልገል ጀመሩ፡፡ በመጀመሪያ እናታቸው እግዚዓርያ በመቀጠል ጸጋ ዘኣብ ከዚህ አለም በሞት ሲለዩ ሃብታቸውን ለድሆች አከፋፈሉ፡፡ ቤታቸውን ክፍት ትተው ወንጌልን ለመስበክ እግዚ/ርን ለማገልገል እየፀለዩ በወደኩኝ ጊዜ የምታነሳኝ በደከምኩን ጊዜ ምደግፈኝ በተራብኩኝ ጊዜ ምታበላን በተጠማሁ ጊዜ የምታጠጣኝ አንተ ብቻ ነህ እያሉ መነኑ፡፡ በሄዱበት ሁሉ መንግስተ ሰማያት ልትሰጥ ቀርባለችና ንሰሃ ግቡ ጌታ ባስተማራት ወንጌል ላይ እመኑ እያሉ ያስተምራሉ፡፡ በቡልጋ አከባቢ በጣኦት የሚያምኑ በዛፍና በእንጨት የሚያምኑና የሚሰግዱ ለሰይጣን የሚገዙ በድንጋይና በባህር የሚያመልኩ መድሃኒትን የሚቀምሙ ጠንቋዮችም ነበሩ አባታችንም ይህን ሲሰሙ አንዲት ወንዝን አቋርጠው ከተታ ገቡ የአከባቢው ሰው እንደሰሙት ከአምለኮተ እግዚአብሔር  ወጥተው ግብራቸው ሁሉ የሰይጣን እንደሆኑ አዩ፡፡
ወዲያውም ይህ ስራቸው የሰይጣን እንደሆነና የእግዚአብሔርን ቃል እየተናገሩ እየገሰጹ በእግዚአብሔር  እንዲታመኑ ሲያስተምሩ ህዝቡ አልተቀበሏቸውም በይበልጥ ተቀወሟቸው እንጂ በአከባቢው አንድ ዛፍ ላይ ሰይጣን አድሮ ዘፉ የሰው ድምጽ እያወጣ እኔ አምላካችሁ ነኝ ለኔ ስገዱ እያለ ይለፈልፋል ህዝቡም ይሰግዱለታል የወደደውንም ይሰውለት ነበር፡፡ አባታችንም ከአከባቢው ሰው ጋር ወደ ዛፉ በቀረበ ጊዜ እያጓራ ይጮሃል ይህንን እንግዳ ሰው ወደኔ አታምጡ እያለ ይጮሃል፡፡ ሰው አባታችንን አርቀው ወደ ዛፉ ቀረቡ አባታችን ግን ፊታቸውን ወደ ምስራቅ መልሰው ስለ ህዝቡ ጸለዩ ‹‹የጻድቅ ሰው ጸሎት እጅግ ሃይል ታደርጋለች እንደተባለ እንዲሁ የእግዚአብሔር  ጆሮዎቹም ወደ እነርሱ ናትና›› አባታችን እጃቸውን ዘርግተው አቤቱ በፍጥረትህ ላይ የሚሰለጥነውን ይህን ሰይጣን ከእግራችን በታች ጣልልን አቤቱ ይህን ሰይጣን አዋርድልን ዘወትር ይረዳሃል ብለህ የነገርከኝን መላዕክህን ሚካዔልን ላክልኝ በዚህ በተሰበሰቡ ህዝብ ፊት ይህ ሰይጣን ይዋረድ ስምህም ይታወቅ ጌታዬ አምላኬ መመኪያዬ አንተ ነህ ብለው ጸለዩ፡፡ ከዚያም ሰይጣን ያደረባትን ዛፍ አንቺ በሰይጣን የምትለፈልፊ ዛፍ ህዝቦች ሁሉ የሚሰግዱልሽ እኔ በማመልከውና በምሰግድለት በእየሱስ ክርስቶስ ስም አዝሻለሁ ህዝቡ የእግዚአብሔር  ሃይል ያይ ዘንድ ካለሺበት ተነቅለሽ ነይ አላት፡፡ በዚህ ጊዜ ዛፏ እየተወናጨፈች ሂዳ አባታችን ስር ቆመች፡፡ ሰው የሰነፍጭ ቅንጣት ያህል እምነት ቢኖረው ይህን ዛፍ ተነቅለህ ወደያ ተተክል ብትሉት ይሆንላችኋል ተብሎ እንደተጻፈ፡፡ በዛፏ ያደረ ሰይጣንም አንተ ክፉ ሰው ካንተ ወዴት እሸሻለሁ መላዋን የጽላልሽን አውራጃ የተውኩልህ አይበቃህም ዛሬ ባሪያዎቼን ልትቀማኝ ነው እያለ ጮኸ፡፡ በዚህ ጊዜም ሚካዔል ከሰማይ እነደ መብረቅ እያበራ ወረደ ሚካዔል ጊዜዬ ሳይደርስ እንዳታጠፋኝ እያለ ሰይጣኑ ጮኸ ከእንግዲህ ሰው ወዳለበት አልደርስም እያለ ጮኸ፡፡ ሕዝቡ ግን የህይወት ብርሃን አባታችን ሆይ ወደ ህይወት መንገድ ምራን ወንጌልን አስተምረን ብለው ከእግራቸው ስር ወደቁ፡፡ እነሆ መጥተው በእግሮችህ ስር ይሰግዱ ዘንድ እኔም እንደወደድኩህ ያውቁ ዘንድ አደርጋቸዋለሁ ተብሎ እንደተነገረ፡፡ (ዮሐ ራ. 3÷9) ይህን ተዓምር የሰሙ ሁሉ አባታችንን አንተ የምታምነውን አምላክ እናምናለን እንቀበለዋለን አንተ ወደ ህይወት መንገዱ ውሰደን አሉት አባታችንንም ተከለ ሃይማኖት መጸዓት ወደ ምትባል ወንዝ ወርደው ወንዙን ባርከው አባረዋቸው የተሰበሰቡትን ህዝብ ከአዋቂ እስከ ህጻን ያሉትን ሁሉ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አንድ ባንድ አጠመቋቸው፡፡ በዚሁ እለት ለከተታ ህዝብ ትልቅ ድህነት ሆነ ሁሉም በአምላካችን በእየሱስ ክርስቶስ በፍጹም ልባቻው አመኑ፡፡ በህዝቡ ላይ የእግዚአብሔር አብ መንፈስ ቅዱስ እንደ እርግብ ሲወርድባቸው ያዩ ነበር፡፡ አባታችን ተክለሃይማኖት ወንጌልን እየሰበኩ የእግዚአብሔርን ቃል እየመሰከሩ ህዝቡን በሃይማኖት እንዲጸኑ አደረጉዓቸው፡፡ ኢትየብር በምትባል አውራጃ ቤተ-ክርስቲያንን አንጸው በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ በማገልገል ለህዝቡ ስርዓተ ቁርባን እየሰጡ ህዝቡን በስላሴ አምነው በእምነት እንዲጸኑ አደረጉ፡፡ በዚች ሃገር በዚሁ ቀን ትልቅ ደስታ ሆነ አባታችን ካደጉበትና ከሚያገለግሉበት ከዞረሬ ቅዱስ ሚካዔል ቤተ- ክርስቲያን ልከው ካህናት እንዲመጡ አስደርገው እርሳቸውም ስርዓተ ወንጌልን እያስተማሩ ሶስት አመት ቆዩ፡፡ በዚህ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ከእርሳቸው ጋር ነውና ቅዱስ ሚካዔልም ይረዳቸዋል፡፡ በከተታ በእግዚአብሔር ስም ብዙ ተዓምራትን በማድረግ ህዝቡን ሁሉ ክርስቲያን አደረጓቸው፡፡
ይህን የሚቃወም ስንቶቻችን ነን ቀጣዩን በቀጣይ ክፍል አጠር አርገን እናቀርባለን፡፡
ብቻውን ለሆነውና አለምን ሁሉ ላዳነው አምላክና መድሃኒታችን ከዘመን ሁሉ በፊት አሁንም እስከ ዘላለም ድረስ ለጌታችን ለመዳህኒታችን ለእየሱስ ክረስቶስ ክብርም ስልጣንም ሃይልና ግርማ ለእርሱ ይሁን የእናቱ የእመቤታችን የቅድስተ ቅዱሳን የድንግል ማርያም ጸጋዋና ምልጃዋ አይለየን፡፡ አሜን

No comments:

Post a Comment